አዲስ አበባ፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የዓረብ ሊግ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ኢትዮጵያ አወገዘች፡፡ውሳኔውን ‹‹ቁልፍ ጉዳዮችን ሳያገናዝብ ለአንድ ወገን ያደላ ›› ሲል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የዓረብ ሊግ የሕግ አስፈፃሚ ካውንስል ከትናንት በስቲያ የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ የደረሰበት ውሳኔ የሚያሳዝን ሆኖ አግኝቶታል፡፡
ኢትዮጵያ ውሳኔውን በፍጹም እንደማትቀበለው ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፣የሱዳን መንግሥት በዓረብ ሊግ ለቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ድጋፍ ላለመስጠት የወሰደውን አቋም እንደምታደንቅ በመግለጫው አመልክቷል:: ሱዳን የተቀነባበረውን የዓረብ ሊግ አቋም ባለመደገፍ የምክንያታዊነት እና የፍትሕ ድምፅ መሆኗን ዳግመኛ ማረጋገጧን አስታውቆ፣ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ለተመሠረተው እና የሁሉም ወገን አሸናፊነትን መሠረት ላደረገው የሱዳን አቋም ትልቅ አድናቆት እንዳላት ገልጸዋል።
መግለጫው እንዳመለከተው፤ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ አገራት ሕዝቦች እና መንግሥታት ጋር በጋራ እሴት፣ ባሕል እና ልማድ ላይ የተመሠረተ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት አላት፡፡የዓረብ ሊግ የተለያዩ ሉዓላዊ ሀገራትን ያቀፈ ተቋም እንደመሆኑ የሁሉንም ወገን ፍላጎት ያካተተ እና ሚዛናዊ መስመር መያዝ ይጠበቅበታል፡፡
ከዚህ መስመር በተቃረነ መልኩ የሚሠራ ከሆነ ግን የሊጉ ተዓማኒነት እና በዚህ እጅጉን በተሳሰረ ዓለም ውስጥ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ትብብርን ለማምጣት ያለው አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንደሚሆን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ቢሆን ‹‹የአሁኑን እና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የዓባይን ውሃ ሃብት የመጠቀም መብት አለኝ›› የሚለውን የዘለቀ እና የማይናወጥ አቋሟን በድጋሚ ገልጻለች ሲል ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው፤የዓባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ በሌሎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሳይደርስ ውሃውን በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም መርህን ተከትላ ትሰራለች፡፡ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አሠራር ላይ መሠረታዊ መፍትሔ የሚሰጠውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነትን ተከትላ እንደምትሰራ በተደጋጋሚ አረጋግጣለች።
የዓረብ ሊግ እውነተኛውን መንገድ ተከትሎ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የዘለቀ እና በጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ እንደሚሠራ ኢትዮጵያ እንደምትተማመን መግለጫው ጠቅሶ፣ወዳጅነትን ማጠናከር እና ለጋራ ግቦች ተቀራርቦ መሥራት የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑንም አስገንዝቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ ም
ዋለልኝ አየለ