ከደብረብርሃን ወደ አንኮበር በሚወስደው የጠጠር መንገድ በተሽከርካሪ እያዘገምን ነው። አቧራው አንዱን ተሽከርካሪ ከሌላኛው ጋር አላስተያይም እያለ ከመሬት እየተነሳ ይጎን ጀምሯል። እታች ላይ የሚያነጥረው የጠጠር መንገድ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከነአቧራው አካባቢውን ጥሎ እንደሚጠፋ ስላወቀ ነው መሰል ኃይሉ በርትቷል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯን እና የተለያዩ ባለስለጣኖችን የያዙ የመስክ መኪኖች 42 ኪሎ ሜትር በሚዘልቀው የደበረብርሃን አንኮበር መንገድ ከፊት ሆነው ይመራሉ። እኛ ከኋላ ነን የአካባቢው መልክአምድር ምስል በተንቀሳቃሽ ስልካችን እያስቀረን ብርዳማውን የሰሜን ሸዋ አካባቢ እያቋረጥን ነው።
መንገዱ በኮንክሪት አስፋልት ደረጃ ሊገነባ በመሆኑ የጅማሮ ሥራ ላይ ለመድረስ ነው ጉዟችን። የጉዟችን መዳረሻ ላይ አንድ የኮንስትራክሽን መኪና አፈሩን እያንጓለለ የመንገድ ሥራውን ጀምሯል። የአካባቢው ሰው የመንገድ ጅማሮውን እየተመለከተ ቄሶቹን እና ሼሒዎቹን ይዞ እንግዳዎቹን በአግባቡ እየተቀበለ ሲሆን፤ ከአንድ የአካባቢው ነዋሪ ጋር ጨዋታ እንደጀመርን ንግግራቸው ቀልቤን ሳበው። ‹‹መንገዱ በእኔ ቤት ላይ ነው የሚሄደው ነገር ግን ካሳ ከመቀበሌ በፊት እንኳን ቢሆን መንዱ ይሠራ እና ሲጋመስ መውሰድ እችላለሁ ብዬ ፈቅጃለሁ›› አሉኝ።
አቶ ናሙዬ ሽፈራሁ ይባላሉ ዕድሜያቸው 50 ነው። ከደብረብርሃን አንኮበር የሚሠራው የአስፋልት መንገድ በይዞታቸው ላይ ያልፋል። ቀድሞም ለሥራ ብርቱ የሆነው የአካባቢው ማህበረሰብ የመንገድ ግንባታውን በጉጉት ይጠብቅ ስለነበር ከገንቢዎቹ ጋር ተባብሮ እንደሚጨርሰው እምነታቸው መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹እኔም መንገዱ በይዞታዬ ላይ ቢያልፍም የካሳ ክፍያው ግንባታውን እንደሚያጓትተው ስለተረዳሁ ፕሮጀክቱ እንዲጀመር ፈቅጃለሁ። ዋናው የመንገዱ መሠራት ነው። ካሳው የትም አይሄድብኝም። የወንድሜ ቦታ ላይም መንገዱ ያልፋል፤ ስለዚህ በደስታ ተቀብለን የመንገዱን መጠናቀቅ እንጠ ብቃለን›› ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ከሆነ፤ አሁን ያለው የጠጠር መንገድ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ ነው። አንኮበርን እና የምኒልክን ቤተመንግሥት ሊጎበኙ የሚመጡ ቱሪስቶች ምቾት አጥተው ነበር የሚመለሱት። በመንገዱ አስቸጋሪነት የተነሳ የአካባቢው ወጣቶችም አነስተኛ ተሽከርካሪ ገዝተው የትራንስፖርት አማራጭ ለማቅረብ አልቻሉም። ወላድ እናቶችን እና ታካሚዎችን ወደ ጤና ጣቢያ ለመውሰድ ሲሞከር መንገዱ ከፍ ዝቅ እያደረገ ስለሚያጉላላቸው በርካቶች በስቃይ ውስጥ ኖረዋል። አሁን የተጀመረው መንገድ ሲጠናቀቅ ግን ችግሮቹ ይቀረፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የአካባቢውም ወጣትም በቱሪስት ገቢ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይታመናል።
ወይዘሮ ጎዝጉዥ አጥላው ደግሞ የአንኮበር ወረዳ ደንገጎ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የአካባቢው ህዝብ የልማት ናፋቂ በመሆኑ ግንባታውን በደስታ ነው የተቀበለው። የካሳ ክፍያ እጥረት ችግር አለብኝ ብለው ግንባታውን ሊያዘገዩ የሚችል ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው ታይቷል። አብዛኛው ሰው ግን ግንባታው እንዳይጓተት በሚል የእራሱን ይዞታ ለግንባታው እየለቀቀ ይገኛል። ይህ የህብረተሰቡ ቀናነት የመንገድ ግንባታው እስኪጠናቀቅ እንደሚቀጥል ውይይት ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት መኖሩን እና የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት በመመልከት ባለሀብቶች ይመጡ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ጎዝጉዥ፤ አስቸጋሪውን የጠጠር መንገድ ሲመለከቱ ግን ኢንቨስትመንታቸውን ሰርዘው እንደሚመለሱ ይናገራሉ። በመሆኑም ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ ሲገነባ የተሻለ የኢንዱስትሪ አማራጮች ለአካባቢው ህብረተሰብ እንደሚቀርብ ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን እንደሚገልጹት፤ የ42 ኪሎሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገዱ የደብረ ብርሃን-አንኮበር-ዱለቻ-አዋሽ-አርባ የ135 ኪሎ ሜትር መንገድ አካል ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅ የደብረብርሃን አካባቢን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ለወጪና ገቢ ንግድ መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ከደብረብርሃን አዋሽ አርባ አማራጭ መንገድ ሆኖ ሲያገለግል በአዲስ አበባ በኩል የሚደረገውን አላስፈላጊ ጉዞ በ229 ኪሎ ሜትሮች ይቀንሰዋል። በተጨማሪ መንገዱ የአካባቢውንም የተፈጥሮ ሀብቶች ወደአግሮ ኢንዱስትሪ ግብአትነት ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ግንባታውን የያዘው አገር በቀሉ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን በተያዘለት የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚያከናውን ይጠበቃል። በዲዛይኑ መሰረት ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የአፈር ቆረጣ ሥራ በማካሄድ የአቃፊ ግንብ ሥራ ይከናወናል። በከተሞች የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 17 ሜትር በገጠር መንደሮች ደግሞ አስር ሜትር ስፋት ይኖረዋል። በተጨማሪም ትላልቅና አነስተኛ የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎች በመቅበር የውሃ መፋሰሻዎች ይገነባሉ። በሌላ በኩል ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ ዳር ትራፊክ ምልክቶች ይተከላሉ። ይህ ሁሉ ሲከናወን የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ስለሚፈጠርላቸው ሰላማቸውን በማስጠበቅ ለግንባታው መጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በመተማመን ነው።
በግንባታው ጅማሮ ፕሮግራም መጠናቀቂያ ላይ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ደግሞ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እና በጥራት መጠናቀቅ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ነበር ማሳሰቢያ ያስተላለፉት። በመጨረሻም ግንባታውን የሚያካሂደው የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ የግንባታው አማካሪ ድርጅት ኮር ኮንሰክልቲግ ተወካይ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካይ እና የሰሜን ሸዋ አስተዳዳሪ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መድረክ ላይ ወጡ። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ እና የመንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር መሃመድ ተካተቱ። ሁሉም እጃቸውን ተያይዘው የመንገድ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን የበኩላቸውን እንደሚወጡ በአካባቢው ህዝብ እና በመገናኛ ብዙሃን ፊት ቃል ከገቡ በኋሏ የዕለቱ መርሐግብር መጠናቀቂያ ሆነ።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
በጌትነት ተስፋማርያም