
በእሥራኤል ምድር አገር ለመምረት ፍላጎት ያለው ማንኛውም የምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲ አሸናፊነቱን ለማረጋገጥ መቶ ሃያ መቀመጫዎች ካሉት የአገሪቱ ፓርላማ 61 ያህሉን ማግኘት ግድ ይለዋል ይህን ያህል ማሳካት ያልሆነለት ደግሞ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ ጋር ድምፁን በማስደመር ጥምር መንግሥት መመስረት ምርጫው ያደርጋል።
እሥራኤልም ቀጣይ መሪዋን ለመምረጥ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ አገራዊ ምርጫ አካሂዳለች በምርጫው ግን አብላጫ የሕዝብ ድምፅ በማግኘት አሸናፊውን ሆኖ አገር ለመምራት ብቁ የሆነውን ፓርቲ ማወቅ አልተቻለም ይህ በመሆኑ ሁነቱ በመስከረም ወር ለሁለተኛ ጊዜ እንዲካሄድ አስገድዷል።
በአገሪቱ ታሪክ ከተካሄዱት የተለየና ከፍተኛ ትንቅንቅ የታየበት ሁለተኛ ምርጫም፣በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁና በቀድሞው የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ ቤን ጋንቴዝ መካከል እልህ አስጨራሽ ብርቱ ፉክክር ተደርጎበታል።
በምርጫው ውጤትም በቤን ጋንቴዝ የሚመራው ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የቀኝ ዘመም (ሊኩድ) ፓርቲ አብላጫውን ድምፅ ማግኘት ችለዋል ይሁንና ሁለቱም አገር መምራት የሚያስችል ድምፅ ማግኘት ባለመቻላቸው እንደ መጀመሪያው ሁሉ ሁለተኛውም ምርጫ አሸናፊውን ማሳወቅ አልሆነለትም።
ይህን ተከትሎም ሁለቱ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አቻችለው ድምፃቸውን በማስደመር ጥምር መንግሥት ይመሰርታሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህም ሳይሆን ቀርቷል ፓርቲዎቹም ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ፊት ተነሳስተው በራቸውን ዘግተዋል ክስተቱም ከሁለት አስርት ዓመታት የፖለቲካ ንግስና በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ከማስገባት ባሻገር አገሪቱን በታሪኳ አይታው ከማታውቀው የፖለቲካ ምስቅልቅል ጋር ለወራት ሲያታግላት ቆይቷል።
በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል የተከሰተው የልዩነት አቋምና ግብግብ ግን በቀላሉ የሚፈታ አልሆነም ይልቁንም ቀውስና ልዩነቱ በሌላ ሦስተኛ ምርጫ እልባት እንዲያገኝ ውሳኔ ላይ አስደርሷል።
እሥራኤልም ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ የመስጠት አቅም አለው የተባለለትን ሦስተኛውን ምርጫ ከቀናት በፊት አካሂዳለች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ምርጫም ከቀደሙት የተለየ አዲስ ውጤት አልተገኘም ሁነቱም አብላጫውን የህዝብ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆኖ አገር ለመምራት ብቁ የሆነውን ፓርቲ ማሳወቅ አላስቻለም።
ይሁንና ከምርጫው ቀድሞ በበርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ተንታኞች ዳግም በዙፋናቸው የሚቀጥሉበት ዕድል እጅግ አነስተኛ ስለመሆኑ ሲነገርባቸው የሰነበቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ፣ከሁለተኛውም በተሻለ መልኩ በሦስተኛው ምርጫ ልቀው ታይተዋል።
በምርጫው ድምር ውጤትም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የቀኝ ዘመም ፓርቲ (ሊኩድ) 58 መቀመጫ ማግኘቱን አልዘጂራ አስነብቧል ይህም መንግሥት ለብቻ ለመመስረት ከሚጠይቀው መስፈርት በሦስት ብቻ ያነሰ መሆኑን ያመላከተው ዘገባው፣ይሁንና ሰውየው‹‹ህዝቡ ከሌሎች ተፎካካሪዎች የበለጠ ድምፅ ሰጥቶኛል፣በማለት አሸናፊ ስለመሆናቸው በመግለፅ ላይ ስለመሆናቸውም አመልክቷል።
እኤአ በ1996 በአርባ ሰባት ዓመታቸው የመሪነቱን ስልጣን የያዙት ኔታንያሁ ከአራት ዓመታት በኋላ ስልጣናቸውን ለኤሁድ ባራክ ማስረከባቸው ይታወሳል ከአስር ዓመታት ቆይታ በኋላም እኤአ በ2009 ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱ መሪ በመሆን ከአስር ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ ቆይተዋል።
ፖለቲካዊ እውቀታቸው ምጡቅ መሆኑ የሚመሰክረላቸውና በፍልስጤምና በኢራን ላይ ባላቸው ጠንካራ ፣ ተጠራጣሪና ግትር አቋም የሚታወቁት የሰባ ዓመቱ ኔታኒያሁ፤ በአገራቸው ፖለቲካ በተለይም በደኅንነት ጉዳይ እጅ አይሰጡም። አገርን መምራት የሚለካው የአገርን ሉዓላዊነትና ደኅንነት በማስጠበቅ መሆኑን አጥብቀው ማመናቸውም ከአረብ አገራት ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው ዓመታትን እንዲዘልቁ እንዳደረጋቸው በርካቶች ይስማሙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠረጠሩባቸው ሦስት የሙስና ወንጀሎች በምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ከባድ ራስ ምታት የፈጠሩባቸው ሲሆን፣ የተለያዩ ምርምራዎች እንዲካሄዱባቸው ምክንያት ሆነዋል ምንም እንኳን ሰውየው በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍንጮች ስለመኖራቸው ቢታመንም ተጨባጭ ማስረጃ ግን አልተገኘባቸውም እርሳቸውም ቢሆኑ ከደሙ ንፁህ ስለመሆናቸው በመግለፅ ውንጀላውም መሰረተ ቢስና ስልጣናቸውን ለመገዳደር የተጠነሰሰ ሴራ ነው በማለት ለታማኝነታቸው ሲሟገቱ ቆይተዋል።
ይህ የሙስና ክስ ከስማቸው ጋር ተሳስሮም ቢሆን በምርጫው ሁነት የሚያንበረክካቸው የጠፋው ኔታኒያሁ፣ ‹‹በሦስተኛው ምርጫ ያገኙት ውጤት ከተቀናቃኛቸው በተለይ ከጋንቴዝ ልቆ መታየት ምናልባት ከወትሮው በተለየ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ብዙም እንዳይቸገሩ ይረዳቸዋል›› ተብሏል።
በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ምሁራንም ሰውየውን በምርጫ ለመዘረር ስላደረጉ ምክንያቶች ሰፊ ሀተታ አስፈረዋል በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ለወጠነቸው እቅድ ስኬታማነት የእሥራኤን ሚና በእጅጉ የሚያስፈልጋት አሜሪካ ፍላጎትም ሆነ ምኞት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነት እንዳይርቁ መሆኑ ሰውየው እንዳይሸነፉ ዋነኛው ምክንያት ነው ተብሏል
የቦክስ ኒውስ ፀሐፊው ዛክ ቢኡቻምፕ፣ ከሁሉም በላይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰላም ለራቀው መካከለኛው ምሥራቅ እልባት እንዲሆን ‹‹ብዙ ደክመንና ተጨንቀን ያዘጋጀነው ነው›› ያሉትን የሰላም እቅድ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም አብራርቷል ‹‹እቅዱም የእሥራኤልን ቀልብ ስቧል›› ሲል ፅፏል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ምሁራን በአንፃሩ፣አሁንም ቢሆን ምርጫው መቋጫውን አለማግኘቱን በማስታወስ፣በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው ምርጫ መሪዋን መምረጥ ያልቻለችው እሥራኤልም ለዳግም አራተኛ ምርጫ ማዘጋጀት ግድ እንደሚላት አትተዋል።
በዚህ ቲያ ጎልደንበር፣ ‹‹ማንም ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥምር መንግሥት መመስረት የሚሆንለት ስለማይመስል ምርጫው ለአራተኛ ጊዜ መካሄዱ አይቀርም›› ስትል አሶሽየትድ ፕሬስ ላይ አስፍራለች የኒውዮርክ ታይምስ፣ ድቪድ ሃልፊንገር በበኩሉ፣ከሦስት የኪሳራ ምርጫዎች በኋላ ማንም ለአራተኛ ጊዜ ሁነቱ እንዲስተናገድ ፍላጎት የለውም›› ሲል አትቷል በተደጋጋሚ ምርጫ እልባት ያላገኘው ፖለቲካም ምናልባት አዲስ መፍትሔ ማስተዋወቅ ሊማስን እንደሚችል ጠቁሟል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ጆንታን ዩሪች፣ዳግም ምርጫ እንደማይካሄድ በሚጠቁመው አስተያየታቸው ‹‹በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለመመስረት ማሟላት ከሚጠበቅብን ድምፆች መካከል የቀሩን ሁለትና ሦስት ብቻ ናቸው፣ከወዲሁም ከፓርቲዎች ጋር ውይይቶች ተጀምረዋል›› ሲሉ ለእሥራኤል ወታደራዊ ራድዮ ተናግረዋል የሰውየውን ንግግርና የስነ ላቦና ጥንካሬ ያስተዋሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ለማዋቀር ብዙም እንደማይቸግራቸው ተማምነውበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ታምራት ተስፋዬ