የደራሲዎች ሕይወት ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው። በእርግጥ የሁሉም ደራሲዎች አይደለም፤ የአብዛኞች ነው ማለት ግን እንችላለን። ይሄውም ሕይወታቸው የቅንጦት አለመሆኑ ነው። ለቁሳዊ ነገሮች ብዙም ቦታ የላቸውም። አለባበሳቸውም ሆነ አካላዊ ገፅታቸው ዘረክረክ ያለ ነው። ይሄ ውጫዊ መለያቸው የተፈጠረው በውስጣዊ ባህሪያቸው ነው። ለውጫዊ ነገሮች ብዙም ትኩረት ስለማይሰጡ ነው።
ደራሲዎች ልዩ የማስተዋል ችሎታ አላቸው። አንድ ደራሲ ሥራው ተወዳጅ የሚሆነውም በዚህ ልዩ የማስተዋል ብቃቱ ነው። ሌላው ሰው ሲኖርበት የነበረውን ቦታ ደራሲ ግን አንድ ቀን አይቶ ብዙ ነገር ይጽፍበታል። ያ ደራሲ የጻፈውን ነገር ሌላው ሰው ግን ልክ አይቶት እንደማያውቅ ሁሉ ‹‹እንዲህም ነበር እንዴ!›› እያለ እንደ አዲስ ያየዋል። ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) 70 ደረጃ የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ያወጣ ሰሞን ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም አንድ ነገር ጽፎ ነበር። ‹‹ማንም ሲወጣበትና ሲወርድበት የኖረውን 70 ደረጃ ቴዲ በልዩ ጥበብ ገለጸው፤ ከዚህ በኋላ 70 ደረጃን በድሮው አይናችን አናየውም›› ነበር ያለው ።
የበዕውቀቱ አስተያየት ልክ ነበር። የቴዲ አፍሮ 70 ደረጃ ነጠላ ዜማ ከወጣ በኋላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ 70 ደረጃን እንደ አዲስ ማየት ጀመረ። ንግድ ቤቶች በስሙ መሰየም ጀመሩ። የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች 70 ደረጃን ይቀርጹ ጀመር። ፊልሞች ቦታውን ማሳየት ጀመሩ። 70 ደረጃ ግን ብዙ ዓመታት የኖረ ቦታ ነበር።
ደራሲ እንዲህ አይነት አካላዊና መልከዓ ምድራዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ስሜቶችንም በልዩ አስተውሎት ይገልጻል። ራሳችን የምናደርገውን ነገር ይገልጽልናል። የሰዎችን ስነ ልቦና ይረዳል። ለዚህም ነው ሥራዎቻቸውን ስናነብ የምንመሰጠው።
እነዚን ሁሉ ነገሮች ለማስተዋልና ሀሳብ ለማግኘት ደራሲ ማንበብ አለበት። ማንበብ ሲባል የግድ መጽሐፍ፣ ጋዜጣ ወይም መጽሔት… በአጠቃላይ የተጻፈ ነገር ብቻ ማለት አይደለም። ሰው ይነበባል፣ ተፈጥሮ ይነበባል፣ ቁስ አካል ሁሉ ይነበባል፣ የሰው ስነ ልቦና ይነበባል። ይሄ ነው የደራሲ ብቃት።
ርዕሰ ጉዳያችን ስለሴት ደራሲያን ለማውራት ነው። ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች ቀን ይከበራል። ይሄን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ስኬታማ ሴቶች ስም ሲጠራ ይሰማል። በመገናኛ ብዙኃንና በልዩ ልዩ መድረኮች ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ፤ ለሌሎች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ ተሞክሯቸውም ሲተረክ ይሰማል። እዚህ ላይ አንድ የተሰለቸ አገላለጽ አለ። በተደጋጋሚ ‹‹ሴቶች ይችላሉ!›› ይባላል። ምን ማለት ይሆን? ሴቶች አይችሉም የሚል አመክንዮ አለ ማለት ነው? እንደእኔ ሴቶች ይችላሉ የሚለው አገላለጽ ፀሐይ በምሥራቅ ትወጣለች ብሎ እንደማስረዳት ነው።
ለመሆኑ ማህበራዊ ሕይወታችንና ስነ ልቦናችን ሴቶች ደራሲ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው? አንድ ደራሲ የሚደርስበት ቦታ የመድረስ ዕድል አላቸው? ነገሮችን ለማስተዋል የሚያስችል ሁኔታ አለ?
አንድ ልብ ያልተባለ ችግር ይታየኛል። በብዙ ነገሮች የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው። ያ የሆነው ግን በተፈጥሮ ችሎታ ልዩነት ሳይሆን በማህበራዊ አኗኗር ውስጥ በተፈጠረ ልዩነት ነው። መንግስት ለራሱ ፕሮፖጋንዳ በሚያዘጋጃቸው የሴቶች መድረክ ላይ በድሮ ሥርዓት ጨቋኝነት ነው ሲል ይሰማል። ዳሩ ግን የሴቶች ቀን ሲከበር ምሳሌ የሚነሱት በዚያ ጨቋኝ በሚባለው ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ሴቶችን ነው። በሌላ በኩል ይሄ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም የሚታይ ነው። አሁን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ እንመልከት።
ሴቶች በብዙ ነገሮች ከወንዶች እኩል እንዳይሳተፉ ያደረገው ማህበራዊ አኗኗራችንና ስነ ልቦናችን ነው። እንደ ማሳያ የምጠቀመው አሁን በማስተዳደር ላይ ባለው መንግስት ሥርዓት ውስጥ ያስተዋልኳቸውንና እየሆኑ ያሉ ነገሮችን ነው። አንዱ ችግር መስሎ የሚታየኝ ቅድሚያ ለሴቶች በሚል ሰበብ ሴቶች ላይ የደካማነት ስነ ልቦና መፍጠር ነው። ‹‹አልችልም እንዴ!›› ብለው ራሳቸውን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ነው። ግልጽ ለማድረግ አንድ ምሳሌ ላንሳ።
የዛሬ ዓመት ነው። 123ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ለማክበር ጋዜጠኞች ወደ ዓድዋ እየተጓዝን ነው። በጉዟችን ውስጥ ታሪካዊ ቦታዎች ይጎበኛሉ። ከእነዚህም አንዱ ወረኢሉ ነው። አካባቢው ምቹ የመኪና መንገድ የለውም። አንድ ቦታ ላይ ስንደርስ መንገዱ ለመኪና አስቸጋሪ ስለሆነ በእግር ለመውረድ ተገደድን። እዚህ ላይ ነው አሁን የምነግራችሁን ነገር የታዘብኩት።
ልክ ጉዞ ስንጀምር ‹‹ሴቶች እዚህ ቆዩ›› ተባለ። ቦታውን የሚያውቁ ሰዎች ‹‹ኧረ ቅርብ እኮ ነው ይሂዱ›› አሉ። ይህኔ ‹‹እናት የላችሁም? እህት የላችሁም? እንዴት በሴት ልጅ ላይ ትጨክናላችሁ?›› የሚሉ ቁጣዎች ተነሱ። ይሄ ሁሉ ሲባል ነፍሰ ጡርም ሆነ በዕድሜ የገፋች ሴት የለችም። ሁሉም ወጣቶችና ጤነኛ ናቸው። በነገራችን ላይ ወደ ቦታው ስንወርድ አንድም ሴት አልቀረችም፤ ሁሉም አብረው ወረዱ። ከአሁን አሁን አደገኛ የተባለውን ቦታ አየዋለሁ ስል የሚጎበኘው ቦታ ላይ ደረስን። እንኳን ለወጣት ለአዛውንት ሴቶችም የሚያስቸግር ቦታ አልነበረም።
አሁን የእኔ ጥያቄ የግድ ቦታው አደገኛ መሆን አለበት አይደለም፤ ትንሽም ቢሆን የሚያስቸግር ከሆነ መቸገር የለባቸውም። ዳሩ ግን ይሄ እንዲህ አይነት ድጋፍ ሴቶችን አይጎዳም ወይ ነው። እያወራን ያለነው ስለሴት ደራሲነት ነው። ታዲያ ያንን ቦታ እንዳታይ የተከለከለች ሴት እንዴት ነው የታሪክ ፀሐፊ የምትሆነው? ያንን ቦታ እንዳታይ የተከለከለች ሴት እንዴት ነው ስለአገሯ ነባራዊ ሁኔታ ከወንዶች እኩል የምታወራው? ልዩ ምልከታና ሀሳብ የሚገኘው ደግሞ ከእንዲህ አይነት ቦታዎች እንጂ ከትልልቅ መዝናኛ ቦታዎችና ከሆቴሎች አይደለም። ደራሲና ጋዜጠኛ የሚጽፈው ከእንዲህ አይነት ቦታዎች እንጂ ከትልልቅ የገበያ ማዕከላትና ከጌጣጌጥ ቤቶች ብቻ አይደለም።
ለሴቶች ቅድሚያ መሰጠት አለበት። እንዲህ አይነቱ ግን ቅድሚያ መስጠት ሳይሆን ቅድሚያ መከልከል ነው። እስኪ የአምስት እና የአሥር ደቂቃ መንገድ በእግር ይሂዱ ማለት ምኑ ነው ‹‹እህት የላችሁም? እናት የላችሁም?›› የሚያሰኘው? እናቴ ወይም እህቴ በዚያ መንገድ ቢሄዱ ምን ይሆናሉ?
ይሄ የሴቶች ጉልበት ብዝበዛ ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይደለም። ይሄ ፆታዊ ጥቃት አይደለም። አንድ ሜትር እንኳን በእግሯ የማትሄድ ሴት ደራሲ ልትሆን አትችልም። በመጽሐፍ ውይይቱ ለምን የሴት ደራሲያን ቁጥር አነሰ የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ይሰማል። ዳሩ ግን ሴቶች እንዲጽፉና እንዲያስተውሉ የሚያደርግ ማህበራዊ ስነ ልቦና የለንም።
የሆነው ሆኖ ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ የጻፉ ብዙ ሴቶችም አሉን። እነዚያ ሴቶች እንዴት ደራሲ ሆኑ ካልን ወንዶች በዋሉበት መዋል ስለቻሉ ነው። እነዚህን ሴት ደራሲዎቻችንን ማየት አለብን።
ሕይወት ተፈራ
ሕይወት ተፈራ ለብዙ ሴቶች ምሳሌ የምትሆን ናት። ለዚያውም ሴቶች ብዙም አይሳተፉበትም በሚባለው ፖለቲካ ውስጥ የተሳተፈች። መሳተፍ ብቻም ሳይሆን የኖረችበትን ዘመንና ያሳለፈችውን ሕይወት የጻፈች። የሕይወት ተፈራን ሕይወት ካየን ‹‹ሴት ስለሆነች›› ከሚለው አጥር ውስጥ እንወጣለን። ምክንያቱም የተጋፈጠቻቸው ፈተናዎች ሁሉ ከባድ ነበሩ።
ሕይወት ተፈራ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረች ናት። ኢህአፓንና የኢህአፓን ዘመን ያስተዋለችና የተሳተፈችበት ናት። ከ1965 ዓ.ም የኢህአፓ የወጣቶች ሊግ ጀምሮ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች። ‹‹ማማ በሰማይ›› በሚለው መጽሐፏ ያን ሁሉ ታሪክ ነግራናለች። ለስምንት ዓመታት ያህል እስር ቤት ውስጥ ቆይታለች።
መጽሐፏ ብዙ ተብሎለታል። ሌሎች መጽሐፎችም አሏት። በነገራችን ላይ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሴት ደራሲዎችን የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸውን መዘርዘር ሳይሆን ስማቸውን እየጠቀሱ ‹‹እንዲህም አሉን›› የሚለውን ማሳየት ነው። በሥራዎቻቸው ዝርዝር ላይ በሌላ ጽሑፍ መመለስ ይሻላል።
ሽቶ መዝገቡ
‹‹ሰው በመሆኔ ደከምኩ›› በሚለው መጽሐፏ ትታወቃለች። ይህ መጽፍ ከ50 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ ከስድስት ዓመት በፊት በ2006 ዓ.ም ከ48 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ታትሞ ለገበያ ቀርቦ ነበር። ሽቶ መዝገቡ ገና በለጋነት ዕድሜዋ በኢትዮጵያ የባህል አብዮት ለማምጣት የታገለችና የጻፈች ናት። በነበረው ኋላቀር አስተሳሰብ ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረው ነገር እንዲቀየር ትሰራ ነበር፤ የአሁኑን ዘመንም ከ50 ዓመታት በፊት ቀድማ ተንብያለች። ‹‹መማር እንጂ ለመማር ብሎ መማር አይገባም›› ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረው ማህበራዊ አስተሳሰብ ለመቅረጽ ጥረት ያደረገች ናት።
የዝና ወርቁ
‹‹መፍቻው እና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች›› የሚል መጽሐፍ አላት። ከ12 እስከ 18 ዓመት ባሉ ታዳጊ ሴቶች ስነ ምግባር ላይ ያተኩራል። በነገራችን ላይ ይሄ መጽሐፏ በነጻ ታድሏል። ለ30 ያህል ትምህርት ቤቶች ታድሏል። የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ላላቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች ተሰጥቷል።
ፀሐይ መላኩ
የሥነ ሥዕል፣ የሥነ ግጥም እና የእደ ጥበብ ሙያተኛ የሆነችው ደራሲ ፀሐይ መላኩ ከአሁን ቀደም አንጉዝ፣ ቋሳ እና ቢስራሔል የተሰኙ ረጅም ወጥ ልቦለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅታለች። ‹‹እመ ምኔት›› የተሰኘው መጽሐፏ ደግሞ በቤተ ክርስቲያንና በገዳማት ታሪክና ትውፊት ላይ ያተኩራል። መጽሐፉን ከመጻፋቸው በፊት ሐይቅ እስጢፋኖስ አንድ ሱባኤ ከመቀመጣቸው በተጨማሪ ዝቋላ፣ አሰቦት፣ ራማ ኪዳነ ምሕረት፣ ዋሸራ እና ሌሎች ገዳማትን በመጎብኘት በመነኮሳት አኗኗር ላይ ጥናት በማድረግ አሥር ዓመታት ያህል ፈጅቶባታል።
ከበደች ተክለአብ
ሠዓሊ ናት፣ ቀራጺ ናት፣ ገጣሚ ናት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር ናት። በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ብላ ነበር።
‹‹…በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት። ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግስት፤ የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት። ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝ። ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን። በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን። በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር። አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ነበር። ይህ መሆኑን ሳናውቅ ነው፣ በእግራችን ጉዞ የጀመርነውና የሶማሌ መደበኛ ጦርና የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን ገባን። በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን። በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍናቸው በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነው። በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በአለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት አግባቢነት ይመስለኛል፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ። እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን…››
የእነዚህን ሴት ደራሲያን ሕይወት መቀንጨብ ያስፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም። ሴትም ትሁን ወንድ ደራሲነት አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ እንደማይሆን ነው። አንድ ደራሲ ያላየውንና ያልሰማውን ሊጽፍ አይችልም። እርግጥ ነው ደራሲ ለመሆን ሲባል መጎሳቆልና መንገላታት ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ ግን አካባቢን እንኳን ለማስተዋል የሚያስችል እንቅስቃሴ መኖር አለበት። ይሄ ደግሞ ለደራሲነት ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም ሥራ ቢሆን አካባቢን ማስተዋል የግድ ነው። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹ሴቶችና ሳይንስ›› በሚል ባዘጋጀው አንድ መድረክ ላይ አንዲት ጥናት አቅራቢ ይህንኑ ጉዳይ ሲናገሩ ሰምቸ ነበር። ሴቶች በሳይንስ ተመራማሪ ይሆኑ ዘንድ አካባቢያቸውን ማስተዋል አለባቸው። ለዚህም ማንኛውም ሰው ሊያደርገው የሚችለውን የእንቅስቃሴ ዕድል ማግኘት አለባቸው፤ ተፈጥሮን ማስተዋል አለባቸው።
ሴት ደራሲያን በጣም ጥቂት ናቸው። በግጥምና በፊልም ላይ ነው አብዛኛው ተሳትፏቸው፤ ብዙ የግጥም መድብል ያላቸው ሴቶች አሉን። ግጥም ደራሲ አያሰኝም ማለቴ አይደለም፤ እንዲያውም ትልቁ የጥበብ ጥግ የሚባለው ነው። ዳሩ ግን በፖለቲካና በታሪክ ፀሐፊነት ደግሞ በጣም አነሱ። እንደነ ገነት አየለ አይነት የታሪክ ፀሐፊዎችም ሊኖሩን ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
ዋለልኝ አየለ