በዓለማችን የተለያዩ ከተሞች በሚካሄዱ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ምስራቅ አፍሪካውያኑ ጐረቤታሞች የርቀቱ ፈርጥ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ከወርቅ እስከ ነሐስ ደረጃ ድረስ በተሰጣቸው የጐዳና ላይና የማራቶን ውድድሮች ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዘወትር ተፎካካሪና አሸናፊዎች ቢሆኑም በዱባይ ማራቶን የኢትዮጵያውያን የበላይነት ሃያል ነው ማለት ይቻላል፡፡
ለዚህም ባለፉት በርካታ ዓመታት በተካሄዱ ውድድሮች በሁለቱም ፆታ ከአንድ እስከ አስርና ከዚያ በላይ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ማሳያ ነው፡፡ ይህም በመካከለኛው ምስራቅ እጅግ ውድ በሆነው የማራቶን ውድድር አረንጓዴውን ጎርፍ ዘወትር እንድናየው ያስቻለ ነው። ከዚህ ባሻገር ዘወትር የፈረንጆች አዲስ ዓመት በገባ ከሁለት ሳምንት በኋላ አርብ እለት በሚካሄደው የዱባይ ማራቶን በርካታ ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት አሸብርቀው የዱባይ ጎዳናዎች ድምቀት መሆናቸው የውድድሩ መለያ እስከ መሆን ደርሷል፡፡
በጣት የሚቆጠሩ ቀናትን ባስቆጠረው የፈረንጆች አዲስ ዓመትም በርካታ ኢትዮጵያን አትሌቶች ለዱባይ ማራቶን እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ ለእያንዳንዱ አሸናፊ አትሌት እንደየደረጃው ከሁለት መቶ ሺ ዶላር በላይ በመሸለም የዓለማችን ከበርቴ ውድድር በሆነው የዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአሸናፊነት በተጨማሪ ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብ የውድድሩን ክብረወሰን ደጋግመው በማንሳት ይታወቃሉ። ለዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም በወንዶቹ ውድድር የተመዘገቡት ሰዓቶች ምስክር ናቸው።
አትሌት ታምራት ቶላ ካቻምና ውድድሩን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው ሰዓት በማራቶን በታሪክ አስረኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ የአስር ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረው ታምራት ለጥ ባለው የዱባይ ጎዳና ፈጣኑን ፉክክር ሲያሸንፍ ያስመዘገበው ሰዓት ቀድሞ የውድድሩ ክብረወሰን ከሆነው ሁለት ደቂቃ የተሻለ ሲሆን በዚህ ውድድር የተገደበውን 2፡o4 ሰዓት መስበር የቻለ የመጀመሪያው አትሌት ያደርገዋል፡፡ አምናም ቢሆን ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው ወደ ውድድር የገባው አትሌት ሞስነት ገረመው ይህን ክብረወሰን በሌላ የተሻለ ሰዓት የግሉ በማድረግ ማሸነፉ ይታወሳል።
የውድድሩ ዳይሬክተር ኮኔርተን «በቀጣዮቹ ሳምንታት በርካታ ድንቅ አትሌቶችን ወደ ውድድሩ ለማምጣት እንጥራለን» ብለዋል፡፡
አሰለፈች መርጊያ ሦስት ጊዜ በዱባይ ማራቶን በማሸነፍ ከሴቶች ቀዳሚ ስትሆን የጀግናውን አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴን ክብረወሰን መጋራትም ችላለች። ሃይሌ ገብረስላሴ ከ2008 ዓ .ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ጊዜ የዱባይ ማራቶንን ያሸነፈ ብቸኛው አትሌት መሆኑ አይዘነጋም። አሰለፈች መርጊያ በ2011፤ 2012ና 2015 የዱባይ ማራቶንን ከማሸነፏም በላይ በርቀቱ የቦታው የክብረወሰን ባለቤት ነች። አሰለፈች ክብረወሰኑን ያስመዘገበችው በ2012 ባሸነፈችበት ውድድር ሲሆን ሰዓቱም 2:19:31 ሆኖ ተመዝግቧል።
አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀ አትሌት ሁለት መቶሺ ዶላር፤ ሁለተኛው ሰማንያ ሺና ሦስተኛው አርባ ሺ ዶላር በሚያስገኘው የዱባይ ማራቶን በወንዶች ባለፉት አስራ ስድስት ዓመታት ኬንያውያን ስምንት ጊዜ ኢትዮጵያውያንም ደግሞ አስር ጊዜ አሸንፈዋል። በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድሉን ተቆጣጥረውታል ማለት ይቻላል። ባለፉት ስድስት ዓመታት የነበረውን ውጤት ብንመለከትም ኬንያውያን ማሸነፍ የቻሉት በአንዱ ብቻ ነው።
2011 ላይ ድሉ የኬንያዊው ዴቪድ ባርማሳይ ቱሞ ነበር። ከእዚያ ወዲያ ያሉትን ውድድሮች ግን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አየለ አብሽሮ(የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ያሸነፈ አትሌት ነው)፤ ሌሊሳ ዴሲሳና ፀጋዬ መኮንን በተከታታይ በማሸነፍ ታሪክ አላቸው።
የሴቶቹን ውድድር በተመለከተ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተጋነነ የበላይነት አላቸው። ካለፉት አስራ ስድስት ዓመት ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስራ ሁለቱን የግላቸው በማድረግ ዱባይ ላይ ነግሰዋል። እ.ኤ.አ በ2000፤ 2001ና 2002 ተከታታይ ዓመታት ሩሲያውያን አትሌቶች ነግሰው ነበር። ራሚሊያ ቡራንጉሎቫና አልቢ፤ኢቫኖቫና ኢሪና ፔርሚቲና የተባሉ አትሌቶች ተፈራርቀው አሸንፈዋል። ከእዚያ በኋላ ድሉ የኢትዮጵያዊቷ ለኢላ አማን ነበር። ከለኢላ ድል ተከትላ በቀጣዩ ዓመት ኬንያዊቷ ዴሊአ አሲጎ በ2006 የውድድሩ ቻምፒዮን ነበረች።
ከእዚያ በኋላ ግን ውድድሩ ላለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያውያን እጅ ወጥቶ አያውቅም። አትሌት ድርቤ ሁንዴ ከለኢላ በኋላ ድሉን ወደ ኢትዮጵያውያን የመለሰች አትሌት ነች። ከእዚያ ወዲህ አስካለ መገርሳ፤ ብርሃኔ አደሬ፤ ብዙነሽ በቀለ፤ ማሚቱ ደስካ፤ አሰለፈች መርጊያ(ሦስት ጊዜ) ትርፌ ፀጋዬና ሙሉ ሰቦቃ ውድድሩን ተፈራርቀው አሸንፈዋል።
በዱባዩ ልዑል ሼክ ሐምዳን ቢን ሙሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቶም የበላይ ጠባቂነትና በዱባይ ስፖርት ምክር ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ ውድድር ከማራቶን በተጨማሪ የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድርና የአራት ኪሎ ሜትር የመዝናኛ ውድድር በእለቱ ያስተናግዳል፡፡ በዘንድሮው ውድድር የ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ እንደሚወዳደር ቀደም ሲል አዘጋጆቹ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ቦጋለ አበበ