ብዙዎች “ይህማ አይቻልም” የሚሉትን ሥራ መሞከር ይወዳሉ። ሴትነታቸው አንድም ቀን ከሥራ አግዷቸው እንደማያውቅ ያስረዳሉ። የወንድ ፣ የሴት ብለው በስራ ላይ ክፍፍል አያደርጉም። ”የወንዶች ብቻ” የሚባለውን ከባድ መኪና(ተሳቢ) ያለረዳት በረሀ አሽከርክረውታል። የመካኒክነት ሙያ ባለቤት ስለሆኑ ከባድ ችግር ካልገጠማቸው በቀር መኪናቸውን ማን ነክቶት ፤ ብቻ እሳቸው ሴቶችን የሚያቅት ምንም ነገር የለም ብለው በመነሳት ሰርተው አስመስክረዋል። ጥንቃቄ በተሞላበት በአሽከርካሪነታቸው 25 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ይህንን ጥንካሬያቸውን ከህይወት ልምዳቸው ጨልፈው ያወጉን ዘንድ ለዛሬው የ‹‹ህይወት እንዲህ ናት ›› አምድ እንግዳችን ያደረግናቸው ወይዘሮ ፀሐይ ዋጋሪ ናቸው ።
የትነበርሽ ?
ትውልዳቸው ሸዋ ክፍለአገር ‹‹ሸቦካ›› እየተ ባለች በምትጠራ ስፍራ ሲሆን እድገታቸው ፊንጫአ ከተማ ነው። በዚህ ቦታ ልጅነታቸውን አጣጥመዋል። ሮጠው ተሯሩጠው ለጎረቤት ተላልከው አድገዋል። ትዝታና ታሪክን በልቦናቸው አስቀርተዋል።
ፊንጫአ ለእርሳቸው ሰፈር ብቻ አይደለችም። የህይወት መስመር መቀየሻ፤ ፍላጎትን ማርኪያ፣ የጥንካሬ መሰረታቸው ነበረች። በአሽከርካሪነት ለመቀጠር ሲሉ በነበራቸው እድሜ ላይ ሰባት ዓመት ጨምረው እድሜሽ አልሞላም ያልተባሉባት ምድር ነች። በ1950 ዓ.ም መስከረም 16 እንደተወለዱ የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሐይ፤ ነፍስ ካወቁ በኋላ ፊንጫአን ቶሎ ያለቀቁት ለአደጉባት አካባቢ ልዩ ፍቅር ስላላቸው ነው። እዛ ሳሉ ባህሪያቸው ወንዳወንድ ፣ የታዘዙትን እንደወንድም እንደሴትም አድርገው የሚፈጽሙ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
በተለይ አልችልም የሚል ነገር ከአንደበታቸው ወጥቶ እንደማያውቅ ያወሳሉ። በእርግጥ ለዚህ መሰረቱ የቤተሰባቸው አስተዳደግ እንደነበር ይናገራሉ። የሚሞክሩትን ሁሉ ‹‹ትችይዋለሽ እንጂ አትችይም›› ስለማይሏቸው የማይሞክሩትና ለወንድ ብቻ ብለው የሚተውት ነገር እንዳልነበረ ያስታውሳሉ።
ብዙዎች ከበድ ያለ ነገር ሲገጥማቸው ‹‹ፀሐይ ካልሆነች ይህንን ማን ያነሳዋል›› ይሏቸው እንደነበር የሚናገሩት ባለታሪኳ፤ በዚያው ልክ ይህች ልጅ በትምህርት የትም ልትደርስ አትችልም የሚሏቸው የአካባቢው ሰው እንደነበሩ አይረሱትም። “ለትልቅ ደረጃ የምበቃ አይመስላቸውም ነበር “ ይላሉ።
‹‹ስራን ለወንድ፤ ለሴት ብሎ መከፋፈል ከልምድ የመጣ እንጂ ማን ለስራ ደረጃና ባለቤት ሰጠው›› የሚሉት እንግዳችን፤ ይህንን አመለካከት ሰብሮ ለመውጣት ባልጠነከረ የልጅነት ጉልበታቸው ጭምር ይታትሩ እንደነበር ያነሳሉ። ስሜታቸው የሚነግራቸውን ሁሉ ማድረግ የልጅነት መለያቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።
‹‹ቤተሰብ ሳይቀር የፈለጋትን ፣ የሚሰማትን ሆና ትደግ ስለሚለኝ ልጅነቴ ደስታና ፈንጠዝያ የሞላበት፤ እገዳ ያልታየበት ፤ ራሴን በራሴ መግዛት የተማርኩበት ነው›› ይላሉ ወይዘሮ ፀሐይ፤ ከልጅነት ውሳኔያቸው ዛሬ ድረስ የሚያስታውሱት “ ሴት ልጅ እግሯን አታነሳም” በሚባልበት ማህበረሰብ ውስጥ ከወንዶች እኩል ኳስ እየተጫወቱ ማደጋቸው ብዙዎችን አጀብ ያሰኘ ነበር።
ፊንጫአ ከተማ እስከ 13 ዓመት እንደቆዩ ያጫወቱን ወይዘሮ ፀሐይ፤ ወላጆቻቸው በስራ ምክንያት ከከተማዋ ራቅ ብለው የመንግስት እርሻ ልማት ካምፕ ውስጥ መኖር በመጀመራቸው ቤተሰባቸው ጋር ለመሄድ በሳምንት 50 ኪሎሜትር የእግር ጉዞ ማድረግ ይገደዱ እንደነበር ይናገራሉ።
በልጅነታቸው ዘፋኝ እንጂ ሹፌር እሆናለሁ ብለው አስበው አያውቁም። ድምጸ መረዋ እየተ ባሉም የብዙዎችን ሰርግ አድምቀዋል። በዚህ የዘፈን ፍቅራቸው ወንድማቸው ሞቶ በማግስቱ ሰርግ ቤት ተገኙ። ይህም ለአለንጋ አስዳረጋቸው። ሆኖም ግን ሀሳባቸውን ያስቀየራቸው የእናትና አባታቸው ፊንጫ ካምፕ መግባት እንደነበር ያወሳሉ።
በልጅነታቸው ግልጽ፣ ደፋር፣ ባለሙያ፣ ታዛዥ ልጅ እንደነበሩ አጫውተውናል። ‹‹ይህቺ አሁን ሰርታ ታበላለች›› ብለው የአካባቢው ሰዎች ያሟቸው እንደነበር የሚያነሱት ወይዘሮ ፀሐይ፤ በቤታቸው ድግስ ስለማይጠፋ እርሳቸው የቤቱን ሥራ ሁሉ ጥንቅቅ አድርገው ሲሰሩ ይታያሉ። ይህ ደግሞ የተሳሳተ ምልከታ የነበረውን ጎረቤት ቀይሮታል ። በዚህም ጎረቤቶቹ ‹‹ሁሉን ነገር አምላክ ሞልቶ የፈጠራት ናት›› ይሏቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፀሐይ በአባታቸው የተወደዱ ልጅ ናቸው። አባት የበኩር ልጃቸው ሴት እንድትሆን ይሹ ነበር። ሆኖም አልተሳካም። ሶስተኛ ላይ ሴት ልጅ ተገኘች። አባትም “የትነበርሽ” ሲሉ ስም ሰጧት። ቀጣዩ ስማቸው ፀሐይ የሚለው ሲሆን፤ ይህ ስም የተሰጣቸው ደግሞ ሲወለዱ በጣም ቀይ በመሆናቸው “ብርሃናችን ነሽ” ለማለት ነው።
ፀሐይ በአካባቢው ብዙ ልጆች የሚጠሩበት በመሆኑ ‹‹ዋጋሪዋ›› እያሉም ይጠሯቸው እንደነበር ይገልጻሉ። ይህ ማለት ደግሞ በአባቻው ስም የመጠራት እድል ነበራቸው ማለት ነው። በእርግጥ የአባትየው ስም ‹‹ዋቅ ጋሪ›› ሲሆን ትርጓሜውም እግዚአብሄር አዋቂ ነው፤ ደግ ነው ማለት ነው። ታዲያ በዚህ ስም መጠራታቸው ያስደስታቸው እንደነበርም አልሸሸጉም።
ትምህርት እስከ ስምንት
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ፊንጫአ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ከዚያ ቤተሰብ በመንግስት እርሻ ካምፕ ለሥራ በመሄዱ ከስድስተኛ ክፍል የተቋረጠውን ትምህርት ፊንጫአ ሸለቆ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ቀጠሉ። እስከ ስምንተኛ ክፍል በዚያ ተማሩ። ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ሲማሩ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሥራ እየሰሩ ስለነበር ለትምህርቱ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ።
የሥራው ፍላጎት ማየል ደግሞ ይበልጥ ትምህርት ለምኔ እንዲሉ እንዳደረጋቸው የሚያወሱት እንግዳችን፤ የምማረው ገንዘብ ለማግኘት ነው ብለው ስለሚያምኑና በአቋራጭ ይህንን እያደረጉ እንደሆነ ሲሰማቸው የቤተሰብን ፈቃድ ለመሙላት ሲማሩ የቆዩትን ትምህርት አቋረጡ።
ቤተሰብ በተለይ እናትና አባታቸው በእርሳቸው ላይ ትልቅ ተስፋ ነበራቸው። በትምህርቷ ከእነርሱ የተሻለች ሆና ማየትን ሁልጊዜም ይፈልጋሉ። በዚህም ዘወትር ከሥራ ይልቅ ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጡ ይጎተጉቷቸዋል። ተምራ የምታስጠራቸው ትሆንላቸው ዘንድ ይመኛሉ የፈለገችውንም ያሟሉላታል። ሆኖም ያሰቡት ሳይሳካላቸው ሲቀር በጣም አዝነው እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹ለትምህርት ትኩረት አለመስጠቴ በተልዕኮ እንኳን መማር የሚቻልበትን ሁኔታ እንዳላይ አድርጎኛል። በዚህም ከስምንተኛ ክፍል ያልዘለለች ተማሪ ሆኜ ቀርቻለሁ። ሆኖም ይሄ ብዙ ቁጭት አልፈጠረብኝም። በትምህርቴ ባልገፋም በአሽከ ርካሪነት ብቁ ባለሙያ መሆን እፈልግ ነበርና ይሄንን ፍላጎቴን አሳክቻለሁ ።
ከትንሽ እስከ ትልቅ የመኪናን የውስጥ ክፍል ብልሽቱን ለይቼ እሰራለሁ። ሜካኒካል ሥራዎችንም ተምሬና በልምድ አዳብሬ ባለሙያ ነኝ። እንደውም ብዙዎች መያዝ ያልቻሉትንና አመላቸውን ሁሉ የማይረዷቸውን መኪናዎች ጭምር ለእኔ ተመርጦ ተሰጥቶኝ ዓመታትን መስራት የቻልኩት በልምዴና በተማርኩት ትምህርት ነው። ›› ብለውናል።
መቼም ቢሆን አለመማር ትክክል ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው፤ ሆኖም በመማር ብቻ ነው ትልቅ ደረጃ የሚደረሰው መባል እንደሌለበት የሚያስረዱት ባለታሪኳ፤ በተልዕኮ አውቶ ሜካኒካል ለመማር ጀምረው በህመም ምክንያት እንዳቋረጡ አጫውተውናል። ስለዚህም ልምድ በትምህርት ቢደገፍ የበለጠ ለመስራት ያግዛልና አሁንም መማር ብችል ደስ ይለኛል ይላሉ ።
ስራን ያለመታከት
ከቤተሰብ ሳይለዩ የመጀመሪያ ስራቸውን ለመስራት ያመለከቱት ይኖሩበት በነበረው ካምፕ ጋራዥ ውስጥ ነበር። ይሁንና በተሰጠው ፈተና ተጠባባቂ ሆኑ። ሆኖም ያለስራ ለመቀመጥ በካምፑ በሚገኘው ካፌ አስተናጋጅ ሆነው መስራት ቀጠሉ።
ከወራት በኋላም ወደ ፈለጉት የሥራ መስክ ገቡ። ከስራ ባልደረቦቻቸውም ሙያውን ቀሰሙ። በጊዜው ትምህርቱን ለመማር ብዙ ልፋት አልጠየቃቸውም። በረዳትነት ስለሚያሰሯቸው ሙያውን በልምድም መካን ቻሉ። ስራውን ከለመዱ በኋላ “ ለእኔ ረዳት ትሁን “ የሚለው ይበዛ እንደነበር ያስታውሳሉ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቁ ባለሙያ መሆን እንደቻሉ ይናገራሉ።
ይህንን ብቃት ይዘው ከረዳት መካኒክነት ከፍ ማለት እንዳልቻሉ የሚናገሩት እንግዳችን፤ ሴት በመሆናቸው ብቻ ኃላፊነት ለመስጠት አለመድ ፈራቸው ስላበሳጫቸው ብቃታቸውን ተማምነው ወደ አሽከርካሪነት ለመዞር ወሰኑ። መንጃ ፈቃድ አውጥተውም ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ ገልባጮችን ማሽከርከር ጀመሩ። ቀጥለውም ትልልቅ መኪኖችን በመያዝ አገር አቋራጭ ገቡ።
‹‹ማህበረሰባችን ሁልጊዜ ለወንድ ያደላል፤ እርሱ የማይሰራው ሥራ የለም ብሎ ያምናል። ሴት ግን ሙያና አቅሙ ቢኖራትም “ አይሆንልሽም” የሚባሉ ብዙ ናቸው። ስለዚህ ይሄንን አስተሳሰብ ሰርቶ በማሳየት መለወጥ ያስፈልጋል። ›› የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይ፤ ሥራን ደፍሮ መስራት መጀመር ብዙ ነገሮችን ይዞ እንደሚመጣ አይቻለሁ። ብዙ በረሃን በአነስተኛ መኪኖች ሳቋርጥ “አትችልም” የሚለውን ስሜት ከሁሉም ሰው አዕምሮ ውስጥ ነቅያለሁ። ሴቶችም ማድረግ ያለባቸው ይህንኑ ነው ብለውናል።
በጋራዥ ሥራ ላይ እያሉ የሚበልጧቸው ብዙ ወንዶች ቢኖሩም ከረዳትነት አላስ ወጧቸውም። ሹፍርናውን ሲጀምሩም እንደሚችሉ ቢያምኑባቸውም የተሰጣቸው መኪና ግን ብዙም ግልጋሎት ይሰጣል የማይባል ነው። እርሳቸው ግን ማሸነፍን ግባቸው አድርገው ነውና የተነሱት የተበላሸውን እየጠገኑ፣ የጎበጠውን እያቃኑ ስራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ይህንን የታዘቡት የስራ ኃላፊዎች የተሻሉ የሚባሉ መኪኖች መስጠት ጀመሩ።
‹‹የተሻለ ደረጃ ለመድረስ የተሻለ ሰራተኛ መሆን ያስፈልጋል። ተስፋ መቁረጥም አላማን ያደናቅፋል። እናም ዘወትር ግብን እያሰቡ መስራት መለመድ አለበት። በእርግጥ የተሻለ ነገር ሲሰጥም ለራስ ጥቅም መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ጥሩ መኪና ሲሰጡኝ ለእኔ ብለው እንዳልሆነ አምናለሁ። ምክንያታቸው ለመኪናው ደህንነት የተሻልኩ እንደሆንኩ በማመናቸው ነው። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ይህንን ማሰብ አለበት። ›› ይላሉ።
ሴቶች ሰርተው ካሳዩ ‹‹ትችላለች›› የማይላቸው የለም። እንዳውም ወንዶች “አንቺ ቅደሚ” የሚሏ ቸው ይሆናሉ። በስራዎቼ ላይ ማንም እንቅፋት እንዲሆንብኝና አትችልም እንዲለኝ አልፈቅድም። ስለዚህ ሁሉም ሴቶች “ ትችላለችን” በሥራ ማምጣት ላይ መትጋት አለባቸው ባይ ናቸው።
ወደ ሹፍርናው ሲገቡ የመጀመሪያ አማካሪ ያቸው እናታቸው እንደነበሩ ያጫወቱን ባለታሪኳ፤ ምንም እንኳን አግብተው የራሳቸውን ህይወት እየመሩ
ቢሆንም ልጆች ነበሯቸውና እነርሱን የሚጠብቅ ያስፈልጋቸዋል። “ይህማ አያቅትሽም” ለሚሏቸው እናታቸው ልጆቻቸውን አደራ ሰጥተው ዳገት ቁልቁለት፤ በረሃ ፣ዝናብ ሳይሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ መኪና ማሽከርከራቸውን ተያያዙት።
በዚህ ስራቸው ታዲያ ባለቤታቸው ደስተኛ አልሆኑም። ስራውን ካላቆምሽ እንለያይ ሲሉም ሀሳብ አቀረቡ። ወይዘሮ ጸሀይም አይናቸውን አላሹም። ” በፍላጎቴ የመጣብኝን መቼም ልገዳደረው አልችልም። ”ብለው ከልጆቻቸው አባት ተለያዩ። “ሥራዬ የህይወቴ መሰረት፤ የነጻነቴና የስሜቴ መገለጫ፤ የደስታዬ ምንጭና ለራሴም ሆነ ለቤተሰቤ መኖሪያ ነው። ስለዚህ የሚገድበኝን ሁሉ ማስወገድና ራሴን ሆኜ መስራት የሁልጊዜ ምኞቴ ነው” ይላሉ።
ስለዚህም ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ችግርን ተጋፍጦ በማሸነፍ መስራት ተገቢ ነው። ለምን ሆነን ወደኋላ መተውም ይገባል።
በሥራና በፍላጎቴ እናቴ እንደማትደራደር ያወቅሁት ልጆቼን ይዛ መንጃ ፈቃድ እንዳወጣ ስታበረታታኝ ነው። ቤተሰቦቼ መስራት ያስከብራል፤ ይለውጣል ብለው የሚያምኑ መሆናቸውን ይናገራሉ። እርሳቸውም በዚህ ማንነት የተሰሩ በመሆናቸው ይህንን እያከበሩም ነው ።
ባለ 22 ጎማውንና 400 ኩንታል የሚይዘውን ተሳቢ ይዤ ለረጅም ዓመታት በረሃ አቋርጫለሁ፤70 ኩንታል የሚጭነውን ገልባጭ መኪናን በመያዝ ከ5ዓመት በላይ ሰርቻለሁ። ይሄ አቅሜንና ፍላጎቴን ያማከለ ግብ በመያዜ ነው። ሆኖም ይህ ንን አልችለውም በሚል ማንነት ብገነባ ኖሮ አይታ ሰብም ።
‹‹የሾፌር ስራ በአንድ ቦታ የሚረጋበት አይደለም። በየበረሃው ብዙ ፈታኝ ነገር ያጋጥማል፤ ረሃብ፣ ውሀ ጥም ሌላው ደግሞ ዝርፊያ… ። ሆኖም እኔ እድለኛ ሆኜ የከፋ ነገር አልገጠመኝም። መንገድ ተዘግቶ በረሃ ላይ ከማደር ውጪ›› ይላሉ።
ወይዘሮ ፀሐይ ብዙ ጊዜ በረሃ የሚያቋርጡት ቀን ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያታቸው በምሽት ከሚያጋጥም አደጋ ይልቅ የቀኑ በረሀ ይሻላል ከሚል ነው። ይህንን ጊዜ መምረጣቸው ደግሞ ጥንቃቄ የሞላበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንደሚያግዛቸው ያስረዳሉ። በተለይ ሎቬት ወይም 22 ጎማ ያለውን ተሳቢ ሲነዱ ምንም እንኳን መንገዱን ቢያውቁት ለመተጣጠፍ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህም በብርሀን መስራት ከችግር እንደሚታደጋቸው ያወ ሳሉ።
ከወንዶች የተሻለ ጥንቁቆች ሴቶች እንደሆኑ ያልተረዱ አንዳንድ ሰዎች ይህንን እንዴት ቻልሽው ሲሉ ይጠይቋቸዋል። መንገድ ላይ አስቁመውም አድናቆት የሚቸሯቸው ጥቂቶች አይደሉም። እሳቸው ግን ይበሳጫሉ ‹‹ሴት አትችልም›› የሚለው አመለካከት መቼ ነው የሚቆመው ሲሉም ይጠይ ቃሉ። መኪናና ልጅ አንድ ነው ብላ የምታደርግ ሴት ናት። ብዙ ነገሮችን በአንድ ጊዜ የምታስብና በጥንቃቄ የምትከውን ሴት ናት። ይሄንን ሁሉም ተረድቶ በሴቶች ብቃት ቢተማመን ደስ ይለኛል።
በጎነት ለራስ
በጉዞ ውስጥ ብዙ ነገር ይገጥማል። አሽከርካሪ ሆነሽ በረሃን ስታስቢ ቅድሚያ የምትማሪው ለሰዎች ደግ መሆንንና መድረስን ነው። እኔም ብዙዎችን መንገድ ላይ መኪና ሲበላሽባቸው አግዛቸዋለሁ። ይህ ደግሞ ሁሌም የውስጥ ሰላም ይሰጠኛል። በጎነት መልሶ ለራስ መትረፍ ነው። ይህንን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ጎማ ብልሽት ገጥሟቸው የተሰጣቸው መልስ እንዳረጋገጠላቸው አይረሱትም። በጉዞአቸው ረዳት አይዙም። ችግሩ በተከሰተበት እለት ደግሞ በራሳቸው ብቻ ጎማውን መፍታት አስቸጋሪ ነበር። እናም ለሌሎች የሰሩት በጎነት ለእሳቸውም ተረፈና ያን ዕለት ሌሎች አሽከርካሪዎች ረዳታቸውን ሰጥተዋቸው የፈነዳውን ስድስት ጎማ በተለያየ ቦታ እየቀያየሩ የፈለጉበት ቦታ ላይ መድረስ ችለዋል።
እርሳቸው መንገድ ዳር መኪና አቁመው ምንም የሚያልፋቸው ሾፌር የለም። ችግራቸው ጎማ እንኳን ቢሆን ጎማ የሚያውሳቸው ብዙ ነው። በረሃ ላይ መጨካከን የለም። እርሳቸውም ብዙዎችን ማገዛቸውን ይናገራሉ። በተለይም የአቅም ውስንነት ሲኖር ለብዙዎች መድረስ ችለዋል።
ብዙዎች መንጃ ፈቃድ ሲያወጡ የመኪናን ችግር በሚገባ ተረድተው አይደለም። እናም ቴክኒካል ችግር በበረሃ ውስጥ ይገጥማቸዋል። በዚህም እርሳቸው የሚቻለውን ማድረግ ግዴታቸው እንደሆነ ስለሚያስቡ እውቀታቸውን ተጠቅመው ይሞክሩ እንደነበር ያጫወቱን ወይዘሮ ፀሐይ፤ ረዳት አብሯቸው አለመጓዙ አንድም ቀን አሳስቧቸው አያውቅም። ጨዋታቸው ሁሉ ከመኪናቸው ጋር እንዲሆንም ይፈልጋሉ። በዚህም ለዓመ ታት በሰሩበት የበረሃ ጉዞ አንድም ቀን ረዳት አልነበራቸውም። ስለሌላቸው የመጣባቸው ከባድ ችግርም እንዳልነበረ ይገልጻሉ። መጫን ከሆነ የጉልበት ሰራተኛ ያደርገዋል። ከዚያ ውጪ ግን የእርሱ ሥራ አይታየኝምና ከረዳት ይልቅ የመካኒክነት ሙያ ለበረሃ ያስፈልጋል ይላሉ።
ገጠመኝ
‹‹ሴቶች ከእናትነት ባህሪነታቸው የተነሳ ድንጉጥ እና ሩህሩህ ናቸው። እኔ ግን ከዚህ የተለየሁ ነኝ። ድንጋጤ የሚባል አያውቀኝም፣ ፍራቻም ቢሆን በውስጤ ተፈጥሮ አያውቅም። ትግዕስትና መረጋጋት ደግሞ መለያዬ ነው›› የሚሉት እንግዳችን፤ በበረሃ ማሽከርከር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ገጠመኞች አሏቸው። አንደኛው ግን ለብዙዎች ማስተማሪያ ስለሚሆን ብለው አጫውተውኛል።
ገጠመኛቸው የሰባት ወር ነፍሰጡር እያሉ የሆነ ነው። በአምቡላንስ መኪና ውስጥ ባለቤታቸው፣ አለቃቸውና አንድ በእድሜ ገፋ ያሉ ሰው አብረዋቸው አሉ። በሰላም እየተጓዙ ባሉበት ወቅት ድንገት ሹፌሩ መንገድ ሳተ። ለማቆም ደግሞ ፍሬኑ እንቢ አለው። ወደገደል ውስጥ መጓዛቸውን ቀጠሉ።
በመኪና ውስጥ ያሉት ሁሉም ጭንቀታቸው ለነፍሰጡሯ ነበር። ድንጋጤ የማያውቃቸው እንግ ዳችን ግን መሪውን ወደቀኝህ ያዝ እያሉ ሾፌሩን ያበረቱት ነበር። ራስሽን ጠብቂ፣ ልጁ እንዳይጎዳ ወዘተ የሚሉት ነገሮች ለእርሳቸው ቦታ አልነበረውም። ለእርሳቸው ዋናው ነገር ሁሉንም ነፍስ ማዳን ነው። እናም ያንኑ ምክረሀሳባቸውን መለገሳቸውን ሳያቋርጡ ድንገት እድል ቀናቸውና መኪናውንም ጭቃ ይዞ አቆመው። በዚህ ሁኔታ ሁሉም ከአደጋው ተረፉ።
በእርግጥ ይላሉ እንግዳችን በእርግጥ የነበርንበት ቦታ ማንም የማያየን ስለነበር አሁንም ሌላ ሥራ እንደሚጠበቅብን አስባለሁ። እናም አንድ መፍትሄ ወሰድሁ። ያለሁበትን ቦታ ለየሁና በቅርብ ያሉ የአውራጎዳና ሰራተኛ ጓደኞቼን ጠራሁ። እነርሱም መጥተው ከዚያ ጉድ አወጡን።
‹‹እኔ ነፍሰጡር ሆኜ ማሽከርከር የለብኝም ብዬ ባምንም የነበረው ሁኔታ ግን እንዳሽከረክር የሚያስገድድ ነበር። ሁሉም በድንጋጤው ይንቀ ጠቀጣል። በተለይ ሾፌሩ መሪውን መጨበጥ ተስኖታል። ስለዚህም ምርጫው ራሴ መንዳት ብቻ ሆኖ አገኘሁት›› ያሉን ወይዘሮ ፀሐይ፤ እራሳቸው እየነዱ የፈለጉት ቦታ እንደደረሱ አይረሱትም። ስለዚህም በዚህ ገጠመኛቸው ብዙዎች መውሰድ አለባቸው የሚሉት መደናገጥ በሾፌርነት ሥራ ላይ ዋጋ ያስከፍላል የሚለውን ነው።
ብርታት ሰጪው ውሃ አጣጭ
ለመውደድ መስፈርቱ ስሜትና ፍላጎትን ማክበር እንደሆነ የሚያምኑት እንግዳችን፤ ውሃ አጣጫቸውን የተውትም ያገኙትም በፍላጎታቸው የተነሳ ነው። ማንነታቸውን የሚያከብርላቸውን ሰው ዛሬ ባለቤታቸው አድርገዋል። በዚያው ልክ ማንነታቸውን አልቀበል ያላቸውን የልጆቻቸውን አባት ተለይተዋል። እናም የትዳር መሰረቱ ለእርሳ ቸው ማንነትን፣ውስጥን ማክበር እና መከባበር ነው። የአሁኑን ባለቤታቸውን ያገቡትም ለ ሥራቸው ብርታት ስለሆኗቸው መሆኑን ያነሳሉ።
‹‹ሴት ትችላለች ብሎ ማመን የወንድ ሁሉ መለያ ባህሪ መሆን አለበት። እድልም በየጊዜው ሊሰጣት ይገባል። ያ ካልሆነ ግን በራሷ ሰርታ የፈለገችው ደረጃ መድረስ እንደምትችል ማሳየት ይኖርባታል። እኔ ይህንን አድርጌ ነው ብቁ የሆንኩት። ስለዚህ ሴቶች ከጥገኝነት ራሳቸውን ማላቀቅ አለባቸው›› ይላሉ። ከባለቤታቸው ጋር በመከባበር ስሜት ዛሬ ድረስ የዘለቁትም እኩል እየሰሩና ቤተሰቡን እየመሩ በመቀጠላቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
ምርጫቸው ፍላጎትን በማክበር ላይ የተመሰረተ መሆኑ የልባቸው መሻት የሚፈጽም ባል ሰጥቷቸዋል። ልጆቻቸውንም በዚህ ማንነት እንዲያሳድጉ ሆነዋል። በዚህም ዛሬ የአምስት ልጆች እናትና የልጅ ልጆችን ያዩ አያት ሆነዋል። ልጆቻቸውንም እርሳቸው ያልደረሱበት የትምህርት ማማ እንዲደርሱ በማድረግ ሁሉንም ለቁምነገር አብቅተዋል። ይህ ደግሞ አገር ውስጥም ሆነ ውጪ አገር ሄደው ሊያርፉ ቢፈልጉ እፎይ የሚሉበትን እንዲያዘጋጁ አድርጓቸዋል።
ምስክርነት
አቶ ዳንኤል በቀለ ይባላሉ። በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ከእንግዳችን ጋር ከ20 ዓመት በላይ ሰርተዋል። ‹‹ፀሐይ እኛ የማናሽከረክረውን መኪና ሁሉ የምታገላብጥ፤ በጥንካሬዋና ባላት እውቀት ሁልጊዜ የምታስደንቅ፤ ትሁትና ቅድሚያ ለሰዎች የምትሰጥ ሴት ነች። በሥራ ላይ ታታሪ ሰራተኛ፤ በማህበራዊ ህይወትም እንደ እናት፣ እንደ እህት ሆና ሁሉን ነገር የምትፈታም ነች። ›› ይሏቸዋል። በተለይ በሥራ ወዳድነታቸው የማይቀናባቸው እንዳልነበር ያነሳሉ።
በሥራ ዘመኔ ከወንድ ጓደኞቼ ይበልጥ የምቀርባትና ወንድ ጓደኛ ሊሸፍነው ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን በእርሷ አቅም ፈታ ከችግር ነጻ የምታደርገኝ ጠንካራ ሴት ሲል በአድናቆት ይናገራሉ። ድፍረቷን፤ ብቻዋን በረሃ ስታቋርጥ ያላትን መረጋጋት፣ ከወንዶች እኩል በስራ መገዳደሯንና የማትሞክረው ሥራ አለመኖሩ ደግሞ ያስደንቀኛል ።
መልዕክተ ፀሐይ
‹‹ ማንም ሴት ሥራዬ ብላ ከሰራች የጾታ እንጂ ሌላ ከወንድ የሚለያት ምንም ነገር አይኖርም። ለዚህም እኔ ምሳሌ ነኝ። ነፍሰጡር ካልሆንኩ በስተቀር ከወንዶች በጉልበት እንበላለጣለን ብዬ አላምንም። ብዙ ጊዜ ወንድ የማያነሳውን፤ የማይሞክረውን በብልሀት አግዤ አደርገዋለሁ። ስለዚህ ሁሌም እኩል ነኝ ብዬ አምናለሁ። እናም ሴቶች እንደማያንሱ ራሳቸውን ማሳመንና ወደተግባር መግባት አለባቸው›› የመጀ መሪያ ምክራቸው ነው።
ብዙ ወንዶችን በሹፍርና የማስተማርና የመምከር ደረጃ ላይ ያደረሳቸው ልምዳቸውና ብልሃታቸው እንደሆነ የሚገልጹት ባለታሪኳ፤ ማንም ወንድ ከሴቶች እኩል ጥበበኛ መሆን አይችልም። እናም ያለንን አቅም በተግባር ማዋል ይገባል። የሰው ልጅ የሚሞተው በረሃ ስላቋረጠ፤ ከባድ የሚባለውን ሥራ ስለሰራ፤ አደጋ ስለደረሰበት ወዘተ ብቻ አይደለም። ትንታ፣ እንቅፋትም ሊገሉት እንደሚችሉ ግልጽ ነው። እናም ይህንን አስቦ መስራትም ያስፈልጋል።
የስራ ፍራቻ ፣ አልችልም ባይነት በተለይ ከሴቶች አዕምሮ ውስጥ መወገድ እንዳለበት አበክረው የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሐይ፤ እናደርጋለን፣ እንሄዳለን፣ እንመለሳለንም ብሎ አምኖ መጓዝ ይገባል። የሰላሙን ጉዳይ ለአምላክ ሰጥቶ ከዚያ ውጪ መስራት ፣ መስራት ብቻ የሚለውን መርህ መከተል ልምድ ይሁን ይላሉ።
‹‹የማልደርስበት ነገር የለም ብሎ ጥሶ መውጣትን ከእኔ ቢወስዱ ደስ ይለኛል›› ያሉን እንግዳችን፤ ሀይማኖቱም ሆነ ባህሉ ገድቦ ቢይዘንም ይህንን በጥበብ ማሸነፍ ይቻላልና አድርጉት። ወንድም ሆነ ሴት በቀጥታ ለስኬት አያበቃምና ለማሸነፍ መታገል የሚለውን መርሄ ቢተገበር ደስ ይለኛል የሚለው የማሳረጊያ መልዕክታቸው ነው። እኛም ምክራቸው ለሁሉም ይጠቅማልና ጠለቅ ብለን እንመርምረው በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2012
ጽጌረዳ ጫንያለው