ኑሮ ማህበራዊም፣ ግላዊም ነው።ግላዊነትንና ማህበራዊነትን በተቻለ መጠን አጣጥሞና አመዛዝኖ መኖር የህላዌ ፍጡር የውዴታ ግዴታ ነው።ሥነ ቃሎች ግላዊ ኑሮ ለማህበራዊ ኑሮና ማንነት ጠንቅ እንዳይሆኑ ትውልድን እያዝናኑና እያስጠነቀቁ የማስተማር ተግባር አላቸው። በኑሮ ላይ የሚንጸባረቁ ግላዊና ማህበራዊ ባህሪያትንና ተግባራትን በእንስሳት አንደበት በደረቁ ሳይሆን ለዛ ባለውና በማይሰለች ሥዕላዊ የአተራረት ዘዴ ሩቁን አቅርበው፤ ረቂቁን አግዝፈው፤ ክፉውን አስጠልተው፤ መልካሙን አስወድደው፤ የማቅረብ ኃይል አላቸው።(ማህተመ ሥላሴ፤ 1952) ዓላማቸውም በአብዛኛው ግለሰባዊ ባህሪ ለማህበራዊ ባህሪ ተገዥ እንዲሆን ማህበራዊው ባህሪም በግለሰባዊ ልዩና በጎ ባህሪ እንዲጎለብት በማድረግ ማህበራዊ ኑሮ በተቻለ መጠን ለሁሉም ምቹ እንዲሆን ማስተማርና ማስጠንቀቅ፤ ይህ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ መቀስቀስ፣ ብሎም ማሳመጽ ሊሆን ይችላል።
እንደኛ ባሉ ማህበረሰቦች ሥነ ቃሎች ጎልተው የሚታዩት ማህበራዊ እሴት እንዳሉ እንዲቀጥሉ ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ነው።ይህንን የሚያደርጉትም በዋነኛነት በማስተማር ነው።ሰው ምን ይለኛል ብሎ የሚጨነቅ፣ አገር ይረግመኛል ብሎ የሚፈራ፣ እመረቃለሁ ብሎ አቅመ ደካማ አረጋውያንን የሚረዳ፣ በዚህ ተግባሩም ለማህበረሰባዊ ባህሪ ኑሮና የአኗኗር ዘዴ እጅ የሚሰጥ ግለሰብ እንዲወጣ የማድረግ አቅም አላቸው።
ተረቶች፣ ምሳሌያዊ ንግግሮች ይህን ያህል ለምን አስፈለጉ? በተራ የዘወትር ቋንቋ ማህበራዊነትንም ሆነ ግላዊነትን መደገፍና መንቀፍ አይቻልም ወይ? ብሎ መጠየቅ ይቻላል።
ከኢ-መደበኛ ማስተማሪያ ስልቶች መካከል ተረቶች ዋነኞቹ ናቸው።አንድን ሰው ስለ ክፉ ባህሪው በቀጥታና በተራ አነጋገር በሰውኛ ከመንገር ይልቅ በኢ-ሰውኛ ማስረዳት የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።ቢያንስ ሰውየው ተወቀስኩ ወይም ተደፈርኩ ብሎ ‹‹እምቧ ዘራፍ›› እንዳይል ይረዳል። ስለዚህ በአግቦ፣ በሽሙጥ አሊያም በእንስሳት ተምሳሌትነት መንገር የተሻለ አማራጭ ይሆናል። የማይናገሩትን እንስሳት ‹‹እንዲህ አሉ›› ብሎ የራስን ስሜት ምኞትና ገበና ለመግለጽ ያስችላል።‹‹ነገር በምሳሌ…›› ይባል የለ።‹‹አይ ሰው አለች ቀበሮ›› ‹‹በካራ ቀልድ የለም አለች ዶሮ›› እያሉ የልብን መናገር የሰው ባህሪ ብቻ ሳይሆን አይቀርም።ሌሎች እንስሳት የዚህ አይነት ባህሪ አላቸው ለማለት ያስቸግራል።የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነገራቸው ሁሉ ፊት ለፊትና ደመ ነፍሳዊ ነው። እነርሱ በደመ ነፍስ እኛ በልበ ነፍስ እንድንመራ ሆነን ተፈጥረናልና።ልባዊነታችን የተለየ ችሎታ ባለቤት እንድንሆን ቢያደርገንም ይህንን ችሎታ በኃላፊነት እንድንጠቀም የልቦና ህግም አስፈልጎናል።ልባዊነት በህግና በልክ መኖር ነው፤ ከዚህ ከወጣ ህይወት ደመነፍሳዊ ይሆናል።
መቼም የተረትና ወግ፣ የስነ ቃልና የአበው ብሒል ባለ ጠጎች መሆናችን እሙን ነው።ነገር ግን እነዚህ ተዘውታሪ አባባሎችና ተረቶች በሰብእና አቀራረጽ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ ማስተዋል መቻል ተገቢ ነው።ምክንያቱም እንደነዚህ ያሉት በቀላሉ ወደ ሰው ጆሮ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰዎች ልብ ዘልቀው የመግባት፣ ኮርኩሮ ስሜትን የመንካት አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ ነው።ድሮ ድሮ በገጠር አካባቢ (ምናልባት አሁንም ጭምር) ሁኔታው በሚጠይቀው መንገድ የተለያዩ አባባሎችን መናገር ልማድ ነበር።ለምሳሌ ሥራ ላይ ሲሆኑ የበለጠ የሚያተጋ፣ የታመቀ ኃይልን ተግባር ላይ ለማዋል የሚያበረታ አባባል ይነገራል።በሐዘን ላይ ደግሞ የሚያጽናና፣ ያለፈውን ትቶ ለፊቱ የሚያሳስብ፣ ለሞተው ቆርጦ ለቆመው የሚያዝን ስነ ቃል ይመዘዛል።በተለይ ቅኔያዊ የሆኑ ንግግሮች መሞካሻም መንቀፊያም በመሆናቸው ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
በዚህ መልክ የሚነገርን ንግግር ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚጠቅሱትና ስለ ሕይወት አንድ ዓይነት ምክር ወይም መረጃ የሚሰጥ አጭር አረፍተ ነገር ነው የሚል ፍቺ ይሰጡታል።ሐሳቦችን በትክክል ወደመረዳት የሚያደርስ ፈጣን ፈረስ ነው።በተጨማሪም በዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ወቅት መተኪያ የሌለው አገልግሎት ያበረክታሉ። አንድ መልእክተኛ ወይም ለሽምግልና የተላከ ሰው በተረትና ምሳሌ መጠቀሙ የተለመደ ነገር ነው።
ተግባራዊ ጥበብን የሚያጎሉ በርካታ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የአስተዋይነትንና የአርቆ ተመልካችነትን አስፈላጊነት በጥሩ ሁኔታ ይገልጻሉ። የሚያደርጋቸው ነገሮች ምን መዘዝ እንደሚያስከትሉ ሳያመዛዝን አንድ ነገር ውስጥ ዘው ብሎ የሚገባ ግድየለሽ ሰው ከሚከተለው ተረት ጥሩ ምክር ያገኛል። ‹‹እባቡን ከማስቆጣትህ በፊት መውጫህን አሰናዳ›› እንዲሉ፡፡
በአገራችን በጋብቻና በቀብር ሥነ ስርዓቶች እንዲሁም በባሕላዊ ዘፈኖች ተረትና ምሳሌዎችን መጠቀም የተለመደ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ተረትም ሆነ ምሳሌያዊ ንግግሮችን መጠቀሙ እየቀነሰ ነው።ተረትና ምሳሌዎች እንደሌሎቹ ባሕሎች የማኅበራዊ እሴቶችና ምግባሮች ማከማቻ መሆናቸው ተዘንግቷል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውበትን፣ እሳቤን፣ ደግነትን፣ ጀግንነትን …የሚያሳድገው ተረት ተረት ደብዛው ጠፍቶ ትውልዱ በሌላ አዲስ ርዕዮት ውስጥ ተዘፍቋል።ምናልባትም እነዚህን መሰል ሀገረሰባዊ እሴቶች ሽግግራቸው ባይላላ ኖሮ የዛሬውን ትውልድ በመልካም ግብረ ገብነት ለመቅረጽ በተቻለ ነበር፡፡
በይዘትና በሥነ-ጥበባት ቅርፅ ከሚገኙ ምሳሌዎች እና አባባሎች ጋር ብዙ ተዛምዶ ያላቸው እንቆቅልሾችም ቢሆኑ ዛሬ ላይ በየትምህርት ቤቱ እንደ ቀድሞ ዘመን አይዘወተሩም፡፡
አሁን አሁን ተረቱም፣ ምሳሌያዊ ንግግሩም፣ እንቆቅልሹም ደብዛው ጠፍቷል።የሁሉም ጨዋታ ከተረት ይልቅ የፖለቲካ ትርክት ሆኗል። መሰዳደቡ ያለከልካይ ነግሷል። ከትውፊታዊ ሀብታችን ይልቅ ለመጤ ባህል መጨነቅ የስልጣኔ መገለጫ እየሆነ ነው።ጉራማይሌ የቋንቋ አጠቃቀሙ ጆሮ አጣሟል።አደንዛዥ እፁ በየጉራንጉሩ ሕዳር ሲታጠን መስሏል።የጫት ዋጋ እና ተፈላጊነት ከዳቦ በላይ ሆኗል።ፍየልም ምግቧን በሰው ተቀምታለች። ሥነ ቃሎቻችንን ከማጤን ይልቅ ‹‹በሞባይል ጌምና›› በማህበራዊ ሚዲያ አልባሌ ወሬዎችን ማነፍነፍ የዘመኑ ፋሽን ሆኗል።ግብረ ገብነት ጠፍቷል።መከባበሩ…መተዛዘኑ መፈቃቀሩ አፈ ታሪክ ሊሆን ከጫፍ ደርሷል። ኧረ እንደውም ተረት ተረቱ በራሱ ‹‹ተረት ተረት›› ሆኗል።
አሁን አሁን በቁሳቁስ አምልኮ የተነደፈ እንጂ በመንፈስና በባህል የበለፀገ ትውልድ እየጠፋ ነው። ለማይረባ አዕምሮ ተላልፈው ተሰጡ እንዳለው ቅዱስ መፅሐፉ……ስልጣኔ በሚመስል መሰይጠን በሀገሪቱ አየር ተንሰራፍቷል። በራቁት ዳንስ መጀዘቡ፣ በሳውና ባዝ መዳራቱ … ይሄ ሁሉ ንፋስ ከወዴት ገባ? አገራዊ ትውፊትን አለመጠበቅና በተለይም የግብረ ገብ ሀብት የሆኑትን ሥነ ቃሎቻችንን ለትውልድ ባለማሸጋገራችን አይመስላችሁም?
በነጋ በጠባ የትናንት ታሪካችንን ነቅሰን እያወጣን ዛሬ ላይ መልሰን በማመንዥክ ነገን በድጋሚ ስህተት የምንጽፍ ግብዞች ለምን ሆንን? ስለ ምን ከተረቶቻችን፣ ከምሳሌያዊ ንግግሮቻችን፣ ከአባባሎቻችን፣ ከእንቆቅልሾቻችን መቋደስ ተሳነን? የትናንት አባቶቻችን በደማቸው አገርን ሠርተው ይልቁንም ኢትዮጵያ የምትባል ከሦስት ሺሕ ዓመት በላይ ዘመን ቆጥሮ፣ ታሪክ ራሱ ሥልጡንነቷን መስክሮ ዓለም በታሪክ መዛግብት ላይ እንዲያነባት የምዕት ዓለሙ የታሪክ ጫፍ የሥልጣኔ ምንጭ ተብላ ዓለም የሚያደንቃትን አገር ያወረሱን ትውፊታዊ ሀብቶችን በሚገባ በመጠቀማቸው ነው፡፡
ይልቁንም እኛ የአባቶቻችንን ታሪክ መሸከም የከበደን ይመስለኛል።ነገ ለልጆቻችን የምናወርሰው አንድ የረባ ታሪክ ሳንሠራ ይህን ያህል ወርደን የማንነታችን መገለጫዎችን ዘንግተናቸዋል።ልጆቻችን ከእኛ ምን ይጠብቁ? ከፍለው የማይጨርሱት የዕዳ ውዝፍ! ታዲያ እንኳን የሚያኮራ ታሪክ፣ ማንነት ታድለን ምንስ ቢሆን ልጅ እንዴት በአባቱ ታሪክ ሲቆዝም ይሞታል! ልጅ ከአባቱ የተሻለ ለመሆን ይሠራል እንጂ፡፡
ዛሬ የዋልንበት የደከምንበት ሁሉ ነገር የሚገለጥ ታሪክ ነው።ዛሬ የኖርነውን ነገ በትዝታ ፈረስ ሸምጥጠን ማየታችን አንዱ የሰውነታችን ባህሪ ነው።ለዛም ነው ትናንትን ታዝቦ ነገን አቅዶ ለመኖር ካልተሰጣቸው እንስሳት እኛን ልዩ የሚያደርገን።በእንስሳት ዓለም እንስሳት አንዱ የነከሰውን ሌላኛው ከመንጋጋው ነጥቆ በደመነፍስ ይመገባል፤ ሲጣሉም በደመነፍስ ይጋጫሉ።ሲታረቁም በደመነብስ ይታረቃሉ።አልፎም ጠንካራው ደካማውን ሊያድነው ይችላል።ይህም ቢሆን ለሕይወት ቅብብሎሽ ተፈጥሮ በወሰነችለት ዓለም ሕይወቱ እንዲቀጥል የሚያደርገው የህልውና ትግል እንጂ አቅዶበት አይደለም፡፡
ታዲያ ከእንስሳት በላይ ‹‹ሰው›› ተብለን በልዩነት የተሾምን ሰዎች ስንለብስ የሚያምርብንን መርጠን፣ ስንበላና ስናወራርድ የሚሰማማንን ወይም ጓደኝነትም ሆነ ጠላትነት ስንፈጥር አልፎ አልፎ በስሜት ተወስደን ካልሆነ በቀር አቅደንበት እንጂ፣ በደመነፍስ ሊሆን እንደማይችል እውነት ነው።ምክንያቱም እኛ ደመነፍስ ፍጥረቶች አይደለንማ።ለዚህ ደግሞ ስነ ቃሎች በጎነትን በማስረጽ ረገድ አይነተኛ ሚና አላቸው፡፡
ቀለል አድርጎ ለመረዳት እስኪ የአንድን ቤት መሠረቱን እንመልከት፤ በደንብ ያልተዋቀሩና ቅርፃቸው የማያምር ትላልቅ ድንጋዮች ከሲሚንቶ አርማታ ጋር ከታች ተደርድረው እናያለን።ቤቱ መሠረቱን አልፎ ከፍ እያለ ሲሄድ ግን ተጠርበው ቅርፅ ባላቸው ድንጋዮች፣ ወይም ደግሞ በቡሎኬት ግድግዳው አምሮ ቆሞ ስንመለከት ታች መሠረቱ ላይ መሬቱን ዳምጠው ከተቀመጡ ቅርፅ አልባ ድንጋዮች ላይ የተስተካከለ ውበት ማን ሊጠብቅ ይችላል?
የአንድ ተረት ተረት የግንዛቤ ጠቀሜታ በመጀመሪያ ሲታይ የእውነተኛ ህይወት ክስተቶች ገጽታዎችን የሚያንፀባርቅ እና ስለ ማህበራዊ ግንኙነቶች ታሪክ፣ ስለ በጎነትና ሕይወት እንዲሁም ስለ ዓለም አተያይና ስለ ስነ-ልቦና ሀሳብ፣ ስለ ሀገር ተፈጥሮ በደንብ የመተረክ ኃይል አለው። የታሪክን ርዕዮተ ዓለምና ትምህርታዊ ጠቀሜታ ለጥሩ ፍላጎት ለማዋልም ያግዛል።የደካሞች ጥበቃ ነው።በክፉ ላይ ድል ለመቀዳጀት ትልቁ መሳሪያ ነው።ለዚህ ሽለላና ፉከራን ማንሳት እንችላለን።በተጨማሪም፣ ተረት ተረት ደስ የሚያሰኝ ስሜትን ያዳብራል።
ሥነ ቃል ጸብን ለማብረድ፣ በጎውን ለመከወን፣ የባሰውን የተሻለ ለማድረግ፣ ክፉውን በበጎ ለመለወጥ ትልቅ ኃይል ነው።እውነትን መሰረት ያደረጉ አባባሎችም ማኅበራዊ ግንኙነትን ቅመም ሆነው የማጣፈጥ አቅም አላቸው።ነገር ግን ይህን ችላ በማለት እውነትን የሚያራክሱ፣ ለሐሰት ዘብ የቆሙ፣ የሰውን ንቃተ ሕሊና የሚያዳክሙ፣ ለነውር የሚያደፋፍሩ አባባሎች ተክተን የመጠቀም ባህላችን እያደገ ነው፡፡
ብዙዎቹ የሀገራችን ሰዎች በአብዛኛዎቹ ገበሬዎች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበት የኖሩና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ በመሆኑ፤ የሥነ ቃሉ ባለቤት እገሌ ነው ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም ዳሩ ግን የማይካደው የሀገራችን አንጡራ ሀብት በመሆኑ ይዘነው ልናቆየው ግድ ይለናል።
አገር ምን እንደሆነች ሁላችንም እናውቃለን።ነገር ግን አገር የምትኖርበትን ዘዴ ገና አጥርተን ያወቅነው አይመስለኝም።ስለዚህም የአንድ አገር ሰዎች መሆናችንን እንድናውቀውና ለአንድነታችን መጠጊያ የሆነችውን አገራችንን ለማገልገል፣ ለማኖርና ለኑሯችንም ለመሥራት የምንችለው በተለይም አንድ የሚያደርጉን ባህላዊ እሴቶቻችንን በአንድ መንፈስ ስንተርካቸው ነው፡፡
የፖለቲካ ትርክቱን ትተን ትውልድን የሚያንጽ ተረትና ምሳሌ ለትውልድ መንገር ስንችል ነው።የእያንዳንዳችን መንፈስ ከደካማነት ወደ ፅኑነት መለወጥ አለበት። መተዛዘንን፣ መተሳሰብን፣ ጠንካራ መንፈስን፣ ቅን ባህሪን፣ ፍቅርን፣ እርስ በርሳችን መተዋወቅንና አለመናናቅን ከሥነ ቃሎቻችን ቀንጭበን መውሰድ አለብን።ይህም በመካከላችን ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም።ወደ መጥፎ መንፈስ የሚመራ ሁሉ መጥፎ ነገሮችን እያራባ ሌላውን ሁሉ ከትቦ እንዳይጎዳ ያሠጋልና በባህሎቻችን ውስጥ ምን ምን እንዳለ ተረድቶ ከአሁኑ መግታት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት›› እንደሆነ ደህና አድርገን እናውቃለን፣ ስለዚህ ዞረን ዞረን የምንገባበትን አገራችንን፣ ቤታችንን፣ ኖረን ኖረን የምንቀበርባትን መሬታችንን እንደዋዛ ሳናያት ትውፊቶቻንን ጠበቅ እናድርግ። ሥነ ቃል በአጠቃላይ በተለይ የሥነ ህይወት ማንጸባረቂያ፣ መታዘቢያና የአኗኗሩ መመሪያ መሆናቸውንም ዘወር ብለን እንመልከት።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
አዲሱ ገረመው