አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ አገራት የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ አሰራር ሂደቶች፣ የንግድና ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን የሚፈትሽ የአፍሪካ ንግድና ፋይናንስ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው፡፡
ጉባኤውን የሚያዘጋጁት አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና የጋናው ሪስኪው የመርከብ አገልግሎት እና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በጋራ ሲሆን፤ ትናንት በሒልተን ሆቴል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጥ እንደገለጹት፤ ጉባኤው ሚያዝያ 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን የአፍሪካ አገራት የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ አሰራር ሂደቶች፣ የንግድና ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ይፈተሻሉ፡፡
አዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባኤ የጋና፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ኮትዲቯር፣ ግብፅ፣ ቶጎ እንዲሁም የቱርክና የቻይና በአፍሪካ የሚገኙ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የዓለም ዓቀፍ፣ አህጉራዊ፣ የግል ተቋማት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ የመሳሰሉ አህጉራዊ ተቋማት ኃላፊዎች እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡
ወይዘሮ መሰንበት እንደገለጹት፤ በአፍሪካ አገራት የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ እጅጉን አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ አህጉራዊና ክልላዊ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የንግድ ልውውጡን ለማሳደግ ያግዛል፡፡ በጉባኤው የአፍሪካ አገራት ልምድ ልውውጥ እና የእርስ በእርስ የንግድ ትስስሩ ደካማነት ምክንያቶችና መፍትሄው ላይ ምክክር ይደረጋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከጉባኤው የፖሊሲ ግብዓት፣ የፋይናንስ ተቋማትና ኩባንያዎች ደግሞ ለንግዱ መስፋፋትና መጠንከር አብረው መስራት የሚችሉበትን መንገድ ለማስፋት ይመክሩበታል፡፡ የሁሉንም አፍሪካ አገራት ስምምነት ያላገኘው የነፃ ገበያ ቀጣና ለመመስረት አህጉሪቱ ላስቀመጠችው ግብም እንዲሳካ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና ለንግዱ መሳካት የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ድርሻ ላይም ምክክር ይደረጋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ሰላማዊት ንጉሴ