የዛሬው የፍልስፍና አምዳችን ከኒኮሎ ማኪያቬሊ ፍልስፍናዎች አንዱ በሆነው የሰው ልጅ ጸባይ እና ስብዕና ላይ ያተኮረ ነው። ምንጫችን ደግሞ “ፖለቲካዊ ፍልስፍና” በሚል ርዕስ በቃኪዳን ይበልጣል አማካይነት በ2005 ዓ.ም ለንባብ የበቃው መጽሃፍ ነው።
መቼም ፖለቲካዊ ፍልስፍናን የነካካ ማንኛውም ሰው ለኒኮሎ ማኪያቬሊ ስምና እርሱ ለሚወክላቸው እሳቤዎች እንግዳ አይሆንም። ቀዝቃዛው የተሰላ ጥርጣሬው፣ግልጽ ያልተሸፋፈነ ተፈጥሮአዊነት፣የተጋነነው ግለሰብ ተኮርነቱ፣መርህ አልባነቱ፣ ሃይማኖታዊና የልዕለ ተፈጥሮ ትረካዎችን ውድቅ ማድረጉ፣አሁን እና እዚያ ላይ ብቻ ማተኮሩ፣ለግብረገብ ግድ ማጣቱ እና ሌሎች የኖረበትን የተሃድሶን ዘመን የሚያንፀባርቁ መገለጫዎቹ ናቸው። እነዚህ ማንነቶቹ ደግሞ ውዝግብን የሚጭሩ ናቸው።
ማኪያቬሊ የፖለቲካን ማሽን በትክክል በሚንቀሳቀስበት አግባብ በማጥናቱ ረገድ ቀዳሚው ነው። አፍላጦንና አሪስጣጣሊስ፣ ቅዱስ አውግሲቲን እና ቅዱስ ቶማስ አኩይናስ በፖለቲካዊ ህልዮቶቻቸው እውነታውን ከሃሳባቢው ጋር የማምታታት አዝማሚያ አላቸው። ተቋማት እና መሪዎች እንደምን ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ መረዳታቸው በፈቀደላቸው ልክ አስተያየት ለግሰዋል። ነገር ግን አንዳቸውም የማኪያቬሊን ያህል እውነታዊነት አላሳዩም።
ማኪያቬሊ እውነታን የሙጥኝ ሲል ፖለቲከኞችን ከንግግራቸው ባለፈ ድርጊታቸው ላይ አተኩሮ አጥንቷል። የየትኛውም ፖለቲካዊ ባህርይ ምንጭ ሰዎች በሌሎች ሰዎች ላይ ስልጣን ይኖራቸው ዘንድ ያላቸው ጽኑ ፍላጎት መሆኑ አያወላዳም ሲል አምኗል። በተጨማሪም ፖለቲካንና ግብረገብን አፋቷል። ከብያኔ ፍጹም ተቆጥቦ ትንታኔ ሰጥቷል። ይህም ከፖለቲካ ፈላስፋ ይልቅ የፖለቲካ ሳይንቲስት እንዲባል አስችሎታል።
በጽሁፍ ስራዎቹም፤ ለምንም አይነት ግብ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ወይንም አስጠብቀህ ማስቀጠል ከፈለግህ፣ ታሪካዊ ሁኔታዎች አሊያም ውሱን አቅርቦቶች የሚፈቅዱልህ የመንቀሳቀሻ ስፍራ ይህ ከሆነ፣ ያሰብከውን ለማሳካት የተሻለው መንገድ ይህ ብቻ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥቶ ጽፏል።
ለማኪያቬሊ የትኛውም ፖለቲከኛ ስልጣን ለመያዝ፣ ከያዘም በኋላ የቻለውን ያህል አስጠብቆት ለመቆየት መሻት ሳይታለም የሚፈታ ሃቅ ነው። ልክ ሐኪም ፊት የቀረበ በሽተኛ ሁሉ ጤናውን ለመመለስ መፈለጉ ግልጽ እንደሆነው ሁሉ ስልጣን መያዝ ትፈልጋለህ ወይ ተብሎ ሊጠየቅ አይገባውም።
ስልጣን ለምን ፈለግከው ብሎ መጠየቅ ጉንጭ ማልፋት ነው። ስልጣን ከያዘ በኋላ ሊያሳካው ያቀደው ግብ የራሱ የፖለቲከኛው ጉዳይ ብቻ ነው። ሐኪም በሽተኛውን እሺ ከህመምህ ከፈወስኩህ በኋላ በህይወትህ ምን ልታደርግበት አስበሃል የማይለውን ያህል ማኪያቬሊም ረጅም የስልጣን እድሜ ሊያጎናጽፋቸው የሚመክራቸውን ነገስታትና መሪዎች ስልጣናችሁን ለምን ልትጠቀሙበት ነው፤ ሲል አያፋጥጥም። ትክክለኛ የአመራር ጥበብ ይህ ነው በማለትም የትክክልና የስህተት ልኬታ አይመትርም። ስልጣን ትፈልጋላችሁ፤ መፍትሄው ደግሞ እኔ እሰጣችኋሁ ነው የሱ ብቸኛ መልዕክት።
ለመሆኑ በማኪያቬሊ እይታ ሰዎች ምን ዓይነት ነገሮችን ይሻሉ? ለምንስ አይነት ጉዳዮች ዋጋ ይሰጣሉ?
“ሰዎች ምንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ ከመወሰናቸው በፊት የሚጠብቃቸውን ፈተና እና አደጋ መመርመር አለባቸው። ከመጀመሪያ ፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣም ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ ከጠቀሜታው ከበለጠ ሊተውት ይገባል።” ይላል “ዲስኮርስ” በተሰኘው መፅሃፉ። ነገር ግን ይህ ሃሳባዊ ሂደት ሲተገበር አይስተዋልም።
ህዝቡ ሊጨበጥ በማይችል ፣ልዩነት ተታልሎ ሁሌም የራሱን ውድመት እንደተመኘ ነው። የሆነን ጉዳይ በተመለከተ የተደረገ የትኛውም ስብሰባ ላይ የተገኙ ሁሉ የሚያቀርቡት አስተያየት ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ይታዘባሉ። እንዲያውም በአንዳንድ ላቅ ባሉ ግለሰቦች የማይሰነዘሩ ከሆነ ከሁሉም ምክንያቶች በተፃራሪ የሚቆሙ ናቸው። ግን ደግሞ በላሸቁ መንግስታት ውስጥ የላቁት ሰዎች አንድም ከቅናት፣ አንድም ከክፉ ምኞት የተነሳ ስለሚጠቀሱ ተመራጭ የሚሆነው ተራውና በስህተት የተጨማለቀው አሊያም ጥቅል መልካምን ከሚያስገኘው ይልቅ የብዙውን ስሜት የሚያስደስተው ሃሳብ ነው።
ስለሰው ልጆች ስብዕና ያለውን አመለካከት “ዘ ፕሪንስ” ላይ ሲያስረዳም “ ሰዎች በጠቅላላው ምስጋና ቢስ፣ ክፉ ተናጋሪ፣ አደጋን ለማስወገድ የሚችሉትን የሚያደርጉ፣ በሌሎች ማግኘት ቅናት የሚያንገበግባቸው ናቸው ሊባል ይችላል” ይላል።
ብልህ የሚባሉት እንኳ በማያቋርጥና አንዴ በሚያሻቅብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቁልቁል በሚንደረደር እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን የሰው ልጅ ሁኔታ አስተካክለው ለመረዳት ይቸገራሉ ይላል ማኪያቬሊ። የየትኛውም ሰው (ነጋዴ፣መሪ፣ ወዘተ) ስኬት እና ውድቀት የሚመሰረተው ራሱን ከየጊዜው ጋር ማጣጣም በመቻሉ ወይንም ባለመቻሉ ላይ ነው። የዘመኑን ጠባይ በትክክል የሚያጤን እና ለዚሁም የሚስማማ ስልት የሚቀይስ የስህተቱ መጠን አናሳ ይሆናል።
የሰዎች ባህርያት በተለያዩ ስልቶች ሊቀረጹ ይችላሉ። ኑሮ የተመቻቸውም፣ ያልተመቻቸውም አዲስ ነገር ይፈልጋሉ። የለውጥ ፍቅር የትም ቦታ ለሚከሰት ፈጠራ መለኮሻው ነው። ስለዚህ አንድ ሰው በብዙሃን እይታ አዲስ ወይም እንግዳ መስሎ ከታየ ሃሰቡ እርባና የለውም። የሌለውም ቢሆን በስኬት መሰላል ወደላይ መመንጠቁ ይገመታል። ሌሎች ሁለት ብርቱ ስሜቶቻችን ድርጊቶቻንን ይወስናሉ፤ ፍቅርና ፍርሃት። ሰዎች እንዲፈሩት የሚያደርግ ሰዎች እንዲወዱት የሚያደርገውን ያህል ተጽኖ መፍጠር ይችላል። ጥልቅ ምኞትም በማንነታችን ላይ ከፍተኛ ጉልበት አለው። ሰዎች የቱንም ያህል ቢያድጉ ከቁመታቸው የሚልቅ ምኞት ላባቸው ውስጥ ይኮተኩታሉ። የምኞት ሃይል የተመኘነውን ስናገኝ ከሚሰማን እርካታ ይበልጣል። ስለዚህ ምኞት ተጨማሪ እየጠየቀ ዘወትር ከጉያችን አይጠፋም። ሰዎች የነጻነት ፍላጎትም አላቸው። ነጻ ሆነው በማንም ሳይገደቡ ህይወታቸውን እንዲመሩ ዝንባሌያቸውን እንዲከተሉ፣ ጥሩ ነው የሚሉትን እንዲያባርሩ ይሻሉ። ነፃ በመሆን (በሌሎች እስር ወይም ጥገኝነት ስር ላለመዋል)ያለው እርግጠኛ መንገድ ሌሎችን ጥገኛ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ሰው የበላይ መሆንን ያፈቅራል። ያለምንም ግርግር የግል ህይወታቸውን መምራት የሚሹት እንኳ ይህንን ለማሳካት ሲሉ የበላይነትን ይመኛሉ። እና ይላል ማኪያቬሊ፣ በግለሰቦችና በመንግስታት መካከል ፍትጊያ የማይቀር ነው።
ሰዎች ከአንድ ምኞት ወደሌላው ይነጥራሉ። በመጀመሪያ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላል ይታትራሉ፤ ከዚያ ሌሎችን ያጠቃሉ።“ተቃራኒያቸው ዝቅ በተደረገ ቁጥር የህዝብ አልያም የመሳፍንነቱ ኩራት ከፍ ይላል። እናም የነጻነት ፍላጎት አንዱን ወገን ወደላይ አንስቶ ሌሎችን የሚጨቁንበት ደረጃ ያደርሰዋል። በዚህ መሰል እንቅስቃሴዎች ሂደትም ሰዎች የራሳቸውን ፍርሃት ለማስወገድ ብለው ሌሎች ላይ ፍርሃት ይጥላሉ። ለዚህ ነው ሌሎችን መጨቆን ወይንም በሌሎች መጨቆን የግድ የሆነ ያህል ከራሳቸው የሚርቋቸውን ጉዳዮች ሌሎች ላይ የሚፈጽሟቸው።”
በሰዎች ልቦና ውስጥ የማጣት ፍርሃት የማግኘትን ፍላጎት የሚያህል ጉልበት አለው። ባሏቸው ነገሮች እርግጠኛነትን ለመጨበጥ መላ የሚሉት ተጨማሪ ለማግኘት ነው። አዳዲሶቹ ግኝቶቻቸው ለምዝበራ ጥንካሬ እና ሃይል ይሰጧቸዋል። የሰው ምኞት ሊረካ የማይችል በመሆኑ በሰው ልብ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ በያዘው ነገር እርካታ ማጣት ነግሷል። ከዚህ እርካታ የለሽነት ነው ያላንዳች ተጨባጭ ምክንያት የአሁኑን ጊዜ መርገም፣ ያለፈውን ማሞካሸት እና የወደፊቱን መናፈቅ የሚወለደው።
ህዝብ የሚባለው የግለሰቦች ጥርቅም ከመወናበድ ጸድቶ ካለማወቁ የተነሳ ሪፐብሊክ መስርቶ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ በደስታ እና በእርካታ ሊኖር አይቻለውም። ይሞከር ቢባብልም ውድቀቱ የማይጠረጠር ነው። ብቸኛው ተግባራዊ ስሜት የሚያስመዘግብ አስተዳደር በአንድ ብርቱ ሰው ዘዋሪነት የሚንቀሳቀስ ንጉሳዊ አሊያም ልዕላዊ አገዛዝ ነው። ንቅዘትን ባነገሰ ማህበረሰብ ህግጋት ያለማወላዳት ይተገበራሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ተፈፃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እጅግ ጠንካራ ሃይል ያለውና በምንም ነገር ላይ የአድራጊ ፈጣሪነት ስልጣን የተሰጠው ፍፁማዊ መሪ የግድ ነው።
የማያቬሊ መጽሃፍት ዋነኛ ተደራሲ በማህረሰብ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ልሂቃን መካከል የአንደኛው አባላት ናቸው፤ የፖለቲካ ልሂቃን። መሰሎቻቸውን ለመምራት ከሚሞክሩ ሰዎች መካከል የሚሳካላቸው በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ማኪያቬሊ የሚያወራው ለእነርሱ እና ስለእነርሱ ነው። ከፖለቲካ ልሂቃን ውስጥም ሁለት ንዑስ ክፍሎች አሉ። ስልጣን የያዙት እና እነሱን ስልጣን ለመንጠቅ አሰፍስፈው የሚጠባበቁ ተፎካካሪዎቻቸው።
በማኪያቬሊ አባባል ልሂቃን የሚባሉት በጥቅሉ በአንድ ሙያ ልቀው የወጡት ናቸው። ለምሳሌ ከጋዜጠኞች ውስጥ ምርጦቹን ብቻ ያካተተ ስብስብ ልሂቃንን ይዟል ሊባል ይችላል። ፖለቲካዊ ስልጣንን በመተግበር የሚልቁት ገዢ ልሂቃንም ከሌሎቹ ይበልጣሉ። ብቃት የዚህ ቡድን አባል ለመሆን የሚፈለግ ብቸኛ መስፈርት ነው። ገዢ መደብ ግን በዘር ላይ የሚያተኩር የጥቂቶች ማህበር ነው። ከትክክለኛው ቤተሰብ መወለድ የገዥ መደብ አባል ለመሆን ይበቃል።
በርግጥ ገዢ መደቦች በብቃታቸው ላቅ ያሉ የፖለቲካ ጠቢባንን በጭራሽ ወደመሪነት ክበባቸው አያመጡም ማለት አይደለም። የልሂቃን ገዢዎችም ሙሉ ለሙሉ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው እውነተኛ ልሂቃንን ብቻ ያካትታል ማለት ያዳግታል። ገዥ መደብና ሊሂቃን በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ጎን ለጎን የሚገኙበት ስልጣንን በፍርርቅ የሚይዙበት አንዳንዴም የሚጋሩበት ሁኔታ አይጠፋም።
የማኪያቬሊ አትኩሮት ስልጣን የያዙ፤ ይዘውም መቆየት የሚሹ፣ የፖለቲካ ልሂቃን ላይ ነው። ነጋዴ ባስመዘገበው ትርፍ ልክ ተመዝኖ ስኬታማ ነው ወይም አይደለም እንደሚባለው የፖለቲከኛ ስኬትም መስፈርያ የስልጣንን እርካብ በመቆናጠጡና ተደላድሎ በመቀመጡ ላይ ነው።
ማኪያቬሊ እንደሚለው በፖለቲካ ውስጥ ብዙሃኑ ህዝብ ያን ያህልም አሳሳቢ አይደለም። በፖለቲካው ንፍቀ ክበብ ሊያደርጋቸው የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም ሊያደርጋቸው የማይችላቸው ነገሮች ጥቂት አይደሉም። እንዲያው በአብዛኛው የህዝብ ሚና ድርጊት ከመከወን ይልቅ ለድርጊት የአፀፋ ምላሽ መስጠት ነው። ስለዚህ ህዝባዊ ባህርይ በጥንቃቄ እና በጥበብ ሊገመት ወይም ሊተነበይ ይችላል። የማኪያቬሊ የፖለቲካ ህልዮት በመሰረታዊነት የተገነባው በህዝብ ተገማችነት ላይ ነው።
ማኪያቬሊ “አንድ ዜጋ በህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ልዑል ወይም ገዥ ለመሆን ከበቃ የህዝቡን ወዳጅነት መጠበቅ አለበት። ይህ ደግሞ ቀላል ነው። ከህዝብ የሚቀርበው ጥያቄ “አትጨቁነን” የሚል ብቻ ነው”ሲል ፅፏል።
ከዚህም ባሻገር አንድ ገዢ መደብ በሰዎች ንብረት ወይም ክብር ላይ ጥቃት እስካልቃጣ ድረስ ህይወታቸውንም በእርካታ (ያለአንዳች ማጉረምረም) እስከመራ ድረስ ጥቂት ተገዳዳሪዎቹን ብቻ መጋፈጥ ይችላል። እነርሱን ደግሞ በቀላሉ ሊቆጣጠራቸው የሚችልበት በርካታ መንገዶች አሉ።
ህዝብ ነፃነትን ቢጠማም እንኳ ነፃነት ለተራው ህዝብ ሌላ ምንም ሳይሆን ደህንነት ነው። “ልዑሉ የበላይ ሆኖ ለመግዛት ሲሉ ነፃነትን የሚመኙ ጥቂቶች ያጋጥሙታል። ሌሎቹ እጅግ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ብዙሃን ግን ነፃነትን የሚፈልጉት ደህንነታቸው ተጠብቆ ለመኖር ሲሉ ነው።
ይህ ሃሳብ የሚያሳየው ብዙሃኑ የሚፈልጉት ንብረታቸው እና የራስ ክብራቸው እንዳይነካ፣ መጠነኛ የደህንነት ስሜት እንዳይነፈጉ እና እንዳይጨቆኑ ነው። ብልህ ገዢ እነዚህን ሁኔታዎች ያሟላል። ከዚያ የስልጣን ቀጣይነት አስመልክቶ ብቸኛ የጭንቀቱ ምንጭ በዙሪያው ያሉ ተፎካካሪ ልሂቃን ይሆናሉ። ህዝቡ ግዙፍ አካል ቢሆንም አቅመቢስ ነው። ገዥው ከላይ የተዘረዘሩትን እውነታዎች ተረድቶ የሚገለገልባቸው ከሆነ የህዝቡን ጡንቻ ግዝፈት በማሰላሰል እንቅልፉን የጣለበት ምክንያት አይኖርም።
ማኪያቬሊ እንደሚለው ፖለቲካዊ ስልጣን በህዝብ ፈቃድ ላይ የሚመሰረት ነው። ይህ ፈቃድ ግን ንቁ አልያም ፍዝ ሊሆን ይችላል። ብልሃት እና ጥበብ በታከለበት ሁኔታ ሊገራ ይችላል። ህዝብ ክብሩ፣ ንብረቱና ደህንነቱ ከተጠበቀለት ስለፖለቲካዊ ፖሊሲዎች፣ ስለመንግስት ስርዓቶች እና ቅርጾች ጠልቆ በመመራመር ራሱን አያደክምም። ደስ እያለው ፈቃዱን ይቸገራል። አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ዜጎች በህይወት ስንክሳራቸው መሃል ቆም ብለው የትኛውን ገዥ አሊያም ህግ መከተል እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው አያሰላስሉም። በተፈጥሮኣቸው ለፍዝ ተፈጥሮኣቸው ያደላሉ። የተገዢዎቹን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ስነልቦናዊ እርካታ መጠበቅ የቻለ ልዑል በፖለቲካው ረገድ የሚረብሸው አይኖርም።
ተራው ማህበረሰብ ለፖለቲካ ግድ የሚያጣው በራሱ የኑሮ ሕጎች ምክንያት ብቻ አይደለም። ፖለቲካ ብርቱ ጥናትና ማሰላሰል የሚጠይቅ፣ ውስብስብ ሂደት በመሆኑም ጭምር ነው። ፖለቲካ በተረት አከል ትረካዎች እና ከፊል እውነቶች የተንቆጠቆጠ እንግዳን የሚያስበረግግ ልዩ ዓለም ነው። ያን ያህልም የማይዋዥቅ ስብዕና መገንባት እና ያን ምስል ይዞ መቆየት ያለመታከት መልፋትን የሚፈልግ ከባድ ተግባር ነው። በሚፈለገው ልክ መልፋት፣ መድከም የሚችሉ እና የሚፈቅዱ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ተራው ህዝብ በሚያየው ገጽታ ብቻ ተረስቶ ሊኖር ዝግጁ ነው።
በዲስኮርስ ላይ እንደተጠቀሰው “ከሰው ልጅ ውስጥ የሚበዙት ተራ ሰዎች ገጽታ እውነት የሆነ ያህል ያረካቸዋል። እና በትክክል ወይም የሚሉትን ከሆኑ ነገሮች ይልቅ በሚመስሉ ነገሮች ይማረካሉ።
ገዥ በጣም ጠንካራ ሰው መሆን አለበት። እንደአስፈላጊነቱም ይህንን ጥንካሬውን ሊያይ ይገባዋል። ሃላፊነቱ መንግስትን ማስተዳደር፣ ማረጋጋት፣ እና ዘለቄታውን ማስቀጠል ነው። ከዚህ የተነሳ ሁልጊዜም “ጨዋ” እንዲሆን አይጠበቅም።ገዥ፣ የተገዥዎቹን ህብረት ለመጠበቅ እና ታማኝነታቸውን ለማስጠበቅ ዓላማ ጭካኔን መተግበር ቅር ሊያሰኘው አይገባም። ከዚህም ይነሳና ወሳኝ ጥያቄ ይለኩሳል፤ ከመወደድ መፈራት ይሻላል? ወይስ በግልባጩ መወደድ ከመፈራት ይበልጣል? ለዚህ መልስ ሲያስቀምጥም ገዢ መፈራትም፣ መወደድም አለበት፤ ነገር ግን ሁለቱ አንድ ላይ ስለማይሄዱ መመረጥ ካለበት ከመወደድ ይልቅ መፈራት አደጋን ይቀንሳል ሲል ያስቀምጣል።
ፍርሃትንም ሆነ ጭካኔን እንዲሁ ያለምንም ግብ መጠቀም አያስፈልግም። ጨካኝ ለመሆን ብሎ ብቻ መጨከን፣ ለመፈራት ብቻ ፍርሃትን መንዛት፣ተገቢ አይደለም። ፖለቲካዊ ዓላማ ያስፈልገዋል። ኮስተር ማለትን ከሚፈልጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ውስጣዊ ተቃውሞ ነው።አዲስ መንግስት ወይም ስርዓት በተቋቋመ ቁጥር ተቃውሞ የሚጠበቅ ነው።
ገዥ ሊጠቀምባቸው ከሚችላቸው በጣም ውጤታማ ብልሃቶች መካከል አንዱ በህዝቡ አእምሮ ውስጥ የኖሩ ስሜቶችን ለአገልግሎት ማዋል ነው። ከነዚህ ስሜቶች ውስጥ ስር የሰደዱት ደግሞ ሃይማኖታዊዎቹ ናቸው። ገዥ ራሱ ሃይማኖታዊ ሰው መሆን የለበትም። ሆኖም በሌሎች እምነት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ከምንም ነገር በፊት ብቸኛው ምኞቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ሃይማኖታዊ መሰረቶችን ማግዘፍ እንደሆነ በሚያስመስል ሁኔታ ድርቶችን መከወን አለበት።
ሰዎች በልማዶቻቸው የታጠሩ ፍጡራንም ናቸው። ለነባር ህይወታቸው ታማኝነት አላቸው። ከማይገመት ይልቅ የሚያውቁት የሚገምቱትን ይመርጣሉ። ይህንን በማወቅም መንግስታት አዳዲስ ንድፎች እና መርሃግብሮች ይዘው መንቀሳቀስ ቢያሰኛቸው የሚያስተዳድሩትን ህዝብ ወግ አጥባቂ የስሜት ቅንጣት ሊገነዘቡት ግድ ይላቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ወርቁ ማሩ