
ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ሲባል ከፊት ለፊት ቀድሞ የሚመጣው ቱሪዝም ነው። ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ በመሆንም ያገለግላል። ብዙ የዓለም ሀገራትም በዘርፉ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ግን ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ከዘርፉ እምብዛም ተጠቃሚ አልነበረችም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።
ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት፣ የአየር ንብረት፣ መልከአ ምድሯ፤ ታሪካዊ እና ሀይማኖታዊ ቅርሶቿ … ሁሉ ሲታሰብ ቀዳሚዎቹ የቱሪስት መስህብ ሀገራት ሊያደርጋት የሚችሉ ነበሩ። ይህም ሆኖ ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ እዚህ ግባ የሚባል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አልተቻለም።
ይህም የሆነው ቱሪዝም ምንም እንዳልሆነ ይቆጠር ስለነበር እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች በሚገባቸው ልክ በመሥራት ለመጠቀም ባለመቻሉ ነው። የነበሩትም የቱሪስት መዳረሻ የሚባሉ ሥፍራዎች መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው፣ በቂ እና ዘመናዊ ማረፊያና መዝናኛ ሥፍራ የሌላቸው ነበሩ።
በየአካባቢው የነበረው አስጎብኚም ሙያዊ ስልጠና እና ሥነምግባር ያልተላበሱ፣ ማንም በዘፈቀደ አስጎብኚ የሚሆንበት ሁኔታ ስለነበር በየአጋጣሚውም ሆነ አስበውበት ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ደጋግመው እንዲመጡ የሚያደርጋቸው ሁኔታ አልነበረም።
የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝም ሳቢና አጓጊ ሁኔታዎች አልሰፉም ነበር። በመሆኑም እንደ ሀገር ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ዝቅተኛ ነው። የተፈጠረውም የሥራ ዕድል እዚህ ግባ የሚባል እንደነበር የሚታወስ ነው። እንደነ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉት ሀገራት ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት በርካታ ቱሪስት እንዲጎበኛቸው በዘርፉም ጠቀም ያለ ገቢ የማግኘት እድላቸው ሰፊ ነበር።
በዘርፉ በሚገባው ልክ ተጠቅመውበታል፤ የሀገራቸውንም ገጽታም በሚገባ ገንብተውበታል። ይሄ ለእኛም ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው። ከሠራንበት የበለጠ የምንጠቀምበት እንደሚሆንም አሁን የተጀማመሩ ሥራዎች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመት ወደህ ግን ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከቴክኖሎጂ እኩል ትኩረት አግኝቶ ከፍተኛ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል።
ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ የተገባውም በዋነኝነት ሁለት ጉዳዮችን ለይቶ በመሥራት ነው። ይኸውም የመጀመሪያው ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማደስ እና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመገንባት ተመራጭነትን ማሳደግ ነው።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጎንደር፣ ሶፍ ዑመር፣ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ጂማ አባጂፋር እና ሐረር ጀጎል ቅርሶችን ለማደስ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ውብና ሳቢ ሆነው ታድሰዋል። ተጨማሪ ሥራዎችም ታክሎበት ቱሪስቱ አይኑን ወደነዚሁ ሥፍራዎች እንዲያደርግ አብሮም ተጓዳኝ ሥራዎች ተከናውነዋል።
ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየክልሎቹ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት የቱሪስት መዳረሻዎችን ሳቢ ለማድረግ እንዲሁም ለቱሪስቱ ተጨማሪ እይታ የሚሆንና መሰረተ ልማቱንም ምቹ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
ከዚህም ባሻገር አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋፋት በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ መርሀግብሮች አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አብርሆት፣ ሳይንስ ሙዚየም… በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች ተሠርተዋል።
ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሀላላ ኬላ በዋናነት ከሚጠቀሱት መስህብ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ሲሆኑ ሌሎችም በመሠራት ላይ ያሉ ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ የቱሪስት መስህብች ለሀገሪቱ ከፍተኛውን ገቢ በማመንጨት ፣ የሥራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንደሚሆኑ ይታመናል። ለሀገር ገጽታ ግንባታም ድርሻው ከፍ ያለ ነው።
ሁለተኛው በልዩ ትኩረት እየተሠራ ያለው የቱሪዝም ሴክተር ማስፋፋት ደግሞ በኮንፈረንስ ቱሪዝም መስክ እየተሠራ ያለው ሥራ እና እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ውጤታማና ወደ በርካታ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የሚበር የአየር መንገድ ባለቤት ናት ሀገራችን ።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ሁነቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ በርካታ ማዕከላት በመዲናችን ይገኛሉ። በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ሥራ የገባውን የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጨምሮ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ የሳይንስ ሙዚየምና ሌሎችም አዲስና ነባር የስብሰባና የኤግዚቢሽን ማዕከላት ይገኛሉ።
ይህንን ከሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና መዲናችን እያሳየችው ካለችው ሁለንተናዊ እድገት ጋር በማቀናጀት መንግሥት የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ከመሆኗ ጋር ተያይዞም ደረጃውን የጠበቀ ኮንፈረንሶች ማካሄድና በከተማው የሚታዩ የቱሪስት መቆያ ሥፍራዎችን ማዘጋጀት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተሥራበት አሁንም እየተሠራበት ያለ መሆኑን በርካታ ማሳያዎች አሉ።
እአአ ከ 2024 እስከ 2027 ድረስ ከ300 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና ኹነቶች ይካሄዳሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም አበረታች እንቅስቀሴዎች ታይተዋል። ለምሳሌ ያህል በ2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ 19 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተካሂደዋል፣ እንዲሁም በያዝነው 2017 ዓ.ም ባለፉት 9 ወራት ብቻ 84 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና ኹነቶች የተካሄዱ ሲሆን በዚህም 30ሺህ 340 የውጭ ሀገርና 171ሺህ 739 የሀገር ውስጥ ሰዎች ተሳትፈውበታል።
በያዝነው የግንቦት ወር አስካሁን ድረስ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ኹነቶች የተከናወኑ ሲሆን በሚቀጥለው ሰኔ ወር ደግሞ 31፣ በሃምሌ ወርም 43 በአጠቃላይ 74 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ይካሄዳሉ። እነዚህ ጉባኤዎች የሚካሄዱት በአዲስ አበባ፣ በባሕርዳር፣ በጎንደር፣ ድሬዳዋ፣ አምቦ፣ ደብረታቦር እና ደሴ ነው።
ይህም ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ለማየት አዳዲስ መዳረሻዎችን እና የተሠሩ ልማቶችን እንዲጎበኙ ሰፊ እድል የሚፈጥር ይሆናል። ከዚህም ጎን በየአካባቢዎቹ ያሉ ሆቴሎች የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ዘርፉን የሚያነቃቁ፤ የውጪ ምንዛሬ ገቢን የሚያሳድጉ ይሆናሉ። እንዲሁም ሀገራችንን ለመላው ዓለም የሚያስተዋውቁ ፣ ለሀገሪቱ ገጽታ ግንባታ ትልቅ እድል የሚሰጥ እንደሚሆንም ይታመናል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ብቻ የሚካሄዱትን 74 ጉባኤዎችና ሁነቶችን ብዛት በማየት ብቻ ከ300 በላይ ጉባኤዎችና ሁነቶች እናካሄዳለን ተብሎ ከተያዘው እቅድ በላይ ማሳካት እና ኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ከወዲሁ አመላካች ነው።
በቅርቡ የተካሄደውን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ፣ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን የቀጠናዊ ደህንነት ፎረም እና የሃይማኖት ጉባዔን ጨምሮ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በመዲናችን ተካሂደዋል። ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ሲሆን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና ስኬቶች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ እና ትስስሮችን ለማጎልበት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የኢትዮጵያን አቅም ለማሳየት ያስቻለ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ነው።
በኤክስፖው ላይ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በድምሩ ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እና ከመቶ በላይ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የታደሙ ሲሆን ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ኅብረተሰብን ለመገንባት እና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እያደረገች ያለውን ጥረትና ያላት እምቅ አቅም ለዓለም ያስተዋወቀችበት መድረክ እንደነበር መመስከር ይቻላል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑ ተቋማት ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው በኤግዚቢሽኑ መታደማቸው ነገ የኢትዮጵያ ግዙፍ ተቋማት ለመሆን ለሚያልሙት የሀገራችን ጅምሮች ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የግብዓትና የእውቀት ትስስር በመፍጠር ለእያንዳንዱ ተቋም ተጨማሪ አቅም መሆን የቻለ ነው ለማለት ያስደፍራል ።
ዓለም አቀፍ ጉባኤው ትኩረቱ በሳይበር ደህንነት፣ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በስማርት ሲቲ ልማት ላይ ያተኮረ ነው። የሳይበር ደህንነት እያደገ ከመጣው ዓለም አቀፍ የሳይበር ምኅዳር ትስስር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ የመከረ እና በርካታ ሀሳቦችና ምርቶች የቀረቡበት ነው።
ሌላው አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ሲሆን ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የሳበ፣ በሁላችንም ጓዳ እና እጅ ላይ የደረሰ የሥራን ውጤታማነት በተለያዩ መስኮች እንዴት ሊያሻሽል እንደሚችል የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ማሳያዎች የቀረቡበት አስደማሚና አስደናቂ የነበረ ነው።
እንዲሁም በስማርት ሲቲ ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ሌላው ነው። ከተሞች በቴክኖሎጂ መመራታቸው ከአስተዳደር እስከ ሰላምና ጸጥታን ማስከበር ድረስ ለሚኖረው ሚና የሀገራችንና የሌሎችም ተቋማት አቅምና ተሞክሮ የታየበት ነበር። በሀገራችን አዲስ አበባን ጨምሮ በአዳማ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ጅማ፣ ሐረር እና ሌሎችም ከተሞች የስማርት ሲቲ ግንባታ ጅምሮች መልካም ውጤት እያመጡ ይገኛል። በመጨረሻም በፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና በቴክኖሎጂ ትምህርት ዙሪያ ውይይቶች፣ የተሞክሮ መቅሰም እና የተግባር ሥራዎች ቀርበው ሰፊ የመማማርና ልምድ የመለዋወጥ ተግራት የተከናወነበት ነበር፡፡
የአይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጉባዔ ደግሞ ሌላው የተካሄደው ጉባኤ ሲሆን በጉባኤው ከመንግሥት ውሳኔ ሰጪዎች፣ የልማት ድርጅቶች፣ ኢንዱስትሪዎች እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነው። ይሄም በአፍሪካ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እድገትን ለማፋጠን የሚያግዝ መሆኑ ነው የተነገረለት።
ከ100 በላይ ሀገራት የተሳተፉበትን ይሄን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንግዶችን ለማስተናገድ መሰረተ ልማት፣ ወደ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የተሳለጠ የአየር ጉዞ ግንኙነት መኖር እና በቂ የኮንፈረንስ አገልግሎት መስጫ አቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
ከዚህም ባሻገር ግምገማው የኢትዮጵያ ፋይዳ የተገነባበት የሕግ ማሕቀፍ፣ ስትራቴጂ እና ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ለብዙ ሀገራት አርዓያ መሆን መቻሉና “መታወቅ ለሁሉም” የሚለውን እቅድ በመተግበር ረገድ ያሳየችው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ለመመረጥ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ሁለት ትልልቅ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ጉባዔዎች ማካሄዳ በራሱ መንግሥት ለዲጂታል ኢኮኖሚ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው። ዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ በኩል በራሱ ሃብትና የሥራ እድል በመፍጠር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ቅልጥፍናና ውጤታማነት በማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
ሌላው ዛሬ የሚጠናቀቀው 20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት አኅጉራዊ ኮንፈረንስ ከ50 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ከ1500 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት “የማይበገር ማኅበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ፦ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል የተዘጋጀው ነው።
ኮንፈረንሱ በዋናነት ያተኮረው ሀገራት በሚተገብሯቸው የተለያዩ የመሰረተ ልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች ወይም ፕሮጀክቶች እንዴት የሰው ኃይልን በስፋት መጠቀም እንደሚችሉ፣ ዘላቂና ጥራት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል እንዲሁም በሂደቱ የሠራተኞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ደህንነት ማረጋገጥ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ነው። ይህም ካለን ሰፊ የሰው ኃይል አቅም አንጻር ጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ ተገቢነት ያለው ነው።
በከተማና በገጠር ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙት የመሰረተ ልማት፣ የቤቶች ልማት እና ሌሎች የግንባታ ሥራዎች ከአካባቢ ጋር የተስማሙ፣ በሕብረተሰብ ላይ የጎላ አሉታዊ ተጽእኖ የማያሳድሩ፣ በሥራ ቦታ የሠራተኞች ጤናና ደህንነት የተጠበቀባቸው፣ ለዜጎች ሰፊና ጥራት ያለው የሥራ እድል የሚፈጥሩ እንዲሁም ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉና አካታች እንዲሆኑ በፖሊሲዎቻችን፣ ሀገራዊ እቅዶችና ፕሮግራሞች በግልጽ አካቶ የተሠሩ ሥራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች የቀረቡበት ነው።
እየሰፋ የመጣው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ከዘላቂ የልማት ግብ ጋር የሚጣጣሙ፣ የአካባቢና ማኅበራዊ ደህንነትን ታሳቢ ያደረጉና ሰፋፊ የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶችን ይበልጥ ለመሳብ፣ ለማበረታታት እና ለማስፋት ዕድሎች የሚፈጠር ነው። ሀገሪቱ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ለማካሄድ ያላትን ብቃት ጭምር ማሳያ ነው። በቱሪዝሙ መስክ አሁንም ሰፋፊ እድሎች መኖራቸውንም አመላካች ይበል የሚያሰኝ ነው።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም