
«ለፍቅር እንሩጥ ጥላቻን እናምልጥ» በሚል መሪ ቃል የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ለማካሄድ ፍቃድ መገኘቱን አዘጋጁ ፍቅር ያሸንፋል በጎ አድራጎት ማኅበር አስታወቀ። የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅና መስራች አቶ ሚስባህ ከድር እንደገለፁት፤ ስፖርት ጉልህ ሚናውን ከሚጫወትባቸው መስኮች አንዱ በሰላም ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅሙ ነው። ማህበሩ ይሄንኑ መሰረት በማድረግ «ለፍቅር እንሩጥ ጥላቻን እናምልጥ» በሚል መሪ ቃል መስቀል አደባባይ ባዘጋጀው ውድድር ላይ 40 ሺ ተሳታፊዎች የሚጠበቁ ይሆናል።
የጎዳና ሩጫው ቀደም ሲል የካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ለማካሄድ ታስቦ እንደነበር የገለፁት አቶ ሚስባህ፣ በወቅቱ በከተማው ላይ ሊከናወኑ የነበሩ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ውድድሩን በተያዘለት ጊዜ ለማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል። አሁን ግን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽፈት ቤት ውድድሩን ለማድረግ በደብዳቤ ጥያቄ በማቅረብ ፍቃድ ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል ለውድድሩ የሰላም ሚኒስቴር ዕውቅና የሰጠው ሲሆን አመስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ውድድር ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
«በዓይነቱና በይዘቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶችና ታዋቂ ግለሰቦችን፣ አርቲስቶች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ያለምንም የፆታና የዕድሜ ልዩነት ይታደሙበታል›› ያሉት አቶ ሚስባህ፣ ከሩጫው መርሐ ግብር በኋላ ትልቅ እንጀራ በማዘጋጀት በአንድ ላይ የመቁረስ ሥነ ሥርዓት እንደሚኖር አስረድተዋል ይህም ‹ሰፊ እንጀራ አለን ተካፍለን እንብላ፤ እርስ በርስ አንባላ› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ እንደሚከናወን አክለዋል።
በሽብር ወንጀል ክስ ከአራት ዓመት በላይ በወህኒ ቤት መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ሚስባህ፣ የማህበሩ የክብር አምባሳደር አርቲስት ቻቺ ታደሰ እና አርቲስት ዳዊት ፅጌን በማድረግ ባለፉት 12 ወራት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል። የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የመጣውን ሰላም በጋራ በመጠበቅ የተሻለችውን ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስ ይቻል ዘንድ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ዳንኤል ዘነበ