
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጂኦግራፊና በጂኦ ፖለቲክስ የትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ትውልዳቸው ቢሾፍቱ ከተማ ሲሆን፤ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ጀርመን ከሚገኘው ኦስና ብሩክ ዩኒቨርሲቲ በጂኦ ፖሊቲክስና ሶሻል ጂኦግራፊ የትምህርት መስክ ተቀብለዋል።
አሜሪካ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስና በጀርመን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል። በሴኔጋል የአፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ካውንስል የምርምር ክፍል ኃላፊና ተመራማሪ በመሆን ለሁለት ዓመታት ሠርተዋል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም የጂኦ ፖለቲክስና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፌሰር ናቸው።
አምስት መጻሕፍት በታዋቂ አታሚዎች አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። እንዲሁም፤ በርከት ያሉ ጽሑፎችን በታወቁ ጆርናሎች አሳትመዋል። በተለያዩ ጉዳዮች፤ በተለይ ደግሞ በናይል ተፋሰስ እና ከጂኦ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጽሑፎችን በመጻፍና በማሳተም ይታወቃሉ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተማራማሪነት ከ25 ዓመታት በላይ ካገለገሉትና አሁንም እያገለገሉ ካሉት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ጋር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከመነሻው ጀምሮ የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በግብፅ፤ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ስለነበረውና ስላለው ድርድር ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- የህዳሴው ግድብ በአባይ ወንዝ ላይ በሱዳን መውጫ አካባቢ እየተገነባ ያለ ነው። አሜሪካኖች እ.አ.አ ከ1958 እስከ 1964 ጥናት አካሂደው ከለዩዋቸው አራት ግድቦች መካከል ቦርደር የተባለው ይህ የህዳሴው ግድብ ነው። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2011 ዓ.ም ይህን ግድብ በራሷ መሬት ላይ በራሷ ገንዘብ ለመገንባት የወሰነችው ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ የሚገነባ ግድብ ሁሉም አገራት ያልተስማሙበት ከሆነ የዓለም ባንክ አይረዳም። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ምርጫ ስላልነበረው በራሱ ህዝብ፤ ጉሊት ከምትቸረችረው ምስኪን ነጋዴ እስከ ከፍተኛ ባለሃብት ድረስ ያሉት ህዝቦች አዋጥተው ቦንድ ገዝተው ለመገንባት ተገድዷል።
ነገር ግን፤ ግብፆች “ውሃችን ይቀንሳል፤ የግድቡ ሁኔታም አስተማማኝ ላይሆን ይችላል።” ሲሉ በወቅቱ ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅ ነው። “መወያየት እንችላለን። መጥታችሁ ግድቡን መጎብኘት ትችላላችሁ” በማለት የሱዳንም ሆነ የግብፅ ልዑካን እንዲጎብኙት ከማድረግ አልፎ “ሶስተኛ ወገን ጥናት ማካሄድ ይችላል” በማለት ሙሉ ለሙሉ ክፍት መደረጉ የሚደነቅ ነው። ነገር ግን፤ ለደህንነት ሲባል እንኳን የተደበቀ አንድም ሚስጢር ሳይኖር ወዳጅነትን በማክበር ክፍት ተደርጓል። ይህ ትንሽ ቢያስከፋም ግልፅ ለመሆን የተደረገው ጥረት መልካም ነው። ከዚያም እ.አ.አ በ2015 መሰረታዊ የስምምነት መርሆዎች (Deceleration of Principles) በአባይ ላይ ሳይሆን በዚሁ በህዳሴው ግድብ ላይ ስምምነት ተደርጓል።
ስምምነቱ የላይኛውንም ሆነ የታችኛውን አገራት ፍላጎት በማጣጣም ሚዛናዊ የሚሆኑበትን መርሆዎች የተከተለ የህዳሴውን ግድብ መገንባት የማይቃወም ነበር። ቢሆንም ቅሉ፤ የህዳሴው ግድብ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ይገንባ የሚል ስምምነት ቢኖርም፤ የሙሊት እና የውሃ አለቃቀቅን በሚመለከት ግን ወደፊት ስምምነት ይደረጋል ተብሏል። ነገር ግን፤ የኢትዮጵያ፤ የግብፅ እና የሱዳን የድርድር ቡድኖች አንዴ ካይሮ፤ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ፤ እንዲሁም ካርቱም እያሉ ለዘጠኝ ዓመት ከ24 ጊዜ በላይ ውይይት ቢያደርጉም መስማማት አልቻሉም።
አንዳንድ ነገሮች ውስብስብ ናቸው፤ ቀላል አይደሉም። ምክንያቱም ሁሉም የራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ስለሚሄድ አንዱ የራሱን ጥቅም ለማስከበር ሲሄድ ሌላውን ይጎዳል። ስለዚህ መቻቻል ያስፈልጋል። እንዲያውም አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፤ አንዳንድ ጊዜ አደጋ ለመቀነስ ሲባል የራስን ብሔራዊ ጥቅም ትንሽ ሸረፍ አድርጎ መተው ያስፈልጋል። ግብፆች ግን ያሰመሯቸው ቀይ መስመሮች አሉ። ኢትዮጵያም፤ ሌሎችም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የማይቀበሏቸው አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊፈፀሙ የማይችሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ።
እ.አ.አ ከ1929 ጀምሮ የነበረ ስምምነት አለ። ኢትዮጵያ ያልተካተተችበት፤ እንግሊዞች ለግብፅ በመወገን 90 በመቶ ውሃውን ግብፅ እንድትጠቀምበት የሚፈቅድ፤ 10 በመቶውን ሱዳን እንድትወስድ የሚደነግግ ስምምነት አለ። ሁለተኛ፤ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ለግብፅ የሚሰጥ ማንኛውም በአባይ ወንዝ ላይ የሚደረግ እንቅስቃሴ እና የሚገነባ ፕሮጀክት የግብፅ ይሁንታ ሳይኖረው እንዳይፈፀም የሚያሳስቡ ነገሮች አሉ። አሁንም ከ90 ዓመታት በኋላ ግብፆች ያ ተቀባይነት የሌለው ስምምነት እንዲተገበር ይፈልጋሉ።
በ1959 ዓ.ም ደግሞ ኢትዮጵያን ሳያካትቱ ሱዳን እና ግብፅ ስምምነት አደረጉ። 11 የተፋሰስ አገሮች ያሉ ቢሆንም ውሀውን ለግብፅ 75 በመቶ ለሱዳን 25 በመቶ በሚል ሁለቱ ብቻ ተስማምተውበታል። ግብፅ “ድርሻዬ ነው፤ ታሪካዊ መብቴ እና አይነኬ ነው” ትላለች። ነገር ግን፤ በቅኝ ግዛት ዘመን ላይ የነበሩትን ስምምነቶች ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም የተፋሰስ አገሮች እነታንዛኒያ እነኬኒያ በሙሉ የሚቀበሏቸው አይደሉም።
የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት የኔሬሬ ዶክትሪን የሚባል ነገር አለ። እርሳቸው “በቅኝ ግዛት ዘመን የተካሄዱ ስምምነቶች በሙሉ ተቀባይነት የላቸውም” ብለዋል። ኢትዮጵያም የኔሬሬ ዶክትሪን ተቀባይ ናት። ኢትዮጵያ የ1959ኙን ስምምነት በዚያ ዘመን “አልቀበልም፤ እኔ አልታሰተፍኩበትም።” እያለች ነበር። ግብፆች ግን በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ትቃወመው የነበረውን ስምምነት “ዋና መሰረታችን ነው” ብለው እርሱን ማዕከል አድርገው መንቀሳቀሳቸው ትልቅ ችግር ሆኗል። ስለዚህ ተደራዳሪዎቹ አንድ ቦታ ይሰባሰባሉ፤ ግን አይስማሙም።
የግብፆች ሌላው ችግር አቋማቸውን ይቀያይራሉ። ለምሳሌ፤ ካርቱም ላይ ተሰብስበው የተስማሙበትን ነገር ካይሮ ላይ ሲቀጥል ያንን ገልብጠው እንዳልተስማሙ ሆነው ይገኛሉ፤ ወይም ሌላ አዲስ ፍላጎት ይዘው ይመጣሉ። ይህ ለተደራዳሪዎች፤ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ከባድ ራስ ምታት ሆኖ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ዓላማቸው ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- እንደኔ እሳቤ የእነርሱ ዓላማ ይህንን ነገር በመጎተት እና ባለመስማማት በማሳደር በደንብ ሂሳብ ሰርተው ነገሩን ወደ አሜሪካ በመውሰድ እና ችግሩን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ ነበር። አሜሪካኖች እነርሱን ይደግፋሉ ብለው ቀድመው አስበው የሚፈረመው ሰነድ ላይም የእነርሱን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለው ገምተው ጎትተው ድርድሩን ወደ አሜሪካ ወሰዱት። እዚህ ላይ በኢትዮጵያ በኩል ችግር ተፈጥሯል።
ግብፆች አሜሪካን ዲሲ ሄደው ፕሬዚዳንት ትራምፕን አነጋገሩ። ትራምፕ ፈቃደኝነታቸውን አሳዩ፤ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አሜሪካን በታዛቢነት እንድትሰየም ተስማማ። በእርግጥ ይህ መሆን አልነበረበትም። ናይል ያለው አፍሪካ ነው። ሶስቱ አገሮች ደግሞ እየተወያዩ ነው። ውይይቱን በንፁህ ልቦና፤ በቀናነት፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ቢያደርጉት የተሻለ ነበር። ነገር ግን ግብፆች ኢትዮጵያውያንን ጥግ ለማስያዝ፤ ኢትዮጵያ መወራጫ ስታጣ ትፈርማለች ብለው በመገመት ጉዳዩን አሜሪካ አድርሰውታል። ይህም በመጠኑ ተሳክቶላቸዋል። ፊርማው ቢቀርም ኢትዮጵያ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። ከዚህ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ግብፅ አሜሪካንን ስትመርጥ ተጠንቅቃ ነው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የተደራዳሪ ቡድኑን መጨመር ከዚህ በበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ አልነበረባትም?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- ትክክል ነው። ግብፆች ጉዳዩን የህልውና ጥያቄ አድርገው ስለሚይዙት በጣም የተጠና መንገድ ይጠቀማሉ። ቀንም ሌሊትም ያስባሉ። ከውሃ ጋር ተያይዞ ህግ ላይ ያተኮሩ፤ የሰለጠኑ እና ያጠኑ፤ በጣም ብዙ ሰዎች አሏቸው። ከውሃ ጋር ተያይዞ በዲፕሎማሲም፤ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ብዙ አማካሪዎች ስላሏቸው እነርሱ በደንብ አድርገው ተዘጋጅተው ይንቀሳቀሳሉ። በኢትዮጵያ በኩልም በእርግጥ ተደራዳሪዎቹ በጣም ብቁ እና ጥሩ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን፤ ሁልጊዜ አንድ አይነት የሚታወቁ ሰዎች ብቻ በድርድሩ ላይ ይሳተፉ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ሌሎችን ሰዎች ማሳተፍ ነበረባቸው?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- አዎ! ከሌሎች ዘርፎችም ማሳተፍ ነበረባቸው። ከዩኒቨርሲቲ ቢያሳትፉ የበለጠ የተለያየ ሃሳብ ስለሚቀርብ ጥሩ ነገር ላይ ለመድረስ ይመች ነበር። በኢትዮጵያ በኩል ይህንን ዕድል አለመጠቀም ጥፋት ነው። ግብፆች ግን በጣም ዝግጁ ናቸው። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ውጤቱን ያውቁታል። ለምሳሌ፤ ኒውዮርክ በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ የግብፁ መሪ ፕሬዚዳንት አልሲሲ በመድረኩ ስለሌላ ጉዳይ ማውራት ቢኖርባቸውም ስለናይል አንስተው ተናገሩ፤ በእርግጥ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ “እዚህ መድረክ ላይ ስለዚህ መወራት የለበትም” በሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ግብፆች ያንንም ያደረጉት አውቀው ነው። ኢትዮጵያ የዋህነት ታበዛለች። ግብፅን ታምናለች። አሜሪካንን የምታክል እንደሞዴል የምትወሰድ ትልቅ አገር እንዲህ ትለዋወጣለች ብለው የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በህልማቸውም ሆነ በዕውናቸው አላሰቡትም።
በደንብ ተለይቶ የተቀመጠው በቅድሚያ አሜሪካ በታዛቢነት እንደምትገኝ ብቻ ነበር። የግምጃ ቤቱ (ትሬዠሪ) እና የዓለም ባንክ ተወካይ የተገኙት በታዛቢነት ነበር። በአንድ ጊዜ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት፤ ከዚያም ወደ አርቃቂነት፤ ወዲያው ወደ አስገዳጅነት ተለውጣለች። በእርግጥ በኢትዮጵያ በኩል ይህ ይሆናል የሚል ግምት አልነበረም። ግብፅ ግን ይህንን ሁሉ አስባበት ያደረገችው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ትምህርት መወሰድ አለበት። ነገር ግን፤ አሁን ግብፅ እየሄደች ያለችበት መንገድ አለ። የአረብ ሊግን ማሳመን፤ የተለያዩ አገራት በመሄድ ድጋፍ የመጠየቅ ሁኔታ ይስተዋላል። ኢትዮጵያም በበኩሏ በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በኩል እየሄደች ያለችበት መንገድ አለ። ነገር ግን አሁንም ግብፅ ከኢትዮጵያ በላይ ብዙ መንገዶችን እየተጠቀመች አይደለም?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- ትክክል ነው። ግብፆች የኢትዮጵያ ቡድን ሳይመጣ ሲቀር እና ጉዳዩ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሽኩሪ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በማቅናት ግብፅ ህልውናዋ አደጋ ላይ እንዳለ፤ የውሃ መብቷ እና ደህንነቷ አደጋ ላይ እንደሚገኝ፤ ካለነርሱ ተሳትፎ ውሃው መሞላት ሊጀምር መሆኑን እና ይህ ደግሞ አደጋ እንደሆነ እያስረዱ ነው። ውሸትም ጨማምረው ብዙ ነገር እየተናገሩ ነው።
የአረብ ሊግ ውሳኔ የሚደንቅ አይደለም። ምክንያቱም ዋና ፀሃፊው ጌት የተሰኙት ሰው ግብፃዊ ናቸው። የአረብ ሊግም ፍላጎቱ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን፤ ሱዳን “ይህ ነገር ልክ አይደለም” በማለት አለመስማማቷ እና ስሟ እንዲወጣ ማድረጓ “አቅጣጫው ልክ አይደለም፤ ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር የሚያጋጭ ነው” በማለት የአረብ ሊግ የፈፀመውን ማውገዟ ትልቅ ተግባር ነው።
በኢትዮጵያ በኩል የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዘግየት ቢልም ተጀምሯል። በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የሚመራው ቡድን ዑጋንዳ፤ ኬኒያ፤ ሩዋንዳ እያለ ይቀጥላል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አንድ ቡድን ይዘው ወደ አውሮፓ ሄደዋል። ነገር ግን፤ በቡድኑ ተመሳሳይ ሰው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ምሁራኖች ቢታከሉ ጥሩ ነው። አዳዲስ ሃሳብ ያላቸውንና በጉዳዩ ላይ ጥሩ ብቃት ያላቸውን በማሰባጠር መንቀሳቀስ ይገባል። ግብፅ ላይ ያለው የተለያየ ነው። ይለዋወጣሉ። ቡድኖች ሲሄዱ በምንም መልኩ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት መቻል ያስፈልጋል። ከህግ አንፃር ሊሆን ይችላል፤ የቴክኒካል ጉዳይ ሊነሳ ይችላል። በተለያየ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ መሆን አለበት።
የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በጣም ጠንካሮች እና የተካኑ ናቸው። በሰፊው ከመዘገብ አልፈው አስፈላጊ ሲሆን ይዋሻሉ። “ኢትዮጵያ ግብፅን ልታስርብ፤ ውሃ ልታስጠማ እና ልትገድል ነው። አንፈርምም ያሉት ለዚህ ነው። ክረምት ላይ ውሃ ማጠራቀም ከጀመሩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገባለን።” ይላሉ። ይህ ከድሮ ጀምሮ ያለ ነው። አዲስ አይደለም። ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሁልጊዜም የሚሉት ነው። ውሃው በተፈጥሮ ዝናብ ሲቀንስም “ኢትዮጵያውያን እዚያ ገድበውብናል” ይሉ ነበር። አሁን ደግሞ እየጨመረ ሄዷል። የኢትዮጵያ ቡድን ከዚህ በላይ መጠናከር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ቡድኑ የሙያ ስብጥርንም ያካተተ መሆን አለበት?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- አዎን! በተለያየ አቅጣጫ ምላሽ መሰጠት አለበት። የውሃ ሚኒስትሩ መሃንዲስ ናቸው። እርሳቸው ጠለቅ ያለ የዓለም አቀፍ የህግ ዕውቀት አይኖራቸውም። የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ዕውቀት ሊኖራቸው አይችልም። አንድ ሰው ሁሉንም ነገር መሆን አይችልም። ቴክኒካሊ የተነሳውን ጥያቄ እርሳቸው ቢመልሱ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከህግ አንፃር እገሌ፤ በዲፕሎማሲ ደግሞ ሌላ ሰው ቢመልስ ጥሩ ምላሽ መስጠት ይቻላል። ስለዚህ በስብጥሩ ላይ በደንብ መታሰብ አለበት። ለመንግስት ቅርብ የሆኑትን ሰዎች ብቻ ማሰባሰቡ ብዙም ውጤታማ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ በትንሹም ቢሆን ብዝሃነት ቢኖር የተሻለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከግብፅ ጋር በተመጣጠነ መልኩ ማለት ነው?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- አዎን! ጉዳዩ መከላከል ነው። የእነርሱ ቡድን የሚሰራውን በተቃራኒው የሚቀይር ቡድን ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች አካላት ለምሳሌ በየአገራቱ ያሉ አምባሳደሮች ይህን ለማሳካት ተልዕኮ ወስደው መስራት የለባቸውም?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- እንዴ! አለባቸው። አንዱ የአምባሳደር ስራ ይህ ነው። የአሜሪካም ሆነ የግብፅ፤ የሱዳንም ሆነ በማንኛውም አገር ያለ አምባሳደር የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዳ መሆን ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ የምትወስደው እርምጃ ትክክል መሆኑን ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን፤ አምባሳደሮቹ የተለያዩ ሰዎች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በኮታ አምባሳደር የሆኑ ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ ብቃታቸው ሳይታይ አምባሳደር ይሆናሉ። እነርሱ ምናልባት ዕውቀቱ ላይኖራቸው ይችላል። ማሰልጠን እና ማንኛውንም መረጃ በፍጥነት ለእነርሱ መላክ ያስፈልጋል። ቢቻል ሰብስቦ ስለናይል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ማሰልጠን አለባቸው። ያኔ በእርግጠኝነት ለዚያ አገርም ህዝብም ማስረዳት ይችላሉ። ለጋዜጠኞች ምላሽ መስጠት ይችላሉ። ኢትዮጵያ መብቷን ተጠቅማ የምትሰራ መሆኑን ማስረዳት እና ማሳመን ይችላሉ። የውሃ ሃብቷን ለመስኖ ሳይሆን፤ ሃይል ለማመንጨት ለዚያውም ተርባይኑን መትቶ ለሚያልፍ ውሃ ግብፅ አትጠቀሙ ማለቷን ለውጭው ዓለም እንዲያሳውቁ ስልጠና ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከአምባሳደሮች በተጨማሪ በየትኛውም አገር ያለ ኢትዮጵያዊ ስለኢትዮጵያ በአባይ የመጠቀም መብት ማሳወቅ የለበትም? ህዝቡ ይህንን ተረድቶ እንዲሰራ በማድረግ ህዝቡ ውስጥ ጉዳዩ እንዲገባ ተደርጓል?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- አልገባም፤ እንደውም ትልቁ ክፍተት ይህ ነው። በእርግጥ ህዝቡ ብሔራዊ ስሜቱ የተነቃቃ ነው። ውሃውን መጠቀም እንደሚገባ ያውቃል። ነገር ግን፤ የሚካሄዱትን ድርድሮች ዝርዝር ምንም አያውቅም። እንኳን ህዝቡ በጉዳዩ ላይ የተማረው ሰው እንኳን መረጃ የሚያገኘው በስንት መከራ የተለያዩ ምንጮችን በመጎልጎል ነው። በኢትዮጵያ መጥፎ የድብቅነት ባህል አለ። በእርግጥ ከአገር ደህንነት አንፃር መደበቅ ይቻላል። ነገር ግን፤ ሁሉንም ነገር መሸፈን አይጠቅምም። ለህዝቡም ቴክኒካዊውን ሃሳብ ትቶ በሚገባው ቋንቋ ድርድሮች ሲኖሩ ሂደቱን ማስረዳት ይገባል።
“ኢትዮጵያ የፈለገችው ምንድን ነው? የህዳሴውን ግድብ ልገንባ ያለችው እንዴት ነው? ይህ ግብፅን የማይጎዳው እንዴት ነው?” የሚለውን ለህዝቡ ማስረዳት ይገባል። ህዝቡ በአባይ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ነገር ግን፤ በቂ መረጃ የለውም። ስለዚህ ግልፅ ሆኖ መታወቅ አለበት። የጉዳዩ ባለቤት ህዝቡ ነው። የአሁኑም ሆነ የቀጣዩ ትውልድ እያለ ይቀጥላል። ግብፅ ውስጥ ህዝቡ ያውቃል። ነገር ግን፤ የሚያውቀው ግብፅን በሚጠቅም መልኩ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተዛባ መልኩ ማለት ነው?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- አዎን! በተዛባ መልኩ፤ የግብፅን ጥቅም ብቻ ማዕከል ባደረገ መልኩ ነው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ናይል ከግብፅ ተነስቶ እዚያው ግብፅ የሚያልቅ ይመስላቸዋል። ግብፅ ውስጥ ከናይል ጋር ተያይዞ አንዳንዴ እውነት አለመናገርም ወንጀል አይደለም። “ኢትዮጵያ ልታስርበን ነው” ሲባል “ኢትዮጵያ ምን አገባት?” የሚለው ህዝብ ብዙ ነው። ወንዙ ከኢትዮጵያ እንደሚነሳም ሆነ መብቱ እንዳላት የማያውቁ አሉ። አንዳንዴ የውሸትም ወሰን ሊኖረው ይገባል። ምንም ለአገር ጥቅም በማሰብ ቢሆንም እነርሱ አብዝተውታል።
አዲስ ዘመን፡- እነርሱ ውሸት ቀላቅለው ይህን ያህል እየሰሩ እኛ ግን…?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- እኛ ግን እውነቱንም እንደብቃለን። ይህንን በመተው ሰው የሚያውቅበትን መንገድ መክፈት ይሻላል። በናይል ላይ የሰሩ ብዙ ምሁራንም አሉ። አንዳንዶቹ መውጣትም መናገርም አይፈልጉም። ነገር ግን፤ ሁሉም ግዴታ አለበት። ምሁሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ግብር ከፍሎ ያስተማረው መሆኑን አስቦ የሚያውቀውን ሃሳብ ማካፈል ይገባዋል። አንዳንዶች እየወጡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የግብፅ ምሁራን ለአገራቸው ስለአባይ በተለያየ መልኩ በደንብ ይታገላሉ። በማህበራዊ ድረገፆችም ሆነ የተለያዩ መፅሃፍትን በመፃፍ፤ ህዝብን በማሳወቅ በኩል ትልልቅ ስራ ይሰራሉ። የኢትዮጵያ ምሁራንስ ተገቢውን ሚና እየተጫወቱ ነው?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- ልክ ነው። የኢትዮጵያ ምሁራኑ መሳተፍ እና መውጣት አለባቸው። ግብፆች ሄሮዶትስ የሚባለው የታሪክ ተመራማሪ እንደገለፀው “ግብፅ የፈጣሪ ስጦታ ናት” ብለው ያምናሉ። ምሁራኑም እዚያ ላይ ትኩረት አድርገው “ግብፅ ማለት ናይል ነች። ናይል ማለት ግብፅ ነች” በማለት፤ ሌሎቹን 10ሩንም አገራት እንዳልኖሩ አድርጎ የመቁጠር ሁኔታ አለ። በኢትዮጵያ ላይ ይህንን ለመመከት ብዙ የውይይት መድረኮች መፈጠር አለባቸው። ያንን መገናኛ ብዙሃን ሲጠቀሙበት ህዝቡ የበለጠ ያውቃል።
ሌላው፤ የግብፅ ምሁራን በስፋት ይፅፋሉ። የኢትዮጵያ ምሁራን ግን መፃፍ ላይ ችግር አለባቸው። በተለይ ዓለም እንዲያውቀው በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጻህፍትን መፃፍ ያስፈልጋል። እኔ በአማርኛ ቋንቋ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እየፃፍኩ ነው። ያ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው ይረዳል። ነገር ግን፤ ዓለም አቀፍ ተነባቢነት እንዲኖር እና የኢትዮጵያ በናይል የመጠቀም መብት እንዲታወቅ ያግዛል። ለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንቀሳቀስ አለባቸው። እታች ድረስ መውረድ አለበት። ይህ ትውልድ እንዲያውቀው፤ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያሳውቅ መደረግ አለበት። ቀጣይነት እንዲኖረው ቢያንስ ከዛሬ መጀመር አለበት።
በእርግጥ በመንግስት በኩል የአቋም መግለጫ እየተሰጠ ነው። ያ ጥሩ ነው። ነገር ግን፤ ውይይት ያስፈልጋል። ካለፈው ትምህርት መውሰድ እና ወደፊት ምን መደረግ አለበት? በሚለው ላይ መወያየት ያስፈልጋል። ቀድሞ መላምት በማዘጋጀት “ግብፅ እንዲህ ብታደርግ ምን እናደርጋለን?” በሚል ቀድሞ መዘጋጀት ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብፆች “በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የሚሳተፉና ግብፅ ውስጥ ያሉ ካምፓኒዎችን እናስወጣለን፤ የግድቡን ግንባታ በማንኛውም መንገድ እናስቆማለን” እያሉ እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- ለማንኛውም ግብፆች ምንም ለማድረግ የማይቆፍሩት ጉድጓድ አይኖርም። ዑጋንዳ እና ሩዋንዳም ጥሩ ነገር እየታየባቸው ነው። ኢትዮጵያን እየደገፉ ይገኛሉ። “በካምፓኒዎች ላይ ማዕቀብ እንጥላለን” የሚለው ዝም ብሎ ተራ ነገር ነው። በህዳሴው ግድብ ላይ ሳሊኒን ጨምሮ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ። እየሰሩ ነው። ማስፈራራት ካልሆነ በስተቀር ብዙ ችግር የለውም። አሁን በተለያየ አቅጣጫ በጥበጥ ለማድረግ ይሞክራሉ። በኢትዮጵያ በኩል ግብፆች በሚሏቸው ሁኔታዎች ላይ መረበሽ አያስፈልግም። መፍትሄው አሁንም ወደፊትም ድርድር ማድረግ ብቻ ነው። ግብፆች ወደ ድርድር የሚመጡበትን መንገድ መፈለግ ይሻላቸዋል።
ኢትዮጵያ እያዘጋጀች ያለው የስምምነት ፅሁፍ አለ። የተለያዩ ሰዎችን በማሳተፍ ሰነድ እየተዘጋጀ ነው። ያ ሲወጣ ከተቀበሉት እሰየው፤ ካለበለዚያ መፍትሄው ድርድር ነው። አንዴ አረብ ሊግ መሄድ፤ ሌላ ጊዜ ማስፈራራት አያዋጣም። ጦርነት ለማንም አያዋጣም። ለግብፅም ለሌሎችም አይሆንም። ዋነኛው መፍትሔ መደራደር ነው። ግብፆች ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ እንድትገባ ብዙ ሞክረዋል። ጦርነት ተካሄዷል። የጉራዐ፤ የጉንዲት ጦርነቶች ከግብፅ ጋር የተያያዘ ነው። ከእስራኤል ጋርም ሲዋጉ ነበር። ነገር ግን ግብፅ ከመሸነፍ ውጪ ያሸነፈችበት ጊዜ የለም። ስለዚህ ለሁሉም የሚጠቅመው መደራደር ብቻ ነው። ሱዳን “እኔ ራሴ አስታራቂ እሆናለሁ፤ አስታርቃለሁ” እያለች ነው። ይህ በጣም ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2012
ምህረት ሞገስ