የተወለዱት በሸዋ ክፍለሃገር በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ሞረትና ጅሩ ወረዳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅሁር መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደብረብርሃን ከተማ ከሚገኘው ሃይለማርያም ማሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወሰደው ውጤት በመጠባበቅ ላይ ሳሉም እሳቸውና ሌሎች ጓደኞቻቸው የመላው አማራ ድርጅትን ተቀላቀሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካና አለም አቀፍ ግኑኝነት ትምህርት ክፍል ገብተው መማር ከጀመሩም በኋላም በድርጅቱ ውስጥ የሚደርጉትን እንቅስቃሴ አላቋረጡም። በዚህም የፖለቲካ ተሳትፎዋቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ለአራት ዓመት ከተከታተሉ በኋላ ለእስር ይዳረጋሉ። ከስምንት ዓመታት የወህኒ ቤት ቆይታ በኋላም ቢሆን በሀገሪቱ ፍትህ እንዲሰፍን በድፍረት መንግስትን በመናገራቸውና ትግላቸውን ባለማቋረጣቸው በተደጋጋሚ ታሰረዋል፤ እንግልትና የስነልቦና ጉዳትም ደርሶባቸዋል።
በድምሩ ለ12 ዓመታት 12 ጊዜ የታሰሩት እኚሁ የፖለቲካ ሰው ታዲያ ለህዝብ እኩልነት መስፈን ሲሉ ወህኒ ቤቶች መኖሪያቸው እንዲሆን ተገደዱ፤ የሰው ልጅ ሊደርስበት የማይገባ መከራ አሳለፉ፤ ዋጋም ከፈሉ። በእውነትና በአገር ተስፋ ቆርጠው እኚህ ብርቱ ሰው ታስረው በተፈቱባቸው አጋጣሚዎቹ ሁሉ እየጀመሩ፤ እያቋረጡ፤ ደግሞም እየቀጠሉ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ፤ እንዲሁም ማርክቲንግ ማኔጅመንት ዲፕሎማ እና በሊደርሺፕ ሰርተፍኬት ማግኘት ችለዋል። በአገሪቱ በ2010 ዓ.ም የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከተፈቱት ፖለቲከኞች አንዱ ሆኑ። አሁን ላይ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዳግም በማደራጀት ፕሬዚዳንት ሆነው በመምራት ላይ ይገኛሉ። አቶ ማሙሸት አማረ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። ከእንግዳችን ጋር በፖለቲካ ህይወታቸውና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያሉ የታሰሩበት ምክንያት ምንድን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ማሙሸት፡- በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደእኔ ያለ በተቋውሞ ጎራ የተሰለፈን ሰው እንግዳ ማድረጉ በጣም እንዳስደነቀኝ ልገልጽልሽ እወዳለሁ። ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ አዲስ ዘመን እንኳን ወደ እኛ መጥቶ ሃሳባችንን ሊጠይቅ ቀርቶ የምንሰጠውንም መግለጫ ሽፋን አይሰጥም ነበርና ነው። በመቀጠል ግን ጋዜጣው የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን እኛ የምንሰጠው ሃሳብና በፖለቲካው ዘርፍ የምናደርገው አስተዋፅኦ ለሕዝብና ለአገር ይጠቅማል ተብሎ ከታሰበ ትክክል ያልሆነውን ትክክል አይደለም በማለታችን እንደአጋዥ እንደወገን ተቆጥረን በፈለግነው ጊዜ ሁሉ ልንስተናገድ ይገባል። በተለይም ደግሞ ይህንን ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅመውን ሃሳብ የምንሸጠው በመገናኛ በዙሃና እንደመሆኑ የሁላችንም ሀብት የሆኑት አዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ቴሌቪዠን በእኩል መንፈስ ሊያገለግሉ እንደሚገባ ማስገንዘብ እወዳለሁ። በእኔ እምነት ለገዢው ፓርቲ በማዳላትና ህፀፁን በመሸፋፋን የሚጠቅመው ነገር የለም።እንዳውም መገናኛ ብዙሃን ከእኛ በበለጠ ይህንን መንግስት ቅርፅ ማስያዝ ይገባቸው ነበር። በመሆኑም ይህ ጅማሬያችሁ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ላሳስባችሁ እወዳለሁ።
ወደ ጠየቅሽኝ ጥያቄ ስገባ በ1984 ዓ.ም
ማትሪክ ተፈትነን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እያለን ነበር የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት የተመሰረተው። በዚያ የወጣትነት እድሚያችን ፓቲውን
ተቀላቅለን ተሳትፎ አደረግን። በወቅቱ ፓርቲውን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ነበሩ የሚመሩት። በወቅቱ ፓርቲው በብዙ ህዝብ ተቀባይነት
አግኝቶ ስለነበር
ኢህአዴግ ተቀናቃኝ መጣብኝ በሚል እንቅስቃሴያችንን አልወደደውም። በመሆኑም እኛን ማሰርና ማሳደድ ጀመረ። በመላው አገሪቱ የነበሩንን ጽህፈት ቤቶች መዝጋት አመጣ። እኛ ደግሞ ይህንን ጫና አንቀበልም ብለን አመጽን። በርካታ ወጣቶች የአማራ ልጆች ሽፍቶች ናቸው እየተባሉ ደብረብረሃን፤ ጠባሴ ጦር ካምፕ፣ ሸዋሮቢት፣ ሰላ ድንጋይ፣ ሞረትና ጅሩ፣ መሃል ሜዳ አምስት ሺ የሚሆኑ የአማራ ልጆች እስር ቤት ገቡ። እኛንም ጨምሮ ማሳደድና ማሰር ሲጀምሩ አሻፈረን ብለን አምጸን ወደ ትጥቅ ትግል ገባን። በ1986 ዓ.ም ደግሞ ፕሮፌሰር አስራትም ታሰሩ። እኛም ከወታደር ጋር ገጥመን ደብረብርሃንና ሰላ ድንጋይ እስር ቤት የነበሩ እስረኞችን አስለቀቅን። የተወሰንነው ተያዝን፣ የተወሰኑት ሞቱ።
እኛም በዚያ ምክንያት መንግስትን በሃይል ለመጣል በሚል ተከሰንና ተፈረዶብን።ይሁንና የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ አላገኙም። በዚያ ምክንያት እኔና ጓደኞቼ ጠባሴ ጦር ካምፕ በመቀጠልም ማእከላዊ ታሰርን። በነገራችን ላይ ማዕከላዊ ደርግ ከወጣ በኋላ በእኛ ነው የተጀመረው። ከዚያም ተፈርዶብኝ በከርቸሌ እስር ቤት ለስምንት ዓመታት ያህል በእስር ቆይቻለሁ። ምንም አይነት አመክሮ ተከልክዬ ስምንቱንም ዓመት ጨርሼ ነው የወጣሁት። ከወጣን በኋላ መአአድን ነው የተቀላቀልነው።ተመልሰን ሰላማዊ ትግሉን እንደገና ጀመርን። ከዚያ በኋላም በየጊዜው እስር ነበር። በጥቅሉ አሸባሪ ተብዬ 2009 ዓ.ም እስከምታሰር ድረስ 12 ጊዜ በዚህ መንግስት ታስሪያለሁ። በቅንጅት ጊዜም እድሜ ልክ እስረኛ ነበርኩ። ከዚያ በኋላ እንግዲህ 2007 ዓ.ም አይ. ኤስ.. ኤስ ተብዩ ታስሪያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከኤይ. ኤስ. ኤስ ጋር ግኑኝነት አሎዎት በሚል ነው?
አቶ ማሙሸት፡- በወቅቱ እነዚያ ዜጎቻችን በሊቢያ ሲታረዱ ኢትዮጵያ መልካም መሪ ቢኖራት ኖሮ ይህ ድርጊት አይፈጸምም ነበር ብዬ ሃሳቤን በመግለፄ የአይ. ኤስ. ኤስ አባሪ ነው ተብዩ ከርቸሌ፤ ማዕከላዊ፤ አዲስ አበባ ፖሊስ፤ አምቼ ፖሊስ ፤ቂሊንጦ፤ እያዘዋወሩ ለስድሰት ወራት አስረውኛል። በመጨረሻ በቀረብኩባቸው ሁለቱም ፍርድ ቤቶች ነጻ ተባልኩኝ። ይሁንና ከዚያው ፍርድ ቤት አፍነው አምጥተው አዲስ አበባ ፖሊስ አሰገቡኝ። ቀጠሉናም እንደገና ማዕከላዊ አሰገቡኝ። እንደገና አራዳ ፍርድ ቤት አቀረቡኝ። በዚያን ጊዜም ስምንት ደህንነቶች ናቸው ምስክር ሆነው የቀረቡብኝ። ስምንቱነም ተከራክሬ ደህነት መሆናቸውን፤ ሃሰተኞች መሆናቸውን ፤ መታወቂያ የሌላቸው መሆናቸውን በፍርድ ቤት ተራ በታራ ተካራክሬ አሸነፍኳቸው።ይሁንና ፍርድ ቤት ነጻ ካለኝ በኋላ ለ15 ቀናት ቅሊንጦ እንደገና አሰረኝ።
አዲስ ዘመን፡- ምክንያታቸው ምን ነበር?
አቶ ማሙሸት፡- ምንም ምክንያት አልነበራቸውም፤ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ እንድለቀቅ አልተፈቀደም ነበር ያሉኝ። ከዚያ በኋላም እንግዲህ በደህንነቱ ቁጥጥር ስር ሆንኩኝ። እንደገና ደግሞ 2008 ዓ.ም ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ግኑኝንት አለህ፤ ጦር ትልካለህ፤ ደብረብርሃን ላይ ሁለት የጦር ማሰልጠነኛ ከፍታሃል፤ ወታደር መልምለህ ወደ ኤርትራ ትልካለህ፤ ከግንቦት ሰባት አመራር ጋር ግንኙነት አለህ፤ ጎንደር፥ ጃኖራ፥ ሳንጃ፥ጋይንት፥ አርማጨሆ፥ ደብረታቦር፥ ሳይንት፥ ባህርዳርና በአንዳንድ ኦሮሚያ ክልል ከተሞች የነበሩትን አመጾች በመሪነት ተሳትፈሃል የሚል የሃሰት ክስ ቀረበብኝ። የሚገርምሽ ይሄ ሁሉ ሲሆን ደግሞ ብቻዩን ነው። አንድ ደህንነት ቁጭ በሎ በጻፈው የሃሰት ክስ በእድሜ ልክ በሚያስቀጣ አንቀፅ ተከስሼ ደግሞ ማዕከላዊ ገባሁ።
አዲስ ዘመን፡- በነዚህ ሁሉ ክሶች በአንዱም ማስረጃ አልተገኘብዎትም?
አቶ ማሙሸት፡- ምንም ወስጥ አልነበርኩበትም፤ ከሻቢያ ጋር ግኑኝነት ሊኖረኝ ቀርቶ በጣም ነው የምጠላቸው የኤርትራንና የኢትዮጵያን ህዝብ ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረጉት ሻቢያና ወያኔ እንዲሁም ኦነግ ናቸው ብዩ ስለማምን በተከታታይ ተቃውሜአቸዋለው፤ ግንቦት ሰባትን በሚመለከት ቢሆን ተጣልተን ነው ከዶክተር ብርሃኑ ጋር የተለያየነው። ማጭበርበር ካልሆነ በስተቀር አሜሪካ ተቀምጠህ ሁሉን አቀፍ ትግል ልታደርግ አትችልም፤ ይልቁኑ እዚሁ መጥተህ ጫካ ግባ በሚል ተቃውሜው ከዚያ ወዲህ ፀብ ነን። ስለዚህ እኔን ለመጉዳት ብቻ ስለተፈለገ የማላውቃቸውን የጎንደር አካባቢዎች ተጠቅሰው በክሱ ላይ እንዲካተት ተደርጓል። አንድም ሰውም የሰነድም ማስረጃ የለውም። ከእኔ ጋር አብሮ የሚሰራ ሰዎ አልነበረም። ዳኛውን ሳይቀር ከሱን አስቀደሞ የሚያስጠይቅ ስለመሆኑ ማጣራት እንደሚገባው ብዙ ተከራከሩኩት። ያው ዳኞቹ ካድሬዎች ስለነበሩ በእናንተ አልዳኝም ብዩ ተጨቃጨኩኝ። በዚያው ጭቅጭቅ ላይ እያለን ዳኞቹ ቶሎ ሊፈረዱብኝ ቸኩለው ነበር። እኔ ግን እናንተ ዳኞች ስላልሆናቸሁ በእናንተ አልዳኝም አልኳቸው።
ምክንያቱም አስማት ካልሆነ በስተቀር አንድ ሰው የፈለገ ያጠፋል ቢባል ይህን ሁሉ ሊያደርግ አይችልም። ይህንን ክስ የጻፈው ሰው ይህንን መንግስት አይጠቅምም፤ ለእናንተም የሚመጥን አይደለም፤ እኔም ነጻ ሰው ነኝ አልኳቸው። ከዚህ ቀደም በሰራሁት ከሆነ ህግ ወደ ኋላ ሄዶ አይሰራም ብዬ ተሟገትኳቸው። እነሱም ችሎት በመድፈር እንከስሃለን በማለት ያስፈራሩኝ ነበር። እኔ ግን ሞት የሚያሰቀጣ ክስ ከሳችሁኝ እያለ ችሎት ብደፍር ምን ይገርማል? ይልቁኑ እናንተ የእውነት ዳኛ ሁኑ፤ ዝም ብሎ ካባ መልበስ ዳኛ አያደርግም፤ የምታገለው እናንተንም ጭምር ነጻ ለማውጣት ነው። ፍትህ በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ነው አልኳቸው። ለራሴማ ቢሆን የሚሰጡኝን ጥቅማጥቅም ይዤ መኖር እችል ነበር የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው። በመጨረሻ እንግዲህ የወጣቱ ትግል እያየለ ሲመጣ ከእስር ቤት እንድንወጣ ተደረግን።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች በተደጋጋሚ ለእስር የመዳረጉዎ ምክንያት ግትር የሚባል ባህሪ ስላሎዎ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ባህሪ እርሶን ይገልጾታል?
አቶ ማሙሸት፡- ምን አልባት ስለእኔ ባህሪ ብነግርሽ ላታምኚኝ ትቺያለሽ፤ እኔ በእውነት ብቻ መኖር የምፈልግ ሰው ነኝ። ስልጣንም ሆነ ንዋይ እኔን አይገዛኝም። በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ድረስ እንስጥህ ተብዬ የተለመንኩ ሰው ነኝ። አብረን እንሰራ እባክህ አትረብሸን ተብያለሁ። ለእኔ ለአንድ ድሃ የገበሬ ልጅ ሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ትልቅ ነው። እውነት ለመናገር ለቦታው አልመጥንም። እኔ በዙ የማውቅና የተማርኩ ሰውም አይደለሁም። እንኳን ሚኒስትርነት አንድ የቀበሌ አስተዳዳሪ ሆኜ፤ የራሴ ገቢ ኖሮኝ ብኖር ደስ ይለኛል። ግን አሰራሩ ትከክል አይደለም። እኔ ያደኩት አትዋሽ፤ አትስረቅ ከሚል ማህበረሰብ ውስጥ ነው። በእርግጥ የትኛውም የኢትዮጵያ ወላጅ አትሰረቅ አትዋሸ እያለ ነው ልጆቹን የሚያሳድገው።
አሁን ዝም ብዬ ተነስቼ ጭንቅላቴ የማያምንበትን፤ የማልችለውን ስልጣን ተሸክሜ፤ ህዝብን ማገልገል የማልችልበት ወንበር ላይ ተቀምጬ ህዝብን ከምበድል እየተራብኩ እየተጠማሁ ትክክል ያልሆኑ ጉዳዮችን እንዲስተካከሉ መንገዱን ባሳይ ይሻላል ብዬ ምርጫውን ወስጃለሁ። እኔ ግትር አይደለሁም፤ ለውይይት ክፍት ነኝ የሚያሳምነኝ ካለ በሃሳብ የሚያሸንፈኝ ካለ ለመቀበል አስር ደቂቃ አይፈጅብኝም። ግን የማልቀበለውን ነገር ሰው በግድ እንድቅበለው እንዲያስገድደኝ አልፈቅድም። ተመልሼ የሚደርስብኝን ሁሉ ለመቀበል እዘጋጃለሁ እንጂ እኔን ማስገደድ አይቻልም።እስካሁንም አልተቻለም። 12 ዓመት ሙሉ ስታሰር አንድቀንም ከአገሬ ለመውጣት አስቤ አላውቅም። የእኔ ጓደኞች እስርና እንግልቱን ፈርተው አውሮፓና አሜሪካ ነው ያሉት። በእርግጥ ይደርስ የነበረውን ግፍና መከራ ተቋቁሞ ለመቆየት ፅናት ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛውን ጊዜዎትን በእስር በማሳለፍዎት እንደሰው አጥቼዋለሁ የሚሉት ነገር የለም?
አቶ ማሙሸት፡- እኔ እንደግለሰብ ያጣሁበት ብዙ ነገር ነው። መማር ሲገባኝ አለመማሬ ይቆጨኛል። ብዙ ጊዜ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርቴን አቋርጠውብኛል። እስካሁንም ያልጨረስኩት ትምህርት አለ። ሌላው በማህበራዊ ህይወቴም ምንም አላፈራሁም ማለት እችላለሁ። እንደሰው ሚስት አግብቼ ልጅ አልወለደኩም። የእኔ የምለው ነገር ምንም የለኝም። አሁን ወደ 46 ዓመት ሊሆነኝ ነው። በዚህ እድሜዬ ከህትና ከወንድሞቼ ጋር ነው የምኖረው። እነሱ በሚሰጡኝ ነው የምተዳደረው። ሌላው በጣም ከሚቆጨኝ ነገሮች አንዱ ሀገርን መለወጥ የሚችሉ ብዙ ወጣቶች ከእኔ ጋር ተሰልፈው መርገፋቸው ነው።
በተለይም በጣም የማከብራቸው በብዙ ህዝብ ዘንድ ብዙ ያልተባለላቸው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በሃሰት ለሀገር የሚጠቅም እውቀት እያላቸው ሲመክሩ ምክራቸው ተቀባይነት አጥቶ እሳቸው ባከሙበት አገር፤ ቆመው ባሰሩት ሆስፒታል እንኳን ህክምና አጥተው ተከልክለው በእስር ቤት ውስጥ ቆይተው በመጨረሻ ከአገራቸው ውጭ መሞታቸው እስካሁን የሚያንገበግበኝ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ከእሳቸው ጋር ብዙ ነገር አሳልፊያለሁ፤ አላጠፉም ነበር፤ ለሀገር የሚጠቅሙ ሰው ነበሩ፤ ምክራቸውን የሚሰማ አጥተው ነው ለሞት የተዳረጉት።እንደሰው ርህራሄ ተደርጎላቸው ቢታከሙና ህይወታቸው አልፎ ቢሆን ኖሮ አይቆጨኝም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እስር ላይ እያሉ ይህ በአገሪቱ ለውጥ ይመጣል ብለው አስበው ነበር?
አቶ ማሙሸት፡- እውነቱን ለመናገር ወንጀል ሰርቺያለሁ ብዬ ስለማላምን አንድ ቀን እንኳን እታሰራለሁ ብዬ አላውቅም ነበር። አገሪቱ ሆነ ህዝቦቿ በተሻለ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማሰብ ውጭ ስልጣንን ከመመኘት ሌሎችን ሰዎች ከመመቅኘት የተነሳሁበት አጋጣሚ የለም። የተናሳሁበት ዋነኛ አለማ ሁላችንም ኢትዮጵውያን በእኩል መንፈስ መኖር አለብን ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ከምንም በላይ የምሻውም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ህግና ፍትህ ሰፍኖ ማየት ነው። በተለይም በአሁኑ በእርግጠኝነት እንደምፈታም፤ ለውጥ እንደሚመጣ አውቅ ነበር። በእርግጥ ስልጣን ላይ ስትሆኚ አይታይሽም፤ ለእኛ ግን ይታየን ነበር።
እኛ በእስር ቤት ሆነን የአገሪቱ ፖለቲካ የት ሊደርስ እንደሚችል እንለካው ነበር። አሁን ያለው መንግስት የት ድርስ ሊጓዝ እንደሚችል እናውቅ ነበር። በየቤቱ ያለውንም ማጉረምረም፤ በየመስሪያ ቤቱ ያለው ሌብነትና ሙሰኝነት ስታዪ የአንድ አገር መንግስት ያለመኖር ምልክቶች እንደሆኑ ትረጃለሽ። ስልጣን ላይ ያለው አካል ግን ከወንበሩ እስከሚነሳ ድረስ አያውቀውም። እኛ ይህንን መክረናል። በነገራችን ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ ተጠይቄበታለሁ። ትልልቅ ባለስልጣናት፥ አይቻቸው ያማላውቃቸው ሰዎች እየተቀያየሩ እየመጡ ምክር ስጠን ይሉኝ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እስረኛ ሆነው ሳሉ እንዴት ነው ከእርሶ ምክር የሚጠበቀው?
አቶ ማሙሸት፡- እሱን እኮ ነው እኔም እስር ቤት ሆኜ ስቃወማቸው የነበረው። አንድ ጊዜ ማዕከላዊ እያለሁ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ሊጠይቁኝ መጡ። በነገራችን ላይ ማዕከላዊ ምርመራ የሚካሄደው ከሌሊቱ አራት ሰዓት ጀምሮ እስከ 10 ተኩል ድረስ ነው። በዚያን ጊዜ ታዲያ መርማሪዎቹ ጠጥተው ነው የሚመጡት። ሰክረው እንደፈለጋቸው ሆነው ነው የሚሆኑት። እናም ርህራሄም የማይኖራቸው ከዚህ አኳያ ነው። ሲጮህ፤ ሲያለቅስ እንዳይሰማችውና እንዳይራሩ ሰክረው ነው የሚመጡት። ያን ጊዜ ሰባት ሰዓት ከሌሊት ለምርመራ ሳይቤሪያ ከሚባለው ክፍል ወስደውኝ እነሱ ሲገቡ የታሰረ እጅና እግሬን ፈቱልኝ። እነዚያን ሰዎች ከዚህ ቀደም አይቻቸውም አላውቅም፤ በጣም የተመቻቸውና ውጭ የሚኖሩ ነው የሚመስሉት። እናም ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ነው ያለችውና እባክህ መግለጫ ስጥልን አሉኝ። እኔም ምን ብዬ አልኳቸው። እነሱም አሁን እንደ ድሮው የምንጓተትበት ሳይሆን አሁን አገር የማዳን ስራ አብረን እንስራ አሉኝ። ይህንንማ ከዚህ ቀደምም ጠይቃችሁኛል፤ እሱን አላደርገውም ብዬ ነው እንጂ ይህ ሁሉ እየደረሰብኝ ያለው ወንጀል ሰርቼ አይደለም እዚህ ያለሁት አልኳቸው።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እኔን ሃሳቤን በነፃነት እንዳልገልፅ አስራችሁኝ፤ ከመሬት በታች አስገብታችሁ የምሰጣችሁ ምክር እውነት ይሆናልስ ብላችሁ ትጠብቃላችሁ ወይ ? ብዬ ጠየኳቸው። የእናንተ አለቆች አገሪቱ የእኛ ብቻ ናት ብለው ይዘው አገር እያጠፉ ባሉበት ጊዜ እነሱን እረፉ ብትሏቸው፥ በየቦታው ያሰሯቸቸው ሁሉ ወንጀለኛ አይደለም ፍቱ ብትሏቸው የተሻለ ነው አልኳቸው። በነገራቸን ላይ በወቅቱ አገሪቱን የሚመራውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም በይፋ አልቻልክም ብዬዋለው። በአካልም ተገናኝተን አገር መምራት አትችልም ስላልኩት ነው የታሰርኩት። እናም ከዚህ ውጭ ሌላ የምሰጣችሁ ምክርም ሆነ የምሰራው አገር የማዳን ስራ የለም አልኳቸው በኋላም ሁኔታዬን ሲረዱ መበስበስ ትፈልጋለህ እንዴ? ዛሬ እንኳን አይበቃህም ወይ አሉኝ። እኔ አንድ ተራ ሰው ነኝ። ከመንግስት ጋር ታግዬ ምንም አላመጣም። ግን ሞቼም ቢሆን የምፈልገውን ነገር እስከማገኝ ድረስ አጥንቴም ቢሆን ይታገላችኋል አልኳቸው። ሱፍ ለብሰው ባዶ እጃቸውን የመጡት ሰዎች
ምላሼን ሲሰሙ መሳሪያዎቻቸውን አመጡ እጄም እንደገና ታሰረ። ከዚያ በኋላ ደግሞ «ትግሬን ትጠላለህ» እያሉ እስከ ሌሌት አስር ሰዓት ድረስ ይመረምሩኝ ጀመር። እኔ ግን ትግሬ አልጠላም ወገኖቼን እንዴት እጠላለው? የምጠላው ህወሓትን ነው አልኳቸው። ከዚያ ደግሞ «አከርካሪውን መተን የገደልነውን፤ የቀበርነው የአማራን ህዝብ የበላይነት እንድገና ልታመጣ ነው» አሉኝ። እሱም ቢሆን ትክክል አይደለም፤ የአማራን ህዝብ አልገደላችሁትም፤ አከርካሪውንም ልትመቱትም አትችሉም። ህዝብ ዝም ስላለ ተሸንፏል ማለት አይደለም በሚል ተከራከርኳቸው። እኔ እንኳ በማስፈራራት ምንም ልታገኙ አትችሉም ስላቸው እዛው እግሬም እጄም እንደታሰረ ጥለውኝ ወጡ።
አዲስ ዘመን፡-በቅርቡ እንደሚያውቀቱ እናንተን ሲያሰቃዩ የነበሩ ግለሰቦችና በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ምህዳሩን ለማስፋት በሚል እንዲፈቱ ተደርጓል። ይህን ጉዳይ በህግ ሚዛን እንዴት ያዩታል? አሉታዊስ ሚና ይኖረዋል ብለው አያምኑም?
አቶ ማሙሸት፡- በመጀመሪያ ደረጃ አንድ አገር ሊኖር የሚችለው በህግ ነው። በአንድ አገር ውስጥ የህግ የበላይነት ከሌለ ዲሞክራሲ፥ ሰብአዊነትና ምርጫ የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ሊኖሩ አይችሉም። የሰው ልጅ በዘመነ ስልጣኔ ሊኖር የሚችለው በህግና በስርዓት ብቻ ነው።የሚጠየቀውም፤ነፃም የሚወጣውም በህግ ነው። እውነት ለመናገር በግሌ ማንም ሰው እንዲታሰር አልፈልግም። ብዙ የታሰርኩባቸው ቦታዎች እጅግ አስቃቂ ቦታዎች ናቸው። እንግዲህ የጠባሴ ጦር ካምፕን ታውቂው እንደሆነ አላውቅም ከአፄ ኋይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው እዚያ ሳይቀር ነው የታሰርኩት። ኢትዮጵውያን እርስበርስችን እንዲህ መሆናችንን ሳስበው ሰው መሆኔን እጠላለው።
ያ ድርጊት በእኔ ላይ ያለፈ ሁሉ በማንም ሰው ላይ እንዲያልፍ አልፈልግም። የበደለኝንም ሰው ቢሆን ያንን አይነት ግፍ እንዲደርስበት አልፈልግም። ግን ለሰራው ስራ መጠየቅ አለበት ብዬ አምናለሁ። በህግ ፊት ቆሞ ቢያንስ ምን እንዳደረገ ሊገነዘብ ይገባል። ምክንያቱም መማሪያ ሊሆን ይገባዋልና ነው። መንግስት ይቅርታ ሊያድርግ ይችላል፤ ህዝብ ይቅርታ ሊያደርግ ይችላል፤ የተበደለ ይቅርታ ሊያደርግ ይችላል፤ እሱ ችግር የለውም ግን ህግ መኖሩን ማወቅ መቻል አለበት። ያን ሁሉ በደል ሲፈፅም የነበረ ግለሰብ ከእሱ በላይ የሚበልጥ ህግ እንዳለ ማወቅ አለበት።
እንዳልሽው ሰሞኑን በተፈቱት ሰዎች ላይ እንድመስክር እኔም ተጠይቂያለሁ። ፍቃደኛ አልሆንኩም። ምክንያቱም በቦታው ላይ ያሉት ዳኞች እነዚያው ዳኞች ናቸው። ትላንትና በሃሰት ምስክርነት ሲያሳስሩ የነበሩት አቃቢ ህጎች ናቸው ያሉት። ዛሬ በተራቸው እነዚያን ሰዎች ከሳሽ ሆነዋል። እኔ የፍትህ ስርዓቱ ለውጥ እንዲመጣ ነው እንጂ የምፈልገው ያ አቃቢ ህግ ዛሬም እየታዘዘ እየደበደበ እንዲመረምር አልፈቅድም። ለምሳሌ እቴነሽ አረፋአይኔ ከተፈቱት ሰዎች አንዷ ናት። ብመሰክርባት ደስታውን አልችለውም። ምክንያቱም ሴት ሆና እንደእሷ ግፍ የፈፀመ ሰው የለም። በነገራችን ላይ ድብደባው፤ ግርፋቱ ይድናል። እሷ ያደረገችው ግን የሚድን አይደለም። በወንድሞቻችን ላይ ያደረገችው ነገር በጣም የሚያሳዝን ነው።
ሞዴስ ሳይቀር እያወጣች በሰዎች አፍ ውስጥ የምትከት ሴት ነች። አሁን እንደዚህ አይነት ሰዎች በእውነት በምን ማስረጃ አጣርታ ነው ያንን ሰው እንደዚያ የምታደርገው? ሽንት በሰው ላይ ትሸናለች። ይህ ያየነውን ነው የምነግርሽ፤ አሉባልታ ወሬ አይደለም። አሁን ይሄ መንግስት ሲፈታት ያልተቃወምኩበት ምክንያቱም ከሷ የበለጠ ብዙ ወንጀል የፈፀሙ በአደባባይ ቁጭ በማለታችው ነው። ዛሬም አሉ። ለምሳሌ ማዕከላዊን ስናነሳ ተክላይ መብራቱ ከፊት ድቅን ይላል። እሱ ነበር ትዕዛዝ ይሰጥ የነበረው። እሱ አሁንም ስልጣን ላይ አለ። ሌሎችም አሉ። ስለዚህ አሁን የፍትህ ስርዓት ለማስፈን አይደለም የተፈለገው፤ አሁን የተፈለገው የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ትክክለኛ የፍትህ ስርዓት ቢፈለግ ኖሮ እመሰክራለሁ። በሌላ በኩል ግን እነዚህ ሰዎች ታስረው እንዲኖሩ አልፈልግም። ሰው በመታሰሩ አልደሰትም። ግን መጠየቅ አለባቸው። ምክንያቱም ለሌሎቹም መቀጣጫ እንዲሆኑ እፈልጋለሁና ነው።
በነገራቸን ላይ ቂሊንጦ ሌላው ማዕከላዊ ነው። ቃሊቲም እንደዚሁ ሌሎቹም ተመሳሳይ ነው። ቂሊንጦ ሲቃጠል እዛው የሞቱ ሰዎችን ቀብረው አምስተኛና አራተኛ ዞን ተብሎ ተሰርቶበታል። ዛሬም ድረስ ያ እሬሳ እዛ ውስጥ ይጮኻል። ፍትህ ከተፈለገ ያ እውነት መውጣት አለበት። እነዚያ ሰዎች ደግሞ በግልፅ ቢያንስ ተፀፅተናል ማለት ይገባቸዋል። ሌላ ምንም አያስፈልገንም። እኛ በዳዮቻችን በመሞታቸው የምንጠቀመው ነገር የለም፤ ደግሞም ሃገር ከችግር ውስጥ እንድትወጣ ከተፈለገ እንዲህ አይነት ነገሮችንም እያለፍሽ መሄድ ይገባሻል።
እኛ ቂመኞች አይደለንም፤ በቂም ብሄድ ኖሮ ማዕከላዊ የደበደበኝ ሰው ብዙ ጊዜ አገኘዋለሁ በጉልበት አያቅተኝም፤ እሱን ገድዬ እስር ቤት ብገባም ደስታውን አልችለውም። እሱ ግን ታዞ ነው ያደረገው። ስለዚህ ቂም ይዞ መኖር ለማንም አይጠቅምም። ቂም ከቋጠርን እናፈርሳታለን አገራችንን። መንግስት ከእነዚህ አይነት አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ዋና ግዴታው ወደ ሆነው ህግ የማስከበር ስራ መግባት አለበት። እሱን ሲያደርግ ሀገር ሰላም ሲሆን ህዝብ ያለማል። ምንአልባት ወደ ሌላ ጉዳይ ገባህ አትበዪኝና አሁን ላይ ልማትና ኢንቨስትመንት ተቋርጧል፤ ይህንን ልንክደው አንችልም። ኢንቨስትመንት ከሌለ በትንሽ ነገር መንገድ የሚዘጋው ወጣት ዞሮዞሮ ለጉዳት ይዳረጋል፤ ይህ ወጣት ስራ የማግኘት ዕድል አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ለዚህ ችግር እናንተ ፖለቲከኞችም የመሪነቱን ሚና እንዳላቸሁ ብዙዎች ይስማማሉ፤ በተለይ ሁሉንም ጉዳይ የፖለቲካ ጥያቄ በማድረጋችሁ ትወቀሳላችሁ። በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ማሙሸት፡- ለዚያ አሁን ለምትይው ችግር መነሻ ህገመንግስቱና የፌዴራል አወቃቀሩ ነው። ህገመንግስቱ በመጀመሪያ ደረጃ በህዝብ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አይደለም።ህገመንግስት የዜጎች የመግባቢያ ሰነድ ነው። ህገመንግስቱ ግን ህዝብ ተስማምቶ አልፀደቀም ። የፌዴራልሊዝም ስርዓቱንም ሲያዋቅሩ በቋንቋና በዘር የተመሰረተ አደረጉት። አሁን ቋንቋና ዘር ቀደመና አገር የሚባለው ነገር ቀረ። ቋንቋ ትልቅ ሆኖ፤ መንደር ትልቅ ሆኖ ሃገር እመራለሁ አለ። የአገራዊ አንድምታው ፈረሰና የጎጠኝነት አንድምታ ነገሳና አንተ ከእኔ ጋር ውጣ መባባል፤ማፈናቀልና እርስበርስ መገዳደል መጣ። የነበረን መልካም እሴት ባህላችን መዋለዳችችን በአንድ መልካምድር ክልል ውስጥ መኖራችንን ረስተን ቋንቋችንን ትልቅ አደረግነው። ለእኔ የዚሁ ሁሉ ምንጭ ህገመንግስቱ ነው። እሱን ማሻሻል የመንግስት ትልቁ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፡-ህገ መንግስቱ እስከከሚቀየር ድረስ እንዲሁ እየተጋጨን ልንቀጥል ነው ማለት ነው?
አቶ ማሙሸት፡- ልመጣልሽ ነው፤ የተዘራ የዘረኝነት መርዝ አለ፤ የተዳፈነ ፈንጅ ማለት ነው። አሁን የዶክተር አብይ መንግስት ሲመጣ ያ የተዳፈነ ፈንጅ በየቦታው መፈንዳት ጀመረ። ህዝቡ ደግሞ የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ አለበት። እነዚህ ጥያቄዎች ለ27 ዓመታት ሲጠየቁ የኖሩ ናቸው። መንግስት ህዝቡ ይርካም፤ አይርካም መልስ የመመለስ ግዴታ አለበት። ምንም ሊሆን ይችላል መልሱ ግን መልስ መስጠት አለበት። አሁን አገራዊ አንድምታውን አፈረስነውና በመንደር ታጠርንና ኢትዮጵያዊ የሚለውን ሰዋዊ ክብራችንን አስቀረንና ከመንደር ጋር ፍጭትና ግጭት ሆነ። ይህንን ደግሞ የሚፈልጉት ፅንፈኛና ዘርን መሰረት ያደረጉ ፖለቲከኞች ያንን እንደትልቅ ማሳሪያ ተጠቀሙበት። አየሽው! ይህ የእኔ መሬት ነው ፤ አንተ መጤ ነህ ወደሚል ተሄደ።
እሱ ትልቅ ማፋለስ ያመጣል። የሩዋንዳ ጭፍጨፋ የመጣው ከዚህ ነው። የመንና ሶሪያም የፈረሱት በዚህ ምክንያት ነው። አየሽ ወደ መንደር ስንመጣ በአካባቢያዊነት ስንሰለፍ አገር ስዕል ይጠፋና እንበተናለን። ከዚህ ነው ፓርቲያችን በአገር አንድምታው ላይ እንነጋገር እያለ ያለው። የምርጫውን ነገር ትተን በቅድሚያ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ታስፈልገናለች? ወይስ አታስፈልገንም? የሚለው ነገር ላይ እንስማማ።አታስፈልገንም የሚል ካለ በምክንያቱ ላይ እንግባባ። ለመለየትም ሆነ አብረን ለመሄድ እንስማማ።
የማያስማሙን ነገሮች ይኖራሉ ተብሎ ከታሰበ ለህዝብና ለጊዜ እንተዋቸውና በሚያግባቡን ላይ እንስራ። ሰው ሲሰራ ይግባባል። ሰው በወሬ መግባባት አይችልም። ተበድለናል፤ ተጨቁነናል የሚል አስተሳብ ይዘው የመጡ ሰዎች አሉ። በዳይ ማነው? ማነው ተጨቋኝ የሚለውን ነገር የምናስታርቀው በጠረጴዛ ዙሪያ ነው። የታሪክ ስህተት ካለ በግልፅ እንመርምር እያልን ነወ። ጨቋኝ የተባለው ምንአለው? ተጨቋኝ የሚባላው ምንአጥቷል? እንነጋገር። በታሪክ ሂደት ውስጥ አስታዋፅኦ የለንም የሚል ግለሰብና አካል ካለ እንነጋገር። አድዋ ላይ የእኔ ዘር አልዘመተም የሚል ካለ እንነጋገር። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ አይወክለኝም የሚል ካለ እንነጋገር። ይህንን ከማስቀደም ይልቅ አሁን እየተደረገ ያለው ነገር ማናችንንም አይጠቅምም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች የአማራ ህዝብ የሚታገልለት ሁነኛ ፖለቲከኛ የለውም ይላሉ፤ ይህ አስተሳሰብ ምን ያህል ተጨባጭ ነው ይላሉ?
አቶ ማሙሸት፡- በመጀመሪያ ደረጃ ለአማራ የሚታገልለት የለውም በሚባለው ብዙም አልስማመበትም። እኔም ገና በ18 ዓመቴ ወደ ትግል የወጣሁት ለዚህ ህዝብ ነፃነት ነው። ብዙ የታገሉለት ሰዎች ህይወት የከፈሉ አሉ። ግን ቅድም እንዳልኩሽ ከክልልም አልፎ የአማራ ህዝብ ትግል ጎጥ ውስጥ ገብቷል። አሁን ክልልን እመራለሁ የሚለው አመራር በጎጥ ነው የሚያስበው። ከእዛ የመንደር አስተሳሰብ ወጥቶ እንደ አማራ አማራነት፣ እንደ አገር ደግሞ ለኢትዮጵያ መታገል ሲገባው በመንደርና በጎጥ በወንዝ አመራሩ ተሰልፎ ያንን በማድረጉ ውስጥ ያለውን ችግር ከመፍታት ይልቅ በአምቻ፣ በጋብቻ፣ በዘመድ አዝማድ አሰላለፋቸውን አበጅተው አንዱ ሲጠጠፋ በህግ ከመጠየቅ ይልቅ ሌላኛው ጥላ ከለላ በመስጠት የሚፈጸም በደል ነው። በሌላ በኩል እንደምታውቂው ህወሐት ከጫካ ሲመጣ ጀምሮ የመጀመሪያ ጠላቴ ብሎ በ1968 ዓ.ም በጻፈው ማንፌስቶ ላይ የመጀመሪያው ጠላታችን ነፍጠኛው አማራ፣ ሁለተኛ ጠላታችን ድህነት ይላል። በእዚህ ማንፌስቶ መሰረት ከእዛ እየተመዘዘ ላለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በአማራ ላይ ከፍተኛ እልቂትና በደል ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን፡- ግን ነፍጠኛ ማለት አማራ ብቻ ነው እንዴ ?
አቶ ማሙሸት፡- ያሉን እንግዲህ በተከታታይ ይህንን ነው። እነ አቶ መለስ፣ እነ አቶ ስብሃት፣ እነ አቶ ስዬ አብርሃ፣ እነ አቶ አዲሱ ለገሰ ያሉት ነፍጠኛ አማራን ላይነሳ አከርከርካሪው መተነዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ይሄንን ቃል በቴሌቪዠን ያሉትን ነው የምልሽ። ይሄንን አስተምህሮ የተቀበለ ካድሬና አመራር ደግሞ በሁሉም አካባቢ በአማራው ላይ በደል ፈጽሟል። የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል አለበት ማለት እርሱ ነው። ዛሬ፣ አሁን ለምሳሌ ህወሓት እዛ ሆና የምትለው ጠላታችን አማራ ነው። ለምን የአማራ ህዝብ ጠላት ይሆናል። ያጠፋ የአማራ አመራር ወይም የትግራይን ህዝብ የጠላ ካለ እርሱ ይጠየቅ። የአማራ ህዝብ ለህዝብ እንዴት ጠላት ይሆናል። የአማራና የትግራይ ህዝብ እኮ የማይለያዮባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ባህላቸው ከማንኛውም ህዝብ የበለጠ የተሳሰረ ነው። ሃይማኖት፣ ቋንቋና የመሬት አቀማመጥ የተሳሰሩ ናቸው። እውነት ለመናገር በድህነት እንኳን እኩል ናቸው።
ወንበራ አካባቢ፣ በወሎ አካባቢ ከትግራይ አካባቢ ራቁትነት፣ ደረቅነቱ ተመሳሳይ ነው። በጋብቻና በመዋለድም በጣም የተሳሰሩ ናቸው። ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃምና ሸዋ ብትሄጂ በጣም ብዙ የትግራይ ሰዎች ከአማራ ጋር ተጋብተው ያፈሯቸቸው ልጆች አሉ። አማራ የትግራይ ጠላት ነው፣ ጨቋኝ ነው የሚለው አስተሳሰብ የሃሰት ትርክት ነው። አማራ ትምክህተኛ ነው የሚለው አስተሳሰብ መቅረት አለበት። የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝበ ጋር ለሰከንድ ጸብ የለውም፣ እኔ አደዋን፣ አክሱምን መቀሌን አውቃቸዋለሁ። ሄጄም አደራጅቻለሁ። ያ ህዝብ ዛሬም በድህነት ውስጥ ነው ያለው። ይሄንን በአደደባባይ በብዙሃን መገናኛ መስክሬያለሁ። የህወሓትንና የትግራይን ህዝብ ለዩ ብያለሁ።
የትግራይ ህዝብ ዛሬም ረሃብ ላይ ነው። ማንም ሄዶ መመልከት ይችላል። እኔ ፖለቲከኛ ነኝ። አጥላልቼ የሆነ ነገር ማግኘት ነው የምፈልገው። ግን እርሱ አይደለም በተጨባጭ ያለው። በባዶ እግሩ የሚሄድ፣ የተራበ፣ ልብሱ በላዩ ላይ የተቀደደ ህዝብ አይቻለሁ። ጎንደር ስሄድ፣ ወሎ ስሄድ ይህንኑ አይቻለሁ። ልዩነት የለም። የባለስልጣን ዘመድ ግን ባለሀብት ሆኗል። ይህንን አንክድም። በእነዛ ስም ሊነገድባቸው አይገባም። አማራ በፍጹም ለትግራይ ህዝብ ጠላት ሊሆን አይችልም። እንደውም ይህችን አገር ማዳን የሚችሉት ሁለቱ ህዝቦች በጋራ ሆነው ሲሄዱ ነው።
ይህንን ለፖለቲከኞቹ ነግረናቸዋል። ለአረና፣ ለህወሓት ሰዎችም ነግረናል። ከድሮ አስተሳሰብ እንዲወጡ ነግረናቸዋል። የታሪክ ስህተት ይዛችሁ ያንን ህዝብ እንደገና ወደ መከራ አትክተቱት፣ ህዝብ ለህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። እኛ ፖለቲከኞቹ ቁስል እየቆሰቆስን፤ የሆነውንና ያልሆነውን ሳንለይ እየነገርን ህዝቡን አጣልተነው ይሆናል እንጂ ህዝቡ አልተጣላም። በክፉ ቀን ተደጋግፈው አልፈዋል። ትናንትና በታሪክ ፊት አብረው ቆመው፣ ተማግደው አገር የሚል ነገር ሰጥተውናል።
አንዱ አንዱን አልብሶና አጠጥቶ ተደጋግፈው አልፈዋል። ዛሬ ያለው ፖለቲከኛ በሚቆሰቁሰው እሳት ንጹሃን ወንድሞችና እህቶች እንዲማገዱ አንፈልግም። የአማራ ህዝብ የህልውና አደጋ አለበት ሲባል ይኸው ነው። በመላው አገሪቱ እንደሚታየው ውጣ የሚባለው እርሱ ነው። እንደምታውቂው በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ከሁሉም ብሄር የሚመጡ ተማሪዎችን ህዝቡ እቀፍ ድግፍ አድርጎ ይዟል።ስለዚህ ተንኮል፣ሸርናና ስልጣን ሊያለያይ ቢሞክር እንኳን እኛ አንለያይም። አንድ ላይ የተገመደ ማንነት አለን። ለጊዜያዊ ስልጣንና ጊዜ ተለያይተን እንዳንቀርና እንዳንለያይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በአሜሪካ ሸምጋይነት ከሚካሄደው ውይይት ኢትዮጵያ እራሷን አግላለች። አሜሪካ ከግብጽ ጋር መወገኗ እንደፖለቲከኛ ያሰጋዎታል?
አቶ ማሙሸት፡- በአባይ ጉዳይ አቶ መለስ በነበሩ ጊዜ ብዙ ጊዜ ተወያይተናል። በእኔ እምነት አባይን ለመገደብ በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ መሪ መሆን ያስፈልጋል። ይህ ማለት ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለት አይደለም። የኢትዮጵያን ህዝብ ማፍቀር፣ ለነገ ማሰብ፣ ይገባል። አባይ ለትውልድ የሚሻገር ፕሮጀክት ነው። ግድቡ ሲጀመር በጀት ሳይኖር ነው። ከህዝቡ አንድ ብር፣ ሁለት ብር አውጣ ከማለት በበጀት የተደገፈ ሊሆን ይገባ ነበር። ታስታውሺ እንደሆነ በወቅቱ የምዕራብ አፍሪካ አመጽ የእነ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ሊሊያ ከርሮ ስለነበረ ያ ወደ ሀገራችን እንዳይመጣ በመስጋት የተቀየሰ የሃሳብ ማስቀየሪያ ስራ ነው የተሰራው እንጂ አባይ ተገድቦ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ አይደለም።
ግን ሳያስቡት ሃሳብ ማስቀየሪያ ብቻ ሳይሆን በህዝቡ ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ። ሀብቱን ንብረቱን አሟጥጦ ሰጠ። በአምስት ዓመት ያልቃል ቢባልም እስካሁን ሊጠናቀቅ አልቻለም። ስለዚህ በጀት ቢኖር ኖሮ ስራው ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ አሁን ለድርድር እንቀርብም ነበር? ግብጽስ ለድርድር ትጠይቅ ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ለድርድር ልንቀርብ አይገባም። ባለቤቶች ነን። ግብጽ እኛን ነው መጠየቅ ያለባት። ከሰብአዊነትና ከወንድምነት፣ ከጎረቤት አኳያ እናንተ ስትለሙ እኛ ልናልቅ ስለሆነ ምን ያህል ትሰጡናላችሁ? ተብለን እንጠየቃለን እንጂ ድርድር ተብለን በሶስተኛ ወገን ልንደራደር አይገባም። ትክክልም አይደም።
ስለዚህ ሀብታችንን ይዘን የመልማት አቅማችንን ለድርድር ማቅረብ አይገባንም። አብዛኛው ውሃ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እምቢ ካሉ በየቦታው ያሉትን ገባሮች ቆራርጠንም ማስቀረት እንችላለን። ለምን አባይ ላይ ብቻ እንታገላለን። እኛ በወቅቱ ያቀረብነውም ሃሳብ ይሄ ነው። ግብጾች እምቢ የሚሉ ከሆነ ወደ አባይ የሚገቡትን ገባሮች በሙሉ ማልማት መብታችን ነው። ሸንኮራም፤ ጌሾም ተክለን ቢሆን ማስቆም እንችላን። ግን ይሄ አይደለም አላማችን።
እነሱም ሳይጠሙ እኛም ሳንራብ በጋራ እንጠቀም ነው እያልን ያለነው። አሁን አባይ ህልውንናችን ነው። በግድቡ ላይ ድርድር ሊደረግበት አይገባም። ባለሙያዎቻችን ገብተው ስለፍትሃዊ ክፍፍሉ ይወያዩ እንጂ በአስገዳጅነት አሜሪካ ኃያል፣ ትልቅ አገር ስለሆነች ታደራድር የሚባል ነገር የለም። ይሄ መንግስት ዋጋ እንዳያስከፍለው የውስጥ ሰላሙን ማጠናከር ይገባ ዋል፡፡ ክፉ ቀን ሲመጣ አብረን ነው መንገጫገጭ ያለብን። ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ማስተላለፍ የምፈልገውም መልዕክት ይህ ንኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ ላመሰግኖ እወዳለሁ።
አቶ ማሙሸት፡- እኔ ጋዜጣው የእኔም መሆኑን ተገንዝባችሁ ሃሳቤን እንዳስተላልፍ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
ማህሌ አብዱል