የካቲት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ገድሎች የተፈጸሙበትና በርካታ ድሎች የተመዘገቡበት ነውና ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል። በተለይ የዛሬ አንድ መቶ ሃያ አራት ዓመት ህዝብና መንግስት በአንድ በመቆም እብሪትንና ማን አለብኝነትን ድል የነሱበት ወር ስለሆነ ይዘከራል። ከመቶ ዓመት በላይ ክብር የተጎናጸፈው ይህ የድል በዓል ደግሞ የየካቲት 23 ቀን 1888ቱ የአድዋ ድል ነው።
የአድዋ ድል ቀን ዘንድሮ ለ124ኛ ጊዜ ይከበራል። ይህ ቀን በወቅቱ “ማን አለብን” ይሉ የነበሩትን የአውሮፓ ነጮች ወክሎ፤ በአገሩ “ተመርቆና ተባርኮ” የመጣው የኢጣሊያ ጦር በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ድል የተደረገበት እለት ነው። ያኔ ኢትዮጵያ በጨለማነት ከተሰየመው የዓለም ክፍል የምትገኝ ነጻ አገር ነበረችና ጣሊያኖች “ድርሻዬ” በሚል እብሪት ቅኝ ሊገዟት ተነሱ።
በርግጥ አንዳንዶቹ መኳንንትና መሳፍንት በንጉሰ ነገስቱ ላይ አኩርፈው፤ አንዳንዶቹም ሸፍተው ጫካ ገብተው ነበርና ወቅቱን ለወራሪው እንደመልካም አጋጣሚ የተፈጠረለት አስመስሎት ነበር። በመሆኑም የጣሊያን ጦር እስከትግራይ ግዛት ድረስ መጥቷል። ይሁን እንጂ፤ የሀገር ጉዳይ ከግል ስሜት ከፍ ያለ፤ ከራስ ፍላጎት የላቀ ነውና ያኮረፈውም ተጸጽቶ፤ የሸፈተውም ይቅርታ ጠይቆ ለአገሩ ሊሞት ከህዝቡና ከንጉሱ ጋር ተሰለፈ።
ህዝቡ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆና መደበኛ ወታደር አሰልፎ የመጣውን ጠላት በአንድ ጀንበር ውጊያ ድል አድርጎ አሳፈረው። በርግጥ ድሉ የኢትዮጵያውያን ይሁን እንጂ በጦርነቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተሰውቷል። ድል ያለመስዋእትነት አይገኝምና ይህ የሚጠበቅ ነበር። ያም በመሆኑ እነሆ ሀገር በልጆቿ ተከብራ፤ ድንበሯ በመስዋዕትነታቸው ጸንቶ ድሉን ዛሬም ለ124ኛ ጊዜ ልናከብረው በቅተናል።
የአድዋ ድል ህዝቦች በአንድነትና በህብረት በመቆም ያስመዘገቡት አኩሪ ታሪካችን ነው። ይህንን ድልና ታሪክ ጠብቀን መቆማችን፤ በአንድ ሆነን መዘከራችን አይበዛብንም። ያኔ አትዮጵያውያን እስከአፍንጫው ታጥቆና ተኩራርቶ የመጣውን ጠላት የመከቱበት፤ መክተውም ያሸነፉበት ትልቁ ምስጢር አንድነታቸው ነው።
አዎን እኛ ለረጅም ዘመን ሳንለያይ እንድናከብረው ያበቁን ጀግኖች ሚስጥራቸው ህብረታቸው ነው። ያኔ ህዝቦች በጾታ አልተለያዩም፤ ብሄር ቆጥረው፤ እምነት ጠርተው ወደኋላ አላሉም። የእድሜና የሀብት ወይም የስልጣን ልዩነት አልገደባቸውም።
ይልቁንም፤ ሁሉም በጋራ ተነስተው፤ በአንድነት ተሰልፈውና በህብረት ተዋግተው ወራሪውን አሳፍረውታል። እናም ዛሬ የምናከብረው ይህንን የድል ምስጢር የሆነውን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነትና በህብረት የመቆም እውነታና ውለታ ነው።
ይህ ድልና የድል ታሪክ በእኛ በኢትዮጵያውያን ብቻ ተወሰኖ የቀረ አልነበረም። ይልቁንም መላውን የአፍሪካ ህዝቦች ያነቃቃ፤ ከአፍሪካም አልፎ በነጮች መዳፍ ስር የነበሩ የቅኝ ተገዥ የዓለም ህዝቦችን ለእምቢተኝነት ያነሳሳ ነበር።
ያም በመሆኑ በየደረጃውና በየወቅቱ በተደረጉ የነጻነት ተጋድሎዎች አውሮፖውያን ወራሪዎች ከአፍሪካ፤ ከኤሽያና ከላቲን አሜሪካ ተነቅለው ወጥተዋል። የአድዋው ድልም የመላው አፍሪካውያን ድልና የፖን አፍሪካኒዝም ጥንስስ ተደርጎ ይቆጠራል።
ዛሬም እኛ ኢትዮጵያውያን የአድዋን ድል ስንዘክር በአንድነትና በህብረት ሊያቆሙን የሚገቡ የጋራ አገራዊ ጉዳዮች እንዳሉን ባለመዘንጋት ነው። ዛሬም በጋራና በህብረት ልንፈታቸው የሚገቡ ችግሮች፤ በአንድነትና በጥምረት መሻገር ያለብን ገደሎች አሉብን። እነዚህን ችግሮች ለመሻገር ደግሞ መነጋገርና መወያየት ያስፈልጋል። የዘመኑ ትጥቅና የህዝቦች ችግር መፍቻ ዋንኛው መንገድ መወያየትና መነጋገር ብቻ ነው።
እርግጥ ነው ሊያስኮርፉንና ለብቻ ሊያስቆሙን የሚችሉ የተናጠል ጉዳዮች ይኖራሉ። እንደሀገርና ሲታለም ግን የጋራ የሆኑትና በህብረት የሚያስቆሙን ጉዳዮች ይበልጣሉና ህብረታችን ሊሸረሸር አይገባውም።ኩርፊያችንና አለመግባባታችን ለችግሮቻችን እድሜ ማራዘሚያ ካልሆነ በስተቀር ለህዝቦች የሚፈይደው ነገር የለም።
አዎን! አባቶቻችንና እናቶቻችን ትናንት ከራሳቸው ቅድሚያ ሰጥተው፤ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን ሀገር እኛም በተራችን ልንጠብቃት ይገባል። ያኔ በአድዋ የታየው የኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት ዛሬ በኛ በልጆቻቸው ጊዜ ሊሸረሸር አይገባም። በአንድነትና በህብረት ቆመን፤ የጋራ ችግሮቻችንን በውይይት ፈትተን አገራችንን በነፃነት በማቆም የድል ታሪካችንንም ማስቀጠል ይጠበቅብናል! አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012