በአንድ ነገር ላይ ከራስ አልፎ በሌሎች ዘንድ ለመታወቅ ድርጊቱ በተግባር ተደርጎ፣ አድራጊውም አስመስሎ ሳይሆን ድርጊቱን በተግባር ፈጽሞ፣ በሃሳብ ሳይሆን በገቢር ሆኖ መገኘት አለበት:: ከዚህ አኳያ ስንመለከተው እኛ ኢትዮጵያውንም በጀግንነታችንና በኩሩነታችን በዓለም ህዝብ ዘንድ የታወቅነው በእርግጥም የጀግንነትን ተግባር ፈጽመን በተግባርም ኩሩ ሆነን ስለተገኘን ነው:: በእርግጥም እኛ ሳንሆን “አመድ የወለዱት” እሳቶቹ ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን በምኞት ሳይሆን በተግባር በእሳት ተፈትነው በፈጠሩት የወርቅ ቀለም፣ በጻፉት ዘመን የማይሽረው አኩሪ ጀግንነት፣ ሥራቸው ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ እነርሱ ባወረሱን ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር እንደመሆናችን መጠን እኛንም ዓለም በዋነኝነት የሚያውቀን በጀግንነታችንና በኩሩነታችን ነው:: የክብር፣ የኩራት፣ የጀግንነት ስማችን ግን ዝም ተብሎ የተገኘ አይደለም፣ የዓለም ህዝብ በችሮታ የሰጠንም አይደለም:: በሥራ የመጣ፣ በተግባር የተፈጸመ፣ በመሆን የተገኘ ውድ ዋጋ የተከፈለበት ነው ጀግንነታችንና ኩሩነታችን! ከፍ ሲል ከአዳም ዝቅ ሲል ከኖህ፣ በጣም ዝቅ ሲል ደግሞ ከሰብታህ የሚጀምር የሃገርነትና መንግስትነት ከራሱ ከሰው ልጅ ዕድሜ እኩል የሚቆጠር የረጅም ዘመን ታሪክ እንዲኖረን ያስቻሉ፣ በዕድገትና በስልጣኔም ቢሆን ከማንም ቀድመው ለዓለም የስልጣኔ እርሾን የጣሉ የራሳቸው ወግ፣ ባህል መገለጫ ያላቸው፣ ነጻነታቸውን በገዛ ክንዳቸው አስከብረው በክብር የኖሩ፣ … ጥበብን ከጀግንነት አዋህደው ታላቅ ሃገርን የፈጠሩ፣ የመሩና ያወረሱን ጀግኖች እናትና አባቶቻችን በተግባር በፈጸሙት አኩሪ የክብርና የጀግንነት ታሪክ ነው በጀግንነትና በኩሩነት ስማችን በዓለም ዙሪያ መታወቅ የቻለው:: የምንኮራውና የምንከበረው በከንቱ መከበርና መወደስ ስለምንፈልግ አይደለም:: አባቶቻችንና እናቶቻችን በተግባር ሠርተው፣ ኮርተው እንድንኮራ ስላደረጉን ነው::
ታሪክ ተዓምር ሳይሆን በሥራ የሚገኝ ነው
ታሪክ ሰዎች በተግባር አድርገውትና ሆነውት ያለፉት እውነተኛ የሥራ መዝገብ እንጂ በመለኮት ፈቃድ የሚፈጠር ተዓምር አይደለም:: ታሪክ የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚቻል ሰዎች በተግባር ሞክረው ያረጋገጡበት፣ ዛሬን ከትናንትና ከወደፊቱ ጋር የሚያገናኝ፣ ትውልድ ሥራ የሚማርበትና የሚለማመድበት ህያው የድርጊት ቤተ ሙከራ ነው እንጂ በሃሳብ ብቻ የቀረ ወይም በቢሆን ምኞት የሚፈጠር በእውነተኛው ዓለም በገሃድ ያልተፈጸመ ልብ-ወለዳዊ ፈጠራ አይደለም:: በሥራ የሚመጣ፣ ቀዳሚው ትውልድ ለቀጣዩ የሚያወርሰው በገቢር የተፈጸመ እውናዊ ቅርስ ነው:: እኛም አኩሪ ታሪክ አለን ስንል ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን ያላደረግነውን ሳይሆን አባቶቻችን በተግባር አድርገው ያወረሱንን የአዕምሮና የሥራ ውጤቶች ስላሉን ነው:: በአፍሪካ የራሳችን የሆነ ፊደልና የዘመን መቁጠሪያ ቀመር ያለን እኛ ነን:: በኪነ ህንጻ ጥበብ ዓለም ገና ባልዘመነበት ጊዜ አሰራራቸው ዛሬም ድረስ ‹‹በዕውቀት ተራቀቅን፤ በስልጣኔ መጠቅን›› ለሚሉት ሁሉ ምስጢር የሆኑ እንደ አክሱም፣ ላሊበላና ፋሲለደስን የመሳሰሉ ህያው የጥበብ ቅርሶችን አቁመናል:: በኪነ ጥበብም ገና በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ከስመጥሮቹ ከነሞዛርት ቀድመን ዜማን በምልክት የቀመሩትን እንደነ ቅዱስ ያሬድ ያሉ ሊቃውንትን ቀድመን አፍርተናል:: በኢኮኖሚና በፖለቲካ ተፅዕኖም ቢሆን ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ተሻግራ እስከ ደቡብ አረቢያና የመን ድረስ የተዘረጋ ግዙፍ ኢምፓየርን የምታስተዳድር፣ በወቅቱ በዓለም ላይ ከነበሩ አራቱ ኃያላን አገራት አንዷና ዋነኛዋ አገር እንደነበረች ታሪክ ይመሰክራል:: በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ ለእስራኤል፣ ለግሪክ ለሌሎች አገሮች ወታደራዊ እርዳታ ታደርግ እንደነበር ከራሳቸው ዛሬ “ሰለጠነ” ከሚባለው ዓለም የተገኙ ድርሳናት ይመሰክራሉ:: ለዚህም እንደነ ሆሜር፣ ሄሮዳተስና ድሩሲላ ዱንጅ ሂውስተን የመሳሰሉ ጉምቱ የታሪክ ምሁራንንና ሌሎች በርካታ የታሪክ ሊቃውንትን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል::
አድዋ የሰውነት ክብር ምንጭ
ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ረጅም ዘመናትን ባስቆጠረው ሃገራዊ ታሪካችን በተለያየ መስክ የሰራናቸው በመላው ዓለም ዘንድ በናኘ ስምና ዝና የምንታወቅባቸው፣ ከፍ ብለን የምንከበርባቸውና የምነደነቅባቸው አኩሪ ታሪኮቻችን ናቸው:: ከዛሬ አንድ መቶ ሃያ አራት ዓመታት በፊት ደግሞ በሰው ልጆች መካከል ተፈጥሮ የነበረን የተዛባ አመለካከት ያስተካከለ፣ እኛን ብቻ ሳይሆን መላ የሰው ልጆችን ያስከበረ፣ የሰውነትን ክብር በተግባር ያረጋገጠ፣ የሁሉም ኩራት የሆነ፣ ጠቢቧ በዜማዋ እንደገለጸችው በጊዜ የማይወሰን- “ትናንትም ዛሬም የሆነ” ሁሌም ትኩስ ሆኖ የሚኖር አዲስ አኩሪ ታሪክ ጻፍን! አባቶቻችን በረቂቅ ዕውቀታቸውና በማይደረስበት ጥበባቸው በአብዛኛው የዓለም ህዝብ ዘንድ መድሃኒት አልባ እንደሆነ ታምኖበት የሰውን ልጅ ክፉኛ እያጠቃ የነበረው “የነጭ የበላይነት” የሚባለው የሰውነት በሽታ አድዋ ላይ መድሃኒቱ የተገኘለት መሆኑን ለሰው ዘር ሁሉ አበሰሩ:: ከራሱ ቀለም ውጭ ያለውን ማንኛውንም ሰው እንደ ሰው የማይቆጥረውና በዚህም ምክንያት በሰው ልጆች ላይ አሰቃቂ ሞትና ወንጀሎችን ሲፈጽም የኖረው “የነጭ የበላይነት” የተባለው የዚህ ሰብዓዊ ተውሳክ ተሸካሚ ከነበሩ እብሪተኞች መካከል አንዱ የነበረው የጣሊያን ቅኝ ገዥ ኃይል አገሪቱን በኃይሉ አንበርክኮ ህዝቦቿን በባርነት ለመግዛት ከጥቁር ሕዝብ ሃገር አንዷ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ መጣ:: የዚህ አደገኛ በሽታ መድሃኒት እዚሁ በኃይል ልትገዛ በታሰበችው ሃገር ከመገኘቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የቅኝ ግዛት ተልዕኮው ዋና አስፈጻሚ ሆኖ የተመረጠውና ወደ ኢትዮጵያ የተላከው የጣሊያኑ ጦር መሪ ጀኔራል ባራቲዮሪም መሪዋን ጥቁሩን ሰው ዳግማዊ አጼ ምኒሊክን “በቀፎ ውስጥ አስሬ ሮማ አመጣዋለሁ” በማለት የሃገሩን ሰዎች አስጨብጭቦ ጦርነቱን ገና ሳያሸንፍ “ታላቁ ድል አድራጊው ጀግና” ተብሎ ተሞካሽቶ ነበር:: ዳሩ ምን ያደርጋል እኛን በኃይል አንበርክኮ ሃገራችንን በቅኝ ግዛት ለመግዛት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ ተራሮች ሥር ከጀግኖች አባቶቻችን ጋር በተደረገው ጦርነት የጦሩ መሪ “ታላቁ ድል አድራጊው ጀግና” ጀኔራል ባራቲዮሪ አይሆኑ ቅጣት ተቀጥቶ እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈርጥጦ ጠፋ እንጅ! ዓለሙን ሲያምሰው የነበረው መድሃኒት የለሹ የነጭ የበላይነት በሽታም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር አድዋ ላይ መድሃኒቱ ተገኘለት! የነጭ ወራሪንና የነጭ የበላይነት ወረርሽኝን ያስቆመው ማርከሻው መድሃኒት ስምም “ኢትዮጵዊነት” የሚባል መሆኑን የዓለም ሕዝብ አወቀ:: እብሪተኞች እንደ ሰው የማይቆጥሩት የጥቁር ህዝብ “ምንጊዜም የበላይ ነን” ብሎ የሚያምነውን የነጭ ወራሪ በጦር ሜዳ ገጥሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸነፈ:: እናም ለጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን ከዚያም አልፎ ለመላው ሰው ልጆች ሁሉ የሰውነት ክብርን ያጎናጸፈውን አኩሪ ድል እኛ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ጻፍን! ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው ሰው ዘር በሙሉ፣ ከራሳቸው ከነጭ ዘር የተገኙ ጭቁን ህዝቦች ሁሉ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ምክንያት፣ ድል አመላካች፣ የአሸናፊነት ምልክት ሆንን! ታዲያ በተባበረ ክንዳችንና በአንበሳ ልባችን የማይደበዝዝ አኩሪ ታሪክ ያስመዘገብን በመሆናችን ብንኮራ ይገባናል፤ ጀግና ብንባልና በዚሁ ብንታወቅም ያንስብናል እንጂ አይበዛብንም- አድርገንና ሆነን ተገኝተናልና!
እናም በአሁኗ ኢትዮጵያ የምንገኝ እኔና የእኔ ትውልድ ጀግንነታችንና ኩሩነታችንን አስጠብቀን ለመቀጠል የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል:: ይህንን የምናደርገው ደግሞ ክብራችንን ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ እንደ አባቶቻችን በጀግንነት ታግለን በድል መወጣት ስንችል ነው:: ከዚህ አኳያ የአሁኑ ትውልድ እንደቀደምቶቹ ጀግና ነኝ ለማለትና ኩሩ ሆኖ ለመገኘት በርካታ ማሸነፍ የሚገባው ጠላቶች ቢኖሩበትም በምኞት ሳይሆን በተግባር ማድረግ የሚገባውን አድርጎ የራሱን ዘመን ሥራ ሠርቶ ጀግንነትን ፈጽሞ እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ፣ እንደ እናት አባቶቹ አኩሪ ታሪክ ፈጽሞ በክብርና በኩራት መኖር ሲገባው ይህንን ማድረግ አልቻለም:: በጣም የሚያስገርመውና ራሱን ትዝብት ላይ የሚጥለው የትውልዱ አነጋጋሪ ባህሪይ ደግሞ ዘመኑ የሚፈልገውን የራሱን የጀግንነት ተግባር ፈጽሞ እንደ ቀደምቶቹ ተከብሮና ኮርቶ መኖር አለመቻሉ አይደለም:: በሥራ ባልተገኘ ኩራት ራሱን በውዳሴ ከንቱ እየደለለ በውሸት ክብር ውስጥ ለመኖር ከመፈለግ በመነጨ ከንቱ ግብዝነት ስንፍናውን ለመደበቅና ታናሽነቱን ለመሸፋፈን ትውልዱ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ የማጣጣል አባዜ የተጠናወተው መሆኑ ነው አስገራሚው ነገር! እናማ ዛሬ ዛሬ ብዙዎቻችን በተለይም የእኔ ዘመን ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ያለን እሳቤና አመለካከት ከአባቶቻችንና ከአያቶቻችን በእጅጉ የተራራቀ ሆኗል:: ኢትዮጵያን አናውቃትም፤ አወቅናት ካልንም የምናውቀው ርሃቧን፣ እርዛቷን፣ ድህነቷንና ጉስቁልናዋን ብቻ ነው:: የምናውቀው ከሁሉም ቀድማ የዕውቀት ብርሃን ያየችውን፣ ከራሷ አልፋ ስልጣኔን ለዓለም ያስተዋወቀችውን ከእርሻ እስከ ማረሻ፤ ከግብርና እስከ ህክምና፣ ከሥርዓተ ጽህፈት እስከ ሥርዓተ መንግስት፣ ከዜማ እስከ ፍልስፍና የሁሉም ስልጣኔ እርሾ የሆነችውን፣ ነጻነቷን ሳታስደፍር ለብዙ ሺ ዘመናት ታፍራና ተከብራ የኖረችውን ታላቋን ኢትዮጵያ አይደለም:: እንዲያውም ዕድሜ ለክፋትና ለውድቀት መሪዎቻችን ቀሽሞቹን ሰምተን በቀሽሙ የብሔር ፖለቲካ ከታላቅነታችን የቀነጨርነው እኛ የዚህ ዘመን ትውልድ “ውበቷ አይታያችሁ፣ ሚስጥሯ አይገለጽላችሁ” ተብለን የተረገምን ይመስል የሃገራችን ታላቅነት አውቀን በታሪካችን ልንኮራና ታሪክ ልንሰራ ይቅርና አባቶቻችን በሰሩልን የትም የማይገኝ አኩሪ የነጻነት ታሪክም የማንስማማና “በቅኝ ግዛት ተገዝተን ቢሆን ኖሮ እንሰለጥን እናድግ ነበር” የምንል ስልጣኔን የማናውቅ ስልጡን መሃይማን ሆነናል:: ታሪክ መሥራት ሲያቅተን ታሪክ የምንሳደብ፣ ታላቅ ሥራ ሰርተን፣ አኩሪ ታሪክ ማስመዝገብ እንደ አባቶቻችን በክብር መኖር ሲያቅተን ታሪካችንን የምናጣጥል ከንቱዎች ተፈጥረናል:: “ታሪክ ታሪክ ቢሉት ምን ዋጋ አለው?”፣ “እንዲያውም ባለፈ ታሪክ እየተኮፈስን ነው አሁን ላይ ምንም ሣንሰራ ከዓለም ወደ ኋላ የቀረነው”፣ “አኩሪ ታሪክ፣ ቅኝ አለመገዛት፣ ነጻነት …ምናምን ምን ያደርግልናል? አሁን ላይ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያሉት በሁሉም ነገር እኛን የሚበልጡን ቅኝ ግዛት የተገዙት አገራት ናቸው፣ እንዲያውም በተገዛን ይሻለን ነበር” የሚል “ጠያቂ ትውልድ” አፍርተናል::
ታሪክ የዕድገት መሰረት ነው
ለመሆኑ ግን አንዳንድ የእኔ ዘመን ትውልድና ጥራዝ ነጠቅ አላዋቂ መሪዎቹ እንደሚሉት ታሪክ ዋጋ የሌለው ተራ ተረት ተረት ነውን? በዕድገት ወደ ኋላ ለመቅረታችንና ትናንትና ቅኝ በተገዙ ሃገራት ሳይቀር ለመበለጣችንስ በእርግጥ እነርሱ እንደሚሉት ተጠያቂው ታሪካችን ማወቃችንና በታሪካችን መኩራታችን ነውን? በተቃራኒው እንደ ሌሎች የአፍሪካና የዓለም ሃገራት በምዕራባውያን ተገዝተን ኖረን ቢሆን ማደግ እንችል ነበርን? በእርግጥ ከመነሻው ጥያቄ ብንጀምር “ተገዝተን ቢሆን ኖሮ” መባሉ በራሱ ከአንድ ጤናማ ዜጋ የማይጠበቅና ፍጹም ያለንበትን የድንቁርና እስር ቤት የሚያመለክት ነው:: በውኑ ቅኝ በመገዛቱ ያደገው የአፍሪካ ሃገር ማንኛው ነው? መቼም ደቡብ አፍሪካ መባሉ አይቀርም:: ደቡብ አፍሪካ እኮ ሰባ በመቶ የሚሆነው ህዝቧ በድህነት የሚማቅቅባት፣ በገቢያቸው የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቁ ዜጎች የሚኖሩባት፣ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ ኢፍትሃዊነት የነገሰባትና በዜጎች መካከል ከፍተኛ የሆነ አለመተማመን የተፈጠረባት፣ ዜጎቿ እርስ በእርሳቸው እንደ ጠላት የሚተያዩባት የድሮ ቅኝ ገዥዎቿ ብቻ በነጻነት የሚነግዱባት “ያደገች” ሃገር ናት:: ናይጀሪያ፣ ኮንጎ፣ ሊቢያ፣ አልጀሪያ፣ ማሊ…ወዘተ ? በቅኝ ግዛት “ሌጋሲ” ምክንያት ዛሬም ድረስ በማያበራ የእርስ በእርስ ጦርነት የሚታመሱ፣ “በመገዛታቸው ያደጉ” ሃገራት::
ደግሞስ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት መሆንና ሳይሆን አባቶች በሰሩት ታሪክ መኩራት ትውልድን ከሥራ የሚከለክለው፣ ለዕድገትም እንቅፋት የሚሆነው በማን ሃገር ነው? ላወቀበትማ እንዲያውም ታሪክ የዕድገት መሰረት ነው::
ምክንያቱም “….ታሪክን እና ዕድገትን ስናነሳ በቅድሚያ ጀርመንና ጃፓን ይታወሱናል:: በተለይ ጃፓን የምናስታውስበት ምክንያት ባህልና ታሪኳን ሳትዘነጋ በማንም ሃገር ያልደረሰና በአንድ ጊዜ ከመቶ ሃምሳ ሺ ህዝብ በላይ ያወደመባትን የአቶሚክ ቦንብ ጥቃት አልፋ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚደርስባትን የርዕደ መሬትና ውቅያኖስ ማዕበል(ሱናሜ) ጉዳት ተቋቁማ በዓለም እስከ ሁለተኛ ደረጃ ሃብታምነትና በቴክኖሎጂም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰች ሃገር መሆኗም ጭምር ነው:: ታሪክ ብሔራዊ ስሜት መዳበር፣ ለስልጣኔና ለዕድገት መሰረት ስለመሆኑ ሌሎችም በርካታ ማስረጃዎች አሉ”(ግዛው ዘውዱ፣ 2005፡113-114)::
አዎ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ግዛው ዘውዱ እንዳሉት ታላላቆቹን ዘመናችን ኃያላን አሜሪካንና ሩስያን ጨምሮ በርካታ እስያና አውሮፓ ሃገራት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት ማስመዝገብ የቻሉት አሉኝ የሚሏቸውን ታላላቅ የጀግንነትና አሸናፊነት ታሪካቸውን እንደ መቀስቀሻ ኃይል እና መነቃቂያ ሞራል በመጠቀም መሆኑን መዛግብቶቻቸው ያመላክታሉ:: ከ1950ዎቹ ጀምሮ እየተስፋፋ እንደመጣው የእኛ ሃገር ታሪክ ጠልነት አባዜ ሳይሆን የታሪክን ጥቅም የተረዱት እንደ ታላቋ አሜሪካ ዓይነት ብልጥ ሃገሮችማ እንኳንስ ብዙ ሺ ዘመናትን ያስቆጠረ የደለበ አኩሪ ታሪክ ኖሯቸው አምስት መቶ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የሰሯቸውን ጥቂት አኩሪ ታሪኮች ከመጠን በላይ በማጋነንና በተወዳጅ ፊልሞቻቸው አማካኝነት የጀግንነት ታሪክ በመፍጠር ሳይቀር ዜጎቻቸውን በአሸናፊነት መንፈስ በመቅረጽ አሁን የደረሱበት ሁለንተናዊ የዕድገት ደረጃ ለመድረስ ተጠቅመውበታል::
የአቻ ምክር
ብዙውን ጊዜ የተለመደው የአቻ ግፊት እንጂ የአቻ ምክር ባይሆንም የተነሳሁበትን ርዕሰ ጉዳይ የማጠናቅቀው በአባቶቻችን ርስት ላይ በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምንኖር በተለይም ታሪክ መስራት ሲያቅተን የራሳችንን አኩሪ ታሪክ ለምናጣጥል የትውልድ አቻዎቼ ይበጃል የምለውን ምክር በመለገስ ነው:: አኩሪ ታሪኮቻችንን ለማጣጣል የምናነሳቸው “አመክንዮዎች” ሁሉ ስንፍናችንን ለመደበቅ ብቻ የምንጠቀምባቸው፣ ግብዝነታችን የወለዳቸው ከንቱ የአላዋቂ ሙግቶች ናቸው:: ምክንያቱም ታሪክ ማለት ቀላል ነገር አይደለም:: ሁለ ነገራችን የተመሰረተበት፣ ማምነታችን የተገነባበት ሥጋና ደማችን ነው:: እናም ከዚህም ከዚያም በቃረምነው ማንነቱን በማያውቅ ከንቱ ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት አኩሪ ታሪካችንን ማጥላላት፣ ማጣጣል፣ መናቅ ከራስ ጋር መጣላት ነው:: ከላይ እንዳነሳነው እንኳንስ የዕድገት እንቅፋት ሊሆን በተግባር መሥራት፣ መቻልና መሆንን በተግባር ከሠሩ፣ ከቻሉና ከሆኑ ቀደምት አያትና ቅድመ አያቶቻችን የምንማርበት የተግባር ትምህርት ቤት በመሆኑ ማምጣት ለምንፈልገው ለማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ ኃይል የሚፈጥርልን አንቀሳቃሽ ሞተር ነው:: ደግሞም የአሸናፊነት፣ የጀግንነትና የነጻነት አኩሪ ታሪካችንን ስናስብ ትርጉሙ እኛም አሁን ማሸነፍ እንችላለን ማለት ስለሆነ ከምንም በላይ ታሪክ ሥነ ልቦና ነው:: እኛም አባቶቻችን አሸናፊዎች እንደነበሩ፣ በዚህም በዓለም ላይ ተከብረው እንደኖሩ እኛንም እንዳኖሩን እኛም የክብራችንና የኩራታችን ጠላት የሆኑ ማናቸውንም የዘመናችንን ጠላቶች ማሸነፍ እንችላለን:: እናም አኩሪ ታሪካችን በመናቅና በማጣጣል ፋንታ ፋይዳውን በአግባቡ ተረድተን፣ ከመጥፎ ታሪካችን ደግሞ ትምህርትና እርማት ወስደን አባቶቻችን ባወረሱን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ላይ ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀት፣ ጥበብና ተግባር በመጨመር ድህነትን ማሸነፍና ክብራችንን መመለስ ይገባናል:: እኛም እንደ አባቶቻችን አኩሪ ታሪክ ሰርተን በክብርና በኩራት መኖር እንችላለን:: ያኔም “እኔን አልሆንም ነበር እኔ” እንዳለው ዙፋን አልባው ንጉስ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን “እኛ እኛን እንሆናለን”!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ይበል ካሳ