አዲስ አበባ፡- ለድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታዎች የሚሰጠው ክትባት በበጀት እጥረት ምክንያት ከታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመቋረጡ ለእንስሳት ጤና ስጋት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ድንበር ዘለል ተሻጋሪ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር አስማማው ዱሬሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የክትባት በጀት መጠኑ ከሶስት ዓመት ወዲህ እየቀነሰ መምጣቱ ፤ እንደ አገር ለማጥፋት የታቀዱ የእንስሳት በሽታዎችንም ለማጥፋት በሚሰራው ስራ ላይ ጫና ይፈጥራል።
መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ካልሰጠ የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት እና የእንስሳቱን ጤንነት ለመጠበቅም አዳጋች እንደሚሆን ጠቅሰው፤በሽታዎቹ ቢከሰቱ በአጭር ጊዜ የመዛመት ዕድል ስላላቸው የክትባቱ መቋረጥ ስጋት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል። ለክትባት የተያዘው በጀት ስምንት ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር አስማማው፤ በ2011 ዓ.ም በስድስት ወር ውስጥ የድንበር ዘለል በሽታዎች መከላከያ ክትባቶቹን ለማሰራጨት 37 ሚለዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ከብሄራዊ እንስሳት ጥበቃ ኢንስቲትዩት ለተወሰዱት ክትባቶች ያልተከፈለ 28 ሚሊዮን ብር እዳ መኖሩን ተናግረዋል። በቀጣይ ክትባቶቹን ለማሰራጨት በጀት ባለመኖሩ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ስርጭቱን ማቆማቸውን በደብዳቤ ለክልሎች ማሳወቃቸውን ገልጸዋል። ክልሎችም በእቅድ ያልተዘጋጁበት በመሆኑ ክትባቶቹን በራሳቸው ወጪ ማሰራጨት እንደማይችሉም ጠቁመዋል። ዶክተር አስማማው እንዳሉት፤በ2011 በጀት ዓመት በአጠቃላይ አገሪቱ በሽታ ተከላካይ ክትባት 94 ሚሊዮን እንስሳትን ለመከተብ እቅድ ተይዟል፡፡
በሩብ ዓመቱ ደግሞ 20 ሚሊዮን እንስሳትን ለመከተብ ታቅዶ 17 ሚሊዮን ያህል እንስሳትን መከተብ ተችሏል፡፡ 103 ሚሊዮን ዶዝ ድንበር ዘለል ለሆኑ የእንስሳት በሽታዎች መከላከያ ክትባት ለማሰራጨት ፣ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ 60 ሚሊዮን ዶዝ ለማዳረስ ታቅዶ፤ 87 ሚሊዮን ዶዝ የተለያዩ ክትባቶች እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡ አፈጻጸሙም ከዕቅድ በላይ 145 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል ሲሉም አመልክተዋል፡፡ በድንበር ዘለል በሽታዎች መከላከያ ክትባት የኦሮሚያ ክልል በብዛት የተሰራጨ ሲሆን፤ አማራና ደቡብ ክልሎችም ተዳርሷል፡፡
ሌሎች አካባቢዎች የበሽታዎቹ ጫና ስለሌለባቸው ሐረሪ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ የተሰራጩ ክትባቶችን መውሰድ ቢኖርባቸውም አልወሰዱም፡፡ በክትባት ዓይነት ደግሞ በብዛት የተሰራጨ ‹‹New cattle disease›› የሚባል የዶሮ በሽታ የሚከላከል ክትባት፣ ‹‹PPR›› የሚባል የፍየልና በጎችን የሚያጠቃ በሽታ የሚከላከል ክትባት እና ‹‹LCD›› የሚባል የዳልጋ ከብት የሚያጠቃ በሽታን የሚከላከል ክትባት ተሰራጭቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
በሰላማዊት ንጉሴ