
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በብዛት ተሳታፊ ከሆነችባቸው የአትሌቲክስና ብስክሌት ስፖርቶች በመቀጠል ይጠቀሳል፤ ቦክስ፡፡ በቦክስ ስፖርት የመጀመሪያው የኦሊምፒክ መድረክ ተሳትፎ እአአ በ1968 በተካሄደው የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ሲሆን፤ በወቅቱም አራት ቦክሰኞች ተካፋይ ነበሩ። ከዚያ በኃላ በተካሄዱ ስምንት ኦሊምፒኮች ላይም ሃገሪቷ ስፖርተኞቿን ማሳተፏን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል፡፡ በመድረኩ ለመጨረሻው ተሳትፎ ካደረገችበት እአአ የ2008 ቤጂንግ ኦሊምፒክ በኋላም ተሳታፊ የሚያደርጋትን እድል ሳታገኝ በመቅረቷ ኢትዮጵያ በስፖርቱ አልተወከለችም፡፡
ከወራት በኋላ ጃፓን በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ የአዘጋጅነት እድሉን ባገኘችበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፤ ከአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቴኳንዶ እና የውሃ ዋና ስፖርቶች በተጓዳኝ ተሳታፊ ለመሆን ያቀደበት ሌላኛው ስፖርት ቦክስ ነበር፡፡ ለእቅዱ መሳካት ይረዳ ዘንድም በማጣሪያ ውድድር ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ተካፋይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሴኔጋሏ ዳካር አስተናጋጅነት በተካሄደው በዚህ ቻምፒዮና ላይም ስድስት ወንድ እና አንዲት ሴት ቦክሰኞች፤ በ48፣ 52፣ 57፣ 63፣ 69፣ 75 እና 81 ኪሎ ግራም ተወዳዳሪ ሆነው ነበር፡፡
ከዳካር የአየር ጸባይ ጋር ለመለማመድ እንዲያስችላቸውም መቀመጫቸውን በአርባ ምንጭ በማድረግ ለረጅም ጊዜ በልምምድ ላይ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥቂቱ መነቃቃት የታየበት የቦክስ ስፖርት በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ሜዳሊያዎችን ማስቆጠርና ተወዳዳሪነቱን በማስመስከር ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ትናንት ወደ ሃገሩ የተመለሰው ብሄራዊ ቡድኑ በማጣሪያው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቶኪዮ ያቀናል የሚል ከፍተኛ ግምትም አግኝቶ ነበር፡፡
በሴኔጋል በነበራቸው ቆይታም የመጀመሪያዎቹን ዙሮች በብቃት በማለፍ ያላቸውን ተስፋ ማሳየት ችለዋል፡፡ ዙሩ እየገፋና እየከበደ መሄዱን ተከትሎም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሶስት ቦክሰኞች እስከ ስምንት ባለው ደረጃ በመግባት ጥቂት ትኩረት ቢያገኙ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ ማረጋገጣቸውን በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድር ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡
በአልጀሪያ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ እንዲሁም በሞሮኮ ራባት የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው የ48 ኪሎ ግራም ተወዳዳሪው ዳዊት በቀለ ስምንት ውስጥ ከገቡት መካከል አንዱ ነው፡፡ የ57 ኪሎ ግራም ተወዳዳሪው ፍቅረማሪያም ያደሳ እና በ81 ኪሎ ግራም ተወዳዳሪው ሰይፈ ከበደም ስምንት ውስጥ መግባት የቻሉ ቦክሰኞች ናቸው፡፡
ቡድኑ ባይሳካለትም ወደ ሴኔጋል ያቀናው በኦሊምፒኩ ተካፋይ ለመሆን የሚያስቻለውን ውጤት ለማስመዝገብ ካልተቻለ ደግሞ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ለመያዝ ነበር፡፡ ነገር ግን የትኩረትና የልምድ ማነስ እንዲሁም በልምምድ ወቅት ባጋጠመው የቁሳቁስ እጥረት ወደ ታላቁ የስፖርት መድረክ ማለፍ ሳይቻል መቅረቱን ባለሙያው ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ዳኝነት ላይም መስራት እንደሚገባም ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ብርሃን ፈይሳ