
አዲስ አበባ፡- ‹‹ግብርናው ሳይቀየር ኢትዮጵያ ልትቀየር ብልፅግናም ሊመጣ አይችልም›› ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
አቶ ሽመልስ፣ ከትናንት በስቲያ በምሥራቅ ሸዋ ቦሰት ወረዳ በመስኖ የለማ የቆላ ስንዴ ማሳ በጎበኙበት ወቅት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የእርሻ ትራክተሮችን፣ ማጨጃ ኮምባይነሮችንና የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን እንዲያገኙ በማድረግ መደበኛ ሰብሎችን በመስኖ እንዲጠቀሙ ማድረግ ካልተቻለ ኢትዮጵያ ልትቀየር አትችልም፤ ብልፅግናም አይመጣም።
ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፤ኢትዮጵያን መቀየርና ብልፅግናን ማምጣት የሚቻለው አርሶ አደሮችን በዘመናዊ ማሽን እንዲጠቀሙ በማድረግ ነው። እንዲሁም አርብቶ አደሮችንና በቆላ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የዝናብ እጥረት ባለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች በሙሉ ፓምፖችን በስፋት በማሰራጨት በመስኖ እንዲያለሙ ሲደረግ ነው።
‹‹ከሽንኩርት፣ ከቲማቲምና ከጎመን በዘለለ በመስኖ የመጠቀም ልምድ በሀገራችን አልተለመደም፤ ነገር ግን እንደ ስንዴ፣ ገብስና በቆሎ የመሳሰሉ መደበኛ ሰብሎችን በመስኖ እንዲያለሙ ግብአቶችን በማቅረብ አርሶ አደሩን ከችግር እንዲላቀቅና ኢትዮጵያም እንድትለማ ማድረግ ይቻላል።›› ብለዋል።
እንደ አቶ ሽመልስ ገለፃ፤ የኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር ከዚህ በፊት ከ350 በላይ ትራክተሮችን በማስገባት በርካታ አርሶ አደሮች በዘመናዊ መንገድ እንዲጠቀሙ ማድረግ ተችሏል።
በቀጣይ ከሁለት ሺህ በላይ ትራክተሮችን ለማስገባት ከፍተኛ እርብርብ እየተደረገ ነው። የፌዴራል መንግሥትም የአርሶ አደሩን ሕይወት ማዘመን ካልቻለ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪውም ሆነ ወደ ዘመናዊ እርሻ እንደማትሸጋገር በማሰብ ትራክተሮች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል።
የክልሉ መንግሥት ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያለውን አቅም አሟጦ ውሃ የሌለበት አካባቢ በፓምፕ እንዲለማ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ከዓመት በፊት አርሶ አደሩ ትራክተር በማስገባት በሜካናይዜሽን እንዲያርስና ሕይወቱን እንዲለውጥ ለማድረግ መንግሥት የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፣ ይሁንና በዚህ ዓመት የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አርሶ አደሩ በከፍተኛ ደረጃ ትራክተር እንዲገዛ ለማድረግ የብድር ዕድሎች እንደተመቻቹለት የክልሉ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል።
‹‹ከዚህ በፊት በቆላዎችና ዝናብ አጠር በሆኑ ቦታዎች ላይ በመስኖ ተጠቅሞ ሰፋፊ እርሻዎችን ማልማት አልተለመደም።›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በዚህ ዓመት በክልሉ በተለያዩ ዝናብ አጠር ቦታዎች ላይ ስንዴን ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
እንዲሁም በባህላዊ መንገድ በመሰብሰብ የሚባክን ምርት እንዳይኖርና የአርሶ አደሩን ድካም ለመቀነስ ኮምባይነሮች በስፋት የማስገባት ሥራም እየተሰራ ስለመሆኑ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 /2012
ሞገስ ፀጋዬ