በዘመን መካከል ሌላ ዘመን አለ፤ ያልተጠቀሙበት፤
ያ ያለፈ ለታ፤ እጅግ የሚያዝኑበት፡፡
የሚል ስለዘመን የተጻፈ ግጥም አስታውሳለሁ።ዛሬን መኖር የምንጀምረው በዛሬው ገጻችን ነው።ነገን ደግሞ ለራሱ ለነገ ትተን ነው፤ የምንቆመው።ነገ የራሱ ክፋት ይበቃዋል፤ እንዲል ትልቁ መጽሐፍ፡፡
ጽሑፌ የሚያተኩረው ትናንቷን በምትወቅስና ዛሬዋን በትናንቷ የምታጥፋፋ ነፍስ በቅርቡ ገጥማኝ እንዲህ ስትል ነግራኝ ነበረ፤ እናም እንደ ወረደ አቀርብላችኋለሁ፡፡
ከተወለደች በኋላ ሁለት ቤተሰቦቿ፣ እናትና አባቷ ተለያይተው በየፊናቸው በመሄድ እናት ለእናቷ (ለልጅቱ አያት) ልጇን ሰጥታ በመተው ለአጭር ጊዜ ትቷት ከቆየው አባቷ ተነጥላ እንድታድግ በማድረጓ፤ አባቷንም እናቷንም እንደማታውቅና ምነው እናቴ በኖረችና ባወቅኳት የምትል ልጅ ናት፡፡
አያቴን ጠይቄያት እንደነገረችኝ፣ አባቴ አንድ ቀን መጥቶ ሲጠይቀኝ፤ መሞትሽን ነግሬው ዳግመኛ መጥቶ አልጠየቀኝም።እርሱ ከሄደ በኋላ ፀፅቶኛል፤ ግን እርሱም ጥረት ስላላደረገ በዚያው ቀረ ብላኛለች።ስለእናቴ ስጠይቃት ሰካራምና ምሬት በሕይወቷ የሞላ ስለነበረ አንድ ቀን ተነስታ ዓረብ ሀገር እሄዳለሁ ብላ ወጥታ አልተመለሰችም፤ ይኼው አንቺም አድገሽ 21 ዓመት አለፈሽ አለችኝ፤ ስትል ነገረችኝ፡፡
አሁን ምን እያደረግሽ ነው አልኳት፡፡
«ቆንጆ ቡና እያፈላሁ እየሸጥኩ ነው፡፡»
«መጥቼ ቡናሽን እጠጣለሁ።ግን የት ጋ ነው፡፡»
አድራሻውን ነገረችኝ፡፡
እና…አለችኝ ቀጥላ…. ልጄን በጣም እወዳታለሁ፤ ከዓይኔ ስር ሳጣት ይጨንቀኛል፤ እናቴ ግን እንዴት ሊጨንቃት እንዳልቻለ አይገባኝም፤ እንዴት አስችሏት፣ ዝም አለች ያልኩ እገረማለሁ፤ አለችኝ፤ እርሷ ለልጇ ያላትን መንሰፍሰፍ አነጻጽራ፡፡
እናትሽ የነበረችበትን አስጨናቂ ሁኔታ አያትሽ በጥቂት ቃላት ገልጸውልሻል።መጠጥ አዘውታሪ ነበረች፤ ምናልባትም ተጨማሪ ሱስ፣ እንደ ጫት ሲጋራና አደንዛዥ እጽ ልትወስድ ትችላለች።አየሽ፣ ከእነዚህ ሱስ አስያዥ ነገሮች ሁለቱ ማለትም ጫትና ሲጋራ እንኳን የራሳቸው የሆነ ሰውን በዓመሉ የማሰር ልምድ አላቸው።
ጫት በባህሪው ቃሚውን ለመቃም ሰዓት አክባሪ አድርጎ ለሥራ ሰዓት አክሳሪ የሚያደርግ፣ ለማህበራዊ ኑሮ ደንታ ቢስ የሚደርግ፣ ጤናን ዕረፍትን ግንኙነትን የሚያውክ እፅ ነው።አንዳንዶች ጫትን ብዙም የማይጎዳ እንደሆነ አድርገው ሊያቀርቡት ይችላሉ።ጫቱን ለመቃም ከምትወስጂው ጊዜ እስከምትቀመጪበት ስፍራና እስከምታሳልፊው ጊዜ እንዲሁም ተዳባይ ጠባያት ጋር የራሱ ጎጂ ነገሮች ያሉት ነው።
በዚህ ብቻ አያበቃም፤ የምትውያቸው ሰዎች መሰል ቃሚዎች በመሆናቸው ዓለምሽ ጠባብ ነው፤ በእነርሱ ዙሪያ ስለምትውይና ስለምታመሺ፣ ወይም ለየት ያለ ትኩረት ስለምትሰጭ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል ታገልያለሽ፤ አንዳንዴም አንቺን የማይረዱሽ አድርገሽ ትስያቸዋለሽ።ስለዚህ ምስኪንነትሽን በመካድ ሌሎችን በማመስከን ትለውጪዋለሽ።ስለዚህ ቃሚ ራሱን በጊዜና በስፍራ ያሰረ ምስኪን ነው፡፡
ማሰር ስትል….?
በሱሱ ከተያዝሽ በኋላ ሱሱ ያዝሻል እንጂ አንቺ ሱስሽን አታዢውም።‹‹አምጣ አምጣ›› የሚል ጠያቂና ጎትጓች አሳሪ መንፈስ አለው።በዚህ ወቅት ስለእናትሽ፣ ስለአባትሽ፣ ስለልጅሽ፣ ስለሥራሽ፣ ስለሚጠብቅሽ ትልቅ ጉዳይ ሳይሆን የምትጨነቂው ዋናው ጉዳይሽ ጫቱ ሲጋራውና ሌሎቹ አጋዥ ነገሮች ናቸው የሚሆኑት።ራስሽን ለማጽናናት ታዲያ ማንንም አልነካሁም ስለዚህ ማንም እንዲነካኝ አልፈልግም ማለት ታዘወትሪያለሽ፡፡
ለምሳሌ ያህል፣ ቤታችሁ ውስጥ ለቅሶ ቢኖርና ሱሰኛው ለሱሱ የመደበው ጊዜ ወይም ሰዓቱ ሲደርስ ሱሱን ለመወጣት ከቤት ወጥቶ ይሄዳል፤ ቀብር እንኳን ቢኖር አያቃብርም፤ ወይም ላይሄድ ይችላል።በራሳቸው ሠርግ ላይ እንኳን ሰዓቱ ሲደርስ የሚቅበጠበጡ ሙሽራዎች ገጥመውኛል።እንዲያውም የሠርጉ ግርግር ባይኖርስ ከማለት አልፈው፣ ሠርግም ባይኖር የሚመርጡ ናቸው፡፡
ስለዚህ በሱስ የመያዝ አደጋ፣ ልጅ ያስረሳል፤ ቤት ያፈርሳል ኑሮ ያበላሻል፤ ቤተሰብ ያናጋል፤ ከዚህ ሁሉ በፊት ግን በቅድሚያ ሰውየው ራሱ ይናጋል።
ስለዚህ እናትሽ፣ በዚህ ዓይነት ኑሮ ውስጥ ከነበረች ላንቺ ደንታ ባይኖራት አትፍረጂባት፤ ራሷን እንኳን መቆጣጠርና ለራሷ መልካም የማታስብ ሰው እንዴት ሆና ለሌላ ሰው ቀናና ደግ ታስባለች? ኃላፊነትንም ትቀበላለች? ብለሽ ታስቢያለሽ? ስለዚህ፣ የእናትሽ ችግር ስለማርገዟም ያለማወቅ ወይ አርግዛም ደንታ ያለመኖር፣ ወይም የእርሷ ብጤ ጓደኞች ግፊትና ጸጸት ተደማምረው ባንቺ በራሷና በቤተሰቡ ላይ ደንታ ቢስነት ፈጥሮባት ይሆናል፡፡
አየሽ፣ የኔ እናት፣ አልኳት ልጂቱን፣ አንቺ አሁን ለልጅሽ ያለሽ ፍቅር ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እግዚአብሔር በእናቶች ውስጥ ያስቀመጠው ፍቅር ነው።ማንኛውም ሰው በተፈጥሮው የተቀመጠለት ብሩህ ህሊና ሚዛናዊ አእምሮ አለው።ሱሰኛ ስትሆኚ ያ፣ አእምሮ በትክክል መስራት ስለሚያቆም በራስሽም ላይ ኢፍትሃዊ ነገር ያሰራሻል።ስለዚህ ጥፋቱ ትክክል፣ አስቀያሚው ቆንጆና ተገቢ መስሎ ይሰማሻል፡፡
እኔ የምለው ታዲያ ሰው ለምን እንዲህ ያደርጋል? አለችኝ፡፡
ሰው ወደሱስ የሚሄደው፤ አንድም ጓደኞቹን ለመምሰል፤ አለዚያም የሰለጠነ መስሎ ለመታየት፤ አራዳ የሆነ ስለሚመስለው፤ ቀልድ ለመፍጠርና ከአካባቢው የዕድሜ አቻዎቹ ወይም ታዋቂዎቹ ሰዎች ጋር ለመመሳሰል ሲል ለመስማማት ሲሆን በሌላ በኩልም በሕይወት ውስጥ ያስከፋቸውን ነገር ለመርሳትና በመሳሰሉት ነገሮች ግፊት ነው፡፡
እና…. ሰውን ለመምሰል ሰው ከራሱ ይወጣል?
በሚገባ….«ትሪፕ» የሚባል ነገር አለ አይደል? አሁን ደግሞ ‹‹ዴይ ፓሪ›› አለ …‹‹ቲኔጅ ፌር›› ይሉታል።«ብሎክ ፓርቲ» (ልክ እንደ ብሎክ ኮርስ) እየተባለ ይጨፈራል፣ ይደነሳል፤ ‹‹ይቀወጣል›› (ጭንቅላት ውስጥ ፍዘት ይነግስበታል) እና እንዲህና እንዲያ ይደረጋል፡፡
ለዚህ ነው ጭንቅ ያለው ሰው ፤……..
«የለህም እንዳልል ያው ነግቶ ይመሻል፣
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፤
ሰዶም ከገሞራ ሀገሬ ላይ በቅሏል›› ብሎ የገጠመው፡፡
እና መፍትሄው ምንድነው አለችኝ።የያዝሽውን ጠበቅ አድርጊና ያዢ።ባለቤትሽን አፍቅሪው፤ አክብሪውና ደግፊው።አልኳት፡፡
ቢጠላኝስ?…ብዬ ፈራለሁ።ጥሎኝ ቢሄድስ ብዬ እሰጋለሁ፤ እና ልጄን ያላባት ማሳደግ ያሳስበኛል፤ አለችኝ።አንቺ ያላባትና እናት አድገሻልና፤ ዓለሙ ሁሉ አድመኛ ይመስልሻል፤ አይደል? እንዲያ ግን አይደለም።የሰው ልጅ ወላጁን በክህደት ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ መልክና ጦስ ሊያጣ መቻሉን አስቢ፤ መለየት በምንም ይሁን በምን የምቀበለውን ያክል በመጣላትና በመለያየት ወይም በሌላ ምክንያት በማይመስለን ሰበብ ሁሉ አንድ ሰው ሌላውን ጥሎ ሊሄድ ይችላል፤ ብለን እናስብ።ግን ሁልጊዜ እንዲህ አይደለም፤ የተደላደለና የተሻለ ቤተሰብ መመስረትን ማንም አይጠላም፤ ሰው በመንፈስና በአካል ጭምር ትዳሩን የተቀበለ ሲሆን ችግሩን ለመቀበል ቀላል ነው።ካልሆነ ግን ያልተዘጋጀ አእምሮ ላልታሰበ ፍጻሜ ምክንያት ሊሆን እኮ ይችላል።እና…ባለፈ ነገርሽ አትታሰሪ።ይህን ጉዳይ ደግሞ በግልጽ ከባለቤትሽ ጋር ተነጋገሪበት፤ ሰልቂውና ፍጻሜ ላይ አድርሽው እንጂ፤ ባለፈ የኑሮ ፋይልሽ አትታሰሪ።እንኳን አንቺ ባልፈጸምሽው ይቅርና የፈጸምሽው ያለፈ ሕይወትሽ አሻራ እንዳይጎትትሽ፤ አልኳት፡፡
እኛ የምንደርስበት የሃሳብ እስረኞች ሳንሆን የሐሳባችን ፈጻሚዎች ነን፤ ደግሞ በደስታ ለመኖር እንጂ በይሆናል እየተጨናነቅን ለመፍገምገም አልተፈጠርንም።
ፈጣሪ የሰው ልጆችን እንደፈጠረ ሁሉ፣ አንቺንም ውብና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮሻል፤ ፈጥሮናል፤ እንዴት አሳምሮ እንደሰራን ማሰብ ትተን ልንወድቅ ስለሆነ አንገባበትም፤ ላይሳካ ስለሚችል አንጀምርም፤ የምንለው መልካም ነገር አይኖረንም።በእግዚአብሔር የተወደደ የታቀደና ሊፈጸም የሚገባውን መልካም ነገር ሁሉ ልንጠብቀው ልንይዘውና ልናደንቀው እንጂ ይሰበራል፤ ይወድቃል፤ ይበላሻል፤ እያልን ልናሳንሰው ስጦታውን ልናንኳስሰው አይገባንም።ልብ ብለሽ ራስሽን እይውና ወደውስጥሽ «አምላኬ ሆይ! እንዴት ውብና ድንቅ አድርገህ ፈጥረኸኛል!!» ብለሽ አመስግኝው።
አመስጋኝ ሕይወት ካለን ከምናጣው ይልቅ የምናገኘውና ያገኘነው እንደሚበልጥ አንጠራጠር። ከተሰጠን ይልቅ የጎደለንን ካየን ወደፊት እልፍ ማለት አይሆንልንም!!
ተነሽና ተራመጂ፤ ልጅሽን በደመነፍስ ሳይሆን በፍቅር እቅፍ አድርጊያት፤ አለሁልሽ በያት፤ ባለቤትሽንም እንዲሁ ንገሪው…እንኳንስ የሰው ልጅ ፍጥረታትም አበቦችና ተክሎችም የፍቅር ቋንቋ ይገባቸዋል።
የጃፓን የአትክልት ሳይንቲስቶች በቅርቡ የጥናት ውጤታቸውን ይፋ እንዳደረጉት የማይሰሙን የማያውቁንና እንዳሻን የምንቆርጥ የምንነቅላቸው እጽዋት እንኳን መልካምነትን ያውቃሉ።በእንክብካቤ እንደያዝናቸው ያወቁ ተክሎች ብዙ ከማፍራታቸውም ሌላ አበቦች ከሆኑም ጸዳላቸው ከሩቅ የሚያበራ ይሆናል።በተቃራኒው ደግሞ ያጎሳቆልናቸውና ክፉ ቃል ያወጣንባቸው ተክሎች ይጠወልጋሉ፤ እንኳንስ በፍሬ ለእይታም ያስጠላሉ ሲሉ በጥናታቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
እኛም ፍቅርን በመቀባበል በቤታችንና በደጃችን በሥራ ስፍራም ማድመቅና ፍሬያማ መሆን ይገባናል፤ ባለፈ የጥላቻ ቁርሾ፣ ባለፈ ጸብና የነገር እርሾ፣ ባለፈ ቅያሜና የቤት አዳፋ ታሪክ አንገፋፋ፤ ሕይወታችንንም አናድፋፋ፤ በቀደመው አሮጌ ነገራችን ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነው በሚባለው ትዝታችንም አንታሰር፤ «ያለፈው አልፎ ሆኗልና፤ ዳግም ላይመለስ ሄዷልና፤» የጥንቱን ክፉ ማገላበጥ፣ የትም አያደርሰንም፤ ትርፉ መፋጠጥ ነው።እርሱን እንርሳው፤ ባንረሳውም አናስታምመው፤ እሽሩሩ አንበለው፤ ወደ ፊትና ወደ መጪው እንዘርጋ፤ በተለይ ክፉ ትዝታ ቸክሎ ያስቀረናልና፣ ከቶውንም ዛሬዬን አትነጥቀኝም እንበለው፤ ልጅቱም እየገረማት ሄዳለች፤ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን መልከ-ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፤ እኛን ባለፈ ነገራችን የሚያስሩን።
በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ቀና ቀና ስንል፣ እንድናጎነብስ ለመስራት፣ ለመኖር፣ ለመለወጥ ስንነሳ ተከታትለው የተረሳ እና ድሪቶ የሆነ «አሮጌ ፋይላችንን» እየመዘዙ ወደኋላ የሚጎትቱን ሰንካዮች በዙሪያችን አሉ።እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ራሳቸውም አይሰሩም ወይም ሌላውን አያሰሩም ከኋላ ቆመው ፊትህን በነገር ጥፊ ያጮሉታል።
እርሱ ማነውና ቀና ቀና ይልብናል፤ አናውቀውም እንዴ? ባለፈው በስካር እየተንገዳገደ አጥር ዘላለሁ ብሎ እግሩን ተሰብሮ የተኛ አይደለም እንዴ? እዚህ ድረስ እውነት ቢሆን እንኳን አንተንም ሰብዕናህን ማውረድ የፈለገው ሰው፣ ቀጥሎ፣ በጓደኞቹ ከመኪና ተገልብጬ ነው፤ የተሰበርኩት አስብሎ መዋጮ በመስሪያ ቤት እንዲዋጣለት ሁሉ አድርጓል፤ ብሎ ነው፤ ባህሪህን አክፋፍቶ መሬት ለመሬት የሚጎትተው።በትንሿ እውነት ላይ ወፍራም ውሸት ካልጨመረበት ወሬው ውሃ አያነሳለትማ፤ ካልቸለሰበት «ጉደኛ የተባለው ሰው ጉድ» ክብደት አይኖረውማ።
እነዚህ የሌላን ሰው ያለፈ አሮጌ ፋይል መዛዦች የራሳቸው ፋይል ቢመዘዝ ሰው በእንጨት ሊነካቸው የሚጸየፍ ሆኖ ሣለ፣ የሰውን «ጉድ በመዘክዘክ» ኤክስፐርትነታቸው «የረቀቁ» ናቸው።አንድ ወዳጄ እነዚህን መሰል ሰዎች «ሙያዊ ነካሾች» (Professional back-biters) ይላቸዋል።እነዚህ ሰዎች፣ ስለአንድ ሰው መዘልዘል ከጀመሩ …ኢኮኖሚካሊ፣ ሳይኮሎጂካሊ፣ ኤትንካሊ፣ ጂኦግራፊካሊ፣ ሪሊጂየስሊ፣ ሜዲካሊ…. ወዘተ… እያሉ አንድም አይቀራቸውም፡፡
የተሾመው ስለሚችል እና ሥራውን ስለሚያስኬደው ሳይሆን የእንትን ቢሮ ኃላፊ የሰፈሩ ልጅ በመሆኑና ቡናና ሻይ አብረው ስለሚጠጡ ነው፤ (ጂአግራፊካሊ) ይልና በሥነ-ልቦና ረገድ የተረበሸ የማይረባና ራሱን መቆጣጠር የማይችል ከንቱ ሰው ነው፤(ሳይኮሎጂካሊ) ብሎ ይቀጥላል።ድሮ በነበረው መስሪያ ቤት፣ ለልጆች ዳቦ የተዋጣ ገንዘብ ወደኪሱ የከተተ «ሙሰኛና የአበል ገንዘብ የሚወድድ»፣ (ሶሺዮ-ኢኮኖሚካሊ)መናገር ብቻ እንጂ መስራት የማይችል ብኩን ሰው ነው፤ ወላጆቹ ያላቸው ቢመስሉም በባንክ ዕዳ ንብረታቸው ለጨረታ በቅርቡ የቀረበ «የችጋራም ልጅ» ነው፤ (ኢኮኖሚካሊ) አሁን እሱ ይህንን ድርጅት (መስሪያ ቤቱ የመንግሥት ቢሆንም) በሐራጅ እንዲሸጥ ካላደረገው ምን አለ ትለኛለህ? ይላሉ።የሚጥል ህመም እንዳለበት ሿሚው መስሪያ ቤት እኮ አያውቅ ይሆናል(ሜዲካሊ) ይሉሃል።
የሚገርመው ከሰውየው ጋር ድንገት መንገድ ላይ ቢገናኙ በሁለት እጃቸው ጎንበስ ብለው ሰላምታ የሚሰጡና ቀና ብለው የማያወሩ አስመሳይ ትህትና የሚታይባቸው፣ ሲመቱ እንጂ ሲወርውሩ የማይታዩ የክፉ መንፈስ እጆች ናቸው።እነዚህ የሀሜት ሊቃውንት፣ ተሳክቶላቸው፣ መጣል ባይችሉም ያንገዳግዳሉ፣ ማፍረስ ባይቀናቸውም ይሰነጥራሉ፤ ማዋረድ ባይሳካላቸውም ነክሰው ለነካሽ አሳልፈው ይሰጣሉ፤ ያብጠለጥላሉ።እነዚህ የአረጀ ፋይል ጎታቾች፣ ከሰውየው ጉድለት ቢያጡ-ቢያጡ «አጎቱ እኮ ሰካራም ነው፤» ይሄን ሰውዬ ፍሪጁን ብትከፍተው አረቄ ከውስጥ አይታጣም ፤ ይሉታል፡፡
በነገራችን ላይ ስም አጥፊዎች ስም የሚያጠፉት በተቻላቸው መጠን ለሌላ ስም አጥፊና ከእነርሱ በሰብእና የወረደ ሰው ፈልገው እንጂ ዝም ብለው አይተረተሩም።እውነተኛና ሐቀኛ ሰው ድንገት ገጥሞ ሊከራከራቸው ተጠየቃዊ በሆነ መንገድ ሊሞግታቸው ስለሚችል በእነርሱ ግምት ዝም ብሎ አዳማጭና ተገራሚ ክፉ ወሬያቸውን ያለጥያቄ የሚጋትላቸው ለምንና እንዴት ብሎ የማይጠይቅ ሰው ነው የሚፈልጉት፡፡
ስለዚህ አንተ የሰው አሮጌ ፋይልም ሆነ ሐሜት የምትሰማ ሰው ሆይ! ሐሜተኛው ወሬውን የሚነግርህ አንተንም ስለሚንቅህና ተላላኪው ሊያደርግህ ስለወደደ መሆኑን እንድታውቅ እንጂ፣ ሐሜተኛው በሚያከብራቸውና በሚፈራቸው ሰዎች ፊትማ ማስረጃ ያለው የሚመስል ወሬ እንኳን ለማውራት ይቆጠባል።ስለዚህ ሐሜት ሲጀምር፣ «ለማን እያወራህ እንደሆነ አውቀሃል?» ብለህ በለውና አስደንግጠው።ያኔም ያቆማል።
እናንተ ያረጀ ፋይል ቀለም ተቀብቶ የሚወረወርባችሁ ወዳጆቻችን አትረበሹ።ወሬኛው ካንተ ጀርባ የሚያወራው አንተን በመጉዳት ከቆምክበት ቦታ ሊያወርድህ እንጂ ባለፈ ስህተትህ ሊወቅስህና ሊያርምህ አይደለምና ይህንን ተገንዝበህ ለአሮጌ ፋይል ጎታቹ አትጎተትለት፤ ሥፍራህን አትልቀቅ።ባለፈ ነገርህ አትታሰር፤ ሌሎች እንዲያሳስሩህም ዕድል አትፍጠርላቸው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ