በ2021 በካሜሩን በምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመካፈል የማጣሪያ ጨዋታዎች በአዲሱ የካፍ የውድድር መርሃግብር መሰረት ከአራት ሳምንታት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከሦስት ሳምንታት በኋላ ጨዋታውን የሚያደርጉ ይሆናል። ለዚህም የፊታችን መጋቢት ስድስት ዝግጅት እንደሚጀመሩ ኢትዮ ኪክ ኦፍ ዘግቧል፡፡ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱም ሰሞኑን ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡
ዋልያዎቹ ከኒጀር አቻቻው ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጪ ከአራት ሳምንት በኋላ አካሂደው የመልሱን ጨዋታ በሳምንቱ በሜዳቸው ያደርጋሉ፡፡ ከኒጀር የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማዳጋስካርን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ይገጥማል። ማዳጋስካር ምንም እንኳን የምድቡ መሪ ብትሆንም ዋልያዎቹ ጠንክረው ከተዘጋጁ ማሸነፍ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው በመጀመሪያ ጨዋታ ማዳጋስካር 1ለ 0 ኢትዮጵያን ካሸነፈችበት ውጤት በመነሳት የተለያዩ ትንታኔዎች ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡
ዋልያዎቹ ከኒጀር የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ ማዳጋስካርን በደጋፊያቸው ፊት የሚገጥሙበት ጨዋታ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመጓዝ በሚያደርጉት የነጥብ ሽሚያ ወሳኝ ነው። ዋልያዎቹ ከእነዚሀ ጨዋታዎች በኋላ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ወደ ኮትዲዮቯር ተጉዘው ዝሆኖቹን የሚገጥሙበት ጨዋታም በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል። ይህ ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አኳያ ከባድ እንደሚሆን ቢጠበቅም የማጣሪያ ጉዞው የሚቋጭበት ከመሆኑም የተነሳ ከዚህ ጨዋታ በፊት ዋልያዎቹ 9 ነጥብ ለመሰብሰብ ሰፊ እድል እንዳላቸው ከመርሃግብሮቹ በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ዋልያዎቹ በሚገኙበት ምድብ ማዳጋስካር በ2 ጨዋታ፣ በ6 ነጥብና በ5 ንፁህ ግብ ቀዳሚ ሆነው ይመራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በ2 ጨዋታ፣ በ3 ነጥብና በ0 ግብ ሁለተኛ ስትሆን ኮትዲቯር ከዋልያዎቹ ጋር በተመሳሳይ ነጥብና የግብ ልዩነት ትቀመጣለች፡፡ ኒጀር በ2 ጨዋታ በ0 ነጥብና በ5 የግብ ዕዳ መጨረሻ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ዋልያዎቹን ከስምንት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ለመመልከት በእጅ የሚገኝ ትልቅ እድል ነው፡፡ የምድቡን ቀሪ ጨዋታዎችና ተጋጣሚዎች ከግምት በማስገባት ዋልያዎቹ አፍሪካ ዋንጫው ላይ ለመድረስ ያላቸውን ተስፋ ካሰላነው ወደ ተወዳጁ መድረክ ለመመለስ ከዚህ የተሻለ እድል እንደሌለ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ዋልያዎቹ ባለፈው ህዳር አስር የምድቡን ጠንካራ ቡድን ኮትዲቯርን ባህርዳር ላይ ሁለት ለአንድ በሆነ ያልተጠበቀ ውጤት በማሸነፍ ከፍተኛ ተነሳሽነት ተፈጥሮባቸዋል፡፡ ዋልያዎቹ ዝሆኖቹን ከመግጠማቸው አስቀድመው ከኒጄር ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም ማዳካስካርን በሜዳቸው ይገጥማሉ፡፡ በዚህ መርሃግብር መሰረት አሰልጣኝ አብረሃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነቡት የሚሄዱት ቡድን እንዳሁኑ አዳዲስ ለውጦችን መፍጠር ከቻለ በሜዳዋ ሁለት ሽንፈቶችን ከቀመሰችውና የምድቡ ደካማ ቡድን ከያዘችው ኒጄር ጋር በሚኖሩት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ቢያንስ አራት ነጥብ ማግኘት ከባድ አይሆንም፡ ፡ ዋልያዎቹ ኒጄርን በሜዳዋ ገጥመው አንድ ነጥብ ይዘው ከተመለሱ በሜዳቸው ሦስት ነጥብ መሰብሰብ ይሳናቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ቀጣይ ተጋጣሚ ማዳካስካር እንደመሆኗ ከዚህ ጨዋታም ቀላል ባይሆንም ሦስት ነጥብ መሰብሰብ የማይቻል ነገር አይደለም፡፡ ምክኒያቱም ማዳጋስካርን የሚገጥሙት እዚሁ በሜዳቸው ነው፡ ፡ ማዳጋስካር በሜዳዋ ዋልያዎቹን 1ለ0 ስታሸንፍ ያን ያህል ከባድ ቡድን እንዳልሆነች ታይቷል፡፡ ይህን ስሌት ዋልያዎቹ ማሳካት ከቻሉ የመጨረሻውን ማጣሪያ ከሜዳቸው ውጪ በኮትዲቯር ቢሸነፉ እንኳን ወደ ካሜሩን የሚወስዳቸውን ትኬት በቀላሉ መቁረጥ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ቦጋለ አበበ