አቶ ግርማ ባልቻ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ያደጉት አዲስ አበባ ጉለሌ ነው። ለእናታቸው አራተኛ እንዲሁም ለአባታቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጉለሌ በሚገኘው ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተከታትለው ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን አርበኞች መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ከተማሩ በኋላ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ችግር ወደ እስር ቤት ገቡ። በዚያም የ 11ኛ ና 12 ክፍል ትምህርታቸውን በመቀጠል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናንም የወሰዱት በእስር ቤት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በፈተናው ያመጡት ውጤት ጥሩ ስለነበር ለሁለት ዓመት ያህል በኮሜርስ ሰፕላይስ ማኔጅመንት የሚባል የትምህርት ዘርፍን ተምረው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ትምህርቱን ወደ ቢዝነስ ማኔጅመንት በመቀየር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከዚያ በኋላ ግን ወደ ትምህርቱ አለም አልተመለሱም ፡፡
ስራን “ሀ” ብለው የጀመሩት በከተማ ልማት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ላይ ሲሆን በዛም ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል። የመንግስት ለውጥ ሲመጣ ወደ ኢምግሬሽን ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ በመሄድ በተለያዩ የስራ ክፍሎች ላይ ሰርተዋል።
ከእነዚህ የስራ ቆይታዎች በኋላም በቀጥታ ያመሩት ወደ ዲፕሎማሲው ነው፤ ብዙ ጊዜ ዲፕሎማሲ ሲባል የውጭ ጉዳይ ብቻ ይመስላል የሚሉት አቶ ግርማ እርሳቸው ዲፕሎማት ሆነው የሰሩት በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ነው።
በዚህ ስራም በቀጥታ ወደ ግብጽ ካይሮ በ1997 ዓም ሄደው ለስድስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል። እኛም የዛሬ የዘመን እንግዳ አምዳችን አቶ ግርማ
ባልቻን በተለይም የአባይ ወንዝን በተመለከተ በሰሯቸው ስራዎች፣ በጻፏቸው መጽሀፍትና በሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ስራዎቻቸው ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በዚህ መልክ አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ዲፕሎማት ሆነው ወደ ግብጽ ከመሄዶ በፊት ስለ አባይ ወንዝ ያለዎት አረዳድ ምን ይመስል ነበር?
አቶ ግርማ ፦ ወደ ግብጽ የሄድኩበት ወቅት በተለይም በወንዙ አጠቃቀም ላይ ሰፋ ያለ ድርድር የተጀመረበት ስለነበር ለእኔ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑም በላይ ህይወቴን በሙሉ ቀይሮታል። በአጋጣሚ አንዲት ፖርቹጋላዊት ሴት ሶስተኛ (ፒኤች ዲ) ዲግሪዋን በናይል ላይ ትሰራ ነበርና እሷን መተዋወቄ የበለጠ ናይልን እንዳውቀው በር ከፍቶልኛል።
ሴቲቱ በጣም ተመስጣ ነበር የምትሰራው፤ እንዲሁም ስለ ወንዙ ሰፊ የሆነ እውቀት ያላት በመሆኑ እኔም ላይ የእሷ ስሜት እንዲጋባ ሆነ ፤ ከዛም እኔም ስለ ናይል ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አደረብኝ። እሷም ብዙ መጻህፍቶችን ትሰጠኛለች፤ እኔም በራሴ ጥረት ስለ ናይል የተባሉትን ሁሉ መሰብሰብና ማንበብ ጀመርኩ፤ ሁኔታውንም መረዳትና በግብጽ መገናኛ ብዙሃን ላይም ተሳትፎ ማድረግ በጠቅላላው በናይል ዙሪያ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በሙሉ ራሴን ማስገባት ጀመርኩ።
በዚህም ሂደቱን በቅርበት እየተከታተልኩ ግብጾች ስለ ናይል ምን እንደሚሉ ፤ እንደሚያደርጉና እንደሚያስቡ እኛ ምን ማድረግ እንደሚገባንና ሌሎች መረጃዎችንም ወደ ሀገሬ መላክ ፤ መጻጻፍ ቻልኩ፡፡
አዲስ ዘመን፦ አቶ ግርማ ናይልን ከመተዋወቁ በፊት ምን አይነት ሰው ነበር?
አቶ ግርማ፦ በጣም ይገርማል! እኔ ከዚህ አገር ስሄድ ስለናይል ምንም እውቀት የለኝም፤ ዝም ብሎ ወንዛችን ምናምን ከሚለው መፈክርና ዘፈን የዘለለም አላውቅም ነበር፤ ሚዲያውም እኮ ያን ጊዜ የሚሰራው ስራ ያን ያህል እውቀት የሚያስጨብጥም አልነበረም። ግን ገብቼ ሳውቀው ደግሞ በጣም የሚያስደንቅ ትልቅ አጀንዳ የሆነ ጉዳይ ነው፤ እንዴውም እንዴት ሊዘነጋና በእኛ ዘንድ ቦታ ሊያጣ ቻለ የሚል ጥያቄን ያስነሳብኝም ነበር።
ከዛ በኋል እኔም ሁለት መጻህፍቶችን ጽፌያለሁ ምክንያቴም የናይል ወንዝ በእኛ ዘንድ እንደማይታወቅ አባይን ለግብጽ መጠቀሚያነት እንደ መብት አድርገን የሰጠናትና እንደዚህ ያለ ግንዛቤም መያዛችን እጅግ የተሳሳተ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ከዛም በላይ አባይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ እንደሆነ ለመልማት እሱን መጠቀም እንዳለብን እኛ ተጠቃሚ መሆናችን ደግሞ ግብጽን ሊጎዳ እንደማይችል ፤ የግብጽ ኢኮኖሚ አሁን ላይ ከግብርና ወጥቶ ወደ ሌሎች ዘርፎች በተለይም አገልግሎት ኢኮኖሚውን እንደሚመራው በመጽሃፎቼ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡
እዚህ ላይ ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ እኔ ለጉዳዩ ባይተዋር ሆኜ የኖርኩትን ያህል ህዝቡም መቀጠል የለበትም በመሆኑም ማወቅ አለበት በሚል “ ናይልና የግብጽ ኢኮኖሚያዊ እንደምታ ከየት ወዴት “ ነው የሚል ነው መጽሀፉ።
በመጽሀፉም የግብጽና የናይልን ሁኔታ እንዲሁም አገሪቱ ያለችበትን የኢኮኖሚ ደረጃ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። ከዛው ጋር በተያያዘ ደግሞ የሰሜናዊ ሲናይ ልማትና የቶሺካ ፕሮጀክት የሚባሉ አሉ ፤ ፕሮጀክቶቹ ከናይል ተፋሰስ ውጪ ወንዙን ከተፈጥሯዊ አካሄዱ ውጪ ቀይሰው ነው የሚጠቀሙት፤ እነሱ በዚህን ያህል ተፈጥሯዊ ጉዞውን ቀይረው በረሃቸውን ሲያለሙበት እኛ ደግሞ በአንጻሩ ምንም ሳንጠቀም መቅረታችንን ህዝቡ እንዲገነዘበው በማድረግ አባይን ማልምት ለኢትዮጵያም ህልውና እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ በአባይ ወንዝ ምክንያት ከግብጽ ጋር የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለንና እርስዎ ይህንን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ግርማ ፦ የኢትዮጵያና የግብጽ ዲፕሎማሲ በጣም ረጅም ዓመትን ያስቆጠረ ነው። ከምክንያቶቹ አንዱ ደግሞ የኢትዩጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከግብጽ ቤተክርስቲያን ጋር በነበራት ግንኙነት የእኛን አገር ቤተክርስቲያን የሚመራው ዻዻስ ከግብጽ አሌክሳንደሪያ ተሹሞ የሚመጣ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ደግም ለረጅም ዓመታት እነርሱ ላይ ጥገኛ እንድንሆን አድርጎን ነው የቆየው። ጥገኛ እንድንሆን ያደረገን ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ንጉስ ለመንገስ በዻዻስ መቀባት ያስፈልገው ስለነበር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ናይል ነው፤ ወደ ናይል ወንዝ
ከሚፈሰው የውሃ መጠን ግብጽ የሚደርሰው 86 በመቶው ከኢትዮጵያ አብዛኛው ክፍሎች ከሚዘንበው ዝናብ የተገኘ ነው። የሰው ልጅ እውቀት በየጊዜው ነው እያደገ የመጣው፤ በጥንት ጊዜ ግብጾች ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ሲመጣ የውሃው መጠን ይቀንስ ስለነበር እዛ ያሉት ነገስታት ኢትዮጵያ ገድባ አቁማዋለች በማለት የተለያዩ መማለጃዎችን እንዲሁም ሽማግሌዎችን ይልኩም ነበር። ይህንን ስናየው እኛና ግብጽ በጣም የተሳሰረ ግንኙነት ያለን መሆኑን ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን ለመገደብ ያሰበችው በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን እንደነበር ታሪክ ይናገራልና ጠንከር ብለን ያልሄድነው ለምንድን ነው?
አቶ ግርማ ፦ ያን ጊዜ በራስ አቅም ለመስራት ከባድ ነው። ይህንንም የሚያደርግ የኢኮኖሚ አቅም አልነበረንም። እንደዛም ቢሆን ግን አጼ ኃይለ ስላሴ ጣና ሀይቅ ላይ ግድብ የማስገደብና ኤሌክትሪክ የማመንጨት ከዛ የተረፈውን ውሃ ደግሞ ለሱዳኖች በሽያጭ ለማቅረብ ሃሳብ ነበራቸው፤ ግን በወቅቱ አስር ሚሊዮብ ዶላር ይፈጃል ተብሎም ነበር፤ የዓለም ባንክንና የሌሎችን እርዳታም እገኛለሁ ብለው ተስፋም አድርገው ነበር ግን አልተሳካም፡፡
በሌላ በኩልም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካኖቹ መጡና ጥናት ማካሄድ ጀመሩ፤ አራት ግድቦችንም አሁን የህዳሴው ግድብ ያለበት አካባቢ ላይ ለመስራት አሰቡ፤ ግን እነሱም ወደ ተግባር ለመቀየር ለጋሽ የሚባሉት አገራት የግብጽን ጥቅም ይጎዳል የሚል አቋም ስለነበራቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። በዚህ ምክንያትም የግድብ ግንባታ ሳይሳካ ቀረ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ግን እኮ በወቅቱ አጼ ኃይለስላሴ በመንግስታቱ ድርጅትም ሆነ በሌሎች ዘንድ የተከበሩ የተሰሙ ነበሩ ፤ እና እንዴት ድጋፍ አጡ?
አቶ ግርማ ፦ ለምሳሌ እኮ የአስዋን ግድብን ጀማል አብዱልናስር ገንብቶታል፤ ግን ያጋጣሚ ጉዳይ ነው እንጂ እሱ የግድቡን ግንባታ አስጠንቶ ወደ ስራ እገባለሁ ባለበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ውስጥ ነው የገባው። ለጋሽ አገራት ብድር እንሰጥሀለን ቢሉትም እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡበት ነገር በጣም ፈታኝ ነበር። በመሆኑም በዛን ጊዜ እንደዚህ ያለ ስራን መስራት ቀላል አልነበረም። እርሱ እንደውም በወቅቱ የጠቀመው ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ያበቃበት ማግስት መሆኑ ነው። ሶቭየት ህብረቶች መካከለኛው ምስራቅ ላይ ቦታን ለማግኘት ሲሉ ለግብጹ መሪ ሙሉ ወጪውን ሸፍነውለታል። እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ነው ግድቡን መስራት የቻሉት፡፡
አጼ ኃይለስላሴም እንዳልሽው ያክብሯቸው ይስሟቸዋል እንጂ በዚህ ደረጃ የሚደግፋቸው አገር ግን አላገኙም። እርሳቸውም በወቅቱ የጣና ሀይቅ ፕሮጀክት እንዲሁም ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በሚችሉበት ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ላይ ነው ትኩረታቸውን ያደረጉት፡፡
አዲስ ዘመን፦ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት አባይ አገሩን ያልማ ተብሎ ስራ ተጀምሯል ፤ ይህንንስ እንዴት ያዩታል ?
አቶ ግርማ ፦ ይህ ፕሮጀክት እንግዲህ ትልቅና አገሪቷ በራሷ አቅም የምትሰራው ብሔራዊ ኩራት ነው። እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት ነገር እነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩበት ህግና ደንብ አለ። በአገሮች ፍላጎት ብቻም አይመሩም ፤ በመሆኑም በተፋሰሱ የሚያልፉ አገሮችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን እንዳለበትም ህጉ ያዛል፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ የወንዙ አመንጪ አገር ናትና ፤ ይህም ቢሆን ግን ውሃው የእኔ ነው ብሎ ከታች ባሉት አገሮች ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳትን ማድረስ ህጉ አይፈቅድም። ስለዚህ ሁል ጊዜም ቢሆን ድርድር ይካሄዳል። የእኛ ግን የሚገርም ሆኖ ውሃውን የማያመነጩት አገራት ከእኛ ቀድመው ግድብ ገነቡ፤ ከዚያም አልፈው የውሃ ክፍፍል ህግ አወጡ። በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን ከፍተኛ ጥረት የተደረገው ይህንን አካሄድ መቀየር ላይ ነው፡፡
ይህ መሆኑ ደግሞ አውሮፓዎቹም ሆኑ አሜሪካ የግጭትና የውዝግብ መንስኤ ከመሆን ይልቅ የልማት መፍትሔ መሆን አለበት የናይል ተፋሰስ አገራት ጥናቶችን እያጠኑ በጋራ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን መፍጠር ቀጠናውን የልማት ማድረግ ይገባል በማለት የናይል ባዚን ኢንሼቲቭ ተቋቋመ። በዛ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎን ስታደርግ ቆይታለች። ይህም ቢሆን ግን ጥረቶቿ ያን ያህል ሚዛን የሚደፉና ስኬታማ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡
ይህንን ሁሉ አልፋም ነው በራሴ አቅም ግድብ ገንብቼ የልማት ጉዞዬን እቀጥላለሁ ብላ በቁርጠኝነት የገባችበት። ግብጾቹ ግን ትብብርን ባለመቀበልና በብቸኝነት እንጠቀማለን ማለታቸውም ነው እንግዲህ እስካሁን ያልተፈታ ውዝግብ ውስጥ ያስገባን።
ሌላው ከግድብ ግንባታው ጋር ተያይዞ የተፋሰስ ህግ ያስፈልግ ነበር ፤ በዚህም እኤአ በ 2010 የወንዙን አጠቃቀም የሚያመለክት የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶም ነበር። ይህ ይህግ ማዕቀፍ እያለም ነው ግብጽ ለብቻዬ ግድቡን እገነባለሁ ብላ የገባችው፡፡
ግን ይህ የግድብ ግንባታ አሁን እንዳለበት ሁኔታ ብዙ ጫጫታ ሊበዛበት የሚገባም አልነበረም ፤ ምክንያቱም በናይል ተፋሰስ ውስጥ 125 ዓመት እድሜ ያስቆጠረ የግድብ ግንባታ ታሪክ ነው ያለው፤ ግብጽ በ 1890ዎቹ ጀምሮ ነው ግድብ መገንባት የጀመረችው ፤ ሱዳን በ 1920 እና 30 ዎቹ ነው ግደብ የገደበችው ኡጋንዳ በ1940ዎቹ ገንብታለች እና ይህ ሁሉ የግድብ ግንባታ ታሪክ ባለበት አህጉር ውስጥ የኢትዮጵያ ግድብ መገንባት የሚገርምም ፤ የሚያንጫጫም ሊሆን አይገባም ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ሁሉ ግድብን የመገንባት ታሪክ ያለን አፍሪካውያን ከሆንን የኢትዮጵያ ግድብ መገንባት ለምን ችግር ሆነ ?
አቶ ግርማ ፦ ይህ ነው ዋናው ጥያቄ ፤ በርግጥ ብዙ ነገሮችን ማየት ሊያስፈልግ ይችላል በተለይም ግብጾቹ የኢትዮጵያን ልማት እንደ ስጋት ነው የሚያዩት፤ ኢትዮጵያ ወደ ልማት እንዳትገባ የሚችሉትን ሁሉ ነው የሚያደርጉት። እነሱ የግድብ ግንባታው በውሃ ፍላጎታቸው ላይ የሚያመጣው ጫና እንደሌለ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ግን ስጋታቸው አገሪቱ ግድቡን ገንብታ አንድ እርምጃ ማደግ ከቻለች ነገ ሌላ ግድብ ለመገንባት ትበረታታለች ያ ደግሞ ኢኮኖሚዋን ያሳድገዋል የሚል ነው ስጋታቸው። ስለዚህ ወደዚህ እንዳትገባ እናቁማት ነው አላማው። ይህ ስጋት ግን በቂ ምክንያት አለው ወይ የሚለው መጠናት ያለበት ነው። ምክንያቱም በመርህ ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ ህግም አይፈቅድላትም። የምትከተለው መርህም ፍትሀዊ የውሃ አጠቃቀም በተፋሰሱ አገራት ላይ እንዲሰፍን ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት በናይል ወንዝ ላይ ብዙ ግድቦች ተገንብተዋል ግን ምንም ዓይነት ነገር ኮሽ ሳይልባቸው ነው የጨረሱት። ኢትዮጵያም ለምን ገነባችሁ ብላ አታውቅም፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የህዳሴው ግድብ ምን ያህል የኢትዮጵያ ህልውና እንደሆነስ እኛ ዜጎቹ ተገንዝበነዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ግርማ ፦ አሁን አሁን ይመስለኛል በተለይም ከአንድ አስርና አስራ አምስት ዓመት ወዲህ ጥሩ ግንዛቤ አለ፤ እንዲህ ያለ ግብብን በራስ አቅም በአፍሪካ ደረጃ የማይታሰብ ነው፤ ህዝቡ አንድነቱን መንግስትም በከፍተኛ ሁኔታ ቁርጠኝነቱን ያሳየበት ነው። ይህ ደግሞ ለግብጾች ኢትዮጵያ በዚህ ልክ በራሷ በአቅም ይህንን ግድብ ከገነባች ለሌሎችም አርአያ ትሆንብናለች፤ ተቀናቃኝም ታበዛብናለች የሚል ስጋት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
አዲስ ዘመን ፦ ግብጾች ከተወለደው ህጻን ጀምሮ አባይ አስትንፋሳቸው እንደሆነ እያስተማሩ ነው የሚያሳድጉት፤ እርስዎ ደግሞ በዚህ ሃሳብ እንደማይስማሙ በመጽሀፍዎት ላይም ገልጸዋል፤ ለምንድን ነው የማይስማሙት?
አቶ ግርማ ፦ አባይ በአንድ ወቅት ለግብጾች እውነት ነው እስትንፋስ ነበር አሁን ላይ ግን እንደዛ አይደለም፤ አሁን ያለው የኢኮኖሚ አካሄድ ተለውጧል። የግብርናው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በግብርናው ላይ የተሰማራው ሰውም 20 በመቶ ቢሆን ነው። አሁን ትኩረታቸው ወይም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተሸክሞ ያለው የአገልግሎት ዘርፉ ነው። ኢንዱስትሪውም እንደዛው። ውሃ ጭራሽ አያስፈልጋቸውም ባይባልም እንደሚባለውና እንደሚቀነቀነው የሞት ሽረት ጉዳይ ግን አይደለም። ከእነሱ በላቀ ሁኔታ ውሃው ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው፡፡
ውሃው ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ሲባል ደግሞ ሃይል ለማመንጨት ብቻ አይደለም፤ ግብርናው ውስጥም ሊገባና ልማት ላይ ሊውል ይገባል። እኛም እንደነሱ በምግብ እራሳችንን መቻል አለብን። አሁን እኮ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ድርቅ እንኳን ባይገጥማት 5 ሚሊዮን በሴፍቲኔት የታቀፈ ህዝብ አላት ። ስለዚህ እነዚህን ሰዎች መመገብ በየጊዜው እያደገ የሚመጣውን የህዝብ ቁጥር ስራ ማስያዝ መመገብ አለብን ለዚህ ደግሞ ግድባችን ወሳኝ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ግብጾች ለ 1959 ዓ.ም
ስምምነት ትልቅ ቦታ ይሰጡታል ፤ እርስዎም በመጽሀፎ አስፍረውታል እስኪ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ነገር ይበሉን ?
አቶ ግርማ፦ ስምምነቱ በመሰረቱ ህገወጥ ነው፤ በተፋሰሱ ያሉ ሀገሮች ምናልባት 10 ወይም 11 ናቸው፤ ስምምነቱ የተካሄደው በሱዳንና በግብጽ መካከል ነው። ይህ እራሱ ውሉ በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት እንዲያጣ ያደርገዋል።
በሌላ በኩል ይህ ስምምነት መሰረት ያደረገው ምን ላይ ነው ያልን እንደሆነ ቅኝ ገዢዎች ያመጡት ፤ እንግሊዝም ቅኝ ተገዢዎቿን በመወከል ያካሄደችው ድርድር ነው። ይህ ደግሞ ከቅኝ ገዚዎች መክሰም ጋር አብሮ የከሰመ ነው። በህግ ፊትም ሄደው ውጤት የሚያመጡበት አይደለም፡፡
ግብጾች ይህንን ስምምነት እንደ ትልቅ ነገር አድርገው እንዲያወሩ ያደረጋቸው ሌሎቹ አገሮች ደካማ መሆናቸውና መፈተን ስላቃታቸው ነው። ግብጾች አሜሪካ ታሸማግለን ምናምን እያሉ ፖለቲካዊ ጨዋታ ውስጥ ይሄዳሉ እንጂ ፍርድ ቤት ይዘው አይሄዱም። ምክንያቱም የህግ መሰረት እንደሌላቸውና እንደሚረቱበት ያውቃሉ።
አዲስ ዘመን፦ በ 2010 ላይ የተፈረመው ስምምነትስ ምን ገጽታ አለው?
አቶ ግርማ፦ የሁሉም ነገር መሰረቱ ይህ ነው፤ ግብጾች ያረጀ ያፈጀው ስምምነት ነው የሚገዛን ሲሉ ኢትዮጵያ ደግሞ የ 2010 ሩ ስምምነት ነው የሚገዛኝ ትላለች፤ ግብጽ በ 2010 ተሸንፋ ስምምነቱን ረግጣ የወጣችበት መንገድ ትልቅ የሆነ ውድቀት ላይ ነው የጣላት፤ አሁን የህዳሴው ግድብ ድርድር ምናምን እያሉ ሌላ ዙር በመፍጠር ይህንን ስምምነት የሚሽር ሌላ ውል ውስጥ ሊከቱን እየሞከሩ ነው፡፡
የዓለም ባንክና የአሜሪካ አደራዳሪነት የተፈለገውም ከ2010 ስምምነት ጋር የሚጋጭ ስምምነት እንድንፈርም ነው። ከዛ በኋላ የህግ መሰረቱን ያጣል ማለት ነው። ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ህግ ከኋላ የመጣ ህግ ተቀባይነት የሚኖረው ስለሆነ የ2010 ስምምነት ይዘን መሟገት አንችልም። በመሆኑም ኢትዮጵያ ጠንከር ብላ ስምምነቱን ያልፈረሙትን አገራት ወደ ፊርማ ማምጣት ብትችል ግብጽ የግዷን የዚህ ስምምነት ተገዢ ትሆናለች።
አዲስ ዘመን ፦ የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት (ናይል ባዚን ኢኒሼቲቭ) ሚናው ምንድን ነው?
አቶ ግርማ ፦ ይህ ተቋም ጊዜያዊ ነው። አገራቱ ተስማምተው ቢፈርሙ እርሱ ይቀርና ኮሚሽን ይቋቋማል፤ ኮሚሽኑ ደግሞ ሁሉንም ማስተዳደር ስለሚችል በአንድ አካል ስር የሚመራ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መካከል ደግሞ አንድ አገር ተነስቶ ለምሳሌ ህዳሴ ግድብን እሰራለሁ ብላ ኢትዮጵያ ብትነሳ በተናጥል ውሳኔ መወሰን አትችልም። ጥያቄዋ በኮሚሽኑ ዕውቅና ውስጥ ነው የሚያለፈው፤ አዋጭነቱ እየታየ በሌሎች ላይ ጉዳት አለማድረሱ ተረጋግጦ በህግ ውስጥ ሆኖ ይተገበራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ኮሚሽን እንዲቋቋምና የተፋሰሱ አገራት በተለይ ያልፈረሙት ወደ ፊርማ እንዲመጡ ማስተባበር ያለባት ኢትዮጵያ ናት እንዴ?
አቶ ግርማ ፦ ማስተባበር ያለባት ኢትዮጵያ ናት፤ ትልቁ ድክመታችንም ይህ ነው። መጀመሪያ የናይል ተፋሰስ አገራት ኢኒሼቲቭን እያስተባበርን ነበር። የህዳሴው ግድብ ሲመጣ እሱን እርግፍ አድርገን በመተው ድርድሩን ሶስት አገሮች ላይ አድርገን ቁጭ አልን። እኛ እኮ እንኳን ሌሎቹን ልናስተባበብር ግብጽ በየጊዜው የተለያዩ ጥያቄዎችን እያመጣች ለእሷ መልስ በመስጠት ጊዜያችንን እያቃጠልን ነው።
አሁን እንኳን አትመለከችም እንዴ ከሙሌቱ ጋር ተያይዞ ምን እያሉ እንዳሉ፤ እኛ ደግሞ ለእነሱ መልስ ለመስጠት የሳት ማጥፋት ስራ ስንሰራ ዋናውን የማስተባበር ስራችንን ወደጎን ብለን ነው ያለነው። እኛ ማድረግ የነበረብን የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት አገራቱን አስተባብረን አስፈርመን ግብጽን ወደ ጠረጴዛ ድርድር ማምጣት ነበረብን፡፡
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ ግብጽ በተለያተዩ ጊዜያት እያሳየችው ያለው ተለዋዋጭ አቋም ጠቅሟታል ማለት ይቻላል?
አቶ ግርማ፦ አዎ ጠቅሟቸዋል እንጂ፤ እኛ መስራት የሚገባንን ያህል እንዳንሰራ አድርጎናል። እንደጅምሩ እስከ አሁን እኮ ኮሚሽኑ መቋቋም ነበረበት፤ በዚህ ደግሞ የተፋሰሱ አገራት ተስማምተው ልማታቸውን በጋራ እየተመራ ሥርዓት ውስጥ ይገባ ነበር። ግን ወደዛ እንዳይኬድ ስድስት አገሮች መፈረም አለባቸው ብሎ ቅደመ ሁኔታ ስለሚያስቀምጥ ይህንን እንዳናደርግ አድርገውናል።
ግብጽ እኮ የናይል ተፋሰስ አገራት ትብብርን አልፈርምም ብላ የወጣች እኮ ናት። ከዚህች አገር ጋር እኮ ነው ኢትዮጵያ መልሳ ድርድር ብላ የጀመረችው። ይህ ሁኔታ በጣም አስገራሚ ከመሆኑም በላይ አሁን የተከሰተው ነገርም የሚጠበቅና ምንም የማይገርም ነው፡፡
እኔ ከሶስት ዓመት በፊት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ታህሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም “አዝጋሚውና ውጤት አልባው የህዳሴው ግድብ ድርድር “ በሚል ግብጾች ምን እያደረጉ እንዳሉ ፣ እንዴት እያዘናጉን እንደሆነ ከመሰረታዊው ሂደቱ እያስወጡን የማይሆን ነገር ውስጥ እየከተቱን እንዳሉን ተናግሬ ነበር። በግብጾች የሚቀመርብንን ጨዋታ አቁመን ወደ ናይል ተፋሰስ አገራት ስምምነት ብንመለስ ነው የሚሻለው በማለት ጽፌያለሁ። ይህንን ስንመለከት ግብጽ እቅዷ ሁሉ ተሳክቷል ለማለት ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ከበቂ በላይ ትምህርት ልትወስድ የሚገባት ጊዜ ላይ ናት፤ ከዚህ በኋላ ባለው አጋጣሚ ሁሉ እነሱን ተጭነን ወደ ሥርዓት የሚመጡበትን መንገድ እንጂ የእነሱ ተከታይ መሆን መቆም አለበት።
ግብጽ እኮ እኛ ደካማ ሆነን ስላገኙን ነው እንጂ እንዲህ አይሆኑም ነበር፤ ለምሳሌ ይህ ተፋሰስ እንዲሁ ኮሚሽኑም ሳይቋቋም ከተለቀቀ እኮ ሁሉም በየፊናው ውሃውን ወደመቀራመት ነው የሚሄደው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ዳር ላይ ላለችው ግብጽ አደጋ ነው ፤ ስለዚህ በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ አስገዳጅነት ኢትዮጵያ ወደምትለው ስምምነት ገብተው በህግና በሥርዓት የሚተዳደር ተፋሰስ መኖሩ ከማንም በላይ የሚጠቅመው እነሱን መሆኑን አውቀው ቢሄዱ ነው የሚሻላቸው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ወደፊት በተለይም ከግብጽ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ምን መልክ የሚኖረው ይመስልዎታል?
አቶ ግርማ ፦ ከዚህ ወዲህ ከግብጽ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ጤናማና ሥርዓት የያዘ ነው የሚሆነው፤ አንደኛ በህጋዊ ሥርዓት ውስጥ ሁላችንም እየገባን ነው። ሁለተኛ ውሃውንም በራስ አቅም ገድበን መጠቀም የምንችል መሆኑን አሳይተናል። ከዚህ አንጻር እንደ ድሮ እንደ አንድ ደካማ አገር ሲያረጉን እንደኖሩት ሊያደርጉን አይችሉም። አሁን ታሪክ ተለውጧል። በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ውስጥ ለመግባት ይገደዳሉ፡፡
በነገራችን ላይ እኮ ይህ ውሃ ለቀጣዮቹ ዓመታትም እንዲኖር ለማድረግ የግብጽም ሚና ሊኖር ይገባል ። አካባቢውን በመንከባከብ ዛፍ በመትከል የተራቆቱ ቦታዎችን በመንከባከብ ላይ መጥተው መሳተፍ አለባቸው ፤ ይህንን ባላደረጉ ቁጥር እኮ ተፈጥሮም ልትጨክን ትችላለች፤ ስለዚህ ግንኙነታችን እስከለዚህ ድረስ መድረስ ያለበት ነው።
ወደ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከመጣንም ለምሳሌ ለሱዳን እነሱ ቆጥረው የሰጧት 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ኩቢክ ውሃ ነው ፤ እሷም ኢኮኖሚዋ ደካማ ስለሆነ እየተጠቀመችበት አይደለም። ግን የህዳሴው ግድብ መገደብ ለሱዳን ትልቅ አቅም ነው የሚፈጥረው፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ብዙ ውሃ ሄዶ ካርቱምን በጎርፍ ያጥለቀልቃትና ለበርካታ ቀውስ ይዳርጋት ነበር። የህዳሴ ግድብ ግን የተመጠነ ውሃ ዓመቱን ሙሉ እንድታገኝ ከማድረጉም በላይ ዓመቱን ሙሉ የግብርና ስራ መስራት ያስችላታል። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ አገናዝበውና ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ጥሩ ሚናቸውን ተጫውተው ወደ ትብብር መምጣት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ግድቡን አስመልክቶ ለህዝቡም ለመንግስትም ሊሉት የሚፈልጉት ነገር ካለ እድሉን ልስጥዎ፤
አቶ ግርማ፦ ህዝቡም መንግስትም በጋራ ተባብሮ ግድቡን እዚህ አድርሰነዋል። አሁን የቀረን በጣም ጥቂት ነው። ከመቀዛቀዝና ተስፋ ከመቁረጥ ወጥተን መጀመሪያ ሲጀመር በነበረበት ስሜት መረባረብና ማጠናቀቅ ይገባል። ይህ ሲሆን ሁላችንም አሸናፊዎች እንሆናለን፤ ዘመናት ጥረታችንም ፍሬ ያፈራል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ግርማ፦ እኔም አመሰግናለሁ ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
እፀገነት አክሊሉ