ወሩ መጋቢት ወቅቱ ደግሞ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቁ የአብይ ፆም ላይ እንገኛለን። በዛሬው የኪነ ጥበብ አምድ ላይም ይህን ታላቅ ፆም ምክንያት በማድረግም ስለ በገና በስፋት መዳሰስ ፈቅደናል።
ነገሩ እንዲህ ነው። የእምነቱ ተከታዮች አምላካቸውን በልዩ ልዩ መልኩ ያመሰግኑታል ፤ ያመልኩታልም። ከዚህ ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ በዝማሬና በዜማ መሳሪያ የሚደረግ ስርዓት ነው። የተዋህዶ እምነት ተከታዮች በመደበኛው ጊዜ በተለያዩ የምስጋና መልዕክት ባላቸው መዝሙሮች ስርዓታቸውን ያከናውናሉ። ለዚህ እንዲረዳቸው የዜማ መሳሪያ የሆኑትን ከበሮ፣ማሲንቆ፣ ክራር፣ እንዲሁም ዋሽንትን ሲጠቀሙም ይስተዋላል።
በአንዳንድ ልዩ ክብረ በዓላት ላይ ደግሞ ጥበባዊ የማመስገኛ ዘይቤው ለየት ብሎና መንገዱን ቀይሮ እናስተውላለን። ለምሳሌ ያህልም በዚህ በያዝነው ወቅት ከባድ እራስን የመግዛት፣ የማምለክና ከዓለማዊው ጩኸት የመራቅ ጊዜ ነው። በመሆኑም አምላካቸው ጌታ እየሱስ ክርስቶስን የሚያስቡበት ለምስጋና የሚጠቀሙበት የዜማ እቃ በዋናነት ‹‹በገና›› ይሆናል።
ይህ መሳሪያ በእርግጥ በሌሎችም የፆም እና አዘቦት ቀናቶች ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም በአብይ ፆም ጊዜ ግን በልዩ ሁኔታ ሰፊውን ቦታ ይይዛል። መነሻችን ላይ ጠቆም አድርገን እንዳለፍነው ለዛሬ በዝርዝር የሚከተሉትን ጉዳዮች እንመለከታለን፤ ይህ የዜማ እቃ በአብይ ፆም ወቅት ለምን ጥቅም ላይ ይውላል? ጥበባዊና ሃይማኖታዊው ፋይዳው ምን ይመስላል? በገናን ለአምልኮ ስርዓት መጠቀም መቼ ተጀመረ? መሳሪያው ከየትኛው የዜማ እቃ ውስጥ ይመደባል? እንዴትስ ይሰራል?…
የበገና- ታሪካዊ ዳራ
የበገና ታሪካዊ አመጣጥ በምንመለከትበት ወቅት ዋና ማጠንጠኛ አድርገን የምንጠቀምበት መፅሀፍ ቅዱስ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ‹‹የሲሳይ በገና የዜማ መሳሪያዎች ማሰልጠኛ ተቋም›› መስራች የሆኑት መምህር ሲሳይ ደምሴ ይጠቀሳሉ። እርሳቸው ስለጉዳዩ ዝግጅት ክፍላችን አንስቶላቸው ምላሽ በሚሰጡበት ወቅት ዳራውን እንደሚከተለው አስቀምጠውታል።
መፅሃፍ ቅዱስን በዋቢነት የሚጠቅሱት መምህሩ፤ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 21ን አጣቅሰው ‹‹ዮባል በገናና መለከት እንደሚይዙ አባት ነበር›› እንደሚል በማንሳት የበገና የዜማ መሳሪያ ከዚያን ዘመን ጊዜ ጀምሮ ጠቀሜታ ላይ ይውል እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን ከዚያም ቀደም ባሉ ጊዜያት ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ከዚህ ሌላ በእስራኤል በዳዊት ዘመን ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር የሚጠቅሱት መምህሩ ኢትዮጵያውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህን የዜማ እቃ አምላካቸውን ለማመስገን ይገለገሉበት እንደነበር ያነሳሉ። ይህን ካስቀመጡ በኋላ በገና መፅሃፍ ባልነበረበት ወቅት (በህገ ኦሪት) ማለትም በብሉይ ኪዳን እንዲሁም አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ ያላ የዜማ መሳሪያ መሆኑን ይናገራሉ። በይበልጥ ግን በዳዊት ዘመን የቃልኪዳኑ ታቦት ተደራጅቶ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩበት ከመሆኑ አንፃር መለከት፣ ነጋሪት፣ እምቢልታ፣ ከበሮን ጨምሮ በገና አብሮ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ድርሳናት ላይ ተከትቦ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።
ቅዱስ ዳዊት ከልጅነቱ ጀምሮ በገና ይደረድር ስለነበር፤ በጊዜው ለመንፈስ መታወክ ፈዋሽ መሆኑ የታየበት መሆኑን ይገልፃሉ። ይህን ሲሉ በተለይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ በጉልህ የሚታወቀው ንጉስ ሳኦል መንፈሱ በታወከ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት በገናውን በመደርደር ውስጡ የነበረውን መንፈስ ያወጣለት እንደነበር መምህሩ በማጣቀሻነት በማንሳት የዜማ መሳሪያውን ቀደምት ታሪክ ያወሳሉ። በወቅቱ የነበረው የህክምና ዘዴ አሁን በዘመናዊው ዓለም ለተመስጦ ወይም በፈረንጆቹ አፍ ‹‹meditation›› እያልን ለምንጠራው የስነ ልቦና ህክምና ጋር ተዛምዶ እንደነበረው ያስረዳሉ።
የዜማ መሳሪያው አሰራር
በገና እንደ ማንኛውም መንፈሳዊ እና ዓለማዊ የዜማ መሳሪያዎች የራሱ የሆነ አሰራር እንዳለው ይታወቃል። በልዩ ሁኔታም ከተለያዩ ግብአቶች ጋር ውህድ ሆኖ ይዋቀራል። በገናን የሚያንፁ የራሱ ባለሙያዎችም አሉት። መምህር ሲሳይ በምን መልኩና በምን አይነት ዘዴ እንደሚሰራ ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተውናል።
በገና ከእፅዋትና ከእንስሳት ክፍለ አካል በሚገኝ ቁስ ይሰራል። ከዘመናት በፊት የነበረውም መሳሪያ ይህንኑ ግብዓት በመጠቀም የሚሰራ ነው። በዋናነት ከእንስሳት የሚጠቀመው የድምፅ ሳጥኑ የሚሸፈንበት ቆዳን ሲሆን፤ አውታሩን ለመስራት ደግሞ የበግ አንጀት ይጠቀማል። ክሩ ደግሞ ከበሬ ጅማት የሚዘጋጅ ነው። መወጠሪያዎቹና ጥፍሮቹም በተመሳሳይ ከቆዳ ውጤቶች የሚዘጋጁ ናቸው። መግረፊያው ከቀንድ አሊያም ደግሞ ከእንጨት የሚዘጋጅ ይሆናል።
ከእፅዋት የሚዘጋጀው ክፍሉ ቀንበሩ፣ የግራና ቀኝ ምሰሶው፣ የድምፅ ሳጥኑ፣ ብርኩማው፣ መቃኛው እንዲሁም መወጠሪያው ነው። በገና በዋናነት የድምፅ መሳሪያ ሲሆን ምድቡም ከክር መሳሪያዎች ጋር ነው። ይህ መሳሪያ ከሌሎቹ የክር መሳሪያዎች የሚለየው በእድሜው አንጋፋ መሆኑ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ሁለት ለየት ያሉ ‹‹ድዝዝና ቅዝዝ›› የሚሉ ድምፆችን ያወጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን በገና ከሌሎቹ ለየት ባለ መልኩ አስር አውታሮች ያሉት መሳሪያ ነው። በተለይ ደግሞ አውታሮቹ ለፀሎትና ለምስጋና፤ ለምክርና ለተግሳፅ መጠቀሚያ መሆኑን ይለየዋል።
በገና ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ
በገና በጥበብ ዘርፍ ውስጥ የዜማ መሳሪያ ከመሆኑ ባሻገር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለየት ያለ ትርጉም አለው። ይህን ልዩ ውክልና መምህርንና ሊቀ ሊቃውንት በተለየ መልኩ ሲተነትኑት ይደመጣሉ። ለዛሬው የአብይ ፆምን በማስመልከት ስለዚህ ተወዳጅ የዜማ መሳሪያ በልዩ ሁኔታ ገለፃ ወዳደረጉልን መምህር ሲሳይ ምልከታ እንመለስ።
እንደ መምህሩ ምልከታ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ህግ ባልተፃፈበት ጊዜ (በህገ ልቦና) የእግዚአብሄር ህዝቦች የሚያመልኩበትን ስርዓት ይከተሉ ነበር። ህግ ከተፃፈ በኋላም (በህገ ኦሪትም) ይህንኑ ህግን በመከተል የአምልኮ ስርዓት ይፈፀም ነበር። ይህ የሚከወነው ደግሞ አሁን እስካለበት አዲስ ኪዳን ድረስ በገናን፣ እምቢልታን፣ መለከትና ከበሮን በመሳሰሉ የዜማ እቃዎች ነው። ይህ ስርዓት ቤተክርስቲያኗን ጥንታዊት መሆኗንና እንደሚያመለክትም መምህሩ ይናገራሉ። በተለይ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በገና በሰማይ የአምልኮ ስርዓት የሚፈፀምበት የዜማ እቃ መሆኑ እንደሚታመን ይናገራሉ። ቅዱስ ያሬድም ወደ አርያን ሄዶ በሰማይ ያለውን ዜማ ሰምቶ የማህሌቱን፣ የሰዓታቱንና የቅዳሴውን ዜማ ነው ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበት።
አብይ ፆምና የበገና ዜማ እቃ
እንደ መምህሩ ማብራሪያ ይህ ፆም አብይ የተባለበት ዋና ዓላማ፤ ሁሉም የክርስትና እምነት ተከታይ ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ ሃጥያትን፣ ስጋን ከሚያነሳሱ ነገሮች፣ ከዓለማዊ ነገር ሁሉ በእጅጉ ተቆጥቦ የሚፆመው በመሆኑ ነው። በተለይ ጌታ መድሃኒት እየሱስ ክርስቶስ እራሱ ይህን ፆም በምሳሌነት ፆሞ ምእመኑ እንዲከተለው ማዘዙን መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚያመለክትም ይጠቅሳሉ። በዋናነትም የፆሙ ስጋን ለነብስ ለማስገዛት ይከናወናል።
በዚህ ጊዜ በተመሳሳይ በገና እንዲያዳምጥ በሃይማኖት አባቶች ይመከራል። መምህሩ ይህ የሚደረገው አማኙ እራሱን ወደ ውስጥ እንዲመለከት በበገና የሚሰራ መዝሙር ስለሚረዳው መሆኑን ያስረዳሉ። የመሳሪያው የመመሰጥ አቅምና በገና በመጫወት መንፈሳዊውን ዜማ ከሚያዜመው ዘማሪ ችሎታም መንፈስን ለመግዛት ይረዳል።
‹‹በገናን ያመነም ሆነ ያላመነ ቢሰማው በከፍተኛ ተመስጦ እንዲመለከት ያግዛል›› ይላሉ መምህሩ፤ ይህ የዜማ መሳሪያ በተለየ ሁኔታ የሰው ልጅ በጥሞና እራሱን እንዲመለከት የሚያግዝ መግነጢሳዊ ሃይል እንዳለው ሲያስረዱ። በዚህ መነሻም ልዩ ተመስጦና መረጋጋትን በሚሻው በአብይ ፆም ወቅት በበገና የተዘጋጁ መንፈሳዊ ዜማዎችን ማድመጥ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ይገልፃሉ። በዚህ አግባብ ፆምና በገና የሰውን ስጋዊ ባህሪ በማረቅ ከአምላኩ ታርቆ የህሊና ሰላም እንዲያገኝ ያስችሉታል።
ከዚህ ውጪ ሁለቱ ይበልጥ እንዲቆራኙ ያደረጋቸው በንጉሱ ስርዓተ መንግስት ወቅት በሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች በገና በፆሙ ወቅት እንዲያጫውቱ ይደረግ ነበር። በዚህ ምክንያት አብይ ፆም ሲመጣ በገና፣ በገና ሲታወስ ደግሞ አብይ ፆም ተያይዘው መነሳት ጀምረዋል።
በገናና ግጥም
በገና በግጥምና ዜማ ታጅቦ ለመንፈሳዊ አምልኮ ስርዓት ይቀርባል። ከዜማው እና ቅላፄው ባሻገር ግን በዚህ መሳሪያ የሚቀርቡ ስሜት ቆስቋሽና አመስጋኝ ግጥሞች ከመደበኛው የመዝሙር ግጥሞች ፍፁም ይለያሉ። በተለይ ጥሞናና ተመስጦን ዋናው ግቡ ከማድረጉ አኳያ በግጥሙ ጥልቅ ፍልስፍናዊ መልዕክቶችን ይሸከማል። ይህ ለምን ሆነ ስንል ለመምህር ሲሳይ ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር። እርሳቸው እሳቤው ትክክል መሆኑን ጠቁመው ምክንያቱን ደግሞ በዚህ መልክ ያስረዳሉ።
እርሳቸው በገና ሰውን መገሰጫ፣እራስን መመልከቻ በተለይ የሰው ልጅ የዚህን ዓለም ከንቱነት የሚረዳበት የተለያዩ ግጥሞች የያዘ መሆኑን ይናገራሉ። በግላቸው ደግሞ በልዩ ሁኔታ ለሞት የተሰነኙ የበገና ግጥሞች እንደሚመስጧቸው ይናገራሉ። በምሳሌነት ሲያነሱም አቶ ደምሴ ወይም አባባ በገና የተባሉ ሊቅ አንስተው ‹‹አላየንም በሉ አልሰማንም በሉ፤ ያ ሞት ሲፈልገን ሲሻን ውሏል አሉ›› የሚለውን ይጠቅሳሉ። ቀጥለውም ‹‹ከፋኝ ሞቴን ስጠኝ ለማይቀረው እዳ፤ ደሞም በስጋዬ ነፍሴ እንዳትጎዳ›› በማለት በገና ደርዳሪው ሞት ሲለምን የዓለምን ከንቱነት ሲናገር ማዳመጥ ወደ ቀልብ መመለስንና መመሰጥን ሲያዜም እንደሚማርካቸውና በውስጣቸው ጥያቄ እንደሚጭርባቸው ይገልፃሉ።
በበገና ዜማና ቅኝት ውስጥ መምህሩ የጠቀሱት ብቻ ይሆን በርካታ መንፈስ ኮርኳሪ ግጥሞችን ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ ያክል የሚከተሉትን አነስተን የሳሬው ርዕሰ ጉዳያችንን እንቋጫለን። «ውሃ ማለት ሰው ነው፤ ሰው ማለትም ውሃ፤ ንጹህ ሆኖ መጥቶ ጅረት የሚገባ፤ የሄደበት መንገድ መልኩን የሚቀርፀው፤ ያለፈበት ምድር የኔ ነው የሚለው፤ ሰው ማለት፤ ሰው ማለት፤ ሰው ማለት ውሃ ነው» መች ይሄ ብቻ ሆነና፤ «ጅረት ነን፤ ጅረት ነን፤ ጅረት ነን ሥረ ምንጭ ፤የምንም መነሻ፤ የመድረክ እርጥባን፤ የባዶ መካሻ፤ የአፍላ ጋት ህላዌ፤ የሃያል ወንዝ ነፍሱ፤ እኛ ነን ቀለሙ የመዋብያ ቅርሱ። ከጠራ ምንጭ ፈልቀን፤ ከተዋበ አፈር ተዳቅለን የመጣን፤ አንድ ቤት አንድ ዘር፤ የመጋመድ አሃድ የጣዕሞች ልኬት ፤ የውህዶች ህብር የመቃረብ ስሌት፤ ጅረት ነን፤ ጅረት ነን ሥረ ምንም፤ የምንም መነሻ የመድረክ እርጥባን፤ የባዶ መካሻ» እያለ…እያለ…..እያዜመ በገና ደርዳሪው ይቀጥላል።
በገና የሰው ልጅ በጥሞና እራሱን እንዲመለከት የሚያግዝ መግነጢሳዊ ሃይል አለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳግም ከበደ