በመዲናዋ ከ400 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች መኖራቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ከ400 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች መኖራቸውን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ከ400 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ይህም አሽከርካሪዎች የገዙትን መኪና በገዙበት ቦታ መሙላት(ቻርጅ) ማድረግ ያስችላቸው ከሆነ እንጂ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

ዜጎች በተለያየ ቦታ ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ ቻርጅ ማድረግ እንዲችሉ ከፍተኛ አቅም ያላቸውና በአንድ ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸውን መኪኖች ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ማበራከት እንደሚያስፈልግም ጠቁመው፤ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች 90 የሚደርሱ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የኃይል መሙያ ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ደንብ አውጥቶ እየሠራ ባለው ሥራ አዲስ አበባ ላይ ጥሩ ጅምር መኖሩን ያነሱት አቶ በርኦ፤ እንደማደያ ሁሉ በርካታ ቁጥር ያላቸውን መኪኖች በአንድ ጊዜ ቻርጅ ማድረግ እንዲችሉ የሪልስቴት፣ የሆቴል፣ የፓርኪንግና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች የቻርጅ መሙያ ጣቢያ እንዲያቋቁሙ በመመሪያ ይገደዳሉ ብለዋል፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ (ቻርጅ) ጣቢያዎች በየአካባቢው መኖራቸው ለአብዛኛው ማህበረሰብ ጠቃሚ ነው ያሉት አቶ በርኦ፤ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ የግል መኖሪያ ግቢ የሌለውና በጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖር እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ይህም በቤቱ ቻርጅ ማድረግ አያስችለውም ብለዋል፤ በየአካባቢው በብዛት ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በእዚህም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 1ሺህ 176 ከፍተኛ አቅም ያላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ለሚገኙ የክልል ከተሞችም እንዲሁ 1ሺህ 50 የኃይል መሙያ ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ከከተማ ውጪ በየ50 ኪሎ ሜትር እና በየ120 ኪሎ ሜትር ርቀት ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቀሱት አቶ በርኦ፤ ለእዚህም ማደያ ያላቸው ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶቹ በየማደያዎቻቸው የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን እንዲያቋቁሙ አስገዳጅ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አመልክተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መኪና አስመጪ ኩባንያዎች በትንሹ ሁለት ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን መትከል እንዳለባቸው መመሪያው ያዛል ያሉት አቶ በርኦ፤ የኤሌክትሪክ መኪና የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ከሆኑ ደግሞ ቢያንስ ሦስት ባትሪ መሙያ (‹‹ቻርጀር›› ማድረጊያ) ጣቢያዎች መትከል አለባቸው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደ ሀገር 2ሺህ 226 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አመልክተዋል።

አቶ በርኦ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሚገኙ የክልል ከተሞች አበረታች ጅምር መኖሩን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የክልል ከተሞች ቻርጀሮች እየተተከሉ እንደሆነና የከተማ አውቶቡሶችም እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ጎንደር፣ ባሕርዳር፣ ደብረብርሃን፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ አሁን ደግሞ ሀዋሳ ላይ የተጀማመሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው አንስተው፤ ጎንደር፣ ደብረብርሃንና ባሕርዳር ከተማ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የከተማ አውቶቡሶች ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የታክሲና የከተማ አውቶቡሶችን ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትር ዴኤታው አቶ በርኦ ሀሰን አመላክተዋል፡፡

በፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You