
አዲስ አበባ እንደተመሠረተች ብዙም ሳትቆይ ውሃ በቧንቧ ገባላት በ18 86ዓ.ም ከእንጦጦ ኪዳነ ምህረት አካባቢ የወጣውን ውሃ በቧንቧ እንዲተላለፍ ያመቻቸው ስዊዘርላንዳዊው የንጉሡ አማካሪ አልፍሬድ ኤልግ ነበር ውሃው እንዲገባ የተደረገውም እምዬ ምኒሊክ ቤት ሲሆን ፣ውሃ ቁልቁለት ይሄዳል እንጂ እንዴት አቀበት ይወጣል ተብሎ ተተቸ።
ውሃው ሲገባ ሰዎች ከእልልታ ይልቅ ኡአታ ያበዙ ይመስለኛል፤ እንዳውም ውሃ አቀበት ከወጣ የሰይጣን ሥራ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያጣጣሉትና ያብጠለጠሉም ነበሩበት በወቅቱ መቼም ውሃ ከቧንቧ ተቀድቶ የሚሰጣቸው ሰዎች ምንጭና ወንዝ እያለልንማ ትቦ (ትንባሆ አላልኩም) አንጠጣም የሚሉ ይመስለኛል።
በአንፃሩ ሥራውን ባደነቁት ደግሞ “እንዲህ ያለ የንጉሥ ቂናጣ
ውሃ በመዘውር ሰገነት አወጣ
አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ “ ተብሎ ተገጥሞ ነበር።
ለንጉሡ የተዘረጋው ውሃ ቀስ በቀስ ለነዋሪውም ተረፈ፤ የአፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆነ ሰባት ዓመታት ቆይቶ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ በ1893 ዓ.ም የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነ አገልግሎቱ ከመቶ ዓመታት በላይ አስቆጥረ ከከተማው ጋር ማደግ የነበረበት ውሃ አቅርቦት በፈረቃ መሆኑ ከፋ እንጂ አሁንም ውሃው በቧንቧ እያለፈ ነው።
በአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት በየአስር ዓመቱ በሚዘጋጁ ማስተር ፕላኖች ከተማዋን ለማሳደግ ትኩረት ቢደረግም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከተማዋ ወደጎን እንድትለጠጥ ከማድረግ ውጪ የመጣ ለውጥ የለም እርግጥ ነው አዲስ አበባ በመልሶ ልማት እና ባለባት የማስፋፊያ ቦታ ችግር ሳቢያ ሽቅብ ግንባታ ውስጥ ገብታለች ፎቅ በፎቅ እየሆነች ነው።
እነዚህ ሁሉ ህንፃዎች ከቀደሙት ቤቶች በበለጠ ውሃ ይሻሉ። በርካታ ነዋሪዎች ስራቸውንና ኑሯቸውን በእነዚሁ ህንፃዎች ውስጥ እያደረጉ ናቸው። ነዋሪው ሲጨምር የውሃ ፍላጎትም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፤የከተማዋ የውሃ እጥረት የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው ።
አዎን፤አዲስ አበባ እየተጨነቀች ያለችውና አፍጥጦ የሚጠብቃት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለመሆኑ ነጋሪ አይፈልግም በአፍሪካ መድረክ ከፍተኛ የፖለቲካ ሚና ያላት አዲስ አበባ የነዋሪዎቿን የንፁሕ መጠጥ ውሃ ጥያቄን ለመመለስ ስትንገዳገድ ብትቆይም፣የ24 ሰዓት የውሃ ሽፋን የሚያገኙ አካባቢዎች እጅግ ውስን ናቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች ውሃ በፈረቃ የሚያገኙ ናቸው በሳምንት አንዴ የሚደርሳቸውም አሉ ችግሩ በጸናባቸው አንዳንድ የፈረንሣይና አስኮ አካባቢዎች ደግሞ ፈረቃው በ15 ቀን እንደሆነም ህብረተሰቡ ይገልጻል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤አዲስ አበባ በቀን እያመረተች ያለችው የውሃ መጠን 500ሺ ሜትር ኪዩብ ነው በቀን የሚያስፈልጋት የውሃ መጠን ግን ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ነው በሁለተኛው የከተማዋ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ አቅርቦት ቢያስፈልግም አልተሳካም።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃውን እጥረት በማየት ያስቀመጠው ጊዜያዊ መፍትሔ በአንዳንድ አካባቢዎች የፈረቃ አጠቃቀም ስርዓትን መዘርጋት፣በከተማዋ መሀል የተለያዩ አካባቢዎች ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን መቆፈር ነው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር ይቀርፋሉ ተብለው የተጀመሩት ሁለት ፕሮጀክቶች መካከል የሰበታ ሆለታ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ከ30 በመቶ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
መረጃው እንዳመለከተው፤በቀን 73 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ይሰጣል የተባለው የገርቢ ግድብ ፕሮጀክት፤ በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል በለገዳዲ ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ ልማት ፕሮጀክትም በአካባቢው የ9 ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮና የመስመር ዝርጋታ ሥራ በሁለት ዓመት ሲጠናቀቅም በቀን 86ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል በሰሜን አዲስ አበባ አቅጣጫ ወደፊት ይገነባል ተብሎ የሚታሰበው የሲቢሉ ግድብ 418 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ይሰጣል ተብሎ ይገመታል።
ጥረቶቹ ሊደነቁ ቢገባም፣ችግሩን በመሰረታዊ መልኩ ሊፈታ የሚችል ተግባር እየተከናወነ ስለመሆኑ ግን እጠራጠራለሁ የከተማ ወደ ጎን መለጠጥ እና ሽቅብ ማደግ ያለ በቂ ውሃ ትርጉም አይኖረውም ዘመናዊ አኗኗር በከፍተኛ ደረጃ የውሃ አቅርቦትን የግድ ይላል መጸዳጃ ቤቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ይፈልጋሉ፤ቤት ማጽዳቱ በራሱ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ይጠይቃል ውሃ በበቂ ሁኔታ ከሌለ ህዝብ ታጭቆ በሚኖርበት ከተማ በሽታ እንዲቀሰቀስና እንዲስፋፋ ምክንያት ይሆናል ውሃና የከተማ አድገት አራምባና ቆቦ የሆኑበትን ሁኔታ በመሰረታዊ መልኩ ለመለወጥ በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ይገባል።
አረንጓዴ ስፍራዎችን በማልማት ከተሞችን ለመኖሪያ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ውሃ ወሳኝ ግብአት ነው ከተሞችን በአረንጓዴ ማስዋብ ያለ ውሃ አይታሰብም የውሃ ይሁን የተሽከርካሪ እጥረት በከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮችና ጎዳናዎች አካፋዮችና ዳርቻዎች የለሙ አረንጓዴ ስፍራዎች በውሃ እጦት ጠውልገዋል፤መድረቅ መድረቅ ብሏቸል አዳዲሶቹ ችግኞች ደግሞ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም።
ለከተማ የውሃ ፋይዳ ተዘርዝሮ አያልቅም ህዝቡ ጤናውን እንዲጠበቅ እያስገነዘቡ፣የራሱንና የአካባቢውን ንጽሕና እንዲጠበቅ እያሳሰቡ ውሃ አለማቅረብ የጤና ትምህርቱን ሁሉ ገደል ይከታል በሕንፃ ላይ እሳት አደጋ ቢነሳ ማርከሻው ውሃ ነው፤ በከተሞች ሁከትና ግጭት ቢነሳ ግርግሩን ሰዎች ሳይጎዱ ለመበተን ሁነኛው መሣሪያ ውሃ ነው ሕንፃዎች ሲገነቡ የውሃ ፍላጎት ይጨምራል፤ የመኪና ሞተርም እንዳይሞቅ ውሃ ይፈልጋል።
የኅብረተሰቡ የውሃ ጥያቄ ከፍተኛ ነው የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ ከተጠናቀቁ የውሃ ጥማችንን በተወሰነ መልኩም ቢሆን መቁረጥ እንችላለን ለከተማዋ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን በዘላቂነት ማልማት ውስጥ መግባት ግን ወሳኝ ተግባር ሊሆን ይገባል።
ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ለከተማዋ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር እና የተጀመሩትንም ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እያደረጉ ያሉትን ክትትል የውሃ እጥረት የሚቀረፍበትን መንገድ በመቀየስና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ይህን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ስር የሰደደ የከተማዋን የውሃ ችግር መፍታት ይጠበቅባቸዋል ችግሩን በዘላቂነት የመፍታቱ ጥረት ከጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ አልፎ ከከተማዋ ራቅ ያሉ ቦታዎች በሚገኙ ታላላቅ ወንዞች ላይ ግድቦችን በመሥራት ላይ እንዲመሰረት ማድረግም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ