ለግድቡ መዘግየት ምክንያቱ የሜቴክ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ነበር
አዲስ አበባ፡- ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በዘንድሮው ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። ለግድቡ መዘግየት ምክንያቱ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆንና የአስተዳደር ችግሮች እንደነበሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ የታቀደው ከቦንድ ሽያጭ፣ በ8100 መልዕክት፣ ከስጦታ፣ በፒን ሽያጭና በተለያየ መልኩ ከሚደረግ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ ነው።
የግድቡ ግንባታ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ መዘግየቱን የተናገሩት ወይዘሮ ሮማን ለዚህም ዋናው ምክንያት የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን እና የአስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ለአፈጻጸሙ መዘግየት የነበሩ ምክንያቶች ተገምግመው በመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ይፋ ሲደረግም በሚዛናዊ መንገድ ባለመገለጹ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ህዝቡ በግድቡ ላይ እምነት እንዲያጣ ማድረጉን አስረድተዋል።
ጽህፈት ቤቱ ከህዝቡ ተሳትፎ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ ባደረገው የዳሰሳ ጥናትም ግድቡ ምንም አይነት ችግር ቢያጋጥመው እስከመጨረሻው ድጋፋችንን እንቀጥላለን የሚለው ህዝብ 46 በመቶ፣ መንግስት ያጠናቀው የሚለው ደግሞ 48 በመቶ እንደነበር አመልክተዋል።
በጥናቱ መሰረት ባለፈው ዓመት ጽህፈት ቤቱ ያቀድነውን ገንዘብ አናሳካም የሚል ስጋት ቢኖረውም ዜጎች ግን ለህዳሴ ግድብ ገንዘብ ማዋጣት ባለማቆማቸው አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለማሰባሰብ ተችሏል። ይህንን በማየት በዘንድሮው ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስካሁን 400 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ማብራሪያ በድርድሩ ሂደት የግብጽ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብና እኔ ብቻ ልጠቀም አካሄድና የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ህዝቡን አስቆጥቷል። በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ምሁራን ጫናውን ለመመከት በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው። አርቲስቶች በሙያቸው ህብረሰተሰቡን እየቀሰቀሱ ነው። ህዝቡም በጉልበቱ፣ በገንዘቡ ጭምር ግድቡ የእኔ ነው በሚል ስሜት ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ጽህፈት ቤቱ ከሲቪል ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች፣ ከህፃናት፣ ከእድሮች፣ ከዩኒቨርሰቲ ምሁራን አደረጃጀቶች ጋር ውይይት በማድረግ ለግድቡ ድጋፍ እንዲያደርጉ መግባባት ላይ ተደርሷል። በተዘረጉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥርዓቶችም ዜጎች ለግድቡ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በ8100 መልዕክት 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የተጀመረ ሲሆን አንድ ወር ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ለአንድ ወር በቀን አንድ ብር ለማዋጣት ከ379ሺ በላይ መልዕክቶች መጥተዋል። ከ50 ብር ጀምሮ በቦንድ ሽያጭ በልማት ባንክና በንግድ ባንክ በኩል ተቋማትና ግለሰቦች መግዛት ጀምረዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፎቶና (አሻራየን አኑሪያለሁ) የሚል ጽሁፍ የያዘ ፒን ተዘጋጅቶም ለተቋማት በ50 ብር እየተሸጠ መሆኑም ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ተሳትፎ እንዲጎለበት ከማድረግ በተጨማሪ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፉትን የሀሰት ዜና እና ኢትዮጵያ የምታራምደውን የጋራ ተጠቃሚነትና ፍትሃዊ አካሄድ በማቅረብ እንዲመክቱ ጥሪ አቅርበዋል። በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ምሁራን ስለ ግድቡ እያደረጉት ያለውን ለዓለም ህዝብ የማስረዳት እንቅስቃሴ በምርምር በማስደገፍ ጭምር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ወይዘሮ ሮማን አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
አጎናፍር ገዛኽኝ