አዲስ አበባ፦ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አሰፋፈር ወቅታዊ ፤ተጨባጭና ታሳቢ ስጋትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን መሆኑ ተገለጸ፡፡ የመከላከያ መማክርት (ካውንስል) ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አድርጓል።
ውይይቱን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ፣ ውስጣዊና ከባቢያዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የሠራዊት አሰፋፈር እንዲኖር የተጀመረው እንቅስቃሴ የአጠቃላይ ተቋማዊ ሪፎርሙ አካል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የሠራዊት እንቅስቃሴው እንደ አዲስ ከማስፈረም ባሻገር ለረዥም ጊዜ በድንበር ምሽግ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ወደ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ሥራዎች ማስገባትንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡
የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ቴክኖሎጂን የሚታጠቅ፤ በራሱ አቅም መጠገን፣ ማሳደግ ብሎም መፍጠር የሚችል እንዲሆን በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን መግለጫው አስታውሶ፣ መከላከያ ከቴክኖሎጂ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውና እንደሌሎች አገራት ከራሱም አልፎ ለሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ምንጭ መሆን የሚችል የቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲሆን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ምክር ቤት መገምገሙን ጠቅሷል፡፡
በሁሉም ደረጃዎች የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋጽኦ የጠበቀ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እና በሁሉም ረገድ መልካም የአፈጻጸም ጅምሮች እንዳሉ የገመገመው መማክርቱ፤ በቀጣይ እነዚህን ለውጦች አጠናክሮ ለመቀጠል የሚስችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ አቅጣጫዎች አስቀምጧል ሲል መግለጫው አመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር