በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በትግራይና በምዕራብ ጎንደር ከመከላከያ ጋር ተያይዞ ችግሮች እንደነበሩ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ቆይቷል። በተለያዩ የፌስ ቡክ ገጾችም እውነታውን የተከተሉ እንዲሁም ከእውነታው የራቁ ወሬዎች ሲነዙ ሰንብተዋል። ይሄንንም አስመልክቶ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት፣የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የመከላከያ ሚንስቴር መግለጫ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይ ህዝብ ደህንነትና ሰላም የሚረጋገጠው በጥይት አይደለም፡፡ የክልሉን ሰላም ያለ ጥይት መጠበቅ ይቻላል፡፡ ትዕግስት በማድረግ የትግራይን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ተችሏል፡፡ ከማንም ኃይል ጋር ጠብና ጦርነት አያስፈልግም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የትግራይን ህዝብ ከሚያከብረው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ጠብ አያስፈልግም፡፡ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ትግራይን እንደሚያከብር ትግራይም መከላከያን ማክበር አለበት፡፡ እዚህም እዚያም ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ጋር እየተፈጠረ ያሉ ምልክቶች ወደ አላስፈላጊ ግጭት የሚያስገባ ነው፡፡
ከሠራዊት ጋር ተረዳድተን ነው መሥራት የምንፈልገው፡፡ ከዚህ ውጪ መጋጨት ለጠላቶቻችን መግቢያ በር መክፈት ነው፡፡ አላስፈላጊ ምልክቶች ስናይ ለሚመለከተው አካል ነው ማሳወቅ ያለብን፡፡የመከላከያ ሥራ ህገ መንግሥትና ፌዴራል ስርዓት መጠበቅ ነው፡፡ ህገ መንግሥት ይከበር ብለናል፡፡ ወደ ግጭት የሚያስገባ ሥራ መሥራት የለብንም፡፡ ይህን ኃይል ማከብር አለብን፡፡ ሃገራዊ ኃይል ነው፡፡አሁን የታዩት ምልክቶች መታረም አለባቸው፡፡ ጥያቄ ካለ መቅረብ ያለበት በተደራጀ መንገድ ነው፡፡ጉድለት ካለባቸው እናስተካክላቸው፡፡ ማንን ለማስደሰት ነው የምንጋጨው፡፡ በትግራይ ጦርነት አንፈልግም፡፡ በዳርም በመሃልም መከሰት የለበትም፡፡
ክስተቱ ከስጋት ከጥንቃቄ የሚመነጭ ነው፡፡ አደጋ ያጋጥመን ይሆን ከሚል መነሻ ነው፡፡ ይህ ጥሩ ቢሆንም በተደራጀ መንገድ እንጂ በተበተነ መንገድ መሆን የለበትም፡፡ መጠንቀቅ ጥሩ ነው፤መጋጨት ግን አያስፈልገንም፡፡ ከፌዴራል ኃይል ጋር መነጋገር ያለበት የክልል መንግሥት እንጂ በየመንደሩ አይደለም፡፡ ከመከላከያ ጋር እየተወያየን ነው የምንሠራው፡፡ እንዳከበሩን እናክብራቸው፡፡ በተደራጀ መንገድ የክልል መንግሥት ነው መሥራት ያለበት፡፡ አደጋ እንዳይኖር እንጠንቀቅ፣ ጠብ አንፈልግም ከሁሉም በላይ ከመከላከያ ጋር ጠብ አያስፈግም፡፡ በድምሩ ያቺ የተለመደችው ትዕግስታችን ትቀጥል ሲሉ ነው መልዕክት ያስተላላፉት፡፡
የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት በትግራይ ክልል ያለው የሰራዊቱ ቆይታ በፕሮግራሙ መሰረት የሚካሄድ ይሆናል። የተያዘውን እቅድ የሚያውቅ ማንም የለም ፤የወጣውም ፕላን አይቀየርም። ህዝቡ እንዲፈራና እንዲሰጋ በመደረጉ ውይይት ይደረጋል። ይሄ መጀመሪያም የተደረገው መንግሥትንና ህዝቡን እንዲሁም ህዝቡን ከክልሉ መንግሥት ጋር ለማጋጨትና ክልሉን ለማመስ ታስቦ ነው። መከላከያ የፌዴራል ተቋም እንደመሆኑ እንቅስቃሴውን የሚወስነው ፌዴራል ብቻ እንጂ የክልል ባለስልጣን አልያም አንድ ቡድንና የጎበዝ አለቃ አይሆንም። በመሆኑም እንቅስቃሴው በእቅዱ መሰረት የሚቀጥል ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም በእቅዱ መሰረት የሚወጣም የሚቆይም ይኖራል።
መከላከያው እንዲንቀሳቀስ የሚወሰነበትን ምክንያት ማወቅ የፌዴራል ጉዳይ ብቻ ነው። ይሄ እንዳለ ሆኖ ከዚህ በኋላ ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት አይኖርም የሚለውም አንዱ ምክንያት ነው። ጦሩም መማር መሰልጠን አለበት። ለውጥ እየተደረገ መሆኑም ከግንዛቤ መግባት አለበት። ሃያ ዓመት እዚያ ስለተቀመጠ ሌላ ሃያ ዓመት መቀመጥ አለበት ማለት አይደለም። ከዚህ በፊት በሻዕቢያ ወረራ ሲደረግ ከጅማ፣ከአሶሳና ከሌሎችም ክልሎች የነበረው ሠራዊት እንዲንቀሳቀስ ሲደረግ ከየትኛውም ክልል ምክንያቱ ምንድነው ተብሎ አልተጠየቀም። ዛሬም የትግራይ ህዝብ የዚህ ዓይነት ጥያቄ አላቀረበም፤ ጥያቄውን የሚያነሳው ሌላ አካል ነው። ጦሩም እዚያ አካባቢ ሃያ ዓመት በመኖሩና የአካባቢውን ህዝብ በመጠበቁ ተመስግኖ ወደ አዲሱ ግዳጅ ሂድ መባል አለበት። አሁን በአካባቢው ችግር የለም። 22ተኛ ክፍለ ጦር ሲወጣ የአካባቢው ህዝብ ደግሶ አመስግኖ ነው የላከው፤መቀጠል ያለበትም ይሄው ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ፤አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት መኪኖቹን ከአንደኛው ፕሮጀክት ወደ ሌላኛው ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ በሞከረበት ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል፡፡
‹‹ታኅሣሥ 28 ቀን 2011ዓ.ም ጭልጋ አካባቢ በመንገድ ሥራ ላይ የሚገኝ ድርጅት በግጭት ምክንያት ሥራውን ለመቀጠል በመቸገሩ መኪኖቹን ከመተማ-አርማጭሆ ወደሚሠራው የመንገድ ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ ሞክሯል፡፡ መኪኖቹን በሚያንቀሳቅስበት ጊዜ ግን ኅብረተሰቡ የተለያዩ ጥርጣሬዎች ስላደሩበት ግጭቶች ተፈጥረዋል›› ብለዋል፡፡
የተቋራጩን ተሽከርካሪዎች አጅቦ ይሄድ የነበረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እንደነበር የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ አንጻር ታጅቦ መንቀሳቀሱ ተገቢ እንደነበርና የተፈጠረው ሁኔታ ግን መሆን ያልነበረበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በተፈጠረው ግጭት አሳዛኝ በሆነ መልኩ ንጹሐን ዜጎች ጭምር ሞተዋል፤ በዚህም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ቤተሰቦች በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እገልጻለሁ፤ መጽናናትንም እመኛለሁ፡፡ ሁኔታው አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ምክንያት ይቅረብለት በዚህ ዓይነት የግጭት ወቅት ንጹኃንን መጠበቅና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን በግጭቱ ውስጥ ምንም ሚና ያልነበራቸውን ጨምሮ ጉዳት ደርሶባቸዋል›› ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ይህን ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው ዕርምጃ መወሰድ አልነበረበትም፤ ችግሩ ቢያጋጥም እንኳ ዕሑድና ሰኞ እንደተደረገው በትዕግስትና በውይይት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት መደረግ ነበረበት፡፡ በድርጊቱ ማን ምን እንደፈጸመ ዝርዝሩን ከፌዴራል የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚያጣራ ቡድን ወደ አካባቢ በአስቸኳይ እንደሚላክ አስታውቀዋል፡፡ ዝርዝሩ ተጣርቶ ያልተገባና ተመጣጣኝ ያልሆነ ዕርምጃ የወሰዱ አካላት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖርም አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡና መንግሥት በጋራ እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የሕግ አስከባሪ አካላት በሲቪል ኅብረተሰብ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ ይገባው ነበር፤ ሪፖርቱ በዝርዝር ወደፊት የሚጠናና ይፋ የሚሆን ቢሆንም እስከአሁን ከአካባቢው አመራሮች በደረሰኝ መረጃ ኃላፊነት የጎደለው፣ ትክክለኛ ያልሆነ ዕርምጃ ተወስዷል።››
በኮኪትም ይሁን በገንዳውኃ በደረሰው ጉዳት ከመከላከያ ጋር ኅብረተሰቡ ወደ ግጭት መግባቱ ተገቢ አልነበረም። ግጭት ቢፈጠር እንኳ ሥርዓት ባለው መንገድ ለመፍታት ጥረት መደረግ ነበረበት፡፡ የኃይል አማራጭ በምንም መንገድ ተመራጭነት የሌለው በመሆኑ በደረሰው ጉዳት ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አካል ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡
በተጨማሪም በምዕራብ ጎንደር አካባቢ የእርስ በእርስ መገዳደል እየቀጠለ ነው። ‹‹የእርስ በእርስ መገዳደሉ ዓላማ ቢስ፣ መዳረሻ የሌለው፣ ንጹኃንን ከመግደልና ከመጉዳት ባለፈ ምንም ዓይነት ጥቅም የሌለው ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ ስለሆነና ንጹኃኑን የአማራና የቅማንት ሕዝብ ለአደጋ ያጋለጠ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በምዕራብ ጎንደር አካባቢ ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ሕጋዊና ጠንካራ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ ‹‹ከሁለቱም ወገን ታጥቀው ሰላማዊ የሆነውን ሕዝብ ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጉ ያሉ ወገኖች በአስቸኳይ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታረሙና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
አጋጣሚውን በመጠቀም የክልሉ ሰላም እንዲናጋ፣ የሕዝቡንና የመንግሥትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማስተጓጎል የልማትና የሰላም እንቅስቃሴዎች እንዲደናቀፉ የሚደረግን ጥረት ለመቆጣጠር የክልሉ መንግሥት ሰፊ ሥራ ይሠራል፤ ሕዝቡም በአንድነት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
የፀጥታ አካላት በክልሉ ውስጥ ሕግ እንዲከበርና ሰላም እንዲሰፍን መስዋዕትነት እየከፈሉ ጭምር ከሕዝብ ጎን ቆመው እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ‹‹የክልሉ ሁኔታ እንዳይረጋጋና ሰላም እንዲጠፋ ሕዝቡን እርስ በእርስ በማናቆር ወደ ግድያ፣ መጠፋፋትና የንብረት ውድመት የሚመሩ ኃይሎችን በመቆጣጠር ለሕግ እንዲያቀርብም ለፀጥታ ኃይሉ ጥሪዬን አስተላፋለሁ›› ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጄኔራል ብርሃኑ የጎንደርን ግጭት በተመለከተ የተምታታ መግለጫ በተለያየ መንገድ እየወጣ መሆኑን ተናግረዋል። የጎንደር ሁኔታ በደንብ መጣራት ያለበት ነው፤ ሁሉም አካላት እየተናገሩ ያሉት ሳይጣሩ ነው። በብዙ ማህበራዊ ሚድያ እየተባሉ ያሉት ነገሮችም አሁን ያለውን ለውጥ የሚደግፉ ሳይሆኑ የሚያፈርሱና የሚያዳክሙ ፤ህዝብ ለህዝብ እንዲጋጭ የሚያደርጉ ናቸው። አሁን እንዲጣራ ተወስኗል የክልል የመከላከያም ሌላም የሚመለከተው አካል ተጨምሮ ይጣራል። መከላከያ ሰው ገደለ የሚል ከፍተኛ ዜና አለ ነገር ግን አሁን ባለው መረጃ መከላከያ ሰው ለመግደሉ ምንም የተገኘ ማስረጃ የለም ይሄ በትግራይ ክልል ከተፈጠረውም ጋር የሚመሳሰል አይደለም።
በትግራይ ክልል ዛላ አምበሳ አካባቢ ሕፃናት ተማሪዎች መንገድ ላይ ተኝተው መከላከያን አትሂዱ ብለው ነበር፤ተማሪዎቹ የጎረቤት ሀገር ሊወረን ይችላል የሚል ስጋት ይዘው ነው ይሄን ያደረጉት። ህዝቡ እንዲሰጋና እንዲወጣ የተደረገው ደግሞ በፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ ሕፃናቱ አስበው አልወጡም እስኪረዱ ብለን ዕርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበናል። ይሄ በተመሳሳይ ሽሬ ላይም በወጣቶች ተደርጓል። ይሄ ሲሆን ለሀገሪቱ ሰላም እንዳይደፈርስና መከላከያን መንገድ የዘጉት ጠልተው ሳይሆን በሌላ አካል ተገፍተው በመሆኑ እንዲሁም መከላከያን ለማንቀሳቀስ አስቸኳይ ነገር ባለመኖሩ ዕርምጃ ለመውሰድ አልተቸኮለም። ለዚህም በውይይት እንዲፈታ ሲደረግ እነዛ ወጣቶችና ሕፃናት እነ እከሌ አነሳስተውን ነው ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል።
የጎንደር ግን የተለየ ነው ምዕራብ ጎንደር ቅማንት መተማ እስከ ጭልጋ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የጸጥታ ችግር ለረጅም ጊዜ ያለበት ነው። እዚያ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ የታጠቀ ነው፤ በአካባቢው የየራሳቸው ተከታዮች ያሏቸው አንዳንዴም በየሚድያው የሚፎክሩ የጎበዝ አለቆችና በአርማጭሆ አካባቢ ሽፍቶችም አሉ። በወቅቱ የተሠራውም ሥራ አደገኛ ሲሆን፤ ሁለት ነገሮች ናቸው የተከሰቱት።
በመጀመሪያ ለእጀባ የተመደቡ የሠራዊቱ አባላት አጅበው እየሄዱ ሸዲ ላይ ህዝቡ ወጥቶ ይሄ ኩባንያ እንዲህ ሲበድለን ስለነበረ መፈተሽ አለበት ይፈተሽ የሚል ጥያቄ አቀረበ። ከዚያ በኋላ ውሃ በሚቀዳ ቦቴ ውሃ ለመቅዳት የሚሄዱ አስር ወታደሮች ደፈጣ ተደርጎ ተተኩሶባቸው ሁለት ወታደሮች ተመተው ከቆሰሉ በኋላ ወታደሮቹ ራሳቸውን መከላከል ስላለባቸው መሬት ይዞ አድፍጦ የሚተኩስ ኃይል ላይ ዕርምጃ ወስደዋል።
ሁለተኛው ይሄን ተከትሎ መከላከያ ራሱን በመከላከሉ ምክንያት ሰው ገድሏል ተብሎ ተፈትሸው እንዲያልፉ የተደረገው ኮምቦይ ህዝቡ ወጥቶ እንደገና እንዲቆም ተደረጎ ህዝብና መከላከያ አብሮ ባለበት ሌላ የታጠቀ ኃይል ጋራና ተራራ ይዞ ተኩስ ከፈተ። በዚህ መሀል የተጎዱ ሰላማዊ ሰዎች አሉ። በዚህ ሂደት ወደ ሰላማዊ ዜጎች የተኮሰ ወታደር ካለ ተጣርቶ ዕርምጃ የሚወሰድ ይሆናል። እስከአሁን ሠራዊቱ በቦታው ህዝቡን እያገለገለ ነበር የሰነበተው አሁንም ምዕራብ ጎንደር መከላከያ ካልመጣ ስጋት ውስጥ ነን የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ማንኛውም አካል በዚያ ሁኔታ መግለጫ መስጠቱ ተገቢ አይደለም፤ መከላከያ አድርጎት ከሆነ ካሳ ይከፍላል ይቅርታም ይጠይቃል።
እጀባ ሲደረግ የነበረው ሱር ኮንስትራክሽን በአካባቢው ካሉት ሁለት ፕሮጀክቶች በቦታ የጸጥታ ችግር ስለተፈጠረ ማሽኖቹን ወደ መተማ አርማጭሆ ላዛውር ብሎ ክልሉንና ዞኑን አስፈቅዷል። እነዚህ ከፈቀዱ በኋላ 30 የሚጠጉ ማሽኖች ስለሆኑና አካባቢው የፀጥታ ችግር ስላለ መከላከያን ጠየቀ። ይሄ ከዚህ በፊትም ለሌሎችም የሚደረግ ነው። የኩባንያው በሥራም ላይ እያለ በመከላከያ ነበር የሚጠበቀው አዲስ ነገር አልተሠራም። አስፈላጊ ሲሆን አንድ መኪና ብቻም ይታጀባል። ይህን ማጀብ ደግሞ የመከላከያ ሥራ ነው፤የክልሉ ማጀብ የሚችል ቢሆንም ብዙ ከመሆኑና በአካባቢው የጸጥታ ችግር አንዳንዴም ዘረፋ ስላለ ከክልል አቅም በላይ ነው ብሎ በማሰብ የተደረገ ነው። በውይይት ለመፍታትም ተኩስ ከጀመሩ በኋላ ጊዜ ስላልነበረ የሚሆን አልነበረም።
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር