በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠ ይገኛል። ተቋማቱ ትኩረት የሚያደርጉት የህብረተሰቡን ችግሮች ሊቀርፉና ሊያቃልሉ በሚችሉ የምርምርና የፈጠራ ግኝቶች ላይ ነው። እነዚህም ግኝቶች በአብዛኛው የህብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚችሉ ናቸው።
የምርምርና የፈጠራ ባለሙያዎችን ስርዓት ባለው መልኩ በማበረታታትና በመደገፍ ስራዎቻቸው ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ሊበረታቱ ይገባል። በ2011 ዓ.ም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በምርምርና በፈጠራ ስራዎቻቸው የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ከሆኑት መካከል ተማሪ ቢኒያም ደረጀ አንዱ ነው። በዛሬ የሳይንስ አምዳችን የዚህን የፈጠራ ባለሙያ ስራዎች አሰናድተን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፤
ተማሪ ቢኒያም ደረጀ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው። ቢኒያም የፈጠራ ፍላጎት ቢኖረውም ስራው “ሀ” ብሎ የጀመረው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ መሆኑን ይናገራል። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከጀመረ በኋላም ምቹ ሁኔታ ስለተፈጠረለት የፈጠራ ስራዎቹን አጠናክሮ ቀጠለ። ቢኒያም ዘንድሮ ተመራቂ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታ በርካታ የፈጠራ ስራዎች እየሰራ ይገኛል።
የፈጠራ ስራዎች ምንነት
የተማሪ ቢኒያም ደረጀ የፈጠራ ስራዎች ኮንቬክሽናል የሆኑ ምጣዶችን ወደ የኢንዳክሽን ቴክኖሎጂ መለወጥ (አሁን በገበያ ላይ ያለውን የኤሌክትሪክ ምጣድ የሚያባክነውን የኤሌክትሪክ ጉልበት በሚፈለገው መጠን እንዲሆን የሚያደርግ ቴክኖሎጂ)፤ ኤሌክትሪክ ቪንት ኢነርጃይዘር (በአጥር ላይ የሚገጠመውን የኤሌክትሪክ ገመድ ሀይል እንዲሰጠው በማድረግ ከፍተኛ መጠን ያለው ንዝረት እንዲኖረው ማድረግ)፤ ስዊች ሞድ ፓወር ሰፕላይ (የመኪና ባትሪ ቻርጅ ማድረጊያ)፤ ፊንገር ፕሪንት አቴንዳስ ቴኪንግ ሲስተም (በአሻራ መፈረም የሚቆጣጣር መሳሪያ )፤ ሦስትና አራት አክሲስ ሲ ኤን ሲ ማሽን (በኮምፒውተር የሚሰሩ የተለያዩ ዲዛይኖችን በሚፈለገው ማቴሪያል ላይ ፅሁፎቹን መጻፍና መቅረጽ የሚያስችል መሳሪያ )፤ ቨርቲካል ዊንድ ተርባይን (በጣም ትንሽ በሆነ ንፋስ ኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጩ) ናቸው።
የፈጠራ ስራው ለየት የሚያደርገው
የቢኒያምን የፈጠራ ስራዎች ለየት የሚያ ደርጋቸው፤ አሁን በገበያ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ምጣድ የኤሌክትሪክ ጉልበት ያባክናል። የሚጠቀመው የኤሌክትሪክ ሀይልም ተመሳሳይ መጠን የሌለው በመሆኑ የሀይል እጥረት በሚኖርበት ወቅት ይዋዥቃል፤ ሀይል መቆጣጠር አይችልም። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ምጣዱ አይሰማም፤ በመሆኑም፤ እስኪሰማ ድረስ መጠበቅ የግድ ይላል። በጣም ሀይሉ ሲጨመር ደግሞ በጣም ስለሚሰማ እያጠፋን ለመጋገር ያስገድዳል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኢንዳክሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሰራው ምጣድ ገበያ ላይ ካለው ይለያል። ምጣዱ የራሱ የሙቀት መቆጣጠሪያ ያለው ሲሆን፤ ተጠቃሚ በሚፈልገው የሙቀት መጠን ላይ አድርጎ መጠቀም ይችላል። ተጠቃሚው እንጀራ ጋግሮ ጥሎ ቢሄድ ወይም ተሰክቶ የማይጋገርበት ከሆነ ሀይል ለመቆጠብ ራሱ ያጠፋል። ምጣዱ መብራት እስካልጠፋ ድረስ፤ የመስማትም ሆነ የመብረድ ነገር አይታሰብም። ሙቀቱን ስለሚቆጣጠር የሚጋገርበት ማዕድ ቤት ቀዝቃዛ ነው የሚሆነው። ህይወት ያላቸው ነገሮች አጠገቡ ቢኖሩ ጉዳት አያደርስም ።
ፈጠራው፤ ሸክላ ተሸካሚው የምጣዱ ክፍል እንዳይበላሽ ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፤ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ሊያገለግል የሚችል ነው። የሚቃጠለውና የሚቀየረው ኤሌክትሮኒክስ ቦርዱ ብቻ ነው። ይህም በተመጣጣኝ ዋጋ፤ ለሁሉም እንዲደርስ ተደርጎ ዲዛይን ሆኗል። ምጣዱ ብልሽት በሚያጋጥመው ወቅት ማንኛውም የኤሌክትሪክ እውቀት የሌለው ሰው እንዲገጣጥመው ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ኤሌክትሮኒክስ ቦርዱን ብቻ ገዝቶ መግጥም ይቻላል።
ፈጠራው አሁን ያለበት ደረጃ
እንደ ተማሪ ቢኒያም ማብራሪያ፤ በዘንድሮ ዓመት ተመራቂ በመሆኑ መላ ትኩረቱ በትምህርቱ ላይ ነው። በመሆኑም፤ እስካሁን የሰራቸውን የፈጠራ ስራዎቹን ጥቅም ላይ በማዋል ህብረተሰቡ ዘንድ በማድረስና ተጠቃሚ ለማድረግ አልቻለም። ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ግን የፈጠራ ስራዎቹን ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅና ለማድረስ በሰፊው ለመስራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ይናገራል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ወርቅነሽ ደምሰው