
– ብርጋዴር ጀነራል አበበ ገረሱ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ
አዳማ፡- አሁንም የሰላሙ በር ክፍት ስለሆነ በተለያዩ መንገዶች ተታለው ጫካ የገቡ አካላት ወደ ቤታቸው መግባት ይችላሉ ሲሉ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ – ብርጋዴር ጀነራል አበበ ገረሱ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የኦሮሚያ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላለፉት ሦስት ቀናት በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ በወቅቱ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የክልሉ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አበበ ገረሱ እንደተናገሩት፤ የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አሁን ላይ መሻሻል ታይቶበታል፡፡ ይህም ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን በርካታ ሥራዎች በመሠራታቸው የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለሁ በሚል ጫካ ገብቶ ማህበረሰባችንን ከሚያውከው ሸኔ ከተባለው ቡድን ጋር የፖለቲካ ልዩነታችንን ይዘን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተነጋግረን ሕዝባችንን ማገልገል እንችላለን በሚል የክልሉ ፕሬዚዳንት ተደጋጋሚ ጥሪ እንዳቀረበ አስታውሰው፤ በእዚሁ መሠረት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡ ታጣቂዎች ውይይቶችን አድርገውና የተሐድሶ ሥልጠናዎችን ወስደው ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል ሰላማዊ ሕይወት እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
የሰላም ጥሪውን አንቀበልም ብለው ሕዝባቸውን የሚያውኩ ቡድኖችን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ የክልሉ ፖሊስ ፣የፌዴራል ፖሊስ ፣ ሚሊሻ እና የሥርዓቱ ጠባቂዎች (ጋቸና ሲርና) በቅንጅት ሆነው ርምጃ ወስደዋል፡፡ በእዚህም አብዛኛው ኃይል ተመትቷል፤ የተረፈውም እጅ ሰጥቷል፡፡ በተለያየ ጊዜ እጅ የሰጡና በሺዎች የሚቆጠሩ የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ሰላማዊ ኑሯቸውን መኖር ጀምረዋል ብለዋል፡፡
አሁንም በጫካ እና በየመንደሩ ያሉና የተለያዩ ወንጀሎችን እየፈጸሙ ኅብረተሰቡን በማወክ ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ቡድኖች አሉ ያሉት ብርጋዴር ጀነራሉ፤ እነዚህ አካላት የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶች የሚሰጧቸውን ኢትዮጵያን የማተራመስ ተልእኮ እየተቀበሉ ሀገር እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ ተላላኪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን እያሉም የኦሮሞን ሕዝብ ተጠቃሚነት በጽኑ ከሚቃወሙ ሌሎች አካላት ጋር በትብብር የሚሠሩ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡
አሁንም የክልሉ መንግሥት የሰላም በርን ክፍት ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ አካላት ይህን እድል ተጠቅመው በሰላም መምጣት የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በየመንደሩ እየዞሩ ሰዎችን እያገቱ በዘመናቸው አይተውት የማያወቁትን ገንዘብ የሚጠይቁ ሽፍታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በእነዚህም ላይ የተቀናጀ ርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የክልሉን መንግሥት የሰላም ጥሪውን አክበረው የሚመጡ ታጣቂዎችን እጁን ዘርግቶ እንደሚቀበላቸው እና የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ መቀበል ባልፈለጉት ላይ ግን ርምጃውን አጠናክሮ የሚቀጥል ስለመሆኑ ብርጋዴር ጀነራል አበበ ገረሱ አስታውቀዋል።
ኅብረተሰቡም የሰላም ጥሪውን አልቀበል ብሎ የሚዘርፈውን፣ የሚገድለውን ፣ ሰላሙን የሚያውከውን ይህን ዓላማ ቢስ ቡድን ቀደም ሲል እንደሚያደርገው ሁሉ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በመሆንና ታግሎ በማጥፋት ሙሉ ለሙሉ ሰላሙን ማረጋገጥ እንዲችል ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም