አዲስ አበባ፡- አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እንደ ጥፋቱ ዓይነት ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ የማጣራት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በፍርድ ቤት ደረጃ የሚቀጡ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችን የጥፋት ዓይነት የማጣራት ሥራ እየተካሄደ ነው።
የማጣራቱ ሥራ የትኛው ጥፋት ወደ ፍርድ ቤት ቅጣት እና አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው።
‹‹ሕጋዊ ሳይሆኑ በንግድ ላይ የተሰማሩና የዋጋ ጭማሪ ሲያከናወኑ የተገኙና ያለ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ።›› ያሉት የንግድ ቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹ያለ ንግድ ፈቃድ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ለኅብረተሰቡ እያቀረቡ የሚገኙ ንግድ ፈቃድ ማውጣትና ሕጋዊ መሆን አለባቸው።›› ሲሉ አሳስበዋል።
በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ከሕግ ውጪ የሚወሰዱ ርምጃዎች ተገቢ አለመሆናቸውን ገልጸው፣ ይህ ዓይነቱ ተግባር ሥርዓተ አልበኝነትን እንደሚያነግስ አስታውቀዋል። በደንብና ሕግ መሠረት እንደ ጥፋቱ ቅለትና ክብደት ታይቶ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰዳል እንጂ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚወሰድ ርምጃ መጠበቅ አይገባም ብለዋል።
አቶ አብዱልፈታህ እንደገለፁት፤ የንግድ ቢሮው ቁጥጥር ድርጅቶችን የማሸግና ሕጋዊ ርምጃ የመውሰድ አይደለም። ዋናው ዓላማ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርትና አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ ማድረግ ነው። ይሄንን ባላደረጉት ላይ ግን ርምጃ ይወሰዳል።
እየተወሰደ ያለው እርምጃ በጎ ተፅዕኖ ማምጣቱን ጠቅሰው፣ አንዳንድ ምርቶችም በሚፈለገው ደረጃ ዋጋቸው ቀንሷል ማለት ባይቻልም ሁሉም አካባቢዎች ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መረጋጋት እየታየ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታው ርምጃ በመውሰድ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በበቂ ደረጃ በማቅረብ ነው መሆኑን አመልክተው፣ በዚህ ላይም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በፍርድ ቤት ደረጃ የሚቀጡ ነጋዴዎች ጉዳይ እየተጣራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ያለ ንግድ ፈቃድ የሚነግዱ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወሰዱ አመልክተዋል። ሕጋዊ ሳይሆኑ በንግድ ላይ የተሰማሩና የዋጋ ጭማሪ ያከናወኑ እንዲሁም ያለአግባብ ምርት ያከማቹም እንደ ጥፋታቸው ዓይነት አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስታውቀዋል።
ከዚህም ባሻገር ሕጋዊ ርምጃ የሚወሰድባቸው እንዳሉ ገልጸው፣ የሕግ ክፍሉም እነዚህን ነገሮች ለይቶ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወሰድ ጠቁመዋል። አስተዳደራዊ ርምጃ የሚወሰድባቸው ደግሞ በአስተዳደራዊ ርምጃ ችግራቸው የሚፈታ እንደሚሆን የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል። ሕጉም እንደ ጥፋቱ ዓይነት ታይቶ ርምጃ ይወሰዳል ይላል እንጂ ለያንዳንዱ ነገር ዝርዝር መረጃ እንደሌለውም አስረድተዋል።
አቶ አብዱልፈታ፣ አቅራቢዎችም ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በበቂ መጠን እንዲያቀርቡ አስገንዝበው፣ ኅብረተሰቡም ሽብርና ጭንቀት ውስጥ ሳይገባ ተረጋግቶ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመከላከል ብርቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል። ንግድ ቢሮው ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በ767 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን መግለጹ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 /2012