በኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የባላቸውን ያህል ሥልጣን በመጎናጸፍ ተጽእኖ ይፈጥሩ ከነበሩ የነገሥታት ሚስቶች መካከል እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ያህል አቅም የነበራቸው ሌሎች እንስቶች በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ እንዳልተስተዋሉ ብዙ የታሪክ ጸሐፍት በማስረጃ እያጣቀሱ ጽፈዋል። እኒህ አቻ ያልተገኘላቸው ንግሥት ከባላቸው ከአጤ ምኒልክ ህመም በኋላ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር የገቡበትን የሥልጣን ግብግብ በአሸናፊነት መወጣት ተስኗቸው ለአድመኞቹ ሤራ እጅ በመስጠት መጋቢት 12 ቀን 1902 ዓ.ም ከወሳኙ የእቴጌነት ሥልጣናቸው ተሽረው የህመምተኛው ባለቤታቸው አስታማሚ እንዲሆኑ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ተዘግቶባቸው የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ተፈረደባቸው።
ከምኒልክ ህልፈት በኋላም እንደ የኪነጥበባት ባለሙያዎች ደማቅ ትርክት በእንጦጦ ቤተ መንግሥት ውስጥ በግዞት ላይ እንዲቆዩ በተደረገበት አንድ አጋጣሚ በግቢው ውስጥ እግራቸውን ለማፍታታት ወዲያ ወዲህ በሚሉበት ወቅት ከእንጦጦ እስከ ታላቁ ቤተ መንግሥት ድረስ እንደ ባለሙያ ሴት መቀነት ዧ ብሎ የተዘረጋውን አውራ ጎዳና ልብ ብለው ያስተውላሉ። መንገዱን ከየት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ ግር ስላላቸው ከጎናቸው የነበረችውን ተንከባካቢያቸውን ደንገጡር ቀረብ ብለው “እቴዋ ይሄ ጎዳና ወዴት ኖሯል የሚወስደው?” ብለው ይጠይቋታል።
ደንገጡሯ “እቴዋ”ም ቀልጠፍ ብላ “እሜቴ! ይህንን ጎዳና ቆመው ያስነጠፉት እኮ እርስዎ ራስዎ ነዎት። ከእንጦጦ ተነስቶ እስከ ጌታዬ ታላቁ ቤተመንግሥት የሚዘልቅ ዋና መንገድ ነው።” ብላ ትመልስላቸዋለች። ይህንን የመርዶ ያህል ምስክርነት ያደመጡት “ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘኢትዮጵያ” በትካዜ ውስጥ እንደተዋጡ፤ “አይሄሄ! አለሁ ማለት ከንቱ። ለካንስ ነበር እንዲህ ቅርብ ኖሯል።” ብለው በለሆሳስ አጉተመተሙ ይባላል።
ከመቶ ዓመታት በፊት ታሪክን የኋሊት፤
ይህ ጸሐፊ ዛሬ ላይ ቆሞ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት የተፈጸሙ ዋና ዋና ክስተቶችን ከታሪክ መጻሕፍት በማመሳከር ሲመረምር “ነበር ለካንስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል?” በማለት የእቴጌዋን አባባል ተውሶ መጠየቁ ተመሳሳይ የታሪካዊ ግጥምጥሞሾችን በስፋት በማስተዋሉ ነው።
በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ በርካታ ታሪካዊ ድርጊቶች የተከናወኑበት ወቅት ነበር። የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ህመምና ህልፈት ተከትሎ የተነሳው የፖለቲካ ዐውሎ ነፋስ በአንዳንድ የፖለቲካ ሹማምንት የሥልጣን ዓይን ውስጥ የሚያደናብር አቧራ አጅሎ ተሰነካክለው እንዲወድቁ ሰበብ ሆኗል። ለአንዳንዶችም የሲሳይ ያህል ከፍ አድርጎ ባልጠበቁት ሥልጣን ወደ ላይ አጉኗቸዋል።
ጉልህ ክስተቶችን አለፍ አለፍ እያልኩ ለመጠቃቀስ ልሞክር። የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ልጅ ከሆኑት ከወ/ሮ ሸዋረገድ እና ከወሎው ገዢ ከራስ ሚካኤል የሚወለዱት ጃዊሳው የ14 ዓመት ብላቴና አቤቶ ኢያሱ ከሚያዝያ 4 ቀን 1903 ዓ.ም ጀምሮ የአባታቸው እስትንፋስ ሳይጨልም በፊት የሥልጣን ወንበር ተቆናጠጡ። የስልጣናቸውን ከረሜላ አጣጥመው ሳይጨርሱም እንዳሻቸው መፋነኑ ያልተዋጠላቸው ወሳኞቹ ሹማምንት በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሱናሚ ወጀብ በማስነሳት ልጅነታቸውም፣ ገዢነታቸውም በአጭሩ ተቀጭቶ ታሪካቸው እንዲደመደም ተደረገ።
ከኢያሱ ውድቀት በኋላ መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት ሁለቱ ዝሆኖች፤ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱና አልጋ ወራሹ ተፈሪ መኮንን፤ በስውርና በይፋ ደጋፊዎቻቸውን በጦርነትና በዲፕሎማሲ እያፋለሙ አልጋውንም ሀገሪቱንም ማንቀጥቀቱን ተያያዙት። በዚህን መሰሉ የፖለቲካ ፍትጊያ መካከል እጃቸውን ለማስገባት ክፉ ቀን ሲመኙ የነበሩት ሦስቱ የወቅቱ ኃያላን ኮሎኒያሊስት መንግሥታት (እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ) ባገኙት ሽንቁርና ስንጥቅ መካከል እየሾለኩ ከሁለቱ ዝሆኖች አንዳቸውን በማማለል ነውጡን ያጋግሉት ገቡ። የዳበረ የነጥሎ መምታት ስትራቴጂያቸውን በመጠቀምም አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንንና ጡንቻቸው የደደረውን ተጽእኖ ፈጣሪ ጎምቱ ሹማምንት አውሮፓ ድረስ በመጋበዝ በመሰሪነት የተለውሰ ወዳጅነት ለመፍጠር ተሸቀዳደሙ።
የፖለቲካው ጡዘትና ሽክርክሪቱ በጋለበት በዚያን ወቅት ቤተኛ በሆኑት ሀገርኛ የሃይማኖት ቤተሰቦች ዘንድ ልዩነትን የሚያባብሱ፣ በሕዝቡ ዘንድ ፍርሃትንና ሽብርን የዘሩ ክስተቶች ይስተዋሉ ጀመር። በድንቅ መጻሕፍታቸው ታሪኩን ካቆዩልን የሀገር ባለውለታው መካከል መርስዔ ኀዘን ወልድ ቂርቆስ “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ – 1999 ዓ.ም) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ዝርዝሩን እንደሚከተለው አስፍረዋል።
“በ1904 ዓ.ም ናዝራዊና ባህታዊ በአዲስ አበባ ከተማ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በብዛት ሲታይ ከረመ። ናዝራዊ ጠጉሩን አስረዝሞ፣ ባለ አንካሴ የብረት መስቀል ተሸክሞ፣ ባሕታዊም ዳባ ለብሶ፣ ጢሙን አንዠርግጎ በየበዓል ስፍራ እየዞረ በአደባባይ ይሰብክ ጀመር። መዓት መጣብህ፣ ጉድ ፈላብህ፣ እግዚኦ በል፣ ንሰሃ ግባ፣ ምፅዋት መፅውት” በማለት አስደንጋጭ ወሬ ለሕዝቡ አፈሰሱለት (ገጽ 89)።
“ስለ ሃይማኖት ነገር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየስፍራው ተቀስቅሶ የነበረው ክርክር በዚህ ዓመትም እንደቀጠለ ነበር። ክርክሩ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል፣ ደግሞም በክርስቲያኖች በእርስ በእርሳቸው መካከል ነበር (ገጽ 100)።
ከሀገራዊ ግራ መጋባት ከፍ ሲልም በዚሁ በክፍለ ዘመኑ መባቻ ላይ ታላቁ የዓለም ጦርነት ፈንድቶ (1908 ዓ.ም) ስለነበር ዓለማችን በአረር ወላፈን መለብለቧ እንዳለ ሆኖ ለሀገራችንም ጦሱ መትረፉ አልቀረም ነበር። በተለይም አቤቱ ኢያሱ የጀርመንና የቱርክ ዋነኛ ወዳጅና ደጋፊ ስለነበሩ በተቀሩት የአውሮፓ መንግሥታት ዘንድ ሀገራችን በጥርስ ውስጥ መግባቷ እውን ሆነ። የመገለጫ ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ ትንታኔውን ለማቅረብ ገጹ አይፈቅድም።
ወደ ሀገር ውስጥ ጉዳይ መለስ ስንል በ1909 ዓ.ም የአገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ደጃዝማች አብርሃ አርአያ የፖለቲካው መገለባበጥ አልጥማቸው ብሎ የልጅ ኢያሱን ግቢ ከለላ በማድረግ ለውጊያ በመዘጋጀት ላይ ሳሉ በለስ ሳይቀናቸው ቀርቶ እቅዳቸው ስለከሸፈ እጃቸው ተይዞ ለግዞት ስለተዳረጉ በዚሁ ብሽቀት በጥቂት ቀናት ውስጥ ሕይወታቸው በማለፉ ከህልፈታቸው በኋላ የተለያዩ ወጀቦች ተነስተው ሀገሪቱ አደጋ ላይ ልትወድቅ ተቃርባ ነበር።
በዚያው ዓመት በመስከረም ወር የወሎና የትግሬ፣ የበጌምድርና የጎጃም ንጉሥ ተብለው ከሁለት ዓመት በፊት ዘውድ የጫኑት “ሚካኤል ንጉስ ጽዮን፣ ሸዋ አድማ መትቶ ልጄን ኢያሱን ከሥልጣን አወረድኩ የሚለው ማን ፈቅዶለት ነው? ብለው በመቆጣት የሰባቱን ወሎ ቤት በማስተባበር ጦር ይዘው በመገስገስ ከሸዋ መኳንንት ጋር ሰገሌ ላይ ጠርነት ገጥመው መሸነፋቸው የዚሁ የክፍለ ዘመኑ መባቻ አንድ ታሪክ ነበር።
በ1910 ዓ.ም የተፈጸመን መሰል የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ ታሪክ ጸሐፊው መርስዔ ኀዘን እንዲህ ተርከውታል። “የትግሬ ገዢ ራስ ስዩም መንገሻ ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ወር ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ልጃቸው ደጃዝማች ካሣ የአድዋ ገዢ ሆኖ ትግሬ ላይ ቀርቶ ነበር። አባቱ አዲስ አበባ ላይ መክረማቸውን ባወቀ ጊዜ ግዛት ለመደረብ ፈልጎ ሸፈተና የሌላውን አገር ይወጋ ጀመር። የትግሬ ወጣቶች አብዛኞቹ ስለተከተሉትና ኃይል ስለተሰማው የተምቤን ገዢ ደጃዝማች ግርማይ መንገሻን (የገዛ አጎቱን) ወግቶ አገሩን በእጁ አደረገ። ወደ ሽሬም ዘምቶ እንደዚሁ አገሩን ያዘ። ከዚህም በኋላ ወደ መቀሌ ሄዶ የአባቱን የራስ ስዩምን እንደራሴ ደጃዝማች ተካን ወጋና ከተማውን ያዘ (ገጽ 215)።
በሰሜን እንዳነበብነው ነውጡ ሲያይል፣ በምስራቅ በልጅ ኢያሱ ምክንያት፣ በመሃል ሥልጣኑን በተቆጣጠሩት የሸዋ ሹማምንት ምክንያት የፖለቲካው ሽኩቻና ፍልሚያው በተጋጋለበት ወቅት የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በ1911 ዓ.ም የተቀሰቀሰው “የህዳር በሽታ” በሺህ የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎችን ነፍስ መንጠቁን በቀዳሚዎቹ ጽሑፎቼ ውስጥ በዝርዝር ማመልከቴን ልብ ይሏል።
ለማስታወስ ያህል በእኛ አጠራር “የህዳር በሽታ” በመባል የሚታወቀው የስፓኒሽ ፍሉ (ግሪፕ) ቸነፈር ከህዳር 7 እስከ 20/1911 ዓ.ም ባሉት 14 ቀናት ብቻ ከንቲባ ወሰኔ ዛማኔልን ጨምሮ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን እንዳረገፈ በታሪክ ተመዝግቧል። በዚሁ በሽታ ምክንያትም ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ መነንና ንግሥት ዘውዲቱም በቸነፈሩ ተለክፈው ስለነበር ከሞት የተረፉት ለጥቂት ነበር።
ታሪክ ጸሐፊው መርስዔ ኀዘን ሁኔታውን ያሰፈሩት በሚሰቀጥጥ አቀራረብ ነው። “በሽታው አዲስ አበባ ደርሶ በጣም የታወቀው በህዳር ወር ስለሆነ በሕዝቡ ቃል “የህዳር በሽታ” የሚል ስም ወጣለት። አንዳንድ ሰዎች ቸነፈር ብለውት ነበር። በሽታው በነፋስ ተዛምቶ መጥቶ ከጥቅምት ጀምሮ ጥቂት በጥቂት በአንዳንድ ሰው ቤት መግባትና መጣል ጀመረ። በህዳር ወር ግን አብዛኛውን ሰው ስለነደፈው ከተማው ተጨነቀ። በሽታው እንደ ሳልና እንደ ጉንፋን አድርጎ ይጀምርና በበሽተኛው ላይ ትኩሳት ያወርድበታል። ከዚያም ሌላ ያስለቅሳል፣ ነስር ያስነስራል፣ ተቅማጥና ውጋት ያስከትላል። አንዳንዱንም አእምሮውን ያሳጣዋል። እንዲህ እያደረገ በሦስት በአራት ቀን ይገድለዋል። ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ ሁለት፣ ሦስት መቶ ከዚህም በላይ ይሞት ነበር። በአንድ መቃብርም ሁለትና ሦስት ሬሳ መቅበር ተደረሰ (ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው ገጽ 125)።
በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር ግራ በሚያጋባ ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ ሣር ቤቶች ያለ አንዳች ምክንያት ቀን በቀን ይጋዩ እንደነበር ታሪክ ጸሐፊዎች በየመጻሕፍታቸው ውስጥ አስፍረዋል። የቃጠሎው ምክንያት እንዲህ ነው ተብሎ ባለመታወቁ “የመዓት ቃጠሎ” ተብሎ ሊጠራ ችሏል።
የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የሀገራችንን ታሪክ በግርድፍ ቅኝት ለመመልከት ተሞከረ አንጂ እያንዳንዱ ክስተት ቢተነተን ቅርንጫፉና ሀረጉ እጅግ ረዝሞ ይሰፋ ነበር። ለማንኛውም መባቻው የሀገሪቱ የፖለቲካ ወላፈን የተንቀለቀለበት፣ ሹም ሽር የበረከተበት፣ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የውስጥ አመጽና የሕግ ጥሰት እምቢታ የተስተዋለበት፣ የውጭ መንግስታት በተቀነባበረ ስልት ሀገሪቱን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለመያዝ ያሤሩበት፣ ሀገራዊ የሃይማኖት ቤተሰቦች እርስ በእርስ የተሻኮቱበት በአጠቃላይም የሀገሪቱን እርምጃና የወደፊት መዳረሻ ለመተንበይ ችግር የነበረበት ወቅት ነበር ብሎ መጠቅለል ይቻላል።
ዛሬ ከመቶ ዓመት በኋላ!
የሀገሪቱ ፖለቲካ ከነውጥና ከለውጥ ነፃ ሊሆን አልቻለም። ያኔም፣ ዛሬም ከሀገሪቱ የአንድነት ጥንካሬ ይልቅ በጎጥ ቅዠት መንፈራገጥ፣ ከውይይት ይልቅ ሸርና በአፍቃሮተ ሥልጣን የሚናውዙ የጎበዝ አለቆች ያገነገኑበት፣ በጦርነት እንሞካከር ከማለት ባልተናነሰ ፉከራ የቡድኖችና የግለሰቦች ቀረርቶ የበዛበት ወቅት መሆኑ ለማንም ግልጥ ነው።
ሥልጣን ተነጠቅሁ፣ ጥቅሜ ቀረብኝ፣ የበላይነቴን ተገፈፍኩ የሚሉ ጩኸቶች በየቦታው ሲደመጡ ይስተዋላል። ከግዞት ነፃ የወጡትም ሳይቀሩ እያስፈራሩ ጭምር ለሥልጣን ሲፋለሙ፣ ከሥልጣን ወንበር የተገፈተሩትም ራሳቸውን ግዞት ውስጥ በፈቃዳቸው አስረው በብብሽቅና በእልህ “ይዋጣልን!” እያሉ ሲዛዛቱ እያደመጥንም፤ እየተመለከትንም ነው። የፋኖነት ግለት ትኩሳቱ ጨምሯል እንጂ ፍሙ አልከሰለም። ዛሬም እንደትናንቱ፤
ጥራኝ ጫካው፣ ኧረ ጥራኝ ዱሩ፣
ላንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ።
እያሉ የሚያቅራሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ዛሬም ቁጥራቸው የትዬለሌ ነው። ጫካው ተመንጥሮ ማለቁ፣ ዋሻው ተቦርቡሮ መጋለጡን አንኳ የተረዱ አይመስሉም።
ከምዕተ ዓመት በፊት የነበሩ ኮስማና ሀገራት በኢኮኖሚያቸው፣ በፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውና በዲፕሎማሲ ጡንቻቸው ፈርጥመው ዓለምን ሲዘውሩ እኛ ግን ዛሬም ከጋራ ሀገራዊ የጸጋ መሶባችን ላይ ተፋቅረን ከመጎራረስ ይልቅ መፋለምን ምርጫ ለማድረግ የተፈረደብን ይመስላል። ያፈጀና ያረጀ አመለካከት በትከሻችን ላይ እንደተጫነ ዘመኑንም ራሳችንንም መቶ ዓመት ወደ ኋላ አሽቀንጥረን ስለወረወርን “ከነበር ታሪካችን” መማር አልቻልንም።
የወቅቱ የኮረና ቸነፈር ልክ በመቶ ዓመቱ አገርሽቶ ጥቂቶችን ነድፎ፣ ብዙኃንን ከቤት ማስቀረቱ ገና ቁጭት ላይ አልጣለንም። ለነግ ተነግ ወዲያ የኢኮኖሚ ድቀት ሰበብ እና ለበርካታ ዜጎቻችንም የሕይወት ህልፈት ምክንያት እንዳይሆን ለመከላከልም የጋራ መግባባት ላይ አልደረስንም። በርካታ የሃይማኖት ቡድኖች አባላትም ከጥንታዊያኑ ናዝራዊያንና ባሕታዊያን በከፋ ሁኔታ የ“ነብይነትንና የሃዋሪያነትን” ክህነት ለራሳቸው አጎናጽፈው በየመንፈሳዊ ቴሌቪዥናቸው ሲያብዱ እየተመለከትን ግራ ተጋብተናል። ዕድሜ ያስቆጠሩ በርካታ የሃይማኖት አገልጋዮችም እንደ እድሜያቸው ከመብሰል ይልቅ ልዩነትን በመስበክ ምዕመናን ግራ ሲጋቡ እየተመለከትን ነው። በሃይማኖት ቡድኖቹ መሠነጣጠርና የትርፋማነቱም ገበያ መድራቱ የዘመናችን መገለጫ ሆኗል።
የሀገሪቱ ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ በአብዛኛው በጎ ገጽታው የጎላ ቢሆንም የታላቁን የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ ግን ግብጽ እያራመደች ያለችው አቋምና እየተጓዘችበት ያለው ጎዳና ባለፈው መቶ ዓመት ብቻ ሳይሆን በሺህ ዘመናት ውስጥም ቋንቋዋም ሆነ የሤራ ተልዕኮዋ አንዳችም የስትራቴጂ ለውጥ ያለማሳየቱ ግራ አጋቢ ሆኗል። በእጅጉ የሚያሳዝነው ግብፅ ባበደች ቁጥር የህሊና ጨርቃቸውን ጥለው አብረው የሚከንፉት በርካታ የአረብ ሀገራት ያለመንቃታቸው ነው። ዘንድሮ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የማር ጨረቃ (Honey Moon) አብረው መግመጣቸው እንቆቅልሹን አወሳስቦታል። ትዝብቱ ለታሪክና ለትውልድ መተላለፉ ካልሆነ በስተቀር የህዳሴ ግድባችንም ሆነ ሉዓላዊነታችን በፍጹም እንደማይደፈር ለፈርኦን ልጆች ይጠፋቸዋል ማለት አይቻልም።
የዛሬ አንድ ምዕተ ዓመት (1911 ዓ.ም) ሱዳን ልትገነባ ያሰበችው የሲናር ግድብ እቅድ እንዳይሳካ ግብጽ ልክ እንደዛሬ ሤራዋ ዊሊያም ዊልክንን በመሳሰሉ ለግብጽ ጥቅም ሲባል በተቀጠሩ ተሟጋቾች አማካይነት የሲናር ግድብ ከተሠራ የግብጽ የውሃ መጠን ሊቀንስ ስለሚችል የቆየ መብቷን ሊጎዳ ይችላል የሚል ማስፈራሪያና ዘመቻ ተከፍቶ ነበር። የፈርኦን ልጆችን አደብ እንዲገዙ የሚመክር ወዳጅ ጠፍቶ እነሆ እንዳበዱ ዛሬንም ሊሻገሩ ነው።
አንዳንድ ነባር ታሪኮቻችን በዛሬዋም ጀንበር መልክና ይዘት ሳይቀይሩ እየተደገሙ መሆናቸው ያሳሰበን አይመስልም። በብዙ ጉዳዮች በድብርት ውስጥ መሆናችንም አላስደነገጠንም። በሃሳብ ለመተማመን ጥረት ከማድረግ ይልቅ ፍልሚያና ቀረርቶ ይቀናናል። ከወቅታዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር የማይገጥሙት ብዙዎቹ ህመሞቻችን የትናንቱ ታሪክ ግርሻ ውጤቶች ናቸው። ከታሪክ ለመማር እስካልፈለግን ድረስ የተፈጸመ የታሪክ ስህተት መድገማችን አይቀሬ ይሆናል። እኒህን መሰል ህመሞቻችን ስር የሰደዱ ቢሆንም እንኳ ተስፋ ግን አለን። ሀገራችንን ከደዌዋ ልንፈውሳት የምንችለው ዋግምቶችም እኛው ልጆቿ ነን። የፈውሱ መድኃኒትም የሚገኘው በእጃችን ላይ ነው። የ“ነበር ለካንስ አንዲህ ቅርብ ነበር!” ጨዋታ እስከዚህ ካጓጓዘን ዘንዳ እየኖርንበት ላለው ዛሬያችን ውበትና ፍሬያማነት አጥብቀን ብንሰራ መጪው ትውልድ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጽም ልናግዘው እንችላለን። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com