ዓላማን ውጤታማ ማድረግ የስኬት ቁልፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው መዝገበ ቃላት ስኬት የሚለውን ቃል፣ የአላማ ወይም የድርጊት ክንዋኔን በጥሩ ሁኔታ እንደታቀደው መፈጸም በሚል ተርጉሞታል፡፡ ይህንን እሳቤ ይዤ ወደ ያዝኩት ጉዳይ ላምራ፡፡
በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሞኑን ለስራ በተጓዝኩበት አጋጣሚ ያገኘኋቸው የዱብቲ ከተማ ነዋሪ አቶ መሀመድ ህሩም ጊዳ ይባላሉ። ባለትዳር እና የዘጠኝ ልጆች አባት ናቸው፡፡ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም በከሰል ንግድ የጀመረው ስራ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ አልተወደደለትም፡፡ መንግስትም በዛን ወቅት ዛፍ የመትከልና የማልማት ዘመቻ ላይ ነበርና ወቅቱ ከሰል ለማምረት ጥሩ አልነበረም፡፡ ‹‹ስራ የለመደ ሰው ቁጭ ሲል ይጨንቀዋል፡፡ እኔም እንደዛ ነበር የተሰማኝ፡፡ በመሆኑም ሌላ አማራጭ በመፈለግ ስራ መጀመር እንዳለብኝ ወሰንኩ›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡ ይሰሩ የነበረውን የከሰል ንግድ እርግፍ አድርገው በመተው ሌሎች አማራጮችን ማማተር ቀጠሉ፡፡
አቶ መሀመድ በትምህርቱ መግፋት ባይችሉ እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ ቆጥረዋል፤ ህይወታቸውን ለመለወጥም ንግዱንም ግብርናውንም ሞካክረውታል፡፡ ከከሰል ንግድ ጀምሮ የእህል፣የፍየል እና የከብት ንግድ፤ በእርሻ ስራም ጥጥ እና በቆሎ በማምረት ሰርተዋል፡፡
በአንድ ወቅት የወጠኑት ስራ ለዛሬው መሰረት ሆኗቸዋል፡፡ለከሰል ንግዱ ማጓጓዣ በገዙት የጭነት ተሽከርካሪ ከዱብቲ ወረዳ የተመረተ እንደ በቆሎ፣ ስንዴ እና የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ኮምቦልቻ እና ደሴ በማጓጓዝ መሸጥ ጀመሩ፡፡
በዚህ አጋጣሚም ምርቱን ይወስዱ የነበሩ የዱቄት ፋብሪካዎችን የመጎብኘት አጋጣሚ አገኙ፡፡ይሄ አጋጣሚ የዱቄት ፋብሪካ ለመጀመር የነበረውን ዕቅዳቸውን እንደሚያሳካላቸው በማመን ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆነው ካፒታል ከየት፣ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ማጠያየቁን ቀጠሉ። በስራ ከሚያገኟቸው ባለፋብሪካዎችም ተመክሮ በመውሰድ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ መበደር እንደሚችሉ መስማታቸው አስደሰታቸው፡፡የውስጣቸው ተስፋም አበበ።
ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና አላቸው ተብሎ ለታመነባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መንግሥት ብድር እንደሚያመቻች ቢሰማም፤ ልማት ባንኩ በወቅቱ በአፋር አካባቢ ስራ ባለመጀመሩ ተጠቃሚ ለመሆን የሚቻልበት አጋጣሚ አልነበረውም፡፡ሆኖም ግን ልማት ባንክ የማበደር ስራ ሲጀምር አቶ መሀመድ ጥያቄያቸውን አቅርበው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በወቅቱ የነበራቸው ካፒታል አምስት መቶ ሺ ብር ነበር፡፡ ‹‹ለፋብሪካው መጀመር ትልቅ ካፒታል የሆነኝ ዓላማ እና ትጋት ነው›› ሲልም ይደመጣሉ፡፡
ወደ ስራ ከገቡም በኋላ ስራው እንዳሰቡት አልቀለላቸውም፡፡ ለባንኩ ተመላሽ የሚደረግ 20 በመቶ የብድር ገንዘብ፣ መብራት ለማስገባት ለትራንስፎርመር የፈጀው 663 ሺ ነበር፡፡ ውሃ ለማስገባት የወጣው ወጪ ተደማምሮ ካሰቡትና ከገመቱትም በላይ እንደሆነባቸው ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ እልህ ብርታት ሰጥቷቸው የማሽን ተከላውን እውን ለማድረግ ገፋበት፤ ስድስት ሚሊዮን ብር የፈጀው የዱቄት ፋብሪካ ተጠናቅቆ ዱቄት ለማምረት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደረሰ፡፡ አሁን የቀረው ማጠናቀቂያ ጥቃቅን ስራዎች እና ስንዴ ማስገባት ብቻ ነው፡፡
መንግስት ለፋብሪካዎች የሚሰጠው የስንዴ ምርት አለ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ለአቶ መሀመድ ተስፋ የሰጠው የአካባቢው ማህበረሰብ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ እናስገባለን ብለው በስፋት ተጠቅመው የነበረውን የሸንኮራ አገዳ ምርት ወደ ስንዴ ማምረት መቀየራቸው ነው፡፡ ስንዴ በብዛት አምርተዋል፡፡ የዱቄት ፋብሪካ መቋቋሙ ደግሞ ለአካባቢው ስንዴ አምራች ማህበረሰብ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነላቸው አቶ መሀመድ ይናገራሉ፡፡
የፋብሪካ ግንባታ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ አራት ቋሚ የጥበቃ ሰራተኞችም ተቀጥረዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ምርት ሲጀምር ደግሞ 50 ሰራተኞችን ቀጥሮ ያስተዳድራል፡፡ በ24 ሰዓታት ውስጥ 420 ኩንታል የማምረት አቅም ያለው መሆኑን አጫወተውናል፡፡
ፋብሪካውን ለማቋቋም ሲጀምሩም የዱብቲ ወረዳ አስተዳደር ቦታ እንዲሰጣቸው አመለከቱ፡፡ እንዲህ አይነት ኢንቨስትመንት ለአካባቢው አዲስ ነገር ነገር ነውና ብዙም ተቀባይነት አላገኙም። ‹‹ቦታ ስጡኝ ብዬ ስጠይቅም ውሸት ነው ፋብሪካ አያቋቁምም የሚል ምላሽ አገኘሁ፡፡ያም ሆኖ ተስፋ ሳልቆርጥ ጥያቄዬን ቀጠልኩ፡፡ 10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ፈቀዱልኝ፡፡ አሁን እየመጡም ይጎበኙኛል፤ ያበረታቱኛል»ይላሉ።
አቶ መሀመድ ወደፊት ኢንቨስትመንትን የማስፋፋት አላማ ሰንቀዋል፡፡ ለቀጣዩ የኢንቨስትመንት ስራ ከሎጊያ ከተማ አምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበዋል፡፡ ይሄም የብስኩት ፣ የፓስታ እና ማኮሮኒ ፋብሪካ ለማቋቋም ነው።አሁን የዱቄት ፋብሪካው ስራ እንደጀመረ የቀጣዩን ፋብሪካ ግንባታ እንደሚጀምሩ ነግረውኛል፡፡
በአካባቢያችን የዱቄት ፋብሪካ አልነበረም፡፡ ለአካባቢው ህብረተሰብም ዱቄት እየቀረበ የሚገኘው ከአዳማ ከተማ ነው፡፡ የዱቄት ፋብሪካ በአካባቢው መቋቋሙ ለማጓጓዣ ይወጣ የነበረውን ወጪ ስለሚቀንስ ዋጋው የተረጋጋ እንደሚሆን አቶ መሀመድ ይጠቁማሉ፡፡
«የሰውን ልጅ ከፍ የሚያደርገው ገንዘብ ሳይሆን ዓላማ ነው» ያሉት አቶ መሀመድ ከገንዘብ ይልቅ ዓላማ ያለው መሆን እንደሚያዋጣም ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው አምስት መቶ ሺ ብር መነሻ ካፒታል ይዘው ነበር ፋብሪካ ለመገንባት ሲያስቡ የነበረው፡፡ ‹‹ እጄ የነበረው ገንዘብ ፋብሪካ አይገነባም፤ በዓላማ እና በተነሳሽነት መጀመሬ፣ ስራ ማጣቴ፣ የገጠሙኝን ፈተናዎች በመጋፈጤ ለዚህ ውጤት በቅቻለሁ›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ከእርሳቸው የሚበልጡ የአፋር ተወላጅ ባለሀብቶች በአካባቢው እንዳሉ የሚናገሩት አቶ መሀመድ፤ አብዛኞቹ ተሽከርካሪ ገዝተው የሚሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ፣ለብዙዎች የስራ ዕድል በሚከፍት ዘርፍ ላይ ቢሰማሩ ጠቃሚ ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡ እርሳቸውን ተከትለው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ባለሀብቶቹ ይሰማራሉ የሚልም ተስፋ አላቸው፡፡እርሳቸው ምንም አይነት ፋብሪካ በሌለበት ቦታ ይሄንን ፋብሪካ ለመገንባት መነሳታቸው በጨለማ መካከል ብርሀን እንደማብራት ይቆጠራል።
ወደ ከፍታ የሚያሻግረው የድልድይ ስራ ነው፡፡ ቢሆንም እያንዳንዱ ሰው የሚደርስበትን ስፍራ ማወቁ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ከአቶ መሀመድ ተሞክሮ መማር ይችላል፡፡ በዓላማ እና በተነሳሽነት ስራዎችን መጀመርና መተግበርም የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመሻገር ጥሩ ስንቅ ይሆናል፡፡
ሁሉም ሰው በምድር ቆይታው አነሰም በዛ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ይጋፈጣል፡፡ መሰናክሉን አልፎ የሚጠቅም እና ለሌሎች የሚተርፍ ነገር ሰርቶ የሚያልፍ፣ የተለያዩ ኃላፊነቶችንም የሚሸከም አለ፡፡ አቅዶ እና ተግብሮ ያሰበውን የሚያገኝም የታደለ ነው፡፡ ዝነኛው ሳይኮሎጂስት ሲግመንድ ፍሮይድ ‹‹ስራ እና ፍቅር የሰው ልጅ ሕይወት የማዕዘን ራስ ናቸው›› ሲል የተናገረው በብዙ አጋጣሚዎች ይነሳሉ፡፡
“Success is the progressive realization of a worthy goal or ideal.” ስኬት አንድ ጠቃሚ ብለን የምናስበውን ሃሳብ እውን ማድረግ ነው›› የሚለውን የኸርል ናይቲንጌል አነጋገርን ወስደን ብንመለከት፤ ስኬት ማለት ዋጋ የሚሰጥን ሃሳብ ወይም ግብ እውን ማድረግ ማለት መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ስኬት በግል ሚዛን የሚለካ፤ በግል መነጽር የሚታይ፤ በግል አእምሮ የሚተረጎም ነገር መሆኑንም ያስገነዝበናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ዘላለም ግዛው