የዘንድሮውን የገና በአል ከፊሉን ቀን በጉዞ ነው ያሳላፍኩት። ላም በረት አካባቢ ከሚገኘው መናኸሪያ የደረስኩት ከጠዋቱ አራት ሰአት ላይ ነበር፤ በጣት የሚቆጠሩ ሚኒባሶችና ሼሼንቶዎች ብቻ በግቢው ቆመዋል። እንደወትሮው የሚርመሰመስ መንገደኛም በግቢው አይታይም የረዳቶቹም ድምጽ በጣም ዝቅ ያለና እየቆየ ነበር የሚሰማው። ደብረብርሃን…. ሸኖ…. አሌልቱ….. ይጣራሉ። በአብዛኛው ግን ጠብ ጠብ እያለ የሚገባውን ሰው የሚያናግሩት በተናጥል ጠጋ እያሉ ነበር።
አንድ ሼሼንቶና አንድ ሚኒባስ የኔን መዳረሻ ደብረ ብርሃንን ይጣራሉ፤ መጀመሪያ ያቀናሁት አናቱ ላይ ማዳበሪያ የሚወርወር ረዳት ወደ እሚጣራበት ትልቁ መኪና ነበር አስር የማይሞሉ ተሳፋሪዎች እናታቸው እንደጠፋችባቸው ጫጩት ተበታትነው ተቀምጠዋል። ይሄኛው በዚህ አያያዙ እስከ ማታም አይሞላም ብዬ ወረድኩና ወደ ሚኒባሱ አመራሁ። እዛም በተመሳሳይ ጋቢና ሁለት ሰው ከኋላ ደግሞ አንድ ብቻ ነበር ያሳፈረው። ገብቼ ከተቀምጥኩ በኋላ ከፊቴ የተቀመጠውን ወጣት እዛ ያሉት ቢመጡ እንሞላ ነበር ብንጠራቸው ብዬ ጥያቄ አቀርብኩ። ዋጋውን ስለማይደፍሩ ነው ይሄኛው እኮ ገና ስንት እንደሚለን አላወቅንም ፤ እኔ ያለንን ቢለኝ ስለማልቀር ነው የገባሁት አለኝ፤ ቅድም ያላስተዋልኩት ነገር አሁን ተከሰተልኝ እዛ መኪና ውስጥ ያገኟኋቸው በፌስታልም በማዳበሪያም የሆነ የሆነ ነገር የያዙ ባለጓዞች ነበሩ።
የሚኒባሱ ረዳት ወደ ሹፌሩ ጠጋ ብሎ ሰንዳፋ ልጫን? አለው ከዛስ ባዶህን ልትሄድ ? አርፈህ ደብረ ብርሃን ጥራ ገና ከዛ ተመላሽ አይኖርም ባዷችንን ነው የምንመጣው ሹፌሩ ቆጣ ብሎ መለሰ። ወጣቱ ወሬውን ቀጠለ ዛሬማ በአል ነው በዛ ላይ ሰው ካልሞላ የሚደራደሩን በዋጋ ነው አለ። በዚህ ጊዜ አዘቅዝቅው ነጠላ የለበሱ እናቶችን ያስከተሉ ወጣቶች ተሰልፈው ሚኒባሷን ሞሏት። በደቂቃ ለውጥ ቦታ ባለመብቃቱ ረዳቱ ለሁለት ሰዎች የጄሬካን መቀመጫ ያዘጋጅላቸው ገባ። የሚጠጋጋውን አጠጋግተው ካስቀመጡ በኋላ ወደ መውጫው በር ስንሄድ የመውጫ ትኬት ከሚቆርጠው ሰው አጠገብ አንድ ጠና ያለ ወጣት መኪናውን በእጅ ምልክት አስቆመው። ተሳፋሪው ጓደኛዬ ከመቅፅበት ብራቮ አለ ፤ ሰውየውንና ሹፌሩን እየቀያየረ እየተመለከተ ምንድነው አልኩት ተቆጣጣሪ ነው አየህ በዚች ቅፅበት እሱ እዚህ በመገኘቱ በእጥፍ አልያም ከዛ በላይ ከመክፈል ድነናል አለኝ። በመጀመሪያ በዛ መስመር የሁል ጊዜ ተጠቃሚ ስላልሆንኩ ነገሩ በደንብ ግልፅ አልሆነልኝም ነበር ። ለካስ ለቀስተኞቹም እንደዛ ግር ብለው የመጡት ተቆጣጣሪዎች መኖራቸውን ስለተመለከቱ ኖሯል።
እነሱ እንዳወሩት በር ላይ ያሉት ደላሎች ከታሪፉ እጥፍ በላይ 100 ብር በሰው ከከፈሉ እንደሚወስዷቸው ጠይቀዋቸው ነበር። መናኸሪያ ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ሰማኒያ ብር ከከፈሉ ለቀብር ደብረ ብርሀን መድረስ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል። ይሄ ሁሉ የሚሆነው እንግዲህ በአል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች አለባበሳቸው ለለቅሶ መሆኑ ስለሚታወቅ እንደማይቀሩ በመገመትም ጭምር የተጫነባቸው እዳ ነበር። ለነገሩ ቀባሪ አያሳጣኝ እያለ የሚኖር ህዝብ ለቀብር ቢጣደፍ አያስገርምም።
ወጣቱ ሹፌሩን ካናገረ በኋላ በበር ዞሮ እኛን በጥያቄ ያጣድፈን ያዘ የት ብሎ ነው የጫናችሁ? ደብረብርሃን ሂሳብ ከፍላችኋል? አልከፈልንም። ስንት ተስማማችሁ? አልተነጋገርንም። ታሪፉን ታውቃላችሁ? አናውቅም። ከኪሱ ወረቅት አውጥቶ እያደለን ያለችሁበት መኪና ደረጃ ሶስት ነው ሂሳቡን እዛ ላይ አይታችሁ ክፈሉ ማንኛውም ችግር ካለ፤ አልሄድም ቢላችሁ፣ መንገድ ላይ ቢያቆም፣ ታሪፍ ቢጨምር፣ በአካል መጥታችሁ ማሳወቅ ትችላላችሁ ብሎን ሄደ። ረዳቱ እየተነጫነጨ እዛው ብንቆይ ይሻለን ነበር አለ አፍ አውጥቶ ይሄ ማለት እንግዲህ በመንገድ ላይ ሆኖ በደላላ ታሪፍ ጨምሮ ለመጫን ነበር።
ተቆጣጣሪውን አይቶ ለተደሰተው ተሳፋሪ ጥያቄ አነሳሁ። በጣም ጥሩ ነው ግን ደግሞ ስልክ እየሰጡን ደውለን ብንነግራቸው የበለጠ አሪፍ ነበር አልኩት። «ያማ አይሆንም» አለ ከአፌ ላይ እየተቀበለኝ «ያማ አይሆንም ሰው አላግባብ እየደወለ ካለ ማስረጃ ሰው ይከሳል ሹፌሮቹና ረዳቶቹ እርስ በእርስ እየደወሉ ያላጠፋ ታርጋ ያስይዛሉ። ሰው ተበድልኩ ካለ በአካል መጥቶ መብቱን ለማስከበር መስራት አለበት። አንድ ሚኒባስ ታሪፍ የሚጨምረው ቢያንስ አስራ ሁለት ሰው ላይ ነው። ይሄ ሁላ ሰው ባይመቸው ሶስቱ ወይ አራቱ ተቀጣጥሮ ቅሬታውን በተጨባጭ ማስረጃ ቢያቀርብ ሁሉንም ማስቆም ይቻል ነበር። ሰው ግን በየትራንስፖርቱ ተቆጣጣሪ እንዲመደብ ይፈልጋል እንደ ህዝብ መብታችንን ለማስከበር እኛ እስከ መጨረሻው መሄድ አለብን። መንግስትን ማውገዝ እንኳ ካለብን እስከ መጨረሻ ተከታትለን ምላሽ ስናጣ እንጂ ገና በይሆናል አይሰራልንም የሚል እሳቤ ይዘን ቤታችን ቁጭ ብለን መሆን የለበትም አለኝ።» ምላሹ አሳማኝና ምክንያታዊ ስለነበር ሌላ ጥያቄ ለማንሳት አልደፈርኩም።
ጸሀይ እያለ ከምትበርደው ደብረ ብርሀን ውሎዬን ጨርሼ ትንሿ የከተማዋ መናኸሪያ የተገኘሁት ደግሞ አስር ሰአት ተኩል ላይ ነበር። ከበር ላይ የተቀበለኝ ወጣት አዲስ አበባ አዲስ አበባ እያለ ወደ አንዲት ሚኒባስ እጁን ይዘረጋል የተደረገልኝን ግብዣ ተከትዬ ገብቼ ተቀመጥኩ ብዙም ሳንቆይ መኪናዋ ስለሞላች ረዳቱ ተሳፋሪ ከመጥራት ሹፌሩን ወደ መጥራት ተሸጋገረ። ሹፌሩ መኪናዋን ትንሽ ካንቀሳቀሳት በኋላ አቁሞ ነግረሃቸዋል ሲል ለረዳቱ ጥያቄ አቀረበለት። ረዳቱ ሰማኒያ ሰማኒያ ብር ነው የምትከፍሉት ብሎ እንደቀልድ የእጥፍ ዋጋ ጭማሬውን አረዳን። እኔ የጠዋቱን እያስታወስኩ ታሪፉ አርባ ሶስት ብር ነው አልኩት።
«ካልፈለክ መውረድ ትችላለህ» አለኝ። አንተ ማነህ ሰው እየመረጥክ የምትጭነው ማነውስ ታሪፍ አውጪ ያደረገህ ስታስወርደኝ አይሃለሁ አልኩ ኮስተር ብዬ። ማምረሬ ያላማረው ሹፌር ከመቅጽበት የጨዋታውን ሜዳ ለኔና ለቀሪዎቹ ተሳፋሪዎች አስተላለፈው። ንግግሩን የጀመረው «አልከፍልም ካለ መብቱ ነው አታስገድደው ደሞ ሰው አታመናጭቅ» ብሎ ረዳቱን በመገሰጽ ሲሆን አያይዞ «ይቅርታ ከአዲስ አበባ ስንመለስ ስለሚመሽብን አሁን መውጣት አንችልም ሁላችሁም ውረዱ ብሎ ደመደመ። ከመቅጽበት ተሳፋሪው በሙሉ እኔ ላይ መንጫጫት ጀመረ፤ ከብዙ ንግግሮች መካከል ከሌለህ እንከፍልልሀለን፣ ይሄ ስልጣን ማሳያ አይደለም» የሚሉት በጣም አስገረሙኝና ራሴን ጠየኩ። ማነው ባለስልጣን? ማነው ብር የቸገረው?። ማነውስ ትክክል?
መቼም በየቦታው መጥፎ ሰው እንዳለ ሁሉ ጥሩም አይጠፋም ፤ አንዲት ልጅ እግር ጣልቃ ገብታ ማረጋጋት ጀመረች። እኔ ግን የሷን ሽምግልና የተቀበልኩት ከተሳፋሪዎች አንዱ ለተናገረው ምላሽ ሰጥቼ ነበር።
«እኛ ከፍለን እንሄዳለን ካልፈለገ እሱ መውረድ ይችላል» ሲል፤ እኔም ድምጼን ከፍ አድርጌ ይሄ መኪና ሊንቀሳቀስ የሚችለው እኔን አርባ ሶስት ብር ከፍየው ለማድረስ ሲስማማ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የደፈረ የፈለገውን ማድረግ ይሞክር አልኩ። ልጁ በዝምታ ተዋጠ ከሹፌሩ አጠገብ ያሉት ምን እንዳሉት አላውቅም ለረዳቱ ግባና የሰጠህን ተቀበለው ብሎ ጉዞውን ቀጠለ።
ልጅቷ ቀስ ብላ ጨዋታ ጀመረች፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪ መሆኗን ከነገረችኝ በኋላ ስለትራንስፖርት ችግር ትንሽ አውርታ እኔ እንዳመረርኩ ብቀጥልና ትራንስፖርት ቢጠፋ ሊገጣማት የሚችለውን ችግር ጠቆም አደረገችኝ። «የመጣሁት መንዲዳ ከሚባል አካባቢ ነው፤ ጠዋት ፈተና ስላለኝ ግቢ መገኘት አለብኝ ፤ ዛሬ ካልተንቀሳቀስኩ ጠዋት ላልደርስ እችላለሁ በዛ ላይ እዚህ ስታድር አልጋ መያዙ ብቻ ወጪው ብዙ ነው ስንት ነገር አለ። እነሱም የአመት በአል ሲሰሩ የሚውሉት ትንሽ የተሻለ እናገኛለን ብለው ነው። ስለዚህ አንዳንዴ ተቻችለን ሲሆን የሚሻል ይመስለለኛል» አለች። በልጅቷ አይነት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሌሎችም እንደሚኖሩ ለመገመት አላቃተኝም። በሰዎቹ ንግግር ትንሽ የተሸናፊነት ስሜት ተሰምቶኝ ስለነበር ከሸሚዜ ኪስ የመቶ ብር ኖት ማውጣት እየቻልኩ ከሱሪዬ ኪስ በማውጣት ከበርካታ መቶ ብሮች መካከል አንዱን ለረዳቱ ሰጠሁትና ሰማኒያውን ቁረጥ አልኩት።
የልጅቷ ንግግር ግን በሃሳብ ለሁለት ከፈለኝ እሷ የሚገጥማትን ችግር ሳስበው ትክክል ነበረች። በበአል ቀን እንዲሰሩ መንግስት የሚያስገድዳቸው ተሽከርካሪዎች ከሌሉ በፈቃደኝነት የሚወጡት ምንም እንኳ ገንዘብ የሚከፈላቸው ቢሆንም ሊመሰገኑ ይገባል። በበአል ቀን ፖሊስ፣ የህክምና ባለሙያ፣ እሳት አደጋና ሌሎችም በስራ የሚያሳልፉ አሉ። እነሱም ቢሆን አነሰም በዛ አበል ይታሰብላቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በአልን ሰውተው በመስራታቸው ምን ሊያገኙ ይችላሉ። መንግስት ለበአል ቀናት የታሪፍ ማስተካከያ ያድርግ? አልያስ ባልተጻፈ ህግ እንዳየሩ ጸባይ አንዳንዴ እጥፍ አልፍም ሲል ከዛ በላይ እየከፈልን እንንቀሳቀስ? ትክክሉ የቱ ነው?
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ