ስልጣኔ እና ዘመናዊነት የሰው ልጅ አካሉን ተጠቅሞ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በእጅጉ አራርቀውታል። የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረጉን ተከትሎም በቀላሉ መከላከል የሚቻልባቸው ነገር ግን ገዳይ ለሆኑ በሽታዎች እያጋለጡት ይገኛሉ። ጥናቶች አንድ ሰው በቀን ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት በእግሩ እንዲጓዝ ይመክራሉ። ከፍተኛ እንቅስቃሴ የማይጠይቀውንና በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግ ጉዞን በእግር በመተካት ብቻም በርካታ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል።
ዕርምጃ አንዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደመሆኑ ለአካልና ለአዕምሮ ጤና የሚሰጠው ጥቅም በርካታ ነው። እንደ ድብርት፣ ጭንቀትና መደበት ያሉ ስሜቶችን ለማስወገድም ሁነኛ መፍትሔ ነው። ጡንቻንና አጥንትን ለማጠንከር፣ የምግብ መፈጨትን ለማፋጠን፣ የደም ዝውውርን ለማስተካከል እንዲሁም የልብ፣ የደም ብዛት፣ የካንሰር፣… ህመሞችን ለመዋጋትም በየዕለቱ ከ3 እስከ5ሺ ዕርምጃዎችን ማዘውተር መልካም እንደሆነም ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። የማስታወስ አቅምን ለማዳበርና ለፈጠራ ሥራዎችም ዝግጁ ያደርጋል። አካባቢን ለመቃኘት እና አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት እንደሚረዳም ያክላሉ። ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማድረግ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳን የተረዱ ሀገራትና በጤና ላይ የሚሠሩ ተቋማትም ይህንኑ ጥቅም በመረዳት ህዝቡ በእግር መራመድን እንዲያዘወትር ያደርጋሉ። ከተሽከርካሪ ነፃ የሆኑ ቀናትን በመመደብም ህዝቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ጤናውንም እንዲጠብቅ ያበረታታሉ። ዕድሉንም ይፈጥራሉ።
የኢትዮጵያም ይህንኑ ልምድ በመቅሰም የዕርምጃ ቀን ነገ ልታካሂድ ቀነ ቀጠሮ ይዛለች። የስፖርት ፖሊሲውም ህብረተሰቡን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማሳተፍ ጤንነቱን እንዲጠብቅ፣ አካሉን እንዲገነባ እንዲሁም አዕምሮውን እንዲያበለጽግ ይጠቁማል። በዚሁ መሰረትም በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀው መርሐ ግብሩ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ይካሄዳል።
«በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ ለላቀ ውጤታማነት» የሚል መሪ ቃል ያነገበው መርሐ ግብሩ በርካታ መልዕክቶችንም የማስተላለፍ ዓላማ አንግቧል። እነርሱም «በህብረት ተጉዘን ጤናችንን እንጠብቅ፣ በዕርምጃ ጉዞ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አካባቢያችንን እንወቅ፣ በዕርምጃ ቀን በመሳተፍ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሳችንን እንጠብቅ እንዲሁም በዕርምጃ ጀምረን ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህል እናደርጋለን» የሚሉ ናቸው።
ዕርምጃው አምስት ኪሎ ሜትር ሲሸፍን፤ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በተመረጡ ቦታዎች ይካሄዳል። በዕርምጃው ላይ ከ85ሺ ሰው በላይ እንደሚሳተፍ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከ30ሺ በላይ ተሳታፊዎች ይኖራሉ። የእግር ጉዞው በአዲስ አበባ ከጀሞ ወደ ለቡ በሚወስደው መንገድ፣ በኦሮሚያ በቢሾፍቱ፤ የተቀሩትንም ክልሎች በየዋና ከተማቸው እንደሚካሄድም ታውቋል። በጉዞው ላይ ለመሳተፍም በክልልና ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ (ስፖርት ኮሚሽን) በመገኘት ወይም መደወል ይቻላል።
በስፖርት እንቅስቀሴ የተገነባ አካልና አዕምሮ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተሻለ ለማምረት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በተጨማሪ ስፖርት ጤንነትን በመጠበቅ ለህክምናና ለመድኃኒት መግዣ የሚወጣውን ወጪ ይቀንሳል። ሰፊውን ህብረተሰብ በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳተፍም ከብሄራዊ የስፖርት ፖሊሲ በመነሳት በየደረጃው ለማነቃቃት በሀገር አቀፍ ዝግጅቱ መጠናቀቁንና ተሳታፊ ለሆኑ አካላትም የምስክር ወረቀት መዘጋጀቱም በድረገጹ ላይ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ብርሃን ፈይሳ