በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ድሎች በ2018 በጀት ዓመት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ḷ

117 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ በተለይ ባለፉት ሰባት ዓመታት አዳዲስ ገጽታዎችን በመላበስ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል:: በተለይም ለቀጣናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል::ከእዚሁ ባሻገር በርዕዮተ ዓለም ታጥሮ ነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማሻሻል ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኑነት መፍጠር ተችሏል::

ኢትዮጵያ ሁሉንም ባማከለ መልኩ ከሀገራት ጋር ግንኙነት ታደርጋለች:: ለሕዝብና ለሀገር እስከጠቀመ ድረስ በገለልተኝነት መርህ ከአራቱም ማዕዘናት ጋር አብራ ትሠራለች፤ ወዳጅነት ትመሠርታለች::በእዚህም ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመስረት በሰላምና ልማት ዙሪያ አብራ በመሥራት ላይ ትገኛለች::

በእዚህ ረገድ ባሳለፍነው 2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያደረገችበት ዓመት ነው:: በበጀት ዓመቱ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ዘርፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ችላለች::

በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ መሪዎችን እና ዲፕሎማቶችን በማነጋገር እና በማወያየት የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል:: የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሞሴ ሳርን የመሳሰሉ ተጽእኖ ፈጣሪ መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አጠናክረው ተመልሰዋል::በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፈረንሳይ፣በጣሊያን፣ በቬትናም አደና መሰል ሀገሮች በመገኘት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አከናውነው ተመልሰዋል::

ለእዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነው ብሪክስ ነው:: ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀል ሰላምን ፣ እድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በመጣር ላይ ትገኛለች::በተለይም በአሁኑ ነባራዊ የዓለም ሁኔታ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የግድ ስለሚል ብሪክስን የመሳሰሉ ጥምረቶች ሰላም እና ልማት በማረጋገጥ ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው:: ኢትዮጵያም ብሪክስን በዋና አባልነት ከተቀላቀሉ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗ የተከተለችው የዲፕሎማሲ መርህ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው::

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ እንደመሆኑ መጠን፤ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ድጋፍ ይሆናታል::በተለይም ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ለሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ብድርና እና ርዳታ ከማግኘት አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው:: የብሪክስ ማህበር የፈጠረው ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (New Development Bank) በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሀብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለው ከመሆኑ አንጻር ኢትዮጵያም የእዚሁ ዕድል ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል የሰፋ ነው::

ሌላው የባለብዙ ዘርፍ ውጤታማነት ማሳያ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ከዓለም ባንክ ጋር የፈጠረችው ሴኬታማ ግንኙነት በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው:: ኢትዮጵያ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ መግባቷን ተከትሎ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምም ሆነ ከዓለም ባንክ ጋር ያላት ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተጠናክሯል::

ከእዚህ ባሻገርም 2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በተደረጉ እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተቀባይነቱ የጨመረበት ዓመት ነው:: በተሠሩ በርካታ የዲፕሎማሲ ጥረቶችም ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ከተለያዩ ሀገራት አዎንታዊ ምላሾችን አግኝቷል::በዓለም አቀፍ መድረኮችም እውቅና ተሰጥቶታል::የተለያዩ መሪዎችም በአንደበታቸው መስክረውለታል::

ለበርካታ ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስና የዘመናዊ ዲፕሎማሲ አዲስ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ አንዱ ክስተት ኢትዮጵያ የተከተለችው አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ነው:: ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓለም አስደንቃለች::በእነዚሁ ዓመታት አረንጓዴ አሻራ የአካባቢው መድህን መሆኑን በመረዳት ከራሷ አልፎ የጎረቤት ሀገራትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክና አብሮ በመትከልም የጋራ አካባቢን በጋራ የመጠበቅ መርህ እውን እንዲሆን መሠረት ጥላለች::

ከእዚሁ ጎን ለጎንም የጎረቤት ሀገራት በኃይል አቅርቦት እንዲተሳሰሩ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለችውም ተግባር አንዱ የኃይል አቅርቦት ዲፕሎማሲ ነው::ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ እና ከግልገል ግቤ ሦስት የኃይል ማመንጫዎች የምታገኘውን ኃይል ከራሷ አልፋ የጎረቤት ሀገራትን ልማት እንዲያቀላጥፍ ለኬንያ፣ለጅቡቲ፣ለሱዳን፣ለደቡብ ሱዳን ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች::

በአጠቃላይ 2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ውጤታማ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን ያከናወነችበት ዓመት ነው::ስለዚህ እነዚህ ውጤታማ ሥራዎች በ2018 በጀት ዓመት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል::

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You