
አዲስ አበባ፡- የግብጽ አጀንዳ የግድቡ ጉዳይ መቋጫ እንዳያገኝና የድርድሩ ይዘት እንዲቀየር እያደረገ በመምጣቱ ኢትዮጵያ የራሷን አጀንዳ ቀርጻ መደራደር መጀመር እንዳለባት የቀድሞ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የምስራቅ ናይል ቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ገለጹ።
አቶ ፈቅአህመድ እንደተናገሩት፤ በየጊዜው በሚደረጉ ድርድሮች ወደ ስምምነት መምጣት ያልተቻለው የግብጽ ብሔራዊ ጥቅም ብቻ የሚታይበት በመሆኑ ነው። በግብጽ በኩል ውሳኔ ሰጪው አካል ተደራዳሪው እንዳልሆነ የሚያነሱት አቶ ፈቅአህመድ፤ የግድቡ ጉዳይ እንዲጓተት ለማድረግ አንድን አጀንዳ በተደጋጋሚ በማንሳት ለውሳኔ ሰጪው ያቀርባሉ። በዚህም ጉዳዩን ባልተረዳ አካል ውሳኔው ይተላለፍና ስምምነቱ ይፈርሳል።
ስለዚህ ኢትዮጵያ አጀንዳ ቀርጻ ለመደራደር ካልሞከረች ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ መስጠቷ እንደማይቀር ተናግረዋል። እንደ አቶ ፈቅአህመድ ገለጻ፤ የግብጾች ተደጋጋሚ የብሔራዊ ጥቅም ፍላጎት የሚፈትነው ግድቡን ብቻ ሳይሆን ተደራዳሪውንም ነው። ቀደም ሲል ግድቡ ለሦስቱ አገራት የሚሰጠውን ጥቅም ያማከለና የሚደርስ ጉዳት ካለ በሚልም ታሳቢ ተደርጎ ይሰራ ነበር።
አሁን ግን እነርሱ ላይ ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ የውይይት አቅጣጫው የእነርሱን ብሔራዊ ጥቅም ይነካል ወይ ወደሚል ዞሯል። ግብጾች በዲፕሎማሲያዊና ራስን አሳልፎ በመስጠት ጭምርም ብሔራዊ ጥቅማቸው እንዲከበር እየሰሩ ናቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያም ያንን አስባ በራሷ መንቀሳቀስ ይጠበቅባታል ብለዋል። በኢትዮጵያ በኩል ሁሌም መነሻ መሆን ያለበት ብሔራዊ ጥቅም እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ፈቅአህመድ፤ ግድቡን እውን ለማድረግ በተደራ ዳሪው ወገን የማያወላዳ አጀንዳ ቀርጾ ማወያየት ላይ መስራት ያስፈልጋል። የግብጽን ተደጋጋሚና አንድ ዓይነት ወሬም መግታት ይገባል። ከዚህ በኋላም ድርድሩ በራስ አጀንዳ እንጂ በሌሎች ላይ ሊሆን እንደማይገባ ተናግረዋል።
በምን ያህል መልኩ ግድቡን ስንሞላና ስንለቅ ስኬታማ እንሆናለን የሚለውም ተሰልቶ ለድርድር የራስ አቋም ተይዞበት መወያየት ያስፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም የራሳችንን አጀንዳና ሰነድ አዘጋጅተን መቅረብ አለብን፤ የምንወያየው በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው ሊባል ይገባልም ብለዋል።
ግብጽ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ካልሆነ በስተቀር ብዙ የውሃ አማራጭ ያላት አገር ናት። እንደውም ለአንድሺህ ዓመት የምትጠቀመው ውሃ ክምችት አላት። ስለዚህም አስቸኳይ የስምምነት አማራጭ ላይ ለመድረስ የራስ አጀንዳን አዘጋጅቶ መደራደር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የውሃ ስምምነት ዲፕሎማሲያው ግንኙነት ቢቋረጥ እንኳን የማይቆም እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ፈቅአህመድ፤ ወሰን ተሻጋሪ ውሃ ሀገራትን ማስተሳሰር የሚያስችል ነውና ይህንን እንዲገነዘቡ ለማድረግ የእነርሱን የመደራደሪያ ሀሳብ ብቻ ይዞ ከማቀንቀን መላቀቅ ያስፈልጋልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም
ጽጌረዳ ጫንያለው