የገጠር ህይወቱ ከልጅነት እስከ ወጣትነት ዕድሜ አላዘለቀውም። በጠዋቱ የጀመረው ትምህርትም ቢሆን ከአምስተኛ ክፍል ሳይሻገር ባለበት ሊቋጭ ግድ ነበር። የቤተሰቦቹን ፍቅር ሳይጠግብ ቀዬውን ጥሎ ሲወጣ በዕድሜው እምብዛም የበሰለ አልነበረም። በስራ ፍለጋ ሰበብ ያጠፋውን ጊዜ ጨምሮ ጥቂት ለማይባል ጊዜ በብዙ ስፍራዎች ቆይቷል። ራሱን ለመቻል ያደረገው ጥረት ተሳክቶም የላቡ ወዝ ያስገኘለትን ገንዘብ አንድ ሁለት ብሎ ለመቁጠር ታድሏል።
ዲታሞ አፍላ ወጣት መሆን ሲጀምር ጆሮዎቹን የሚስቡ ጉዳዮች በረከቱ። እኩዮቹ ከተማ ዘልቀው የተሻለ ህይወት መኖራቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ከነዚህ መሀል የበረቱ ጥቂቶችም አቅማቸውን አደራጅተው ወደ አገር ቤት ገብተዋል። ከፊሎቹም ባሉበት ሆነው ለቤተሰብ የሚሹትን ይልካሉ። ይህን የሚያውቁ በርካቶችም በነሱ መንገድ ተከትለው የልባቸውን አድርሰዋል።
ዲታሞ ወላይታን መልቀቁ ካልቀረ ስም ያለው ተግባር መፈጸም እንዳለበት ካሰበበት ቆይቷል።ለዚህ ስሜቱ የልቡን የሞላለት ደግሞ ከሌሎች እኩዮቹ ለየት የሚል ሀሳብ ሆነ። ከነበረበት ርቆ ራሱን ጦላይ ውትድርና ማሰልጠኛ ባገኘው ጊዜም በውሳኔው ደስተኛ ሆኖ ዘለቀ።
የስልጠናው ክብደት፣ ውጣውረድና ልፋቱ ቀላል አልነበረም።ነገን ብቁ ወታደር ሆኖ ዘብ ለሚቆም ወጣት ግን ይህ ሁሉ የሚጠበቅ ነበር።ዲታሞም ቢሆን በስፍራው ያለውን ግዴታ ለመቀበል ትከሻው ሰፊ ነበር።ከስልጠናው በኋላ ለሚጠብቀው ሀገራዊ ግዴታ ከማሰብ ባሻገር ነገን የተሻለ ሆኖ ለመታየት ሲለፋ ቆይቷል።
ስልጠናው እንዳበቃ ዲታሞ ወደ ትግራይ ተጓዘ። ወታደር ሆኖ ደመወዝ እያገኘም በሙያው ማገልገል ቀጠለ።አካባቢውን ሲላመድና ግዴታውን መወጣት ሲጀምር ለኪሱ ገንዘብ አላጣም።ውሎ ሲያድር ሁኔታው ባይመቸውም በጀመረው ለመቀጠል ከራሱ ጋር ትግል ሲገጥም ቆይቷል።
አሁን ወጣቱ የወታደርነት ስራው ካሰበው በላይ ከብዶታል።ከትውልድ አገሩ መራቁና ለጥብቅ ህጎች መገዛቱም የተመቸው አይመስልም። በቆመበት ሙያ የሚወጡ መመሪያዎችና ግዴታዎች ሁሉ ትናንት ሲያስበው ከነበረው ዕቅድ ጋር የሚራመዱ አልሆኑም።እናም ጠዋት ማታ መሳሪያውን ተደግፎ ስለነገው ያስባል።
የወጣቱ አርቆ አሳቢ ልብ አንድ ቀን ከውሳኔ አደረሰው።ተቀጥሮ ደመወዝ የሚበላበት የውትድርና ሙያ ከማንነቱ ጋር የሚዘልቅ አለመሆኑን ከተረዳው ቆይቷልና ውስጡ ቆረጠ።በድንገት ማመልከቻ ጽፎ ስራውን በገዛ ፈቃዱ ስለመልቀቁ ለክፍሉ አስታወቀ። ህግና መመሪያው በሚፈቅደው መንገድም ከነበረበት ክፍል ተሰናበተ።ከስንብቱ በኋላ ዲታሞ ወደ ትውልድ ሀገሩ ወላይታ አቀና። ከስፍራው ሲደርስ የሚያውቃቸው እኩዮቹ ከመንደሩ አልነበሩም። በርካቶቹ እንጀራ ፍለጋ በየቦታው ተበትነዋል።
ጥቂት ጊዜያትን በሀሳብ ሲናውዝ የቆየው ወጣት ከቀናት በኋላ የአሳ መረቡን ይዞ ወደ ኦሞ ወንዝ ወረደ።በወንዙ ላይ አሳ እያሳገረ ለመሸጥም ከሌሎች ጋር ተደራጀ።እንዳሰበው ሆኖ አሁንም ለኪሱ የሚሆን ገቢ አላጣም።ውሎ ሲያድር ግን የሚያገኘው በቂ አለመሆኑ ገባው።
ከውትድርና መልስ አሳ አስጋሪ የሆነው ዲታሞ በጀመረው ስራ መቀጠሉ አስጠላው።ውሎው፣ የልብሱ ጠረንና የሚያገኘው ገንዘብ አለመመጣጠን ያሳስበው ያዘ።ይህን ደጋግሞ ማሰቡ ደግሞ አሁንም ከሌላ ውሳኔ አደረሰው።የጀመረውን ትቶ ከሌላ ከተማ ከሚገኝ የጥጥ ፋብሪካ በጉልበት ስራ ተቀጠረ።
የዲታሞ የህይወት ጉዞ ቀጥሏል።በከባድ የስራ ልፋት የሚደክመው አካሉ ዝሎ ምሽቱ ሲደርስ ከቤቱ ይገባል። አሁን ላይ ግን ካለፉት ጊዜያት በከፋ መልኩ መማረሩን አልተወም።በጉልበት ስራ የሚያገኘው ክፍያ ከድካሙ ጋር የሚመጥን አልሆነም። አሁንም ይህን ሲያስብ ልቡ ርቆ መሻገር ይዟል።
አንድ ቀን ዲታሞ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወስኖ ጓዙን አነሳ።በስፍራው በርካታ የአገሩ ልጆች እንጀራ እንደወጣላቸው ያውቃል።እሱም በነሱ መንገድ ቢከተል ያሰበውን እንደሚሞላ እርግጠኛ መሆን ከጀመረ ቆይቷል።
አዲስ አበባ ሲገባ መኖሪያው ኮተቤ አካባቢ ሆነ። ስፍራውን ከልቡ ወደደው። የአካባቢው ድምቀትና የነዋሪው ብዛት ግራ አላጋባውም። በእንግድነት ተቀብሎ ያስጠጋው ዘመዱ ከቀናት በኋላ ከተማውን አላምዶ የሊስትሮ ዕቃ አሰጨበጠው። ዲታሞ በአዲስ አበባ ውሎ ሲያድር ሌሎች የአገሩ ልጆችን አገኘ።እንደሱ ጫማ የሚጠርጉትን ጨምሮ በሌላ ስራ የሚውሉትን እየፈለገም ገንዘብ ማግኘት የሚችልባቸውን ዕቅዶች አማረጠ።
የወላይታው ወጣት በአዲስ አበባ ሊስትሮ ከሆነ ወዲህ በርካቶችን ተዋወቀ።ጥቂት የማይባሉ ደንበኞችን አፍርቶም ከብዙዎች ተወዳጀ። መውጫ መግቢያውን ጠንቅቆ ባወቀ ጊዜም ስፍራ እየቀየረ መዋያዎቹን አፈራረቀ።ይህ አጋጣሚ የፈጠረለት ትውውቅም ምልከታውን እያሰፋ አማራጮቹን አመቻቸለት።
ዲታሞ በሊስትሮነት የተዋወቃትን አዲስ አበባ ከእግር እስከራሷ ለይቷታል።አብረውት ውለው ከሚያድሩ ባልንጀሮቹ ጋር በቅርቡ የጀመረው አዲስ ስራም የገንዘብ ኪሱን ከመሙላት አልፎ ያሻውን ሁሉ እንዲፈጽም እየረዳው ነው።
አሁን እንደትናንቱ ከገንዘብ ጋር መነፋፈቅ ካቆመ ሰንብቷል። መሸት ሲል እንደዋዛ ይዞት የሚገባው ረብጣ ከዕለት ዕለት እየጣመው ነው። ዲታሞና ጓደኞቹ በስራ ደክሞ መዋልን እንደ ነውር ከቆጠሩት ሰንብተዋል።ምሽቱን ተግነው የሚፈጽሙት ንጥቂያ የሚያስገኝላቸው ሲሳይም ለሱስና ለመዝናናት ፍላጎታቸው ውሎ ሌሎችን መሳብና መማረክ ይዘዋል።
ዲታሞ ከውትድርና አቋሙ ያተረፈው ብቃት ነጥቆ ለመሮጥና ፈጥኖ ለማምለጥ እያገዘው ነው። አንዳንዴ መረጃና ጥቆማው በጠበቀ ጊዜ በንጥቂያ ወንጀል ተከሶ ለአጫጭር እስር ይዳረጋል።ባስ ያለ ድርጊት መፈጸሙ ሲረጋገጥም የዓመታት ውሳኔ ተፈርዶበት ከማረሚያ ቤት ይገባል። እስሩን አጠናቆ ሲወጣ ግን በመንገዱ ለመመለስ ጊዜ አይፈጅበትም።
ሁሌም ቢሆን ዲታሞ የዝርፊያ ድርጊቱን ለመፈጸም ረዳቶችን ይፈልጋል።ከሚያገኘው ገቢ ጥቂቱን ወርውሮም የበዛውን ድርሻ ለእሱ ማስቀረቱን ለምዷል።ከእሱ ጋር ከሚቆሙት መሀል ብዙዎቹ ሊስትሮዎች ናቸው። የሚያገኙት ጥቂት ቢሆንም ገቢውን ማጣት አይፈልጉም። እናም በሀሳቡ ተስማምተው ለዝርፊያው ይተባበራሉ።
ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም
የኮተቤን አካባቢ በሊስትሮነት ከሚያዘወትሩ ወጣቶች መካከል መስፍን ኮይሻ አንዱ ነው።መስፍን ካገሩ ከመጣ ጀምሮ ስፍራውን ለስራ መርጦ በርካታ ደንበኞችን አፍርቷል። አንዳንዴ ከዲታሞ ጋር ይገናኛሉ። ዲታሞ የአገሩ ልጅ በመሆኑ ከሌሎች በተለየ ይቀርበዋል።እሱን ለማግኘት በመጣ ጊዜም ገለል ያለ ስፍራ መርጠው የልባቸውን ያወጉና ይስማማሉ።
በዚህ ቀን በስፍራው ድንገት የደረሰውን ዲታሞን መስፍን ባየው ጊዜ ዓይኖቹ ፈጠጡ። ያለምክንያት ወደ እሱ እንደማይመጣ ያውቃልና የያዘውን እስኪጨርስ ተጣደፈ። ወዲያው የሊስትሮ ዕቃውን ከአንድ ጥግ አስቀምጦ ዲታሞ ወዳለበት ተጠጋ።
ዲታሞ ለመስፍን የተለመደውን ሰላምታ እንዳ ደረሰ ወዲያውኑ ወደ ጉዳዩ ገባ። በተለየ ጉጉት የሚያዳምጠው ሊስትሮ የሚለውን ሁሉ ከሰማ በኋላ የስራ መመሪያውን ጠበቀ። ዲታሞ የዕለቱ የንጥቂያ አቅጣጫ ሾላ አካባቢ እንደሚሆን አስረዳ።አያይዞም ከእነሱ ጋር ሌላ አጋዥ እንደሚኖርና እንደተለመደው ቅልጥፍናና ፈጣን ሩጫ ግድ እንደሚል አከለበት።
ምሽት 3፡00 ሰዓት
ሁለቱ ያገር ልጆች በታሰበው ሰዓትና ቦታ ላይ ለመገኘት መንገዳቸውን ይዘዋል።ሶስተኛውን አጋራቸውን ለማስከተል ወደ ቤቱ አምርተውም ዲታሞ እንደተለመደው የንጥቂያ ስልቱንና የሚጠበቅባቸውን ግዴታ አስረድቶ ጨርሷል።
አሁን ለምሽቱ ከታሰበው የሾላ ሰፈርና አካባቢው የጨለማ መንገድ መርጠው ማድፈጥ ከጀመሩ ደቂቃዎች ተቆጥረዋል።እስካሁን በአይናቸው የሚገባ መንገደኛ ዝር ያለማለቱ እያስገረማቸው ነው።ያሰቡት ሆኖ ዕቅዳቸው የማይሰምር ከሆነ ደግሞ ቦታ ቀይረው ዕድላቸውን ሊሞክሩ ተስማምተው ጨርሰዋል።
በድንገት ሁለት መንገደኞች በርቀት መታየት ጀመሩ። ቀረብ ሲሉም ወንድና ሴት መሆናቸውን አወቁ። ሁለቱ የጨለማ ተጓዦች እጅ ለእጅ ተጣምረው የልብ ጨዋታ ይዘዋል። በፍቅር አብሮነት የተሞላው ስሜታቸው ሌሎችን የሚያስተውል አይመስልም።እየሳቁ፣እየተያዩና ቆም እያሉ የቀስታ መንገዳቸው ያዘግማሉ።
ሶስቱ የጨለማ አድፋጮች የመንገደቹ ሁኔታ ተመችቷቸው መቁነጥነጥ ጀምረዋል።ሁኔታቸው ለከፋ ትግልና ትኩረት እንደማይጥላቸው ገብቷቸው ጉዳያቸውን በድንጋይ ብቻ መጨረስ እንዳለባቸው ተስማምተዋል።
የምሽቱ ጥንዶች እነሱ ወደሚገኙበትና ወደተጠ መደላቸው ክልል ሰተት ብለው ገብተዋል።ይህ መሆኑን ያረጋገጠው ዲታሞ ፈጥኖ ከጨለማው ወጣ። በእጁ ከእግረኞች መንገድ የተፈነቀለ ትልቅና ጌጠኛ ድንጋይ ጨብጧል።ሌሎቹ ከኋላው አጅበው ተከተሉት።ሁኔታውን ያስተዋሉት መንገደኞች በድን ጋጤ መራመድ ጀመሩ።ጊዜ አልሰጣቸውም የያዘውን ድንጋይ በወንዱ ጭንቅላት ላይ አሳረፈው።
መንገደኛው ፊቱ በደም እንደተሸፈነ ተንገ ዳግዶ በቁሙ ወደቀ።ይህን ያስተዋለችው ወጣት በድንጋጤ እየጮኸች ወደወደቀው ወጣት ተንደ ረደረች። መስፍንና ሌላው አጋሩ ግን በደረቷ ከያዘችው ተንጠልጣይ ቦርሳ ላይ አተኮሩ። ወዲያው አንደኛው ከአንገቷ ላይ በጥሶ ለሌላው በማቀበል ወደ ጨለማው ተፈተለኩ። ዲታሞ በቀስታ ርምጃ ከኋላቸው ተከትሎ ደረሰባቸው።
ከጨለማው መንገድ ራቅ እንዳሉ የልጅቷን ቦርሳ ከፍተው መፈተሽ ጀመሩ።በውስጡ ያገኙትን ለይተውም ለዲታሞ አስረከቡ። ዲታሞ በቦርሳው ሁለት ሞባይሎችንና ሁለት መቶ ሀምሳ ብር መኖሩን አረጋገጠ።ከገንዘቡ መሀል ሰባ ብር ቆጥሮም ለሊስትሮው መስፍን ሰጠ።
አብሮት ያለው ባልንጀራው አንዱን ሞባይል በተለየ ፍቅር እያስተዋለ እሱ እንደሚጠቀምበትና ቀሪው ግን ተሸጦ ገንዘቡን በእኩል እንደሚካፈሉት አሳወቀ።ምርጫ ያልነበረው ሊስትሮ በተባለው ሀሳብ ተስማምቶ ሰባ ብሩን ኪሱ አኖረ።ሁለቱን ተሰናብቶም በጨለማው አቋርጦ ወደ ማደሪያው ገሰገሰ።
በማግስቱ ሊስትሮው መስፍን ከሞባይሉ ሽያጭ ይገኛል የተባለው ገንዘብ የውሀ ሽታ ቢሆንበት ሲያሳስበው ዋለ።ዲታሞ ስልኩን አጥፍቶ ለቀናት መጥፋቱ እያበሸቀውም ወደ ጫማ ጠረጋው ተመለሰ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በምሽቱ የደረሰውን የስልክ ጥሪ ይዞ በስፍራው ደረሰ።ከአንዲት ሴት ጋር በጨለማ ሲጓዝ የነበረ ወጣት ህይወት እንዳለፈ ባወቀ ጊዜም አስፈላጊውን ምርመራ አጠናቆ አስከሬኑን ከስፍራው አነሳ።በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 991/09 የተመዘገበው የወንጀል ድርጊት በመርማሪ ዋና ሳጂን መስፍን ሀብተሚካኤል አየተመራ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትሉን ቀጠለ። በዕለቱ ከሟች ጋር አብራ የነበረችውን ወጣት ለምርመራ ይዞም ዘረፋና ግድያ የፈጸሙትን በቁጥጥር ስር ለማዋል አሰሳውን ቀጠለ።
ፖሊስ ተደጋጋሚ ወንጀል ፈጻሚዎችን አድኖ ለመያዝ ባደረገው ጥረት አንድ ቀን ኮተቤ 32 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ ደርሶ በሁለት ሰዎች ላይ አነጣጠረ። ሰዎቹ ዲታሞና መስፍን ሊስትሮው ናቸው።ዲታሞ ጠፍቶ የቆየበትን ጉዳይ ለመስፍን እያስረዳ ነበር። በተመሳሳይ ድርጊት ተይዞ ጣቢያ በመታሰሩም የሚገባውን ድርሻ እንዳልሰጠውና በዛሬ ምሽቱ ቅሚያ ግን ሊክሰው እንዳሰበ እየነገረው ነው።ፖሊስ ሀሳቡን አላስጨረሰውም ከነግብረአበሩ ይዞና ካቴና አጥልቆ ወደ ጣቢያ አደረሰው።
ውሳኔ
በፖሊስ፣ በዓቃቤ ህግ ምርመራና በተገቢው መረጃና ማስረጃዎች ሰነዱ ተመርምሮ የቀረበለት ፍርድ ቤት በከባድ የውንብድና ወንጀል የሰው ህይወትን ባጠፉ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል።የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎትም አጥፊዎቹንና ሌሎችን ያስተምራል ያለውን የ18 ዓመት ጽኑ እስራት በእያንዳንዳቸው ላይ ወስኖ መዝገቡን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
መልካምስራ አፈወርቅ