ህይወት ባለብዙ መልክ፤ባለብዙ ፍርጅ ናት። ለአንዱ ጸጋዋን ለሌላው ችግሯን አውርሳ ሁሉም እንደ አርባ ቀን ዕድሉ ኑሮውን ይገፋል።የመከራ ዕድሜ አሰልቺ ቢሆንም እስትንፋስን ለማቆየት መታተር ግድ ነው።ተዝቆ በማያልቀው የመከራ ህይወት ተወደደም፤ተጠላም የኑሮን ውጣ ውረድ መጋፈጡ የሚቀር አይደለም።በዚህ እንደድር በተተበተበው የመከራ ህይወት ውስጥ ኑሮን ለማቃናትና በልቶ ለማደር ደፋ ቀና ከሚሉት ውስጥ መሰረት ግርማ አንዷ ናት።
ከደሴ እስከ አረብ ሀገራት ድረስ የተዘረጋው የመሰረት ፈተና የበዛበት የኑሮ ውጣ ውረድ የበርካታ እህቶቻችንን የመከራና የስቃይ ህይወትን ለአፍታ እንድናስታውስ ያደርገናል።
ደሴ
መሰረት ግርማ ተወልዳ ያደገችው ደሴ ከተማ በ1970 ዓ.ም ሲሆን ለቤተሰቦችዋ ሶስተኛ ልጅ ነች።መሰረት የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እዛው ደሴ ተከታትላለች።በትምህርቷም እምብዛም ስላልነበረች ማተሪክን አልፋ እንደጓደኞቿ ኮሌጅ መበጠስ አልቻለችም።በወቅቱ ማትሪክን አለማለፏ ብዙም ባያስቆጫትም እያደር ግን የቤተሰብ ጥገኛ መሆኗና የወደፊት ህይወቷም ጭምር ያሳስባት ያዘ። በዚህ ጊዜ ያለው ብቸኛ አማራጭ ስደት መሆኑን ለልቧ ነገረችው።
የኑሮ ውጣ ውረድ ምርጊት ሆኖ አላላውስ ሲል የሰው ልጅ እጅ ላለመስጠት መላ መዘየዱ አይቀርም። መሰረት ተወልዳ ያደገችባት ደሴ እንደልቧ እንደምኞቷ አልሆንልሽ ስትላት ስደትን በተስፋ አማተረች። ሩቅ ያለውን ሀገር ናፈቀች። እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል የሚለውን ብሂል አስታውሳ ከደሴ ባሻገር ያለውን ሀገር ለመርገጥ ተመኘች።ይህንኑ ምኞቷን እውን ለማድረግም ሁነኛ ሰው አማክራ፤ከወዳጅ ዘመድ ተበድራና በመጨረሻ ከደላላ ተዋውላ ቅሌን ማቄን ሳትል ተወልዳ ያደገችባትን ውቧን ደሴ ከተማን ለቃ ወደ አረብ ሀገር ውልቅ አለች።
ዱባይ
መሰረት ከሀገር መውጣት እንጂ የምትደርስበት ሀገር ብዙም አላሳሰባትም ነበር። ይሁን እንጂ የረገጠቻት ምድር ዱባይ ውበት የደፋባት እና በሀብት የተንቆጠቆጠች ሆና ስታገኛት ከሀገሯ ጋር በማነጻጸር አጀብ ተሰኘች።በፎቆቿ እርዝመትና በመንገዶችዋ ዘመናዊነት ተደመመች።የዱባይን ውበት አድንቃ ሳትጨርስ ግን እሷን በሰራተኝነት ለመቅጠር ከደላላ ጋር የተዋዋሉት አሰሪዎችዋ እያካለቡ ወደ መኖሪያቸው ወሰዷት። ያደነቀ ቻትንም ከተማ በወጉ አጣጥማ ሳትጨርስ ከአንድ የመኖሪያ ህንጻ ውስጥ በድንገት እራስዋን አገኘችው። የምትሰራበት ቤት በርካታ የቤተሰብ ዓባላት የሚኖሩበት በመሆኑ በርካታ ክፍሎች ያሉት ባለአራት ወለል ህንጻ ነው።
የመሰረትም ዋነኛ ተግባር በየቀኑ በርካታ ክፍሎች ያሉትን ይህንን ባለአራት ወለል ህንጻ ማጽዳት፤ለቤተሰቡ አባላት የሚሆን ቁርስ ፤ምሳ እና እራት ማዘጋጀት፤ልብስ መተኮስና ልጆችን ማጫወትና መንከባከብ ነው። ሥራው በጣም አሰልቺና ፋታ የሌለው በመሆኑ መሰረት የመጣችበትን ቀን ለመርገም ጊዜ አልወሰደባትም። አሰሪዎቿ ካላይዋት ወደ ውጪ ሲያይዋት ደግሞ ወደ ውስጥ ማልቀስ የዕለት ተዕለት ተግባሯ ሆነ።
ሌሊት ‹‹አላህ አክብር›› ሲል ተነስታ ለቤተሰቡ የሚሆን ቁርስ በማዘጋጀት የዕለት ሥራዋን ትጀምራለች።በርካታ ፍላጎት ያላቸውን የቤተሰቡን አባላት ለማርካት በርካታ የቁርሶች አይነቶችን ከትኩስ መጠጦች ጋር አዘጋጅታ ማቅረብ ከመሰረት የሚጠበቅ ግዴታ ከመሆኑ ባሻገር ከአሰሪዋ የሚደርስባትን ቁጣና ግልምጫም በመፍራት የምታቀርበው ቁርስ ሁሉንም የቤተሰቡን አባላት የሚያስደስት እንዲሆን ላቧን ጠብ አድርጋ ትሰራለች። ይህም ሆኖ ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ አሰሪዋ ቁም ስቅሏን ማሳየቷ አይቀርም።በተለይም በመጀመሪያዎቹ ወራት በቋንቋ መግባባት ስለማትችል የጎደለውን ነገር መረዳትና ማስረዳትም ስለማይሆንላት የአሰሪዋን ቁጣ በጸጋ ከመቀበል ውጪ አማራጭ አልነበራትም።
የቤተሰቡን አባላት ቁርስ አብልታ ከሸኘች በኋላም በዛ ግዙፍ የመኖሪያ ህንጻ ውስጥ የሚገኙ ክፍሎችና በረንዳዎችን ማጽዳቱን ትያያዘዋለች።ወገቧ ቁርጥ እስኪል ሁሉንም ክፍሎችና መወጣጫዎችን ይህ ቀረሽ በማይባል ጥንቃቄ ካጸዳች በኋላ አሰሪዋ ክፍሎቹን እየተዘዋወረች ምን ያህል እንደጸዱ በእጇ ጣት እየፈተገች አንዲት ቅንጣት አቧራ አለመኖሩን ታረጋግጣለች።ምንም እንከን ካልተገኘባት ወደ ቀጣዩ ምሳ ማብሰል ተግባሯ ታቀናለች።ለምሳ የምትሰራቸውን የምግብ ዝርዝሮች ከአሰሪዋ ትዕዛዝ ከተቀበለች በኋላ የሚጠባበሰውን መጠባበስ፤የሚበስለውን ማበስል ትጀምራለች።የምሳ ሰዓቱ ከመድረሱ በፊትም ምግቦቹን ጨራርሳ ዝግጁ ማድረግ እንዳለባት በየሰዓቱ ማብሰያ ክፍሉ ከምትመላለሰው አሰሪዋ ትዕዛዝና ማስፈራርያ ስለሚደርሳትም በጥፍሯ ቆማ ሁሉንም ዝግጁ ታደርጋለች።የምሳ መስተንግዶው እንዳለቀ ከምሳ የተራረፉ ምግቦች ላይ ተጨማሪ ለእራት የሚሆኑ ምግቦች ዝግጅት ይጀመራል።
ከቤተሰቡ አባላት ውጪ የሚጋበዙ እንግዶች ሲኖሩ ደግሞ የሚሰራው የዓይነት ምግብ ስለሚበዛ መሰረት ትንፋሽዋ እስኪቆም ድረስ ሰርታ ግዴታዋን ትወጣለች።አልፎ አልፎም የአሰሪዋ ዘመዶች ጋር በውሰት ሄዳ ምግብ አብስላና ቤት አጽድታ ትመለሳለች።ከእራት በኋላም ልብስ መተኮስና ልጆችንም ማጫወት ከመሰረት ግዴታዎች ውስጥ የተካተቱ ናቸው።በአጠቃላይ የዕለቱ ሥራ ከምሽቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ ያልቃል።በድካም የዛለውን አካሏን ይዛ ከአራት ሰዓት ለበለጠ ጊዜ መኝታዋ ላይ በድን አካልዋን ይዛ ትዘረራለች።እንቅልፍዋን በወጉ ሳትጨርስ ‹‹አላህ አክበር›› ከማለቱ በፊት ለቀጣዩ ቀን ስራ እራሷን ታነቃለች።በዚህ አይነት ሁኔታ አምስት ዓመታትን በዱባይ ያሳለፈችው መሰረት ከዚህ በላይ በዚህ ስቃይና መከራ ህይወት ውስጥ መክረም አልቻለችም።ቤተሰብ ታሟል በሚል ሰበብ መሰረት ወደ ሀገሯ ለመመለስ ፍላጎት እንዳለት አሰሪዋን ጠይቃ ለመመለስ ብትሞክርም ከአሰሪዋ በጎ ምላሽ አላገኘችም።እንዳውም መውጫ መግቢያዋን በመከታተል ይበልጡኑ ከአሰሪዋ የሚደርስባት ጫና በረከተ።ቀደም ሲል አልፎ አልፎ ትፈቅድላት የነበረውን ወደ ቤተሰቦችዋ የምትደውለውንም ስልክ አቋረጠችባት።በዚህ ተስፋ ያልቆረጠችው መሰረት ነጋ ጠባ ወደ ሀገሯ የምትመለስባቸውን ስልቶች ስታወጣና ስታወርድ ቆይታ በመጨረሻ ከውጭ የመጡ እንግዶችና ቤተዘመዶች የተሰባሰቡበትን አጋጣሚ በመጠቀም እናቷ መታመማቸውን በማስረዳት ወደ ሀገሯ መመለስ እንደምትፈልግ እያለቀሰች ተናገረች። የቤተሰቡ አባላትና ቤተዘመዱ በሁኔታው ስሜታቸው ስለተነካ አሰሪዋ እንድትፈቅድላት ጫና አደረጉባት። አሰሪዋም በሁኔታው ስለተናደደች ደመወዝዋን ቆርጣ ወደ ሀገሯ ላከቻት።
መሰረት የሀገሯን ምድር እንደረገጠች የተሰማት ደስታ ልዩ ነበር።ለዚህ ያበቃትን አምላክን በማመስገንም የአገሯን አፈር ዝቅ ብላ ስማለች። ከባርነት የወጣች ያህል ነጻነት ተሰምቷታል።ደሴ ስትደርስም በወዳጅ ዘመድ ታጅባ ቀናትን አሳለፈች።ቀናትም እያለፉ በወራት ተቆጠሩ።ዓመትም ደፈነች። በዚህ ሁሉ መሃል አረብ ሀገር ሰርታ በቋጠረቻት ገንዘብ የቤተሰቦቿን በርና መስኮት ቀየረች።ለእራሷም ቢሆን ቀናትን ገፋችበት።ገንዘብ ካልሰሩበት ስር የለውምና መሰረት መልሳ የቤተሰብ ጥገኛ ሆነች።ከእጅ ወደ አፍ በሆነው የቤተሰቦቿ ኑሮ ላይ ተጨማሪ ሸክም መሆኗ የራስ ምታት ሆነባት።ዳግም በኑሮ ተፈተነች።በመጨረሻም ወደ ጠላችውና እርም ብላው ወደ ነበረው የአረብ ሀገር ለመመለስ ወሰነች።ዳግም ወደ አረብ ሀገር በረረች።
ኩዌት
ኩዌት ሁለተኛዋ የስደት ከተማዋ በመሆኗ እንደቀድሞው ጉዞዋ አልተደናገረችም።እንደተለመደው የኩዌትን ውበት ሳታጣጥም አሰሪዎችዋ እያዋከቡ ወሰድዋት።አሁን የተሻለው ነገር ቋንቋ መቻሏ ነው።በዱባይ በቆየችባቸው አምስት ዓመታት አተረፍኩት የምትለው ነገር ቢኖር አረቢኛ ቋንቋን አቀላጥፋ መናገር መቻሏ ነው።ስለሆነም ከአዳዲሶቹ አሰሪዎችዋ ጋር ለመግባባት ጊዜ አልወሰደባትም።
የአረብ ሀገር ቀጣሪዎች በብዙ መልኩ የሚመሳሰሉ በመሆኑ መሰረት የአሰሪዋም ባህሪ ሆነ የምትሰራቸው ሥራዎች ብዛትና አይነት አዲስ አልሆኑባትም።እንደተለመደው ሌሊት ተነስቶ ቁርስ መስራት፤ቤት ማጽዳት፤ለምሳ እና እራት የሚሆኑ ምግቦችን ማብሰለ፤ልብሶችን መተኮስና ልጆችን ማጫወት ኩዌትም የጠበቋት ግዴታዎቿ ናቸው። ከአረብ ሀገር ውጪ አማራጭ እንደሌላት አይምሮዋን ማሰማኗ እና የአረብ ሀገራትን ጠባይ በመላመዷ ምክንያት በኩዌት የነበራት ቆይታ አስቸጋሪና ፈታኝ ቢሆንም እንደዱባዩ ተስፋ አስቆራጭ አልነበረም።ይሁን እንጂ በዱባይ የነበራት የሥራ ጫና የፈጠረባት የወገብ ህመም በኩዌት እንደልቧ አላንቀሳቅሳት አለ።የተለመደውን የዕለት ግዴታዋን ለመወጣት እያቃታት መጣ።ይህን ሁኔታዋን ደግሞ የሚታገሳት ባለመኖሩ ቢያማትም ያላመማት በመምሰል እንደምንም ከበሽታዋ ጋር ሁለት ዓመታትን ገፋች።በሽታዋ ግን እየበረታባት በመምጣቱ ከዚያ በላይ በኩዌት መቆየት አልቻለችም።በቂ ጥሪት ሳትቋጥርም እንደገና ወደ ሀገሯ ለመመለስ ተገደደች።
ሀገሯ ከገባችም በኋላ የወገብ ህመሟ ለውጥ ከማሳየት ይልቅ እየባሰባት በመሄዱ ኩዌት ሰርታ በቋጠረቻት ጥቂት ገንዘብ ህክምናዋን መከታተል ጀመረች። በቂ እረፍት ባለማግኘቷ የመጣ ችግር እንደሆነ ከሐኪሟ በቂ ምክር አግኝታ ህመሟን ማስታገስ ቻለች።በቤተሰብ ድጋፍ ጭምር ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከህመሟ ተፈወሰች።መሰረት ወደ ጤንነቷ እንደተመለሰች ያለሥራ መቀመጧ እንቅልፍ ይነሳት ጀመር።በተለይም ቤተሰቦችዋን እረዳለሁ ብላ ሄዳ ሳይሳካላት ታማ መጥታ እንደገና ቤተሰቦችዋን ለወጪ መዳረጓ ሆድዋን ያብከነክነው ጀመር። በየዕለቱ ፈቅ የማይለውን የቤተሰቦችዋን ህይወት ስትመለከትም እዚህ መቆየት እንደሌለባት እንደገና እራስዋን አሳመነች። ለሶስተኛ ጊዜም ከነምሬቱም ቢሆን የአረብ ሀገርን ለመርገጥ ተነሳች።
ሳኡዲ አረቢያ
መሰረት ከበረከቷ ለመካፈል በነዳጅ ወደ በለጸገችው ሳኡዲ አረቢያ አቀናች። በዱባይ ለአምስት ዓመታት፤ በኩዌት ለሁለት ዓመታት በድምሩ ለሰባት ዓመታት ከቆየችባቸው የአረብ ሀገራት ያተረፈችው የአረብኛ ቋንቋንና የወገብ ህመምን ነው። የሳኡዲ ዕጣ ፋንታዋን ገና ጊዜ የሚወስነው ነው። መሰረት ሳኡዲን ጨምሮ በቆየችባቸው የአረብ ሀገራት የአረቦቹ የተንደላቀቀ አኗኗር ያስገርማታል፤ ያስቀናታል። ሳይወጡ፤ ሳይወርዱ በሃብት መንበሽበሻቸው ያስደምማታል። የአገሯን ሰዎች አኗኗር መለስ ብላ ታይና ከንፈሯን ትመጣለች፤‹‹ምናለ ግማሹን እንኳን ለእኛ ቢሰጠን ›› ብላ በወቀሳም፤በምስጋናም መልክ ወደ ፈጣሪዋ ታንጋጥጣለች።
የሳኡዲ አሰሪዎቿም ልክ እንደቀድሞዎቹ ሁሉ የቤት ሰራተኛ የሚደክማት የማይመስላቸውና ሰውን እንደማሽን የሚቆጥሩ ሞልቃቆች ናቸው፡የድሃ መከራው የትም ይሁን የትም ተመሳሳይ ነውና መሰረት ሳኡዲም የገጠማት ልፋትና ውጣ ውረድ ተመሳሳይ ነበር። ሳኡዲን ለየት የሚያደርገው ደግሞ ህጻናቱ ያላቸው ባህሪ እጅግ አስቸጋሪና እልህም አስጨራሽ መሆኑ ነበር። በዚህ ላይ የሳኡዲ ቤተሰቦች በልጆቻቸው የመጣን የሚታገሱበት ሀሞት ስለሌላቸው በህጻናቱ ድርጊት ቆሽትን ከማሳረር እና ደህነትን ከመርገም ውጪ ሊመጣ የሚችል ነገር አልነበረም።መሰረት በሥራው ብዛትና በህጻናቱ አመል እየተማረረች አንድ ዓመት አስቆጠረች። ልክ በአንድ ዓመቷ ግን እናቷ ማረፋቸው በስልክ ተደውሎ ተነገራት።ለፍተው ያሳደጓት እናቷን አንድ ቀን እንኳን ያማራቸውን ሳታደርግላቸው ሞት ቀደማት።አንጀቷ ብጥስ አለ።መኞትና ተስፋዋ እንደጉም በነነ።ተስፋን አዝላ መጥታ ተስፋዋን አጥታ ወደ ሀገሯ ተመለሰች።
ከአረብ ሀገራት ተመላሾችን እንደግፋለን
መሰረት ብዙ የለፋችለትና መስዋዕት የከፈለችበት የአረብ ሀገር ሥራ ከስም በስተቀር አንዳችም ነገር ጠብ አላደረገላትም። እናቷን እንኳን አጠገባቸው ሆና ሳታስታ ምማቸውና የአማራቸውን ሳትሰጣቸው እንዲሁ ባክና ቀርታለች። በዚህ ስሜት ውስጥ እያለች ግን መንግስት ከአረብ ሀገራት የተመለሱትን ዜጎች እንደሚደግፍ ጎረቤቶቿ አበሰሯት።አስዋም በተስፋ ተሞልታና አረብ ሀገር ያየችውን እንግልት በአገሯ ልትካስ መሆኑን በማሰብ ወደ ቀበሌ ሄዳ ከአረብ ሀገር ተመላሽ መሆኗን አመለከተች። ከጥቂት ቀናትም በኋላ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መሰረትና ሌሎች 25 ከአረብ ሀገር ተመላሾችን በላውንደሪ ሥራ በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ አደረገ።
የነመሰረት ዋነኛ ሥራ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎችን ልብስ በተመጣጣኝ ዋጋ እያጠቡ ገቢ ማግኘት ነው። ይሁን እንጂ የተሰጣቸው ቦታ አመቺ ካለመሆኑም በተጨማሪ ገቢውም ዝቅተኛ መሆኑም መሰረትና ጓደኞችዋ ይናገራሉ። ወደ ሥራው ከገቡ አምስት ወራት ያለፋቸው ቢሆኑም እያንዳንዳቸው በአምስት ወራት ውስጥ ያገኙት ከመቶ ብር የበለጠ አይደለም። ብዙ ተስፋ ያደረጉበት በሀገር ሰርቶ የመለወጥ ምኞት ከንቱ ሆኖባቸዋል።‹‹ከአረብ ሀገር ተመላሾችን እንደግፋለን ››፤‹‹ዜጎች በአገራቸው ሰርተው መለወጥ ይችላሉ›› የሚሉት ንግግሮች ለመሰረትና ጓደኞችዋ ከቃላት ባለፈ ዳቦ አላስገኙላቸውም። በተደጋጋሚም የተሻለ ነገር እንዲፈጠርላቸው ቢወተውቱም ሰሚ ጆሮ አላገኙም። ይህ ደግሞ መሰረትና ጓደኞችዋን በአገራቸው ዳግም ተስፋ ቆርጠው ለአራተኛ ጊዜ ወደ አረብ ሀገራት ለመመለስ ልባቸው እንዲነሳሳ አድርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
እስማኤል አረቦ