ባንተ ላይ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ የሚለው ወርቃማ አባባል በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ያለ ይመስለኛል:: አንዱ ሌላውን መረዳት አለበት። ስግብግብነት ማንንም አይጠቅምም። እንደ ጥቁር አባይ ምንጭነቷ ኢትዮጵያ የመጠቀም መብቷን ማግኘት አለባት።ፍትሃዊ አጠቃቀም ካለ ለሁሉም ይበቃል። እስካሁን ባለው እውነታ ኢትዮጵያ የወንዙ በረከት ለሁላችንም ይበቃል የሚለውን አቋም እያራመደች ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ለሁላችን ይበቃል ስትል መጠቀም ያለባትን ያህል እየተጠቀመች እንጂ ሰሞኑን በግብጽ ፊታውራሪነት በእነ አሜሪካ እየተሞከረ እንዳለው በተጽእኖ እየተንበረከከች መሆን የለበትም።
በዚህ አጋጣሚ የተለያዩ ተጽእኖዎች እና መደለያ ሳይበግራቸው ለእውነት ብለው የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እየደገፉ ያሉትን ግለሰቦች በሙሉ ከመቀመጫ ተነስቶ ማመስገን ያስፈልጋል።
ጥቁር አባይ ከኢትዮጵያ አሥራ ሁለት ዋና ዋና የወንዝ ተፋሰሶች አንዱ ነው። በዓለም ረጅሙ ወንዝ ከሆነው አባይ ወንዝ (Nile) አጠቃላይ ውሀ 86% ይይዛል። ቀሪው ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን አቋርጦ ወደ ሜዲትራንያን ባሕር ከሚፈሰው ነጭ አባይ የሚገኝ ነው።
የአባይን ውሃ አጠቃቀም አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ጋር ከተደረጉ ስምምነቶች አንዱ እ.አ.አ በ1902ዓ.ም በእንግሊዝ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመው የአዲስ አበባ ስምምነት ነው። እንግሊዝ ስምምነቱን ቅኝ ግዛቶቿ የነበሩትን ሱዳንን እና ግብጽን ወክላ ነው የተፈራረመችው። በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝም ሆነ በማንኛቸውም ገባሮቹ ላይ ምንም አይነት ግንባታ ማካሔድ አትችልም የሚል ነበር።
ይኼ አሁን አይሠራም። ምክንያቱም ስምምነቱ የቅኝ ግዛት ውል ከመሆኑም ባሻገር በቅኝ ግዛት ያልተገዛችውን ብቸኛዋን ጥቁር አፍሪካዊት ሀገር በምንም ዓይነት መልኩ በቅኝ ገዢዎች ውል እንድትገዛ የሚያደርግ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የሚመጥን አይደለም። ከኢትዮጵያ ይልቅ መዳረሻ ግብጽ እና ሱዳንን የሚጠቅም መነሻይቱን ሀገር ክፉኛ የሚጎዳ ውል ነው። ይህ አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን አይሠራም። ታሪክ ግን በፍርደገምድል ውልነቱ ይዘክረዋል።
ይህም ከአዲስ አበባው ስምምነት 13 ዓመታት በፊት ከኢጣልያ ጋር ከነበረው ውጫሌ ስምምነት ዓንቀጽ 17 የኢጣልያንኛ ቅጂ ጋር ያመሳስለዋል። ሁለቱም ውሎች የአንድ ወገንን ስግብግብነት ብቻ ስለሚያሳዩ አሁን ፉርሽ ናቸው።
የአባይ ውሃ በተለይ የግብጽ የአባይ ውሃ አጠቃቀምን የተመለከቱ በ1929 እ.ኤ.አ እና በ1959 እ.ኤ.አ የተደረጉ ውሎች /ስምምነቶችም አሉ። እነዚህም ስምምነቶች የላይኛ ተፋሰስ ሀገሮችን (ምንጮችን) በተለይ የኢትዮጵያን ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገቡ አልነበሩም። ስለዚህም በዚሁ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ተራማጅ ሀገሮች በፍጹም ተቀባይነት የላቸውም- ሁሉንም ከሞላ ጎደል በእኩልነት የሚጠቅሙ አይደሉምና። ለተቀባይነት ማጣቱ በቂ ምክንያት አለ።
ኢትዮጵያ አሁን በሕዝብ ብዛት ናይጀሪያን ተከትላ ሁለተኛ ነች። ግብጽ ደግሞ ሦስተኛ ነች። በፊት ግብጽ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ሦስተኛ ነበሩ። በሕዝብ ቁጥር መበላለጡ ብዙም አያስከፋም። ሁለተኛ የሆነውም ሦስተኛ የሆነውም ግን በልቶ ማደር አለበት። በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ የምትታወቀው በድርቅ እና በአትሌቶቿ ነው። ሌላ ቀርቶ በዓለማችን በስፋት ከሚሰራጩ የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት አንዱ የሆነው ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት የረሃብ/ የድርቅ ምሳሌ ያደረገው አትዮጵያን ነው። የቱንም ሃይማኖት ይከተል ከየትኛውም ብሔረሰብ ይገኝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህ እንዲቀጥል አይፈልግም። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ባትሆን እንኳ ቢያንስ ከ110 ሚሊዮን የበለጠውን ሕዝቧን ለመመገብ እንደ አትሌቶቿ መሮጥ አለባት።
ይሁን እንጂ አሁን ሀገሪቱ ዜጎቿን ለመመገብ በብዙ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር ታስገባለች። መንግሥት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ቀስ በቀስ በመቀነስ በሀገር ውስጥ ስንዴ ለመተካት አስቦ እየተሰራ እንደሆነም ይታወቃል። ይህ ጥረቱ መጣ ቀረ በሚባል ዝናብ ብቻ ይሳካ ማለት አይቻልም- ሌሎችን ሳይጎዱ እንደ አባይ ያሉ ወንዞችን ለመስኖ ተግባር በመጠቀም እንጂ። ቀደም ሲል የጠቀስነው የአዲስ አበባ ስምምነት ግን በገዛ ወንዛችሁ ድርሽ አትበሉ ያለ ነበር። በነገራችን ላይ ጉዳዩን በግለሰብ ደረጃ ካወረድን በምግብነት የምንጠቀመው ማርማላታ በግብጽ የተሰራ ነው-ኢትዮጵያ ውሃውን ግብጽ ደግሞ በመስኖ የለማ ፍራፍሬውን አቅርባ ማለት ነው።
በእርግጥ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋነኛ አላማ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንጂ መስኖ ልማት አይደለም። የኤሌክትሪክ ኃይሉ በዋነኝነት ኢትዮጵያን ከዚያም እንደ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሳኡዲ አረቢያና ሱዳንን ይጠቅማል ተብሎ ነው የታሰበው።
እናም የአስዋን ግድብ፣ የመርዌ ግድብም ሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የየራሳቸው ዓላማ ያላቸው ናቸው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል እያመነጨ እግረ መንገዱንም አላስፈላጊ ደለልን ለግብጽ እና ለሱዳን ይከላከላል። የአስዋን እና የመርዌ ግድቦች ግን ኢትዮጵያን አንዳች ነገር ይጠቅማሉ ብዬ አላስብም።
ሦስቱ ሀገራት ምንም አይነት ፍላጎት ይኑራቸው የወንዙን የውሃ መጠን ከፍ እና ዝቅ የማድረጉ ሚና የተፈጥሮ ነው። ግብጽ ግን የሕዳሴ ግድቡ ቋት ገና ውሃ መያዝ ሳይጀምር ለኔ የሚደርሰው ውሃ ከዚህን ያህል ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር ማነስ የለበትም እያለች ነው። ከውሃ ሙሌቱ ጋር በተያያዘ ግብጽ የምታቀርበው የጊዜ መጠንም አንድ ትውልድን በከንቱ እንዲያልፍ የሚያደርግ ነው።
ግብጽም ደግሞ የኢትዮጵያን ፍላጎት መረዳት አለባት። ኢትዮጵያ በጭለማ ስትዋጥ፣ ፋብሪካዎቿ በኃይል እጥረት ሲያንጎላጁ ቀን በጸሐይ ሌሊት በጨረቃ ብርሃን ተጠቀሙ የፋብሪካ ምርት ከኔ ግዙ ኃይል እንዳታመነጩ የማለት ምንም መብት የላትም። ሰሞኑን በዋሺንግተን፣ በአዲስ አበባ እና በካይሮ እየተደረጉ ካሉ ድርድሮች ግን ግብጽ እኔ ብቻ ልጠቀም እናንተ የራሳችሁ ጉዳይ እያለች ይመስላል። ኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎች ግን ይህን አልተቀበሉም። የኢትዮጵያውያን ባህልና ታሪክ እንደሚያሳየውም ሁልጊዜም ቢሆን ኢፍትሃዊነትን መዋጋት በመሆኑ ግብጽና አደራዳሪዎቿ የጫኑባትን ፍርደ ገምድል ውሳኔ ለመቀበል የሚያስችል ጫንቃ የላትም።
ተጽእኖ ማሳደሩ በአሜሪካ መንግሥት እና በዓለም ባንክ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በታዛቢነት የገቡት እነ አሜሪካ ውል አርቅቆ እስከመላክ ደርሰዋል። ተጽእኖውን ለመቀነስ እና ብሔራዊ ክብራችን ማስጠበቅ የኛው ኃላፊነት ነው። የወከልነውም በሁሉም ደረጃ ያሉ ተደራዳሪዎቻችንን ነው። ተደራዳሪዎቻችን እስካሁን አኩርተውናል። በዚህም እንደሚቀጥሉ እተማመናለሁ።
የሦስተኛ አካል ጣልቃ መግባት የግድ ከሆነም የነ ግብጽን ተጽእኖ ለመቀነስ ኢትዮጵያ እንደጀመረችው ደቡብ አፍሪካን የመሰሉ ገለልተኛ መንግሥታትን አደራድሩን ማለት አለባት። ሩስያን በአሜሪካ፣ የዓለም ባንክን በቻይና ብንተካስ የሚሉ የዋሐን ሀገር ወዳዶች አጋጥመውኛል። ግብጽ ማለት ለሩስያ በአፍሪካ ዋነኛ የምጣኔሀብት አጋር እና የጦር መሳሪያ ሸማች መሆኗን ማስታወስ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን ከነ አሜሪካ እና ከነ ሩስያ ምረጪ ማለት ለኔ ጉማሬ ይደፍጥጥሽ ወይስ አዞ ያኝክሽ እንደማለት ነው::ባይሆን አፍሪካ ህብረትን በአደራዳሪነት ብትመርጥ የተሻለ እንደሆነ ይሰማኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)