በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠን ከ80 በመቶ በላይ ነው

– የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራሮችና ሠራተኞች ሀገር በቀል ችግኞችን ተከሉ

አዲስ አበባ፦ በሁሉም ክልሎች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠን ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ። የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች አምስት ሺህ የሚደርሱ የሀበሻ ጽድና የወይራ ችግኞችን በየካ ተራራ ላይ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አጠቃላይ የደን ሽፋን ለማስተካከል እንዲሁም ዘላቂነት ያለውን ሀገራዊ ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የደን ልማት ሥራ ግቡ ኅብረተሰባዊ ተጠቃሚነት ነው ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉት ችግኞች ስለመጽደቃቸው መከታተል እና መንከባከብ እንደሚገባው የገለጹት አቶ ከበደ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሁሉም ክልሎች የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ሠራተኞች እና አመራሮችም በተለያዩ ጊዜያት የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለፍሬ እንዲበቁ ክትትል የማድረግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በሚቀጥሉት ጊዜያትም በተቋማት የተተከሉ  ችግኞችን የመመልከትና የመንከባከብ ሥራ እንደሚከናወን አቶ ከበደ ጠቁመዋል።

የደን ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ማናጀርና የየካ ተራራ የመልሶ ማልማት አስተባባሪ አለማየሁ ነጋሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በየካ ተራራ 100 ሺህ የደን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው።እስካሁን በተሠራው ሥራ 50 ሺህ የሚደርሱ የደን ችግኞች ተተክለዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራሮችና ሠራተኞች  አምስት ሺህ የሚደርሱ የሀበሻ ጽድና የወይራ ችግኞች በየካ ተራራ መትከላቸውን አመላክተው፤ የካ ተራራ ለምነቱን ያጣ እና የተራቆተ ቦታ ነበር። አሁን ግን ኮምፖስትና ኖራ በመጠቀም በአካባቢው ያለውን አሲዳማ አፈር ወደ ለምነት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባለፈም አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ የማድረግ ሥራም እየተሠራ መሆኑን አለማየሁ ነጋሳ(ዶ/ር) የገለጹት።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You