በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 7 ቀን 2020 የተከሰተውና በዓለም ጤና ድርጅት ‹‹ኮቪድ 19›› የሚል አዲስ ስያሜ ያገኘው የኮሮና ቫይረስ መላው ዓለምን ስጋት ውስጥ ከቷል። የዓለም ህዝቦች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ቫይረሱ ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላኛው ሃገር በፍጥነት እየተዛመተ መምጣቱ ደግሞ የስጋቱን ደረጃ ይበልጥ አሳድጎታል። በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ከመምጣቱ በሻገር የሟቾች ቁጥርም በዚያው ልክ ማሻቀቡን ቢቢሲና አልጀዚራ ከሰሞኑ ይዘዋቸው የወጡት መረጃዎች ያሳያሉ።
መረጃዎቹ እንዳመለከቱት፤የኮሮና ቫይረስ በሰዎች ጤና ላይ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስም አስክትሏል። በተለይ ሰዎች ከአንዱ ሃገር ወደሌላኛው ሃገር የሚያደርጓቸው ጉዞዎች በዚሁ ቫይረስ ምክንያት በመገታቱ በመካከላቸው ያለው ማህበራዊ መስተጋብር ተስተጓሏል፤ቫይረሱ ይገኝበታል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ሰዎችም ባሉበት እንዲቆዩ በመደረጋቸው እንቅስቃሴያቸው ተገቷል።
የቫይረሱ መነሻ በሆነቸው ቻይና የሚደረጉ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን በረራዎች በአብዛኛው ቆሟል፤ በርካታ ሀገራትም በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶበት ከቆየው ከቻይና ሁዋን ግዛት ዜጎቻቸውንም ባስቸኳይ አስወጥተዋል። በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ጣጣ በርካታ ትላልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ሃይማኖታዊ ጉዞዎች፣ ኮንፍረንስና ስብሰባዎች በመሰረዛቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አስከትሏል።
ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ለዓለም ጤና ድርጅት በየጊዜው ሪፖርት የሚያደርጉ ሀገራት ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ አስከአሁን ድረስ ቫይረሱ እንዳለተከሰተ ተነግሯል። ይህንንም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት በየሳምንቱ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጧል። ኢኒስቲትዩቱ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሰባቱ መግቢያዎችና በሠላሳ የየብስ መግቢያዎች ወደሃገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ሃገር ዜጎች በሙቀት ልየታ ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ ቫይረሱ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ ብረቱ የመከላከል ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ጠዋት የኖብል ኮሮና ቫይረስን አጠቃላይ ሁኔታ ለመከታተል ከተቋቋመው ቡድን ጋር ተወያይተዋል። ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣው ይህ ቡድን በፌዴራል እና በክልል ደረጃ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት እየተመራ ቁልፍ የመከላከልና የቅድመ ዝግጁነት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።
መረጋጋት፣ የጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የመከላከል መመሪያ ተግባራዊ ማድረግና ማኅበረሰባችን በመከላከልና ቅድመ ዝግጅት ላይ ያለውን ግንዛቤ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ኮሚቴው ተያያዥ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጽዕኖዎችን በውጤታማነት ለመቋቋም የሚቻልባቸውን አማራጮች እንደ ሚያፈላልግ የገለጹ ሲሆን፣ እስከአሁን በተወሰዱ ዕርምጃዎች እንደሚተማመኑም አስታውቀዋል።
የኮሮና ቫይረስ በዋናነት ጉንፋን የሚያስከትለው የቫይረስ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የመተንፈሻ አካላት ችግርን የሚያስከትል ሲሆን፣ቫይረሱ በዋናነት ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋል። ሰዎችን ያልበከሉ ሌሎች የኮሮና ቫይረሶችም በእንስሳት ውስጥ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ ተብሎም ይታመናል።
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ፤ሳል፣ ትኩሳት፣ ለመተንፈስ መቸገር የትንፋሽ የኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽን ምልክቶች ናቸው፤ከዚህ ከፍ ሲልም ቫይረሱ የሳምባ ምች፣ የሰውነት አካላት ሥራቸውን ማቆምና ሞት ሊያስከትል ይችላል። የቫይረሱ ምልክቶች በሰውነት ላይ ለመታየት ከአንድ አስከ አስራ አራት ቀናት ይወስድበታል። ቫይረሱ ያለባቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ግን ምልክቶቹ ከአምስት አስከ ስድስት ባሉት ቀናት ውስጥ ሊታዩባቸው ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ቫይረሱ በሰውነታቸው ያለባቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ምልከት ሳያሳዩ ረጅም ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።
የሳይንስ ሊህቃን አዲሱ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ እንዴት በፍጥነት እየተሰራጨ እንደመጣ ለማወቅና ስጋቱንም ለመቀነስ ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛሉ። እነዚሁ ሊህቃን ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዳ አንድ ክትባት ለመፍጠር እየተጣደፉ ቢሆንም፣ክትባቱን ከ2021 በፊት በጅምላ አሰራጭቶ በግለሰብ ደረጃ ማዳረስ እንደማይችል አስጠንቅቀዋል።
የበቢሲ ዘገባ እንደሚያሳየው ደግሞ፤ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ አውሮፓዊቷ ሀገር ጣሊያን በቫይረሱ የሞቱ ዜጎቿ ቁጥር ወደ 197 በመድረሱ ከቻይና ቀጥሎ በርካታ ዜጎች የሞቱባት ሁለተኛዋ ሃገር ሆናለች። የጣልያን መንግሥት ባለስልጣናት በ24 ሰዓታት ውስጥ 49 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ ከ4 ሺ 600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው፤ ይህ ዘገባ አስከተጠናቀረበት ያለፈው ቅዳሜ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮነና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ሺ ደርሷል፤ 3 ሺ 381 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። ከዚሁ ቫይረስ ጋር በተያያዘ አብዛኛዎቹ ሰዎች የሞቱት የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ቻይና መሆኑንም ነው፤በቻይና እስከአሁን ድረስ 3 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ህይወ ታቸውን አጥተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የቫይረሱን ስርጭት ‹‹በጥልቅ የሚያሳስብ›› ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ቫይረሱን ለመከላከል ሁሉም ሃገራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ቫቲካን፣ ሰርቢያ፣ ስሎቬኪያ፣ ፔሩና፣ ቶጎ የኮሮና ቫይረስ በሃገራቸው እንደተገኘ ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት አድርገዋል፤ይህም ቫይረሱ የተገኘባቸውን የዓለም ሀገራት ቁጥር ወደ 87 ከፍ አድርጎታል። በእንግሊዝ የሰማኒያ ዓመት እድሜ ባለፀጋው እንግሊዛዊ ኮሮና ቫይረስ ተገኝቶበት የሞተ ሁለተኛው ሰው ሆኗል። በግላስኮ ስታዲየም ሊካሄድ የነበረው የስኮትላንድና የፈረንሳይ ሴቶች እግርኳሰ ጨዋታም በሜዳው ከሚጫተው የስኮትላንድ ቡድን በኩል አንዲት ሴት ተጫዋች በኮሮና ቫይረስ መያዟን ተከትሎ ጨዋታው ለለሌ ጊዜ ተላልፏል።
ሀገሮች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚል እየመደቡ ይገኛሉ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት የሚያስችል 8 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ለማድረግ ሰሞኑን ፊርማቸውን አኑረዋል። የዓለም ባንክ 12 ቢሊየን ዶላር የመደበ ሲሆን ፣ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ደግሞ 50 ቢሊዮን ዶላር በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት መመደቡን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
አስናቀ ፀጋዬ