ያለአግባብ መበልጸግ ምንድን ነው?
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ያለአግባብ መበልጸግ (Unjust Enrichment) በሌላ ሰው ድካም ወይም ንብረት በማይገባ ሁኔታ መጠቀም ነው፡፡ በትክክለኛው የሕሊና ሚዛን ካየነው ማንም ሰው በሌላው ኪሳራ እንዲበለጽግ ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ ያለአግባብ በልጽጎም ከሆነ ካሣ መክፈል አለበት፡፡
ሕግም፣ ኃይማኖትም ሆነ ሞራል የሚያዙት እያንዳንዳችን በድካማችን እንድንደሰት፣ በላባችን ፍሬ እንድንበለጽግ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያልደከሙበትን ወይም የሌላውን ሰው የላብ ፍሬ ያለአግባብ መብላት ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡
በፍትሐብሔር ሕጋችን በቁጥር 2162 ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው በሌላ ሰው የሥራ ድካም ወይም የሌላ ሰው ሀብት በሆነ ነገር በመገልገል በቂ ባልሆነ ምክንያት ጥቅም ያገኘ ሰው አላግባብ ጥቅም ባገኘበት መጠንና ለባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመው ሰው በደረሰው ጉዳት መጠን ልክ ለባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመው ሰው ኪሳራ መክፈል ይገባዋል፡፡
ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ያለአግባብ የበለጸገው ሰው ለባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመው ሰው ሊመልስ የሚገባው ነገር ወይም ጥቅም እንዳለው ነው፡፡
የሆነው ሆኖ በአንድ በኩል ያለአግባብ የበለጸገው ሰው ያገኘው ጥቅም፤ በሌላ በኩል ባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ የደከመው ሰው የደረሰበት ጉዳት (ኪሣራ) የሚከፈለውን ካሣ ወይም የሚመለሰውን ጥቅም ለመወሰን ሕጋዊ መመዘኛዎች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ተበዳዩ የሚያገኘው ካሣ ኪሳራ ከፋዩ ካገኘው ጥቅምም ሆነ ራሱ ተበዳዩ ከደረሰበት ኪሣራ አይበልጥም፡፡
ከዕለት ተዕለት ማህበራዊ መስተጋብሮቻችን እንደምንረዳው ሰዎች በሌላ ሰው ሀብት ወይም ድካም በብዛት ያለአግባብ የሚበለጽጉት በንብረት ላይ በተቋቋመ ግዙፍ መብት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ነው፡፡ ይህም ማለት ንብረትን በባለቤትነት በመያዝ፣ እጅ በማድረግ፣ በአላባው በመጠቀም ወይም በንብረቱ በመገልገል ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ባለሃብቱ ወይም ጉልበቱ የደከመው ሰው ከውል በሚመነጭ ግዴታ ወይም ከውል ውጭ በሆነ አላፊነት ከሌላ ሰው የሚጠይቀውን መብት በእሱ ቦታ ከሕግ ውጭ የተተካ ሌላ ሰው ያለአግባብ ሊበለጽግበት ወይም ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ያለአግባብ የበለጸገው ሰው የነበረበት ዕዳ ተሰርዞለት ወይም ግዴታው ቀርቶለት አልያም ከኪሳራ ድኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ የምንረዳው ያለአግባብ በልጽጓል የተባለው ሰው ከሕሊና እርካታ በዘለለ በገንዘብ ሊተመን የሚችል ጥቅም ማግኘቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው፡፡
በሌላ በኩል ባለሀብቱ ወይም ጉልበቱ የደከመው ሰው በዛኛው ሰው ድርጊት ምክንያትም የሀብት መቀነስ፣ ዕዳ ውስጥ መግባት፣ ሀብት ለማግኘት አለመቻል ወይም ክፍያ የሚያስገኝ ዕድልን ማጣት የመሳሰሉ ጉዳቶች (ኪሳራዎች) የደረሱበት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ንጋቱ ተስፋዬ “ከውል ውጭ አላፊነትና አላግባብ መበልጸግ ሕግ” በሚል ባሰናዳው መጽሐፍ ውስጥ እንደሚያብራራው ያለአግባብ በመበልጸግ ጉዳይ የተከሳሹ ብልጽግና (Enrichment) እና የተከሳሹ ድህነት ወይም ጉዳት (Impoverishment) ሁልጊዜም ቢሆን የጋራ መንስዔ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ይህም ማለት ለከሳሹ (ለባለሃብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመው ሰው) መደህየት ወይም ጥቅም ማጣት እና ለተከሳሹ (አለአግባብ በልጽገሃል ለተባለው ሰው) መበልጸግ ወይም ጥቅም ማግኘት ምክንያቱ አንድ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡
ይህንን በአጭር ምሳሌ ግልጽ እናድርገው፡፡ የሌላውን ሰው ቤት ያለአግባብ ከሕግ ውጭ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ለሌሎች ሰዎች በማከራየት ኪራዩን እየሰበሰበ የሚወስድ ሰው በዚህ አድራጎቱ ጥቅም በማግኘቱ ያለአግባብ በልጽጓል፡፡ የቤቱ ሕጋዊ ባለቤት (ባለይዞታ) ደግሞ ከቀዬው በመፈናቀሉና የኪራይ ገቢውን በማጣቱ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ስለዚህ የተከሳሹ አለአግባብ መበልጸግና የከሳሹ ጉዳት የጋራ መንስዔያቸው የቤቱ በተከሳሹ እጅ ከሕግ ውጭ መያዙ ነው፡፡
ያለአግባብ በልጽጓል የተባለው ሰው ከሚያገኘው ጥቅም ጋር በተያያዘ “ጥቅም” የሚለው አገላለጽ ሲያከራክር ይስተዋላል፡፡ ለዚህም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እልባት ያገኘ አንድ የክርክር ዶሴን በጥቂቱ ገርበብ አድርገን ከፍተን እንቃኘው፡፡
አቶ ደስታ ጁላ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የአንድ የሥራ ክፍል ከፍተኛ ኃላፊ ናቸው:: መስሪያ ቤታቸውም ለሥራቸው ጠቃሚ ልምድና ዕውቀት ገብይተው እንዲመለሱ በሚል ለአውሮፕላንና ለሥልጠና 180 ሺ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ወደ አውስትራሊያ ይልካቸዋል፡፡
ይሁንና የተላኩበትን ትምህርት አጠናቀው ወደ አገር ቤት በመመለስ የቀሰሙትን ዕውቀትና ልምድ በሥራ ላይ ማዋል ሲገባቸው በዛው ይቀራሉ፡፡ አገር ዞሮ መግቢያ ናትና የኋላ ኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ መስሪያ ቤቱ ያለአግባብ በልጽገዋልና ያወጣሁትን ወጪ ይመልሱልኝ ሲል ፍርድ ቤት አቆማቸው፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ታዲያ አንድ ሰው ያለአግባብ በመበልጸግ ሕግ ተጠያቂ የሚሆነው ከሳሹ የደረሰበትን ጉዳት በማስረዳት ብቻ ሳይሆን ተከሳሹም ያገኘውን ጥቅም በማረጋገጥ መሆኑን በመጥቀስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግን ግለሰቡ ያገኙት ጥቅም ስለመኖሩ አላስረዳም በሚል ውሳኔው አሳለፈ:: ይግባኝ የተባለበት ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ይህንኑ ውሳኔ አጸደቀው፡፡
በፍጻሜው ታዲያ የመስሪያ ቤቱ ነገረ-ፈጆች ዶሴያቸውን ሸክፈው ወደ ሰበር ችሎት አቤት ይላሉ:: የሰበር ችሎቱም በውሳኔው ግለሰቡ ከመስሪያ ቤቱ የትራንስፖርትና የሥልጠና ወጪዎች ተሸፍኖላቸው ወደ ባህር ማዶ ማቅናታቸው አከራካሪ ጉዳይ አለመሆኑን እንዲሁም ግለሰቡ ወደውጭ አገር ለሥልጠና እንዲሄዱ ወጪ ማውጣት የግድ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
አያይዞም ግለሰቡ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ባይሆኑና ከሥራቸው ጋር ለተያያዘው ሥልጠና ወደ ውጭ አገር የማይሄዱ ቢሆን ኖሮ ይህንን ወጪያቸውን መሸፈን የሚገባቸው ራሳቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻል:: እንዲህ ከሆነ ደግሞ ግለሰቡ በመስሪያ ቤታቸው የተመቻቸላቸውን ዕድል ተጠቅመው ወደ ውጭ ለሥልጠና ሄደው እያለ ጥቅም አላገኙም ብሎ መደምደም የሕጉን መንፈስ ያልተከተለ መሆኑን አስምሮበታል፡፡
በዚሁ መሰረትም የሥር ፍርድ ቤቶች ግለሰቡ ከመስሪያ ቤታቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና በዚሁ ግንኙነት መነሻ የተፈጠረላቸውን ዕድል፤ ወደ ውጭ አገር ሊሄዱ የቻሉበትን ምክንያትና አንድ ሰው ወደ ውጭ አገር ሲሄድ የግድ ወጪ የሚያስፈልገው መሆኑንና ግለሰቡም በራሳቸው ወደ ውጭ አገር ቢሄዱ ኖሮ ወጪያቸውን ከኪሳቸው ሊከፍሉ ይችሉ የነበረ መሆኑን እንዲሁም መስሪያ ቤታቸውም ከተላኩበት ተመልሰው ሊያገለግሉኝ ይችላሉ በሚል ሙሉ ዕምነት ወጪውን አውጥቶ ልኳቸው እያለ ያለመመለሳቸው በመስሪያ ቤቱ ገንዘብ በመገልገል ጥቅም ማግኘቻቸውን እንደሚያረጋግጥ ባለመገንዘብ “ጥቅም ማግኘታቸው አልተረጋገጠም” በሚል ምክንያት የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ በምትኩም ግለሰቡ መስሪያ ቤቱ ያወጣውን ወጪ እንዲመልሱ ወስኖባቸዋል፡፡
ከዚህ ውሳኔ የምንረዳው ታዲያ በሕጉ የተቀመጠው የተከሳሹን ጥቅም የማግኘት መመዘኛ በአግባቡ ሊመረመር እንደሚገባው ነው፡፡
ያለአግባብ መበልጸግ ሕግ
ያለአግባብ የመበልጸግ ሕግ ወሳኝ የሕግ ክፍል ቢሆንም በሕግ አውጭዎችም ሆነ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ተገቢውን ሥፍራ እንደማይሰጠው አንዳንዶች ይገልጻሉ::
በተለይም ይህ ሕግ የውል ሕግና ከውል ውጭ የሆነ አላፊነት ሕግ ጋር መሳ ለመሳ ሆኖ የፍትሐብሔር ግዴታ የሚቋቋምበት ሶስተኛው ምሰሶ ሊሆን ሲገባው የክፍተት መሙያ ሕግ እንዲሆን ተደርጓል ባይ ናቸው፡፡
ይህ ያለአግባብ የመበልጸግ ሕግ የንብረት ሕግ፣ የውል ሕግና ከውል ውጭ የሚመጣ አላፊነት ሕግ በየበኩላቸው ያልደፈኗቸውን ቀዳዳዎች እንዲሞላ በሚያስችል መልኩ መቀረጹ ደግሞ ለዚህ ቅሬታቸው ማሳያ ነው፡፡
ያለአግባብ የመበልጸግ ሕግ የሰዎችን ንብረት፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጥረት አግባብ ካልሆነ ብዝበዛ ለመጠበቅ ያለመ ነው፡፡ የአገራችን ያለአግባብ የመበልጸግ ሕግ መሰረታዊ መርሁ ከላይ በጠቀስኩት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2162 ሥር ተደንግጓል፡፡
በዚሁ መሰረት ጥቅም መገኘቱ፣ ጥቅሙም የተገኘው በባለሀብቱ ንብረት ወይም ጉልበት መሆኑ እንዲሁም ጥቅሙ የተገኘው በባለሃብቱ ንብረት ወይም ድካም ላይ በተፈጸመ አለአግባብ (Unjust) በሆነ ድርጊት መሆኑ ከተረጋገጠ ያለአግባብ መበልጸግ ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ሕጉ ያለአግባብ የተገኘ መበልጸግ የለም የሚባልበትን ሁኔታም አስቀምጧል፡፡ በሕጉ መሰረት ተከሳሹ ያለአግባብ ያገኘኸውን ጥቅም መልስ (ካሣ ክፈል) በሚባልበት ጊዜ ላለመበልጸጉ ማስረጃ ባቀረበበት መጠን ልክ ኪሳራ ሊከፍል አይገደድም፡፡
ከዚህ ውጭ ግን እራሱ ያለአግባብ መበልጸጉ ሳያንስ በክፉ ልቡና ንብረቱን ለሌላ ሰው አስተላልፎት እንደሆነ ወይም ንብረቱን መመለስ እንዳለበት ማወቅ ሲገባው አስተላልፎት እንደሆነ ኪሳራ ከመክፈል አይድንም፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን ያለአግባብ የበለጸገበትን ኃብት ያለዋጋ ለሶስተኛ ወገን ቢያስተላልፈው እንኳ ያ ንብረቱን በእጁ ያደረገ ሶስተኛ ወገን ያለዋጋ የወሰደውን ንብረት እንዲመልስ ክስ ሊመሰረትበት ይችላል፡፡
ተገቢ ያልሆነ ክፍያ መፈጸም
በፍትሐብሔር ሕጋችን ያለአግባብ የመበልጸግ ምክንያቶች የሚባሉት ወይም ያለአግባብ መበልጸግን መነሻ በማድረግ ክስ የሚቀርብባቸው ምክንያቶች የሚባሉት ተገቢ ያልሆነ ክፍያ መፈጸም እና አስፈላጊ ወጪዎችን ማውጣት ነው፡፡
ተገቢ ያልሆነ ክፍያ መፈጸም የሚባለው መክፈል የማይገባን ነገር በስህተት ለሌላው ሰው መክፈል ነው:: በዚሁ መሰረት ሊከፍል የማይገባውን ነገር ለሌላው የከፈለ ሰው ይኸው እንዲመለስለት መጠየቅ ይችላል፡፡
በተጨማሪም ያለአግባብ የበለጸገው ሰው ክፍያውን የተቀበለው እምነትን በሚያጎድል ሁኔታ ከሆነ የማይገባውን ነገር የከፈለው ሰው ክፍያውን ከፈጸመበት ቀን አንስቶ የከፈለው ነገር ያስገኘውን ፍሬ ወይም ሕጋዊውን ወለድ ጭምር ሊመልስ ይገደዳል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ከፋዩ ሊከፍለው የማይገባው ዕዳ መሆኑን እያወቀና የሚያስከፍለውም ምክንያት ያለመኖሩን እያወቀ በራሱ ፈቃድ ክፍያ የፈጸመ ሰው ገንዘቡ ወይም የከፈለው ነገር ይመለስልኝ ብሎ መጠየቅ አይችልም፡፡ ከዚህም ሌላ በይርጋ የታገደ ዕዳውን የከፈለ ወይም የሕሊና ግዴታውን ለመወጣት ሲል የበጎ አድራጎትን መንፈስ በመከተል ክፍያ የፈጸመ ሰው በተመሳሳይ ይመለስልኝ ማለት አይችልም፡፡ ክፍያውን የተቀበለው ወገን ያለአግባብ በልጽጓል ለማለት ስለማይቻል፡፡
ከዚህ የምንረዳው ታዲያ መሰረታዊው ጉዳይ በከፋዩ በኩል ስህተት መኖሩ ነው፡፡ በስህተት ክፍያ ለፈጸመው ሰው ደግሞ እንዲመለስለት የሚጠይቀው በስህተት የከፈለውን ነገር ወይም ገንዘብ አልያም የዚህኑ ተመጣጣኝ ካሣ ነው፡፡ አውቆ የከፈለ ግን ይመለስልኝ ቢል በሕግ ተቀባይነት አያገኝም፡፡
ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ከመፈጸም ጋር በተያያዘ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ የማይመለስ ዕዳን የተመለከተው ነው፡፡ አንድ ሰው ለሌላ ሰው ገንዘብ አበድሮ ሳለ ያበደረው ገንዘብ እየተመለሰለት መስሎት ከሌላ ሶስተኛ ሰው ገንዘብ ከተቀበለ በኋላ በቅን ልቡና የብድሩን ሰነድ ቢቀድድ (ቢሰርዝ) ወይም ዋሶቹን ነጻ ቢያወጣቸው አልያም ከእውነተኛው ተበዳሪው ላይ ያበደረውን ገንዘብ የሚቀበልበት ጊዜ በይርጋ ቢያልፍበት ካላበደረው ሰው ገንዘብ ተቀብሏልና ያለአግባብ በልጽጓል አይባልም፡፡
ስለሆነም ያልተገባ ክፍያ የፈጸመው ሰው ያለአግባብ በመበልጸግ ሊከሰውና ሊያስመልሰው በሕግ መብት የለውም፡፡ ይሁንና ይህ ገንዘቡን ያለአግባብ የከፈለ ሰው ገንዘቡን ከዋናው ባለዕዳ (ገንዘብ ከተበደረው ግለሰብ) መጠየቅ እንዲችል ሕጉ ፈቅዶለታል፡፡
አስፈላጊ ወጪዎች ማውጣት
ያለአግባብ መበልጸግን መነሻ በማድረግ ክስ ሊቀርብበት የሚችል ሁለተኛው ምክንያት አስፈላጊ ወጪዎችን ማውጣት ነው፡
አንድ ሰው የሌላን ሰው ንብረት ለተወሰነ ጊዜ በእጁ ከቆየ በኋላ ለባለመብቱ እንዲመልስ ሊገደድ ይችላል:: ይህ ሰው ታዲያ ዕቃው በእጁ በሰነበተባቸው ጊዜያት የተለያዩ ወጪዎችን ማውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
በዚሁ መነሻ ዕቃውን እንዲመልስ በሚገደድበት ወቅት “ይሄን ይሄን ወጭ ስላወጣሁ ገንዘቤ ይመለስልኝ” የሚል ጥያቄ እንደሚያነሳ እሙን ነው፡፡ እናም የተቀበለው ዕቃ በእጁ በነበረበት ወቅት ያስገኘውን ፍሬ ለራሱ እንዲያስቀር ሕግ ከሚፈቅድለት በላይ በዕቃውና ለዕቃው ያወጣቸውን ወጪዎች እንዲመለሱለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡
በመሆኑም በሕጋችን ዕቃ እንዲመልስ የሚገደድ ሰው እንዲመለሱለት የሚጠይቃቸውና ሊጠይቅ የማይፈቀዱለት ወጪዎች የትኞቹ ናቸው? ወጭውን ከመጠየቅ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ሌሎች መብቶችስ አሉት? የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
የመጀመሪያው ጉዳይ ዕቃውን እንዲመልስ የተገደደው ሰው ያወጣውን ወጪ ይመለከታል:: ይኸውም የያዘውን ዕቃ እንዲመልስ የተገደደ ሰው ዕቃው በእጁ በነበረበት ጊዜ እንዳይጠፋ ወይም እንዳይበላሽ ለማድረግ ያወጣው ወጪ ሁሉ ይመለስለታል፡፡ በተጨማሪም ለዕቃው ያወጣው ወጪ የዕቃውን የዋጋ ግምት ከፍ አድርጎት ከሆነ ያወጣው ገንዘብ ሊመለስለት ይገባል፡፡
ይሁንና ወጪው ዕቃው እንዳይጠፋ ወይም እንዳይበላሽ በርግጥም ጠቃሚ ሳይሆን ከቀረ ወይም ወጪው የተከሰተው በራሱ ወይም እርሱ አላፊ በሚሆንለት ሰው ጥፋት (ለምሳሌ በልጁ) ከሆነ ተገዳጁ ሰው ያወጣው ገንዘብ አይመለስለትም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ዕቃውን ለመጠበቅ ወይም በዕቃው ይዞታ ምክንያት የከፈለው ግብር ካለ እንዲመለስለት መጠየቅም አይችልም፡፡
በተጨማሪም ወጪውን ያወጣው ዕቃውን ለመመለስ ግዴታ ያለበት መሆኑን ባወቀበት ወቅት ከሆነ ክፉ ልቡና የነበረው መሆኑን ስለሚያመለክት ይመለስልኝ የሚለውን ገንዘብ ዳኞች እንዲቀንሱበት ወይም ጭራሹኑ እንዳይመለስለት ለመወሰን ይችላሉ፡፡
የያዘውን ዕቃ እንዲመልስ የተገደደ ሰው ሌላኛው መብቱ የራሱን ዕቃ ለይቶ የመውሰድ መብት ነው፡፡ ይኸውም ተገዳጁ ዕቃውን ከመመለሱ በፊት በዕቃው ላይ አገጣጥሞት የቆየውን የራሱን ነገር (ዕቃ) ከፍ ያለ ጉዳት በዕቃው ላይ ሳያደርስ ለማላቀቅ የሚቻለው ከሆነ ለይቶ ለመውሰድ መብት አለው፡፡
ሶስተኛው መብት የመያዝ መብት ነው፡፡ የያዘውን ዕቃ እንዲመልስ የተገደደ ሰው ከላይ ባብራራሁት ሕጋዊ ሁኔታ ያወጣውን ወጪ ከንብረቱ ጠያቂ ካልተመለሰለት እስከሚቀበል ድረስ ወይም ወጪው በሚከፈልበት ቀን መከፈሉን የሚያረጋግጥለት በቂ ዋስትና ካልተቀበለ ዕቃውን አልመልስም የማለት መብት ሕግ አጎናጽፎታል::
ከመብቶቹ ባሻገር ሕጉ ግዴታዎችንም አስቀምጦበታል፡፡ ግዴታው የሚመነጨው ዕቃው ከተበላሸ ወይም ከጠፋ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ዕቃውን እንዲመልስ የተገደደው ሰው ለባለመብቱ ኪሳራ እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ የዕቃው መበላሸት ወይም መጥፋት ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል የደረሰ እንኳ ቢሆን ኪሳራ ከመክፈል አይድንም፡፡
የኪሳራውን ልክ በተመለከተ ደግሞ ዕቃውን ለመመለስ ባልተቻለበት ቀን ከነበረው የጠፋው ወይም የተበላሸው ዕቃ ዋጋ ጋር እኩል መሆነ እንዳለበት ሕጉ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ገብረክርስቶስ