‹‹ከባድ ሸክም ለመሸከም ከፈለግክ፤ ሌሎች እንዴት እንደተሸከሙ ለማወቅ ሞክር›› የሚል የአፍሪካውያን የቆየ አባባል አለ፡፡ እናም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ለገጠማቸው ሀገራዊ ጉዳይ ምክር ፍለጋ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ጉዳዩ እንዲህ ነው፤አፍሪካ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ተከትላ ሌሎች ሁለት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድቦችን በራሷ አቅም ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነች፤ታላቁ ኢንጋ 3እና ባቶካ የተሰኙ ግድቦች፡፡
በ14 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባውና 11 ሺህ በላይ ሜጋዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ግዙፉ ኢንጋ-3 ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሊገነባ መሆኑን ይፋ የሆነው እ.ኤ.አ በ2013 ነበር ፡፡ ለደቡብ አፍሪካ፣ለናይጄሪያ እንዲሁም በምስራቅ ኮንጎ ለሚገኙ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ያለመ ፕሮጀክት ነው፡፡ የዓለም ባንክ ለግድቡ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ሊተገበር ባለመቻሉ የኮንጎ መንግስት ሌሎች አማራጮችን ሲያፈላልግ ቆይቷል፡፡ እናም ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ በዛምቤዚ ወንዝ ላይ ባቶካ ሃይል ማመንጫ ግድብ በጋራ በመገንባት ላይ ካሉት ዚምባቡዌና ዛምቢያ ለተመሳሳይ ጉዳይ ከመጡ ልኡካን ጋር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጎብኝተው ነበር ፡፡
የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግድቡን ለመገንባት እንዴት ቆርጣ እንደተነሳችና ምልአተ ህዝቧን ለማነቃነቅ ያስቻላትን ምስጢር ለማወቅ ነበር፡፡
ሙዙንጉዲያከሎ በደቡብ አፍሪካ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዲፕሎማት እና የታላቁ ኢንጋ 3 ፕሮጀክት ተጠሪ ናቸው፡፡ እሳቸውም‹‹ ህዳሴ ግድብ ከግንባታው ግዙፍነት አንጻር ህዝቡ ተሳታፊ መሆኑ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥርና አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ለታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት የህዝቦች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ማሳያ ነው ››ብለዋል፡፡
‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ያለውጭ ብድር በመንግስት እና በህዝብ መዋጮ እየተገነባ ያለ ግድብ ነው፡፡ ግድቡን በመደገፍ ረገድ ህዝቡ እየተሳተፈ ነው፡፡ አፍሪካ እንደነዚህ ዓይነት ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም መገንባት መጀመሯን ማየት በጣም ያስደስታል፡፡ ይህ ታላቅ ነገር ነው፡፡ በሀገራችንም ይህን ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ኢንጋ-3 የተሰኘውንና ከ11 ሺ በላይ ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጭ ግድብ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነን፡፡ ይህን በመሰለ ግዙፍ ፕሮጀክት ላይ እንዴት ነው ህዝቡን ማሳተፍ የሚቻለው? የሚለውን ልምድ መውሰድ እንፈልጋለን›› ነበር ያሉት፡፡
ኢንጅነር ቶቢ ሻሎንዳዋ በኢንጋ-3 ፕሮጀክት የልማትና ፕሮሞሽን ኤጀንሲ ውስጥ በኤክስፐርትነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እሳቸውም ከጉብኝቱ በኋላ የሚከተለውን ተናግረው ነበር፡፡‹‹በቅርቡ ኮንጎ ውስጥ ኢንጋ-3 ሃይል ማምንጫ ግድብ ፕሮጀክት መገንባት እንጀምራለን፡፡ የእኛ አመጣጥም የኢትዮጵያ መንግስት ታላቁን የህዳሴ ግድብ እንዴት እየገነባ እንዳለ ትምህርት ለመውሰድ ነው፡፡››
‹‹በዛምቤዚ ወንዝ ላይ ባቶካ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየገነባን ነው፡፡ እዚህ የተገኘነው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ልምድ ለመቅሰም ነበር፤ ይህንኑ በቦታው ተገኝተን ፈፅመናል፡፡››የሚሉት ደግሞ የዚምባቡዌ የሃይል ሚኒስትር ኢንጅነር ቤንሰንኚያራቲ ናቸው፡፡
‹‹ብዙዎች አፍሪካ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደማትችል ያስባሉ፡፡ ነገር ግን አንዲት አፍሪካዊ ሀገር ናት ይህንን ግዙፍ ግድብ እየገነባች ያለችው፤ እናም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እና አፍሪካውያን በራሳችን አቅም መስራት እንደምንችል ያሳየ ፕሮጀክት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዴት ግድቡን በገንዘብ እየደገፉ እንደሆነ በቂ ትምህርት አግኝተናል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት ከለጋሾች በሚገኝ ገንዘብ አሊያም በብድር ነው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የፋይናንስ ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተሸፈነ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ባለውና በውጭ በሚኖረው ዳያስፖራ የሚደገፍ መሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ ይህን ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ለመገንባት መነሳት በራሱ አስገራሚ ነው›› ነበር ያሉት፡፡
አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ የምስራቅ ናይል አህጉራዊ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በዓለማችን፤ በጣም ድሀ ተብለው በተፈረጁ ሀገራት ታላቁ ህዳሴ ግድብን የመሰሉ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች በራስ አቅም ሲገነቡና ፋይናንስ ሲደረጉ ታይቶ አይታወቅም ባይ ናቸው፡፡ በአብዛኛው በአፍሪካና በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ ያሉት ትላልቅ መሠረተ ልማቶች፤ በቅኝ ገዢዎች አሊያም በበለጸጉ ሀገራት እገዛ ወይም ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተገነቡ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት ፡፡› ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጀመር የአፍሪካ ሀገራት ደግፈዋል፡፡ ይህም ፤ ግድቡ ለእኛም አቅጣጫ ጠቋሚ ነው ከሚል እሳቤ በመነጨ ነበር፡፡ ፈርቀዳጅና ተምሳሌት አድርገው ነው የወሰዱት፡፡ ግድቡ በራስ አቅም መገንባቱ፣ የገንዘብ ምንጩ ከሀገር ውስጥ መሆኑ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስብስብ መመሪያዎችና መርሃግብሮች ምክንያት የገንዘብ ድጋፍ ላጡ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ሆኗቸዋል፡፡››
‹‹እንደ ናይል ባሉ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች፣ ከፍተኛ የውሃ ፖለቲካ ያለመግባባት የሚታይባቸው ተፋሰሶች እንደመሆናቸው መጠን እንዲሁም አንዳንድ ሀገሮች በሌሎች ሀገራት ላይ ልማት እንዳያካሂዱ ጫና በሚፈጥሩበት ሁኔታ ውስጥ ይህ ግድብ መገንባቱ ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ልምድ እንደሚሰጥ መረዳት ይቻላል›› የሚሉት አቶ ፈቅአህመድ፣የብዙዎቹ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች ‹‹ከኢትዮጵያ ተምራችሁ ተመሳሳይ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለምን አትገነቡም ?በማለት በመሪዎቻቸው ላይ ጫና ሲፈጥሩ ተስተውለዋል፡፡ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እና በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ በስፋት ሲወጡ አይተናል፡፡ እስካሁን የበርካታ ሀገራት መሪዎች፣ተወካዮችና ዲፕሎማቶች የግድቡን ግንባታ ጎብኝተዋል፡፡ ይህም የህዳሴ ግድብን የአፍሪካ ተምሳሌትነት እንደሚያረጋግጥ ማሳያ ነው ነበር ያሉት።››
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ያጋጠመውን የመዘግየት ችግር ለመፍታት እና ግንባታውን ለማፋጠን መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችን እና የማሻሻያ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ትላልቅ የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የሚፈጁት ጊዜ እንደታቀዱበት ጊዜ የሚወሰን ቢሆንም በአብዛኛው በዓለም ላይ የተከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከታቀደላቸው በላይ ጊዜና ወጪ የመፍጀት ሁኔታ ታይቶባቸዋል፡፡
አቶ ፈቅአህመድ፤ እንደ ግድብ፣መንገድ ፣የአየር ማረፊያዎች፣የኑክሊየር ሃይል ማመንጫዎች የመሳሰሉት ትላልቅ መሠረተ ልማቶች በአማካኝ በጊዜና በወጪ ከ40 እስከ 60 በመቶ ጭማሪ እንደሚያስከትሉ በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት አመላክቷል ይላሉ፡፡ በአደጉ ሀገራትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የፕሮጀክቶች መዘግየት የሚታይ መሆኑን በጥናት የተደረሰበት ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ፈቅአህመድ ፤ ከሀገር ውስጥ እንደ ጊቤ-3 የመሳሰሉት የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ዘግይተው መጠናቀቃቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ዋናው ነገር ችግሩን አንጥረው ከለዩ በኋላ መፍትሄ በማስቀመጥ በቶሎ ግድቡን ወደ መጨረሱ መፍጠን የሚመረጥ መሆኑን ነው አቶ ፈቅ አህመድ ያሳሰቡት፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅነትን በቅርቡ የተረከቡት ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በፕሮጀክቶች መዘግየት ዙሪያ ከአቶ ፈቅአህመድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹በዓለም ያሉ ፕሮጀክቶች ሁሉ ይዘገያሉ፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ ነው፡፡ የሲድኒ ኦፔራ ሀውስ የአውስትራሊያውያን መለያ ምልክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአራት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጀመርም በ14 ዓመት ነው የተጠናቀቀው፣ 10 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ሺሊንግ ይፈጃል ተብሎ ከ102 ሚሊየን ሺሊንግ በላይ ፈጅቶ ነው ያለቀው፡፡ እንግሊዝና ፈረንሳይን የሚያገናኘው የቻናል ካናል በዓለም ላይ ትልቅ የምህንድስና ውጤት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ዘግይቶ የተጠናቀቀ ሲሆን 80 በመቶ በላይ ተጨማሪ ወጪ አስከትሏል፡፡
ዊምብሌይ ስታዲየም የእንግሊዛውያን የእግር ኳስ መለያ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስታዲየሙ ሲገነባ ከታሰበው ጊዜ በላይ ሁለት እጥፍ ዘግይቶና ተጨማሪ ወጪ አስከትሎ ነው የተገነባው›› ካሉ በኋላ የህዳሴ ግድብ የመዘግየት ወሬ እንደተሰማ እንደ ትልቅ ነገር እንዲወራ እና ህዝቡን ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገው ምክንያት በወቅቱ ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ ማቅረብ አለመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ፕሮጀክት ይዘገያል፤ የዘገየበትን ምክንያት ገልፆ መፍትሄ መፈለግ እንጂ መደበቅ ተገቢ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዕውቀትና ሳይንቲስቶች ይገኙበታል በሚባለው የአሜሪካ ጠፈር ምርምር ተቋም (NASA)እንኳን ፕሮጀክቶች ይዘገያሉ›› የሚሉት ኢንጅነር ክፍሌ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የዘገየ ቢሆንም እሱን በማካካስ በጥራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀውናል፡፡
ኢትዮጵያውያን ዘር፣ሃይማኖት ፣የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው ከጫፍ ጫፍ የተነቃነቁትና የደገፉት ያለምንም ጎትጓች ነበር፡፡ ይህን ዓይነቱን የህዝብ ድጋፍ ማግኘትና እስከ ግድቡ ግንባታ ፍጻሜ ማቆየት መታደል ሲሆን፤ ይህን የህዝብ ድጋፍ አለመጠቀም ግን ውድቀት ነው፡፡
የሞራል ጉዳይም መታሰብ አለበት የሚሉት አቶ ፈቅአህመድ ‹‹የግድቡ ግንባታ መዘግየት የህዝብን ሞራል ይነካል፡፡ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ ከህዳሴ ግድብ በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ ግድቦች ለመገንባት የነበረው ዕቅድ ላይ ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዳይለግስ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡እንዴት ወደነበርንበት ስሜት ተመልሰን በላቀ ሞራልና ወኔ ግድባችንን እናጠናቅቃለን ? የሚለው ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል››ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ዛሬ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊገነቧቸው ላሰቧቸው ግድቦች ህዳሴ ግድብን እንደ ሞዴል በማየት ልምድ ለመቅሰም ወደ እኛ መምጣታቸው ለእኛ ኩራት ሊሆነን ይገባል፡፡ህዳሴ ግድብ ‹‹ይቻላል››ን ለአፍሪካውያን ያስተማረ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ግድብ ከኢትዮጵያውያንም በላይ የአፍሪካ ሀብት መሆኑን ለአፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት እንደሆነ ሁሉ የህዳሴ ግድብም የጥቁር ህዝቦች ከድህነት ነጻ የመውጣት ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ምንም ነገር ይወራ፣ምንም ያህል ሀብት ይባክን ተጠያቂ ወ
ገኖች ያለባቸው የህግ ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ በምንም ምክንያት የግድቡ ግንባታ ሊስተጓጎል አይገባም፡፡ ህዝባችንም ካለበት ጥርጣሬ ወጥቶ ወደቀደመው ወኔና እልህ በመመለስ ግድቡን ማጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ግድቡ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ሀገራችንን በየዓመቱ ስምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር እያሳጣት ይገኛል፡፡ ድህነታችንን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የተባለውን ግድብ በወቅቱ አለማጠናቀቅ ከድህነት ጋር ተስማምቶ መኖርን መምረጥ ማለት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ህብረተሰቡ ግልጽና ወቅታዊ መረጃ እንዲኖረው በማድረግ እየተፈጠሩ ያሉ ብዥታዎችን ማጥራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ግድቡን ወደ ኋላ ሊመለስ የማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሰነዋል እና ማጠናቀቅ አለብን ፡፡
የግድቡን የሃይድሮ-ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች በራሳችን ባለሙያዎች መሥራት አለብን በሚል ቀና ሃሳብ የተጀመረው ሥራ ከሚገባው በላይ መዘግየቱን የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 10ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል መናገራቸው ኢትዮጵያውያንን ተስፋ ሲያስቆርጥ ግብጻውያንን ጮቤ አስረግጦ ነበር፡፡ ይሁንና በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል የማስተካከያ እርምጃ በመወሰዱ የግድቡ ግንባታ ከአራት አመታት በኋላ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2022 ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ስራ እንደሚጀምር ግንባታውን በስራ አስኪያጅነት በመምራት ላይ የሚገኙት ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በማያሻማ ቋንቋ ነግረውናል፡፡
ይህ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት ነው፤ በመሆኑም ዳግም ወደ ቀደመው ወኔያችን በመመለስ ግድባችንን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የምንተጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011