
አቶ ሰለሞን ተስፋዬ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤቴል አካባቢ ነዋሪ ናቸው። በልማት ኮሜቴ ውስጥ ይሠራሉ። ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር በአካባቢው ከተዘረጋ አምስት ዓመት እንደሞላው ጠቅሰው፣ ባለሥልጣኑ ቤት ለቤት ሊያገናኝላቸው እንዳልቻለ ይጠቁማሉ።
መስመሩ ከመኖሪያ ቤት ፍሳሽ ጋር ባለመገናኘቱ ነዋሪዎች መቸገራቸውን አመለክተው፣ በተደጋጋሚ ወደ ባለሥልጣኑ ብንመላለስም ችግሩን የሚቀርፍልን አካል ልናገኝ አልቻልንም ሲሉ ይጠቁማሉ። ቅጥያ የሚባለው ከየቤቱ ወደ ዋናው ፍሳሽ ማስወገጃ የሚያገናኘው መስመር አልተገናኘም ያሉት አቶ ሰለሞን፤ መስመሩ እንዲገናኝላቸው ለአምስት ዓመታት ወደ ወረዳና ውሃ ፍሳሽ ወደ ባለሥልጣን መመላለሳቸውን ያስታውሳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በቅርቡ ከዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድ ጋር ተያይዞ መሰረተ ልማቱ ከተዘረጋባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር በራስ ሆቴል በመከረበት ወቅትም አቶ ሰለሞን ተገኝተዋል። በመድረኩ የተገኘነው በፍሳሽ መስመሩ ተጠቃሚ አድርጉን፣ ቅጥያውንም አገናኙልን ለማለት ሲሉ የገለፁት አቶ ሰለሞን፣ ሰው ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቱን ወዶት መጠቀም ቢፈልግም ምላሽ አልተገኘም ይላሉ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሽመልስ መርጊያ በአካባቢያቸው ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ መዘርጋቱን ይገልፃሉ። በዚህም ነዋሪው ያለስጋት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፣ እሳቸውም በአገልግሎቱ ዘመናዊነት ርካታ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ፤ መፀዳጃ ቤቱ ሞላ ላስጠርግ ብሎ መመላለስ የለም፤ ጊዜንና ጉልበትን ማባከን ቀርቶልናል ሲሉ አቶ ሽመልስ ያብራራሉ።
ኅብረተሰቡ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት እንዲጠቀም ግንዛቤ ለመስጠት ባለሥልጣኑ ጥረት ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበው፣ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦው ተዘርግቶ እያለ በፍሳሽ ማስወገጃ አቅራቢያ የመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ የሚቆፍሩ ሰዎች በተደጋጋሚ ማየታቸውን ያመለክታሉ። ይህም ከግንዛቤ ማነስና ከቤቴ ወደ ፍሳሽ ማስወገጃ ለማስቀጠል ብዙ ክፍያ እጠየቃለሁ ከሚል ሥጋት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።
የባለሥልጣኑ የፍሳሽ መስመር ቅጥያ ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ዘላለም ከተማ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት፤ አዲስ አበባን የዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ በሦስት ቦታዎች የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል።
ከነዚህም መካከል በቀን መቶ ሺህ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም ያለው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። 30 ሺህ ሜትር ኪዩብ በቀን የማጣራት አቅም ያለው የደቡብ አቃቂ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታም የተጀመረ ሲሆን፣ በምሥራቅ ተፋሰስ የሚገኘውና ሰማንያ ሺህ ሜ. ኪዩብ የማጣራት አቅም ያለው ጣቢያም በጥናት ላይ ነው። በከተማዋ በስምንት የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች ሃያ ሰባት ሺህ ሜትር ኪዩብ በቀን የሚያጣሩ 12 ያልተማከሉ ማጣሪያ ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ።
ፍሳሽ ቆሻሻን በዘመናዊ መንገድ ማስወገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት አቶ ዘላለም፣ መፀደጃ ቤት ሞላብኝ የሚል ሥጋት እና ፍሳሽን ለማስወገድ የሚደረግ የተሽከርካሪ ምልልስን በማስቀረት ጊዜና ጉልበትን ለመቆጠብ እንደሚረዳ ይገልፃሉ። የትራፊክ መጨናነቅ፤ ብክለትና መጥፎ ሽታን ያስቀራል እንዲሁም ፅዱ፣ ውብና ለመኖር የምትመች ዘመናዊ ከተማን ለመፍጠር ያግዛል ይላሉ።
ጠጣር እና ባዕድ ነገሮችን በፍሳሽ መሥመሮችና ማጣሪያ ጣቢያዎች በመግባት የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ዘላለም፣ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መስመሩን ሊጠቀም እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋለም ባዩ በቤቴል አካባቢ የፍሳሽ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ቀሪ የማገናኘት ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ መስመር የማገናኘቱ ሥራ መጓተቱን ይገልፃሉ። ችግሮቹን ለማቃለል ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር እንደሚዘረጋ ጠቅሰው፣ ከ12ሺ በላይ ለሚሆኑ ቤቶች ደግሞ የቤት ለቤት ቅጥያ አገናኝተን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራን ነው ሲሉ አስታውቀዋል። ከአራት ዓመት በፊት 10 በመቶ ብቻ የነበረው የዘመናዊ ፍሳሽ አገልግሎት ተጠቃሚ ቁጥር አሁን 27 በመቶ መድረሱን የባለሥልጣኑ መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ