
በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀቶች ውጤታማ የሆነችው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ በትኩረት ከሚታዩ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ እንደነበረች ይታወሳል። ይሁን እንጂ ለዓመታት ባከናወነችው ስራ ለሌሎች አገራት ተሞክሮ የሚሆን በመሆኑ ልትመሰገንበት ችላለች። ዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች መድሃኒት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲም ባለሙያዎቹን በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ጭምር ስራው አበረታች መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል። ይህ አበረታች ውጤት ግን አገሪቱን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስጋት ካለባቸው ከቀዳሚዎቹ አገራት ተርታ እንዳላወጣት ዓለም አቀፍ ተቋሙ ሰሞኑን አሳውቋል።
የአትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት(የአትሌቲክስ አበረታች መድሃኒት ጉዳዮች ገለልተኛ አጣሪ ቡድን) ቦርድ ባወጣው መግለጫ እንዳስነበበው ከሆነም፤ የዓለም አትሌቲክስ አባል ከሆኑት ፌዴሬሽኖች መካከል ባህሬን፣ ቤላሩስ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩክሬን፣ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ ስለ አበረታች ንጥረ ነገር በማህበሩ ደንብ አንቀጽ 15 በተደነገገው መሰረት ስጋት አለባቸው ተብለው የተደለደሉ አገራት ሆነዋል። በደንቡ መሰረት አገራቱ ባለባቸው የስጋት ደረጃ ‹‹ኤ፤ ቢ እና ሲ›› በሚል ይመደባሉ፤ ይህም ማለት በ‹‹ኤ›› ምድብ የተደለደሉ አገራት ስጋቱ ከፍተኛ የሆነባቸው እንዲሁም ምድብ ‹‹ሲ›› ዝቅተኛ ስጋት ያለባቸው አገራት ናቸው። በመሆኑም አገራት እንዳሉበት ስፍራ ራሳቸውን ከስጋት ነጻ ለማድረግ በሙሉ ትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በምድብ ‹‹ኤ›› ከተደለደሉት ሰባት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም እኤአ በ2020 የስፖርት አበረታች መድሀኒት አጠቃቀምን በሚመለከት ከፍተኛ ስጋት ካለባቸው የዓለም አገራት መካከል አንዷ ሆና እንደምትቀጥል ተቋሙ አረጋግጧል። አገሪቷ ባለፈው ዓመት ከዚህ ስጋት ለመላቀቅ ከፍተኛ የሚባል ስራ ብትሰራም ሙሉ በሙሉ ከስጋት ነጻ ለመባል ግን ቀሪ ስራዎች የሚኖርባት መሆኑን አስታውቋል። መግለጫውን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ሰጥቷል። በድረገጹ እንዳስነበበው ከሆነም ድልድሉን ለማድረግ በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ ውድድሮች በተለይም ዓለም ሻምፒዮና፣ በኦሊምፒክ እና የተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች ተሳትፎ፣ ውጤት እንዲሁም የስፖርት አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶች ያሉበት ደረጃ በመስፈርትነት የሚቀመጥ መሆኑን ያስረዳል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በመጀመሪያው መስፈርት ‹‹ኤ›› ምድብ ሊካተት ችሏል። ይህ አሰራር የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንቅስቃሴ ውስጥ የተለመደ ሲሆን በግለሰብ ደረጃም በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተሻለ ደረጃ ያላቸውና ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶች ተለይተው ከሌሎች በተለየ መልኩ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የዓለም አትሌቲክስ በጸረ አበረታች መድኃኒት ጋር በተያያዘ የሚሰራው አካል (የአትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት) በፌዴሬሽኑ የተጀመሩና እኤአ በ2019 የተመዘገቡ አበረታች እንቅስቃሴዎች በ2020ም ተጠናክረው መቀጠላቸውንና ቀጣይነታቸው መረጋገጡን ይጠበቃል። ስለዚህም ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ንጹህ ስፖርትን ለማስፋፋትና በአለም አቀፍ ደረጃ አገሪቷ የምትታወቅበትን ስፖርት አዎንታዊ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ጽህፈት ቤቱ ይጠቁማል።
ነገር ግን ከሁለተኛው መስፈርት አኳያ በዓለም ላይ ካሉ አገሮች ጋር ሲነጻጸር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ የሚመዘገቡ የስፖርት አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶች እጅግ በጣም ውስን ናቸው። በቁጥር ሲገለጽም በዓመት በአማካይ ከሁለት እስከ ሶስት የሚደርሱ ናቸው። ምንም እንኳን ስፖርቱ እስካለ ድረስ ማጭበርበሩ ሙሉ በሙሉ ይቆማል ተብሎ ባይታሰብም ቁጥሩን ወደ ዜሮ ለማውረድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በየደረጃው ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋል ተብሎ ይታመናል።
ዓመቱ ለኦሊምፒክ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት እንደመሆኑ ሁሉም ስፖርተኞች ራሳቸውን ከአበረታች ቅመሞች ነጻ ሆነው በታማኝነት የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችላቸውን በቂ ስልጠና ማካሄድና በስነልቦናም መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም ባሻገር በስፖርቱ ውስጥ በማናጀርነት፣ በአሰልጣኝነት፣ በኤጀንት እና በመሳ ሰሉት ሙያዎች እያገለገሉ ያሉ ባለሙያዎች ንጹህ ስፖርትን ለማስፋፋትና የአትሌቲክሱን መልካም ገጽታ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ማስገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ
የጸረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤትም የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ምርመራና ቁጥጥር አጠናክሮ
የሚያስቀጥል ሲሆን፤ የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይም አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
ብርሃን ፈይሳ