ዓለም በተለያየ ጊዜ አስከፊና አሰቃቂ ወረርሽኞችን አስተናግዳለች። እንዲያውም አንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ነጥቀው አልፈዋል። ከመቶ ምናምን ዓመታት በፊት ሚሊዮን በጣም ብዙ ነበር። እነዚህ አሰቃቂና ጨካኝ የበሽታ ወረርሽኞች ግን ያለርህራሄ ሚሊዮን ዜጎችን ቀጥፈዋል።
ዛሬ የዓለም ሁሉ መነጋገሪያ የኮሮና ቫይረስ ነው። አገራት ሌላ አጀንዳ የላቸውም። ከግለሰብ እስከ አህጉራት መነጋገሪያው ይሄው አስከፊ ወረርሽኝ ነው። ከመንገድ ላይ ሻይ ቡና እስከ ዓለም አቀፍ አዳራሾች መነጋገሪያው ይሄው ነው። የጋዜጦችና መጽሔቶች የፊት ገጽ ይሄው አስከፊ ወረርሽኝ ነው። የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የዜና ማስጀመሪያ የኮሮና ቫይረስ የጥንቃቄ መልዕክት ነው። የመዝናኛ ፕሮግራሞች ሁሉ ወደ ኮሮና መልዕክት ተቀይረዋል።
የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሮና ቫይረስን ከሌሎች ሁሉ ለየት የሚያደርገው የሥርጭት ፍጥነቱ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን አጥለቅልቋል። ምናልባት ግን የዓለም ህዝብ የእንቅስቃሴ ሁኔታ ከድሮው የተለየ ስለሆነ ነው የሚሉም አሉ። ያም ሆነ ይህ ከዚህ በፊት ከተሰከቱ ወረርሽኞች ጋር አነፃፅረው የፍጥነቱን አስከፊነት ተናግረዋል። በገዳይነት ግን ከዚህ የከፉ በርካታ ወረርሽኞች ታይተዋል።
ዓለም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ከ1347 እስከ 1351) ‹‹ጥቁሩ ሞት›› በሚል በታሪክ የተመዘገበውን አስከፊ ወረርሽኝ አስተናግዳለች። የታሪክ ድርሳናትና የበይነ መረብ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ዓለም በዚህ ወረርሽኝ 200 ሚሊዮን ህዝብ ተነጥቃለች። እንግዲህ ከ670 ምናምን ዓመታት በፊት የዓለም ህዝብ ብዛት ስንት እንደነበር ማሰብ ነው።
‹‹ጥቁሩ ሞት›› የሚል ስያሜ የተሰጠው በአስከፊነቱ ነው እንጂ ሳይንሳዊ ስሙ ‹‹ኤርሺየ›› እና ‹‹ፔስትስ›› ይባላል፤ የሚመጣውም በዚሁ ስም በሚጠሩ ባክቴሪዎች ነው። ‹‹ቡቦኒክ›› ወረሺኝ ሲሉም ተጨማሪ ስም ሰጥተውታል። ባክቴሪያው ከአይጥ እንደመጣ ነው የሚነገረው፤ ቁንጫዎች ደግሞ ከአይጦች ወደ ሰዎች አስተላለፉት። የአውሮፓና የእስያ አገራት ላይ አስከፊውን ጉዳት አደረሰ። በወቅቱ የፈጣሪ ቁጣ ነው ተብሎም ነበር። ልክ ባለፈው ቅዳሜ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ‹‹ተስፋችን ከሰማይ ነው›› እንዳሉት ማለት ነው። ወረርሽኙ በአጭር ጊዜ ሊቆም አልቻለም፤ ለአምስት ዓመታት ያህል ህዝቡን ፈጅቷል።
ምናልባትም ይህን ወረርሽኝ አስከፊ ያደረገው በዘመኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ የህክምና አቅም ስለሌለ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው የበሽታውን ባህሪና ምንነት የሚያሳዩ ምርምሮች የተገኙት ከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ነው። ሳይንቲስቶች ‹‹አሁን ዘዴው ተገኝቷል›› ቢሉም ጅብ ከሄደ ውጫ ጮኸ ሆኗል። ምን ዋጋ አለው! ሳይንቲስቶችን የሚፈታተን በሽታ ግን አሁንም አልጠፋም፤ ለዚህኛው አገኘን ቢሉም ሌሎች አዳዲስ በሽታዎች እየተከሰቱ ደግሞ ይፈታተኗቸዋል። በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ ሌላ አስከፊ ወረርሽኝ ተከሰተ።
ይሄኛው ወረርሽኝ ደግሞ በእኛው አገር አገርኛ ስም ተሰጠው። የህዳር በሽታ በሚል ይታወቃል። ይሄን ስያሜ ያገኘው በህዳር ወር ውስጥ ስለተከሰተ ነው። እነዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ህዳር ሲታጠን በሚል ቆሻሻ የማቃጠል ሥራ እየተሰራ ነው። እኛ የህዳር በሽታ ብንለውም የዓለም ማህበረሰብ ‹‹ስፓኒሽ ፍሉ›› በሚለው ዓለም አቀፍ ስሙ ያውቀዋል። ስያሜውን ያገኘው የመጀመሪያው ታማሚ ከስፔን በመሆኑ ነው። በዚህ ወቅት የዓለም ኃያላን በሁለት ጎራ ተከፍለው የጦፈው አንደኛው የዓለም ጦርነት ላይ ነበሩ። በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ የተመዘገበው ሰው ሰራሽ የሆነው የጦርነት ወረርሽኝ የ14 ሚሊዮን ዜጎችን ሕይወት ሲቀጥፍ የተፈጥሮው ወረርሽኝ ደግሞ የ100 ሚሊዮን ዜጎችን ሕይወት ቀጠፈ። መረጃዎቹ የሚያሳዩት ቁጥር የተለያየ ስለሆነ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ይሆናልም ተብሏል።
መነሻው ከአሜሪካ ነው የተባለው ይሄው የስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ በሰው ሰራሽ (ጦርነት) የተጎዳውን ህዝብ በቀላሉ አንኮታኮተው። ወረርሽኙም ከጦርነቱ ወታደሮች ጋር ተዛመተ። የበሽታው ምልክቶችም ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ነስር፣ የጆሮና የአንጀት መድማት፣ ተቅማጥ፣ የአይን ማስለቀስና ውጋት ሲሆኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስም የአእምሮ ህመም ያስከትላል። የበሽታው አስገራሚ ባህሪ፤ አንድ ሰው በበሽታው በተጠቃ በአምስት ቀን ውስጥ ወይ ይሞታል አልያም ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ይድናል። ልክ እንደሌሎቹ የቫይረስ በሽታዎች ሁሉ በሽታ በሰው የተፈጥሮ የመከላከል አቅም ላይ የሚወሰን መሆኑ ነው። ከፍተኛ የመከላከል አቅም ያለው ሰው በስድስተኛው ቀን ጤነኛ ይሆናል። የዚህ በሽታ መዲሃኒትም የተገኘው ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው።
ይሄ በሽታ ለመጀመረያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር የታየው በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታዎን ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ተስፋፋ። በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ላይ በሰፊው ተሰራጨ። በምዕራብና ደቡብ አፍሪካ አካባቢዎች የከፋ የከፋ ጉዳት አድርሷል።
ይሄ ወረርሽኝ ኢትዮጵያም አልቀረላትም፤ ለዚህም ነው የህዳር በሽታ የሚለውን ስያሜ ያገኘው። በኢትዮጵያ በሽታው የታየው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወራት በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም ነው። በዘመኑ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በሽታው መግባቱ አይቀርም በሚል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መስራት የተለመደም አልነበረም። ፈንጣጣ ሊሆን ይችላል በሚልም የፈንጣጣ ክትባት ሲሰጥ ነበር። ለዘመናዊ ህክምና ያለው የህዝቡ ግንዛቤም ያን ያህል ነበር። ሆኖም ግን ክትባቱም ትክክለኛ የራሱ ክትባት አልነበረም። በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ አስከፊ እልቂት አስከተለ። የ40 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት በቀጠፈው በዚህ ወረርሽኝ ቀዳማዊ አጼ ኃይላሥላሴና ባለቤታቸው እቴጌ መነንም ተይዘው እንደነበር ተነግሯል። ይህ የህዳር ወረርሽኝ ህዳር 12 ቀን አስከፊ ጉዳት ያደረሰበት ቀን በመሆኑ ቀኑ ህዳር ሲታጠን እየተባለ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቀን ሆኗል።
ፈተና አይጣሽ ያላት ዓለም አሁንም አላረፈችም። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1980ዎቹ ደግሞ ‹‹ኤች አይ ቪ ኤድስ›› የሚባለው መጣ። ይሄ እንግዲህ የታሪክ ድርሳናት በማገላበጥ ሳይሆን ብዙዎቻችን በመኖር የምናውቀው ነው። የወጣቱን ስነ ልቦና የሰበረ ይህ በሽታ በተለይም በ1990ዎቹ የኢትዮጵያም ዓብይ አጀንዳ ሆነ። በየትምህርት ቤቱ፣ በየእምነት ተቋማቱ፣ በየአደባባዩ… ወጣቱን ‹‹ውልፍት እንዳትል›› የሚሉ መልዕክቶች በዙ። የሬዲዮ ጣቢያዎች ከዜና እስከ ፕሮግራም፣ ከማስታወቂያ እስከ ሙዚቃ፣ ከዜና መሸጋገሪያ እስከ ዜና ማሳረጊያ የጥንቃቄ መልዕክቶቻቸው ሁሉ ስለዚህ በሽታ ሆነ። ይሄም ወረርሽን ጊዜውን ጠብቆ የመረሳት ደረጃ ላይ ደረሰ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እሱን የሚያስመሰግኑ ሌሎች ወረርሽኞች ሲከሰቱም አጀንዳ መሆኑ ቀረ። በነገራችን ላይ ያን ያህል ገናና ባይሆኑም ሌሎች ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችም ነበሩ።
እነሆ አሁን ደግሞ ተረኛው ወረርሽኝ የኮሮና ቫይረስ ሆኗል። ገና ባህሪው እንኳን በትክክል አልታወቀም። ጥርት ያሉ አስተማማኝ መረጃዎች የሉም። ያለው አማራጭ በህክምና ባለሙያዎች የሚነገሩ ምክሮችን መከተል ነው። የዚህ ቫይረስ አደገኛነት ደግሞ የሥርጭት ፍጥነቱ ነው። በአየር የሚተላለፍ ቫይረስ ነው። ገና የመከሰቱ ዜና ሳይበርድ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው። እርግጥ ነው የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሌሎች ወረርሽኞች ጋር ሲነፃፀር ገዳይነቱ ዝቅተኛ ነው። ከሥርጭት ፍጥነቱ አንጻር ግን አስጊ የሚባል ነው። ባለሙያዎች እንደሚሉት የአንድ ሰው ጥንቃቄ ሌላውን ይታደጋል። ጀግና ማለት ደግሞ ለሌሎች የሚኖር ነው። ይሄ በሽታ ለወገን እንጂ ለራስ የሚታሰብበት አይደለም። የአንተ መታመም የብዙዎች ሞት ነው። የአንተ ጥንቃቄ ብዙዎችን ያድናል።
እንጠንቀቅ! እናድን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
ዋለልኝ አየለ