
በክረምት መጊቢያ ዋዜማው ግንቦት ወር ላይ ሆነን በከተማችን ስላሉ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ስናስብ ብዙ፤ ብዙ ነገሮቻቸው በአእምሯችን ይመጣል። አንዱ እና ዋነኛው ትዝታቸው በክረምት በየዳርቻቸው ይኖሩ የነበሩት ነዋሪዎቻቸው ስጋት ነው።
ሥጋቱ እንዲህ እንደቀላል ስጋት አልነበረም። ዛሬ እንደዋዛ አለፈ እንጂ ስጋቱ ወንዞቹ በክረምቱ ወራት ሲሞሉ በሚፈስ እና በሚትረፈረፍ ደራሽ ውሃ ተጠራርጌ በጎርፍ እወሰዳለሁ የሚል እንቅልፍ የሚያሳጣ ዘግናኝ እንደነበረ ይታወሳል።
እንደ ከተማ አስተዳደር በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ እነዚህን ወገኖች ከስጋት ለመታደግ ክረምት በመጣ ቁጥር ነዋሪዎችን ከዳርቻቸው ተለዋጭ ቤት በመስጠት እና በድንኳንም ሆነ በተለያየ መልኩ የማንሳት ሥራ ሲከናወን መቆየቱም አይዘነጋም ። እዛው ባሉበት የጎርፍ መከላከያ በማድረግ ስጋታቸውን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ ይሠራ የነበረ መሆኑም ይታወሳል ።
ሆኖም ደግሞ እንደ ሀገር በተለይም እንደ ከተማ አስተዳደር ሁሉንም ነዋሪዎች የሚታደግ ጥሪት አቅም ውሱን ከመሆኑ አንጻር ጥናት ተሠርቶ ቁጥራቸው በውል አልታወቀም እንጂ በየክረምቱ በነዚሁ ወንዞች ጎርፍ በመወሰድ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች የሉም ማለት አያስደፍርም ። በእርግጥ አንድ ሁለትም ቢሆኑ በመገናኛ ብዙሃን እንዳሉ የሰማንበትም ጊዜ አለ።
በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነቶቹን ነፍስያዎች ሙሉ በሙሉ በዘላቂነት መታደግ የቻለው ከኮሪዶር ልማት ጋር ተያይዞ በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ጊዜያት ሲተገበር የቆየው እና አሁንም እየተተገበረ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ነው ።
የወንዝ ዳርቻዎች ልማቱ የዳርቻ ነዋሪዎቹን ሕይወት በዘላቂነት ከመታደግ ባሻገር በርካታ ጥቅሞች አሏቸው ። በተለይ በኮሪዶር ልማት ታቅፈው መተግበር ከጀመሩ በኋላ አያሌ ሀገራዊ ፋይዳዎችን እየፈጠሩ መሆኑን እየተመለከትን ነው ። ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተያይዘው በመተግበራቸው ውጤታማነታቸው በእጅጉ እየጨመረ ሲመጣም ማየት ተችሏል።
“የወንዝ ዳር ፕሮጀክት” የከተማውን ነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ምቹ እያደረገው ነው ። ስልጡንነትንም ከጽዳት አጣምሮ እያስተማረው ነው። ከዚህ አኳያ ከተማዋን ውበቷን እና ጽዳቷን ከመጠበቅ አኳያ በብርቱ በማሻሻል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት መስመር ውስጥ ገብቶ ይገኛል ።
በመዲናዋ የሚገኙ ወንዞችንም ከመጥፋት በመታደጉ ረገድ ዓይነተኛ መፍትሄ ሲሆን እየታየ ነው። እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያበረክትም ማስተዋል ተችሏል። አሁን ላይ የተበኩሉ፤ በብክለታቸው አረፋ የሚደፍቁ ፤ ወጪ ወራጁን አፍንጫ የሚተፈንግ ወንዞች ቁጥር እየቀነሰ ነው።
ከየፋብሪካው የሚወጣ ኬሚካል እንዲሁም ከየቦታ የወጣ ቆሻሻ እየወጣ ይደፋባቸው የነበሩት ወንዞችም ቢሆኑ ከዚህ አደጋ በተወሰነ መልኩ ነጻ ወጥተዋል ። ከተማይቱ የኮሪዶር ልማቱ ጋር በመዳመር ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት እየሆኑ መጥተዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ብክለት ከመቀነስ ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ከአረንጓዴ ዐሻራ እንዲሁም ከኮሪዶር ልማት ጋር ተዳምረው ብክለትን በብርቱ እየቀነሱ ይገኛሉ። የጤና ሁኔታን በማሻሻል የዜጎችን በተለይም የከተማዋን ነዋሪዎች የመኖር ዕድሜ ጣራም ከፍ ከማድረግ አንፃር ሚናቸው ከፍ ያለ እንደሚሆን መገመት የሚያስቸግር አይደለም ።
በዚህ መልኩ የከተማይቱን ገጽታ በብርቱ ከለወጡት የወንዝ ዳር ልማቶች መካከል ከጣሊያን መንግሥት በተገኘ 277 ሚሊዮን ብር ርዳታ እየተተገበረ ያለው የቀበና ፤ የራስ መኮንን ድልድይ ወንዝ ዳር ልማት ብቻ መልካም ማሳያ ናቸው። ሌሎቹንም በርካታ የመዲናችን ወንዞች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመዲናችን አዲስ አበባ እየለሙ ያሉ የወንዝ ዳርቻዎች ተደራሽነት ሰፊ ነው። ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ ወንዝ ያሉት ተፋሰሶች ሲቃኙ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሽፋን አላቸው። ከፍ ከፍ ያሉት ተፋሰስ ወንዞች ቀርተው ጅረቶቹ ብቻ ከስድስት ኪሎ ሜትር ስለመብለጣቸውም እንዲሁ መረጃዎች ያመላክታሉ ።
እነዚህ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ስጋት ውስጥ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪ ዜጓችን ችግር የፈቱ መሆኑን አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸውም መሬት ላይ ካለው እውነታ ማብራሪያ መስጠት ይቻላል።
የወንዝ ዳር ፣ የኮሪዶር ልማቱን ጨምሮ በአረንጓዴ ዐሻራ እየተተገበሩ ያሉ ከተማይቱን አረንጓዴ የማልበስ ሥራዎች ፤ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት ዜሮ ነጥብ ሶስት ሜትር ስኩዬር ወደ ሰባት ሜትር ስኩዬር በማሳደጉም ረገድ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ተገምቷል።
ዛሬም ይሄን ጽዱ የመዲናዋን ገጽታ እያየ የራሱን ድርሻ ከመወጣት ይልቅ ግንብ አጥር እና ቀለበት መንገድ ስርቻ የሚፀዳዳ ግለሰብ ባይጠፋም በልማት የታቀፉት የወንዝ ዳርቻዎች ግን ከሚተነፍግ የመፀዳጃ ስፍራነት ወጥተዋል። ቆሻሻ ለመጣል የሚጋብዝ የቀድሞ ገጽታቸው ለዓይን ሳቢ እና ማራኪ ሆኗል ። ይልቁንም ለመናፈሻ ስፍራነት ለመመረጥ በቅተዋል።
ይሄም ለውጥ ሊመጣ የቻለው ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የመዲናዋ ነዋሪዎች ስለ አካባቢ ብክለት ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ስለመሆኑም መዘንጋት የለበትም። ይሄ የግንዛቤ ተደራሽነት አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ አልፋ ፤ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ በየጊዜው የሚወጣ የሚገባውንም ታሳቢ ማድረግ አለበት።
አሁን በመዲናችን የተካሄደውን እና በመካሄድ ላይ ያለውን የወንዝ ዳርቻ ልማት ውጤታማነት በዘላቂነት ለማጣጣም ግንዛቤው መስፋት፤ ነዋሪውም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል። ይሄ ሲሆን አስተዋጽኦው እያደገ ተደራሽነቱም እየሰፋ ይሄዳል። ከነዋሪዎቿን ጨምሮ በከተማዋ በልዩ ልዩ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶችም ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም