የውል ግዴታ ቀሪ መሆን
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከጥቂት ጊዜያት በፊት ውልን ከመሰረዝና ከማፍረስ ጋር በተያያዘ አንድ ጽሑፍ ለአንባብያን ማድረሳችን ይታወሳል።በዚያ ጽሑፍ ታዲያ በውል ውስጥ የተቋቋመ ግዴታ ቀሪ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች ውስጥ የውል ስረዛና የውል መፍረስን በዝርዝር ተመልክተናል።በዚህኛው ጽሑፍ ደግሞ የውል ግዴታ ቀሪ የሚሆንበትን ሌላኛውን ምክንያት – ውለታን ስለማስቀረት እንዳስሳለን።
ውል ግዴታን የሚያቋቁም ተግባር ነው።በዚህ ግዴታ ውስጥ ያሉት ተዋዋዮች አንዱ ከሌላው መብት ጠያቂና አንዱ ለሌላው ግዴታ ፈጻሚ ናቸው።በተለመደው አነጋገር ባለዕዳ (Debtor) የሚባለው ተዋዋይ አንድ ነገር የመፈጸም ግዴታ አለበት፤ ባለገንዘብ (Creditor) የሆነው ወገን ደግሞ አንድ ነገር እንዲፈጸምለት የመጠየቅ መብት አለው።
ውልን የተረጎመው የፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 675 «ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው» በማለት ይገልጸዋል።
ከዚህ የምንረዳው በመሠረቱ ውል ሁለትና ከዚያ በላይ ሰዎች የሚያደርጉት ስምምነት መሆኑን ነው።ነገር ግን ስምምነት ሁሉ ውል አይደለም።አንድ ስምምነት ውል ለመባል እንደ ሕጉ አነጋገር ስምምነቱ ግዴታን ማቋቋም ይኖርበታል።
ከዚህም ሌላ ግዴታው መኖሩ ብቻ ሳይሆን ለአፈጻጸሙ በሕግ ዋስትናን ያገኘ በመሆኑ መብት ያለው ወገን ውሉ እንዲፈጸምለት ማስገደድ ወይም በፍርድ ቤትም መክሰስ ይችላል።የዚህ ሁሉ መሠረቱ ታዲያ ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ነው የሚለው ነው።
የውል ግዴታ በተዋዋዮቹ ፍላጎት የሚመሰረተውን ያክል የሚለወጠው፣ የሚሻሻለው ወይም ቀሪ የሚሆነውም በራሳቸው ነው።በዚሁ መነሻ ውሉ ከተፈጸመ ግዴታው ቀሪ ይሆናል።ውሉ ከተፈጸመ አንዱ ከሌላው ጋር የተሳሰሩበት የውል ገመድ ይበጠሳል።
ከዚህም ሌላ ውሉ ውጤት እንዳይኖረው ተዋዋዮቹ ከተስማሙ የውል ግዴታ ቀሪ ሊሆን ይችላል።ይህ ብቻ ሳይሆን ውሉ በአንዱ ወገን ባለመከበሩ፤ አፈጻጸሙን አስቸጋሪ የሚያደርጉ ሁኔታዎች (ለምሳሌ ከአቅም በላይ ነገር ሲያጋጥም) እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች የውል ግዴታ ቀሪ ሊሆን ይችላል።
የውል መሰረዝና መፍረስ፤ በተዋዋዮች የውል ግዴታ ማስቀረትና የዕዳ ምህረት ስምምነት፤ የቀደመውን ውል በአዲስ መተካት፤ የዕዳ መቻቻል፣ የግራቀኙ የመብት መቀላቀልና ይርጋ በሕጋችን የውል ግዴታን የሚያስቀሩ ምክንያቶች ናቸው።
ውልን ማስቀረት (Termination)
ተዋዋዮች የውል ግዴታ ለማቋቋም እንደሚችሉ ሁሉ ይህንን ግዴታ ለማስቀረት የመስማማት መብት አላቸው።ይህ መብት ታዲያ ውልን በጥቅሉ በሚተረጉመው የሕጉ ቁጥር 1675 ላይ በግልጽ ሰፍሮ እናነበዋለን።ውል ንብረትን የሚመለከት ግዴታ የሚቋቋምበት፤ የተቋቋመው ግዴታ ቀሪ የሚደረግበት ወይም የተቋቋመው ግዴታ የሚሻሻልበት ስለመሆኑ በሕጉ ተመልክቷል።
ውልን ማስቀረት የውል ግዴታ የሚቀርበት አንዱ መንገድ ነው።ውልን መመስረትና ውል ማስቀረት የተለያዩ ሕጋዊ ክንዋኔዎች ናቸው።ሁለቱም የተለያዩ ውጤቶች ያሏቸውና በሕግም ፊት የተለያየ ዋጋ የሚያወጡ ናቸው።ውል ሲመሰረት መሟላት የሚገባቸው የፈቃድ፣ የችሎታ፣ የሕጋዊነትና የውል ፎርም ቅድመ ሁኔታዎች ውሉ ቀሪ ሲደረግም መሟላት አለባቸው።
ውል ሲመሰረት አንዱ ወገን ግዴታውን ለማቋቋም ያለውን ፍላጎት በሕግ በተመለከተው የውል አቀራረብ ደንብ መሠረት (በቃል፣ በጽሑፍ ወይም በተለመዱ ምልክቶች) እንደሚገልጸው ሁሉ ግዴታውን ቀሪ ለማድረግ የሚፈልገው ተዋዋይ ወገን በተመሳሳይ አቀራረብ ይህንን ፍላጎቱን ለሌላው ተዋዋይ ወገን ያስታውቀዋል።
የተጠየቀው ተዋዋይ በበኩሉ በዚህ ሀሳብ የሚስማማ ከሆነ ለውል ምስረታ በተገለጸው የአቀባበል ደንብ መሠረት (በቃል፣ በጽሑፍ ወይም በተለመዱ ምልክቶች) ውሉ ቢቀር የተስማማ መሆኑን ይገልጽለታል።በዚህ ዓይነት በተዋዋዮች ሥምምነት ቀሪ የተደረገ ውል ዋነኛ ውጤት ውሉ ለግራ ቀኙ ወገኖች ያስገኘውን መብትና የጣለባቸውን ግዴታ ማስቀረት ነው።
ውል ቀሪ እንዲሆን በተዋዋዮች መካከል የሚደረግ ስምምነት ከውል ማፍረስና ከውል መሰረዝ የሚለይባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ።ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ «የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሠረተ ሐሳቦች» በሚል ባሰናዱት መጽሐፋቸው እንደሚያብራሩት የመጀመሪያው መለያ ውልን ቀሪ ለማድረግ ሁልጊዜ የተዋዋዮች ሥምምነት አስፈላጊ መሆኑ ነው።ውል ለመሰረዝና ለማፍረስ ግን ሥምምነት ሁልጊዜ አስፈላጊ አይደለም።የውሉ ግዴታ አልተፈጸመም የሚል ወገን ሊሰርዘው ይችላል።ውልን የማፍረስ መብት ያለው ወገንም ይህንን መብቱን ለመጠቀም የሌላውን ወገን ሥምምነት ማግኘት አያስፈልገውም።
ውልን ቀሪ ማድረግ ከውል መሰረዝና ውልን ከማፍረስ የሚለይበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከውጤታቸው እንደሚመነጭ የፍትሐብሔር ሕጉን አርቃቂዎች ማብራሪያ ዋቢ በማድረግ ፕሮፌሰር ጥላሁን ያስረዳሉ።እሳቸው እንደሚያብራሩት የውል መሰረዝና የውል ማፍረስ ዓይነተኛው ውጤት ወደኋላ ተመልሶ የተሰራውን ሥራ እንዳልተሰራ፤ የተከፈለም ገንዘብ ካለ እንዳልተከፈለ ማድረግ ነው።
የውል ግዴታ ቀሪ የማድረግ ሥምምነት ግን ውሉ በተደረገበትና ቀሪ በሆነበት ጊዜ ውስጥ የተከናወኑትን ተግባራት የማይነካ ነው።ይልቁንም ውል የማስቀረት ስምምነት የግራ ቀኙን የወደፊት ግዴታዎች የማስቀረት ውጤት ነው ያለው።
በመሆኑም ውል ቀሪ ሲሆን እንደ ፈራሽ ወይም ዋጋ አልባ ውሎች ከቶውንም እንዳልተደረገ አይቆጠርም።በሕጉ ዓይን ሁለቱም ራሳቸውን እንደቻሉ ሁለት ውሎች ነው የሚቆጥራቸው።
ውልን ቀሪ የማድረግ ሌላው ውጤት የሦስተኛ ወገኖችን መብት መንካት የሌለበት መሆኑ ነው።የውል ቀሪ ማድረግ ውጤት ከውል መመስረት ውጤት ጋር ሁልጊዜ ተመሳሳይ አይደለም።በተለይም ሦስተኛ ወገኖች ውሉ ከተደረገ በኋላ በጉዳዩ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመግባት መብት አግኝተው ሊሆን ይችላል።
ወይም የውሉ ባህርይ ከተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታ በተጨማሪ ሌሎች ወገኖችንም መብት ጠያቂና ግዴታ ፈጻሚም ሊያደርጋቸው ይችላል።በዚህ መነሻ ነው እንግዲህ የመጀመሪያው ውልና ውሉ ቀሪ የተደረገበት ሥምምነት ውጤቶች የተለያዩ የሚሆኑት።
ይህንን ጉዳይ ግልጽ ለማድረግ ፕሮፌሰር ጥላሁን የጠቀሷቸውን ምሳሌዎች እንመልከት።አንድ ተቋራጭ ከባለሀብቱ ጋር የሕንፃ ግንባታ ሥምምነት አድርጎ ይዋዋላል።በውሉ ላይ ባለሀብቱ ተቋራጩ ሥራውን ለንዑስ ተቋራጮች እያከፋፈለ ለማሰራት የሚያስችለው መብት ተሰጥቶታል።
በዚሁ መሠረት ተቋራጩ የቁፋሮውን፣ የመሰረቱን ግንባታ፣ የቧንቧ ዝርጋታውን እንዲሁም የኤሌክትሪክ ሥራዎችን ለሌሎች ንዑሳን ተቋራጮች ይሰጣቸዋል።በዚህ ሁኔታ ሥራው ተጀምሮ የተወሰነ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ባለሀብቱና ተቋራጩ ውላቸውን ቀሪ ለማድረግ ቢስማሙ የሦስተኛ ወገኖችን መብትም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው።እናም የንዑሳን ተቋራጮቹን መብት በማይነካና ጥቅማቸውንም በሚያስጠብቅ መልኩ ውሉን የማቋረጥ መብት ነው ያላቸው።
በሌላ ምሳሌ ቤት ሻጭና ገዥ በውላቸው መሠረት ገንዘቡን ተቀባብለው ቤቱንም ይረካከባሉ።ገዥው ሕጉ የሚጠይቀውን ሥርዓት አሟልቶ ቤቱን የራሱ ካደረገ በኋላ ይህንኑ ቤት መያዣ በማድረግ ከባንክ ገንዘብ ይበደራል።ውሎ አድሮ ሻጩና ገዥው ውሉን ቀሪ ለማድረግ ቢስማሙ ይህ ሥምምነታቸው የሦስተኛ ወገኑን ጥቅም እንደሚጎዳ ግልጽ ነው።
ውልን በተናጠል ቀሪ ማድረግ
ከላይ እንደተብራራው በመርህ ደረጃ የውል ግዴታ ቀሪ የሚሆነው በግራ ቀኙ ስምምነት ነው።ይሁንና አንደኛው ተዋዋይ ብቻ ውልን ቀሪ ለማድረግ የሚችልባቸውን ሦስት ሁኔታዎች ሕጉ አስቀምጧል።
እነዚህም የመጀመሪያው በውሉ ውስጥ የውል ቀሪ ማድረጊያ ቃል ከገባ ነው።ሁለተኛው ደግሞ ውሉ በባህርዩ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቀጥል ሲሆን ነው።ሦስተኛው ምክንያት በሁለቱ ተዋዋዮች መካከል የነበረውና ለውሉ መነሻ የነበረው የመተማመን ግንኙነት ቀርቶ ከሆነ ነው።
የውል ቀሪ ማድረጊያ ቃል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ወይም ከአንድ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።በውሉ ውስጥ «ያለምንም ምክንያት ተዋዋዮች በመረጡት ጊዜ ማስታወቂያ በመስጠት ብቻ ግዴታውን ሊያቋርጡ ይችላሉ» የሚል ቃል ካለ ማንኛውም ተዋዋይ ይህንን ሥርዓት አሟልቶ ውሉ ወደፊት ከሚያስከትለው ግዴታ ራሱን ነፃ ማድረግ ይችላል።
ውሉ ቀሪ የሚደረገው ከሁኔታ ጋር በተያያዘ መንገድ ከሆነ ይደርሳል ተብሎ ከሚጠበቅ ወይም አይደርስም ተብሎ ከሚጠበቅ አጋጣሚ አንጻር እየታየ ተግባራዊ መሆን ይችላል።ሥራ-አልባ የሆነ ታናሽ ወንድሙን ሥራ እስከሚያገኝ ድረስ ወርሃዊ ተቆራጭ ለማድረግ የተስማማ ሀንገፋ ወንድም ታናሽ ወንድሙ ሥራ አግኝቶ ደመወዝ ቆጣሪ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በውል የገባው ግዴታ ቀሪ እንዲሆን የመጠየቅ መብት አለው።
በሌላ በኩል ላልተወሰነ ጊዜ የሚደረጉ የኪራይ፣ የቅጥር፣ የአላባ ጥቅም፣ የአገልግሎት እና መሰል ውሎችም በአንዱ ወገን ጥያቄ ብቻ ቀሪ ሊሆኑ ይችላሉ።በሥራ ቅጥር ውል ውስጥ አንደኛው ተዋዋይ ቢሞትና ውሉ ከሟቹ የግል ችሎታና ባህርይ ጋር የተያያዘ በሚሆንበት ጊዜ ግዴታው ቀሪ ሊሆን ይችላል።አሰሪ ከሟች አባቱ ጋር አድርጎት የነበረው የሥራ ውል የተቋረጠበት ወራሽ የአባቴ የሥራ ቦታ ይሰጠኝ ብሎ እንደመብት ለመጠየቅ አይችልም።
ከዚህም ሌላ ተዋዋዮችን ለውል ያበቃቸው የመተማመን ግንኙነት አለመኖሩ ሲረጋገጥ ወይም ሲቋረጥ ውሉ ባለበት ሁኔታ መቀጠል ስለማይችል ቀሪ ይሆናል።የንግድ ሸሪኮች በመካከላቸው አለመግባባት ከተፈጠረ፤ በአደራ ሰጪና በአደራ ተቀባይ መካከል አለመተማመን ከታየ፤ በንብረት ጠባቂና በአስጠባቂ መካከል የጥርጣሬ ነፋስ ከገባ ውሉን ቀሪ ለማድረግ ይችላሉ።
አንደኛው ወገን ውልን ቀሪ ለማድረግ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም የውሉን ግዴታ ቀሪ ለማድረግ የሚፈልገው ወገን በሕግ፣ በልማድ ወይም በአዕምሮ ግምት በቂ የሆነ የመዘጋጃ ጊዜ ለሌላው ወገን የማስጠንቀቂያ ጊዜ የመስጠት ግዴታ በሕግ ተጥሎበታል።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የሥራ ውል ነው።በሥራ ውል ውስጥ የውሉን ግዴታ በተናጠል በሚሹ ጊዜ አሰሪና ሠራተኛ ሁለቱም ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡
በአንዳንድ ሁኔታዎች ሕጉ ራሱ የውል ቀሪ ማድረጊያ የማስጠንቀቂያ ጊዜውን ገድቦ ያስቀምጣል።በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ መስጠት ግዴታ ከመሆኑ በስተቀር የጊዜ ገደብ ላይቀመጥ ይችላል።
በዚሁ መሠረት በሕግ የተወሰነ የውል ቀሪ ማድረጊያ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ባልተቀመጠባቸው ሁኔታዎች ውሉ የተደረገበት ጉዳይ ከልምድ አንጻር እየታየ እንዲሁም በአዕምሮ ግምት እየተመዘነ የማስጠንቀቂያ ጊዜው በዳኞች ተወስኖ ሊቀመጥ ይችላል።
ለምሳሌ ቁልፍ በሆነ ሥራ ላይ የተመደበ ሠራተኛ ሥራውን በቅጽበታዊ ማስጠንቀቂያ ቢለቅ በአሰሪው ላይ ያልተጠበቀ ኪሳራ ሊያደርስ ይችላል።ምናልባትም ከአሰሪው አገልግሎት በሚያገኘው ኅብረተሰብ ላይም ችግር ሊፈጥር ስለሚችል አሰሪው ተተኪ ሠራተኛ የሚፈልግበት ለሕሊና ግምት በቂ የሆነ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16 /2012
በገብረክርስቶስ