
4ተኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ችቦ መለኮስ ሥነ ሥርዓት ከትናንት በስቲያ በመቖለ ሮማናት አደባባይ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት ተከናውኗል። በሥነ ሥረዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የትግራይ ክልል በተለያዩ ስፖርቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን በማስመረጡ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል የትግራይ ክልል በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ በአትሌቲክስ 10 እና በብስክሌት 1 አትሌት ማስመረጥ መቻሉን ያስታወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ ስፖርቱን ለማጠናከርና የኦሊምፒክ ቡድኑን ለመደገፍና የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ከኦሊምፒክ ኮሚቴው ጎን እንደሚቆም በማረጋገጥ ከወዲሁ ለኦሊምፒክ ቡድኑ መልካም ዕድል ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የቶኪዮ 2020 ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በትግራይ የተለኮሰው የኦሊምፒክ ችቦ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ትግራይ ብዙ ጀግኖችን አፍርታለች፣ በስፖርቱም በቀጣይ በተለያዩ ስፖርቶች አገርን የሚወክሉ አትሌቶች ማፍራት ይጠበቃል›› ብለዋል አቶ አባዱላ ንግግራቸውን በድንገት ገታ አድርገውም በቶኪዮ 2020 በብስክሌት ኢትዮጵያን በብቸኝነት የምትወክለው የትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ብስክሌት ጋላቢዋን ሰላም ዓመሀን ወደ መድረክ በመጥራት ‹‹በብቸኝነት ኢትዮጵያን በመወከልሽ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ከህዝብ በስጦታ የተበረከተልኝ ነው›› በማለት ከአንገታቸው የወርቅ ሀብል አውልቀው ሽልማት አበርክተውላታል።
በችቦ መለኮስ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ችቦውን ከትግራይ ክልል የተረከቡት የጋምቤላ ክልል አፈጉባኤ አቶ ላክደር ላባክ በበኩላቸው ‹‹የኦሊምፒክ ቡድኑን ለመደገፍ በቀጣይም በስፖርቱ መሠረተ ልማት ላይ የበኩላችንን ለመወጣት እድሉን በማግኘታችን ደስተኞች ነን›› በማለት ተናግረዋል 5ተኛው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ችቦ መለኮስ ሥነ ሥርዓት መጋቢት 6/2012 በጋምቤላ ክልል የሚከናወን ሲሆን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ታይዶር ቻምባንግ መቖለ በነበረው የችቦ መለኮስ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ችቦው ሲረከቡ ‹‹በስፖርት ህብረተሰቡን ተሳታፊ ማድረግ እንዴት እንደሆነ ከትግራይ ክልል ትምህት ወስደናል›› ብለዋል። ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ቡድን እደክልል በተገቢው መንገድ እንደሚደግፉም አብራርተዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ከጀግናው አትሌት ሻበል ምሩፅ ይፍጠር ልጅና የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቢኒያም_ምሩፅ ጋር መገናኘታቸውን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅትን በተለየ መልኩ ለማከናወንና ለትውልድ የሚተላለፍ ዘመናዊ የኦሊምፒክ አካዳሚን የመገንባት ዕቅድ በመያዝ የብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎችን ከጀመረ ሰንብቷል። ኮሚቴው ሕዝቡን በነቂስ የሚያሳትፍ የመጀመሪያ መርሐግብሩን የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የኦሊምፒክ ችቦ በመለኮስ መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲዞር በማድረግ መጀመሩ ይታወሳል። የኦሊምፒኩን ችቦ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተረከበ ሲሆን ከድሬዳዋ ተከትሎ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይ መጨረሻውን ያደርጋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ቦጋለ አበበ