
አዲስ አበባ፡- መንግሥት የህዝብ አንድነትና አብሮነት እንዲሸረሸር በሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንገለፁት፥ በህዝባዊ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በአገር አንድነትና አብሮነት ላይ አደጋ ይደቅናሉ። ከዚህ አንፃርም በመሰል ድርጊት በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከትናንት በስቲያ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በተመለከተ በአዳማ ከተማ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ባዘጋጀው መድረክ በ”ኦ ኤም ኤን” (OMN) አማካኝነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን የጣሰና ኢትዮጵያዊ እውነታን ያላገናዘበ የጥላቻ ንግግር ለዘመናት በአብሮነት ወደኖሩ ህዝቦች መተላለፉን ተከትሎ ፓርቲውም ሆነ የመገናኛ ተቋሙ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል። የተፈጠረው ነገር ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥፋት መሆኑንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።
አቶ ንጉሱ መንግሥት ለረጅም ጊዜ በመማማርና መመካከር ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴን አማራጭ አድርጎ በትዕግስት መቆየቱን ጠቅሰው፣ አሁን ግን በአገሪቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ተግባራት በግልፅ እየተበራከቱ በመምጣታቸው መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በፍጥነት እንዲታረሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ ዜና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መንግሥት የሐሳብ ነፃነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያድግ የፖለቲካ ምህዳሩን ቢያሰፋም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ፈር እየለቀቁ እንደመጡ መመልከቱን ገልጿል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም እንዳሉት፥ ከትናንት በስቲያ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በተመለከተ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ባዘጋጀው መድረክ በ”ኦ ኤም ኤን” (OMN) አማካኝነት የተላለፈውን የጥላቻ ንግግር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለባለሥልጣኑ ደርሶታል።
አሁን ላይ መልዕክቱ በባለሙያዎችና አመራሮች እየተገመገመ መሆኑን አቶ ወንደሰን ጠቅሰው፣ በአጭር ጊዜ መረጃውን በማጥራት ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም አመልክተዋል። በማጣራት ሂደት ውስጥ የሚገኙ ውጤቶች የሚያስጠይቁ ሆነው ከተገኙም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ተቋሙ በሁሉም ዘርፍ የሚዲያ ነፃነት ለማረጋገጥና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን ለማገዝ ኢ ፍትሐዊ ሐሳቦች ሲተላለፉ በተለያየ መንገድ ለመፍታት እየጣረ መሆኑን ጠቅሰዋል። ባለፉት ስድስት ወራትም ለ49 የመገናኛ ብዙሃን ግብረ መልስ መሰጠቱን ጠቅሰው፥ ለአራት መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የማስጠንቀቂያ መልዕክት በስልክና በደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን አስታውቀዋል።
በሂደቱ የተወሰኑ ለውጦች ቢታዩም ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከብሮድካስት ባለሥልጣን አዋጅ ተፃራሪ በሆነ መንገድ የሚጓዙ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውንም ገልፀዋል። ባለሥልጣኑ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮሩ እና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መገናኛ ብዙሃንን እንደማይታገስ አስረድተዋል። ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ቁርሾ የሚፈጥሩ ሐሳቦችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃን ላይ በአዋጁ መሰረት እስከ መዝጋትና ከዛም ያለፈ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012